እየተዘነጋ ያለው የተዋሕዶ አባቶች ሚና በዐድዋ ዘመቻ
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on March 4, 2018
-
“ውጊያው የተጀመረው በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ቃል ነው፤“
-
“ጦርነቱን ድል ያደረግነው በካህናት አባቶቻችንም አስተዋፅኦ ነው፤“
-
“ወደ ሮም ከሔዱት ዲፕሎማቶች ቄስ ወ/ሚካኤል አንዱ ናቸው፤“
†††
(ዘ አዲስ/Ze Addis)
የዐድዋን ጦርነት ዘመቻ ከመሠረቱ እስከ መደምደሚያው ድረስ ለድል ካበቁት ኢትዮጵያውያን ወገኖች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ::
የዐድዋ ዘመቻ ከመታወጁ በፊት ጉዳዩ በሰላም እንዲያልቅ ካህናት አባቶች በዲፕሎማሲው ተመድበው ሮም ድረስ ተጉዘዋል:: ጦርነቱም ከመጀመሩ በፊት ምሕላ አስይዘው ሕዝቡን ለውጊያ ሲያዘጋጁ ነበር:: ጦርነቱ ሲታወጅም የወቅቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ዕጨጌው፣ እጅግ በርካታ ካህናት እና መነኰሳት ታቦታትን ይዘው ዘምተዋል:: በዝርዝር እንመልከተው፡፡
ቅድመ ውጊያ
የዐድዋ ዘመቻ ከመታወጁና ጉዳዩ ወደ ጦርነት ከማምራቱ በፊት በሰላም ለመጨረስ ኢትዮጵያ ብዙ ርቀት ሔዳለች:: ተወካዮቿን ሮም – ጣልያን ድረስ በመላክ ኹኔታውን በሰላም ለመጨረስ ሰፊና ብልሃት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ጥረት አድርጋ ነበር:: ይኸው በራስ መኰንን የተመራው የዲፕሎማቶች ቡድን ወደ ጣልያን በማምራት ከጣልያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ክሪስፒ ጋራ ዝርዝር ውይይት አድርጓል::
የዲፕሎማት ቡድኑ አባልና ዋና ሰው ከነበሩት መካከል፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ካህን፣ ቄስ ወልደ ሚካኤል አንዱ ናቸው:: ካህኑ፣ ከራስ መኰንን ቀጥለው የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ቡድን ኹለተኛው ሰው ነበሩ:: በሐርቫርድ ዩንቨርስቲ የታተመው የፕሮፌሰር ሬይመንድ ጆናስ “Battle of Adwa : African Victory in the Age of Empire” የተባለው መጽሐፍ ገጽ 82 ላይ እንዲህ ይላል፡–
“Ras Mekonnen delegation included translator Joseph Niguse, Orthodox priest WoldeMichael, and five other high ranking figures. They were supported by thirteen bodyguards and twenty one persola aides.”
የዐድዋ ዘመቻ እና አበው ካህናት፤
የጣልያን ጉዳይ በዲፕሎማሲ እንደማያዋጣና መፍትሔውም ራስን የመከላከል ፍልሚያ መኾኑን በተደጋጋሚ ያስታወቀችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት:: የወቅቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ጉዳዩን ጠንክረው የገፉበት ሲኾን፣ በቤተ መንግሥቱም ግፊት አድርገዋል:: ለጦርነቱ ክተት ሲታወጅም የቤተ ክህነቱ ዋና ዋና ሰዎች፣ እጅግ በርካታ ካህናትና መነኰሳት ወደ ዘመቻ ተመዋል:: ከታቦታቸው ጋራ ሦስት ወራት የፈጀ መንገድ ተጉዘዋል:: በየመንገዱ ከመገዘት ጀምሮ እስከ መጨረሻው የውጊያ ግንባር ድረስ በአካል ተሰልፈው ተዋጊዎችን በማበረታታት፣ የደከሙትን በማጽናት፣ የተሠዉትን በመፍታት( ጸሎተ ፍትሐት) በአካል መሣርያ ይዘው በመዋጋትም ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል::
ይህን እውነት በወቅቱ የነበረ ካፒቴን ሞልቴዶ የተባለ የኢጣልያ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጽፎታል (Moltedo , G L assedio Di Maccale)፤
“የሐበሾች ጦር .. ከሁሉም ብሔረሰብ ተውጣጥቶ ቀርቧል:: ..ጦርነቱንም ከወታደሮች ጋር ብቻ አልገጠምንም:: ..ቄሶች ሳይቀሩ ወጉን፤” በማለት ውጊያ ላይ የተሳተፉት ካህናትም ጭምር እንደነበሩ ይነግረናል:: (ጳውሎስ ኞኞም፣ “ዐጤ ምኒሊክ” በሚለው መጽሐፉ ገጽ 162 ጠቅሶታል)
በተለይ ከዘማቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ጋራ ተያይዞ ገና ከመነሻው ብዙ ተኣምራት ይታዩ ነበር:: በዘመቻው ወቅት ታሪክ ጸሓፊ የነበሩት– ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ በወቅቱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላት ጋራ የነበረውን ተአምራት– “ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 230 እንዲህ ሲሉ ዘግበውታል፡–
“በዚህም ዘመን በጥቅምት ሁለት ቀን ካዲስ አበባ ከተማ ተነሥተው ወደ ትግሬ ዘመቻ ተጓዙ::.. በዚያም ቀን እንደ ቀስተ ደመና ያለ እሳት የሚመስል ከሰማይ ላይ በምዕራብ በኩል ሲሔድ በአራት ሰዓት ታየ:: ጢሱም ሳይጠፋ ብዙ ቆየ፤ የጢሱም መልክ አረንጓዴ ይመስል ነበር፤ ድምፁም እንደ መድፍ ተኩስ ኾኖ ተሰማ::”
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና መነኰሳት፣ “በገዳማችን ወይ በደብራችን ቁጭ ብለን ስለ ዘመቻው እንጸልያለን፤” አይደለም ያሉት:: ከዘማቹ ጋራ አብረው ታቦታቸውን ይዘው ዘመቱ:: ታቦቱን ተሸክመው ሦስት ወር ሙሉ ተጓዙ::
“ሒዱና ተዋጉ” ብለው ባርከው ያሰናበቱት ሊቀ ጳጳሱ ነበሩ፤
አንቶኒ ሞክለር ስለ ዐድዋ ጦርነት የመጨረሻ ምዕራፍ ሲጽፍ እንዲህ ይላል፤
“ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ቅዳሴውን በሚመሩበት ግዜ ኹለት ጥይት ከውጭ ተተኮሰ:: .. ራስ መኰንንም የኢጣልያኖችን መምጣት ተናገሩ:: .. አቡኑም መስቀላቸውን በቀኝ እጃቸው ይዘው፣ “ልጆቼ ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚገለጽበት ቀን ነው:: ሒዱ:: ለሃይማኖታችሁና ለንጉሣችሁ ተከላከሉ:: ኹላችሁንም ከኃጢአት እግዚአብሔር ይፍታችሁ፤ አሉ:: መኳንንቱም መስቀል ተሳልሞ ወደ ውጊያ ገባ ይላል፤“ ጳውሎስ ኞኞ፡፡ (ዐጤ ምኒልክ፣ ገጽ 203)
የኢትዮጵያ ዋና ዋና የጦር መሪዎች ቅዳሴ ላይ ነበሩ:: ጣልያን የመጀመርያውን ጥይት እንደተኮሰ –ቅዳሴውን አጠናቀው የጦር መሪዎቹን ባርከው “ሒዱና ተዋጉ” ብለው መንፈሳዊ ቡራኬና የማበረታቻ ቃል ሰጥተው ኢትዮጵያውያንን ያሰናበቱት ጦርነቱን ያስጀመሩት – እዚያው በቦታው የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ናቸው::
የጦር አዝማቾቹ ወደ ውጊያ ሲገቡም ሊቀ ጳጳሱና ሌሎቹ ካህናት እጃቸውን ዘርግተው ይጸልዩ ነበር:: ይህን ጉዳይ ጸሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ፣ በ“ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ዐጤ ምኒሊክ” ገጽ 268 እንዲህ አስፍረውታል፡–
“አቡነ ማቴዎስም ታቦተ ማርያምን ይዘው ካህናቱም መነኮሳቱም ኾነው ምሕላ ይዘው የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁር ሳይጨርሱ ድል ለኢትዮጵያ ኾነ:: እኛም ለጊዜው የፊተኛ ሰልፍ ድል ቢሆን የተኩሱ መጨረሻ መስሎን ደስ አለን፡፡“
የዐድዋ ጦርነት ላይ በአካል ተገኝተው ታሪክ ሲዘግቡ የዋሉት ጸሓፌ ትእዛዝ፣ በዚሁ ዘገባቸው ገጽ 264 ላይ እንዲህ ሲሉ ይቀጥላሉ፤
“የዘመቱትም የኢትዮጵያ መነኰሳት እጅግ ብዙ ነበሩ:: ወይባ፣ ኣጥፍ፣ የዳባ ቀሚስ የለበሱ፣ የሰሌን ቆብ ያደረጉ ብዙ ነበሩ:: የጦርነቱም ለት እኩሉ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር፣ እኩሉ ደግሞ ከንግሥቲቱ ከእቴጌ ጣይቱ ጋር፣ እኩሉ ደግሞ ከሰልፈኛው ጋር ኾነው ወደ ጦሩ የሚሔደውን እየናዘዙ፣ የደከመውን እያወገዙ ሲያዋጉ ዋሉ::”
በዐድዋ ዘመቻ ድል አድርገው ነጻነታችንን የሰጡን አርበኞች አባቶቻችንና እናቶቻችን ብቻ አይደሉም:: ሰማዕት ኾነው ነጻነታችንን የሰጡን፣ አበው ካህናት እና መነኰሳት አባቶቻችንም ጭምር ናቸው:: ለሀገራችን ነጻነት ካህናትና መነኰሳት ከወታደሩ እኩል እንደ ወታደር ተጉዘዋል:: እንደ ጦረኛ ተዋግተዋል:: አዋግተዋል:: ካህናቱ ብቻ ሳይኾኑ ታቦታቱም ዘምተዋል::
ድሮ የዐድዋ በዓል ሲዘከር፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት በምልዓት ይነገር እንደነበር ድርሳናት ይገልጻሉ:: በዐድዋ ክብረ በዓል የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕልም ይታተም ነበር:: ይህ ሥርዓት ከቀድሞው መንግሥት የኮሚኒዝም አስተሳሰብ ወደ ሥልጣን መምጣት ጋራ ተያይዞ እንደቀረ ከዚያም በኋላ እስከ አኹን የቤተ ክርስቲያኗ ድርሻ እንዲወሳ አይፈለግም::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የዐድዋ ድል ዋነኛ ባለውለታ ናት:: ዐድዋ ሲወሳ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዋፅኦ ይነሣ! ሌላው ባያደርገው ለእኛ ለኦርቶክሳውያን ግን ታሪካችን ነው:: በዓሉ በሚከበርበት ጊዜ ኹሉ የቤተ ክርስትያንዋ አስተዋፅኦ ይወሳ፤ ይነሳ::
የኢትዮጵያ ጦር የተዋጋው ሑዳዴን እየጾመ ነው፤ ታቦተ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ጦር መሀል ነበረ
-
“የኢትዮጵያ ጦር አሰፋፈሩ የቤተ ክርስቲያንን ፕላን የተከተለ ነበር፤“
-
“ጦርነቱ የተደረገው በሑዳዴ ጾም ውስጥ ነው:: ጾም እንዳይሻር ጳጳሱ ገዘቱ፤“
-
“አቡነ ማቴዎስ ከዋናዎቹ የጦር አማካሪዎች አንዱ ነበሩ፤“
†††
እየጾመ የተዋጋው የኢትዮጵያ ጦር፤
የዐድዋ ጦርነት የተካሔደው በገና እና በሑዳዴ አጽዋማት ወቅት ነው:: የዓምባላጌ እና የመቐሌው ውጊያዎች የተካሔደው በገና ጾም ሲኾን ዐድዋ ላይ በአሻሾ፣ ራዕዮ እና ሰማያታ ተራራ እና ሜዳ ላይ የካቲት 23 ቀን የተደረገው ዋናው የዐድዋ ውጊያ ደግሞ የተደረገው በሑዳዴ ጾም ነው:: የያኔው ጾም ደግሞ እንዳሁኑ አልነበረም:: ምእመኑ ቀኑን ጾሞ ምሽት ላይ ነበር የሚመገበው::
በዚህ ምክንያት “ሠራዊቱ እንዳይደክምብኝ በማለት ንገሠ ነገሥቱ ዐፄ ምኒልክ፣ ለጦርነቱ ሲባል የዘንድሮውን ጾም እንዳይጾም ዘማቹን ወታደር ይፍቱልኝ:: ጾሙ ለወታደሮቼ ይሻርልኝ፤” ብለው አቡኑን ጠይቀው ነበር:: አቡነ ማቴዎስ ግን እምቢኝ አሉ:: “ወታደርም ቢኾን፣ ዘመቻም ቢኾን ጾምን ሻሩ አልልም፤” ብለው እምቢ አሉ::
ጳውሎስ ኞኞ፣ “ዐጤ ምኒልክ” በሚለው መጽሓፉ ላይ ይህን አስገራሚ ታሪክ እንዲህ አስፍሮታል፡–
“የዐድዋ ጦርነት የተካሔደው በገና እና በሑዳዴ ጾም ነው:: ክርስቲያኑ ዘማች በዚያን ግዜ እንደነበረው አጿጿሙ ራቱን በልቶ እስከሚቀጥለው ጀምበር መጥለቅ ምንም አይቀምስም:: ውኃ እንኳን አይጠጣም ነበር:: ይህን የተገነዘቡት ዐጤ ምኒልክ ጳጳሱን አቡነ ማቴዎስን፦ ጦርነት ላይ መኾናችንን ያውቃሉ:: ሠራዊቱ በጦርነቱም በጦሙም ተደራራቢ ጉዳት እንዳይደርስበት ያገኘውን እየበላ እንዲዋጋ ይፍቱት:: ቢያስፈልግ ከጦርነት መልስ ይጾማል፤ ቢሏቸው አቡኑ፣ አልፈታም፤ ብለው እምቢ አሉ:: ምኒልክም በዚህ አዝነው፣ እግዚአብሔር የየዋህ አምላክ ይርዳው፤ አሉ::” ይላል::(ገጽ 172)
ሌላኛው ደራሲ ደግሞ፣ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ዐፄ ምኒልክን፣ “ስለ ኢትዮጵያ የሚዋጋው እግዚአብሔር ነው:: ሰልፉ የሰው ሳይኾን የእግዚአብሔር ነው:: ድሉም የኢትዮጵያ ይኾናል፤“ ብለው መናገራቸውን ዘግቧል:: አቡኑ ተሳስተው ይኾን? ያነ የኾነውን እስኪ እንመልከት?
የካቲት 22 ቀን ሌሊት የጣልያን ጦር ለውጊያ ከመነሣቱ በፊት ከባድ ድግስ ተዘጋጅቶለት በፌስታ ነበር:: የጣልያን ወታደሮችም የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመውጋት ከሳውራ ተነሥተው ገንዳብታ ሲደርሱ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ነበር:: ውጊያ ከመግባታቸው በፊት ዕረፍት እንዲያደርጉና በሚገባ እንዲመገቡ ታዘዙ:: በቆርቆሮ የታሸጉ ምግቦችን በልተው የሚበቃቸውን ያህል ውኃ ጠጥተው ዝግጅታቸውን አጠናቀው የኢትዮጵያ ሠራዊት ወዳለበት መሥመር በደፈጣ መግባት ጀመሩ::
የኢትዮጵያ ጦር መኰንኖች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት ላይ ነበሩ:: የጣልያኖች የተኩስ ድምፅም እንደተሰማ ኢትዮጵያውያኑ የጳጳሱ አቡነ ማቴዎስን መስቀል እየተሳለሙ ወደ ውጊያ ገቡ:: እህል አልቀመሱም:: ውኃም አልጠጡም:: በጥድፊያ ወደ ሰልፋቸው አመሩ:: ውጊያው ተጀመረ:: የጣልያን ጦር በሦስት አቅጣጫ ተለጥጦ በመምጣቱ ጦርነቱ ከጠዋቱ ዐሥራ ኹለት ሰዓት ጀምሮ ቀኑን ዋለ::
የኢትዮጵያ ጦር ቀኑን የተዋጋው እህል ውኃ ሳይቀምስ ነበር:: ጦርነትን ምክንያት አድርጎ የገናን ጾም ሳይሽር፣ አሁንም ውጊያውን ምክንያት አድርጎ ሁዳዴን ጾም ሳይሽር እየጾመ ተዋግቶ የኢትዮጵያ ሠራዊት ደል አደረገ:: አቡነ ማቴዎስ አልተሳሳቱም ነበር:: ጳጳስ ይሉሃል እንዲህ ነው:: ሐሞተ ኮስታራ:: የእምነት ሰው::
አቡነ ማቴዎስ የዐድዋን ጦርነት ከሚመሩት ሰዎች አንዱ ነበሩ፤
አቡነ ማቴዎስ በመንፈሳዊው ጉዳይ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያን ጦር የበላይ ኾነው ከሚመሩትና ከሚያስተባብሩት አዝማች መሪዎች ውስጥ አንዱ ነበሩ:: የጦር ዕቅዱ ላይ ከጦር መሪዎቹ ጋራ አብረው ይመክራሉ:: የጦር ውሎ ግምግማ ላይም ተሳታፊና ዋነኛ ተዋናይና ገምጋሚም ነበሩ:: ለምሳሌ፣ የዓምባላጌን የጣልያን ምሽግ የሰበሩትና ድል ያደረጉት ጀግናው ራስ መኰንን መቐሌ ላይ ያን መድገም ባለመቻላቸው ራስ መኰንን ላይ የሰላ ትችትና ወቀሳ ካቀረቡት መሀል አንዱ አቡነ ማቴዎስ ነበሩ::
“The Battle of Adwa” የሚለውን ግሩም መጽሐፍ የጻፉት ፕሮፌሰር ሬይመንድ ጆናስ፣ አቡነ ማቴዎስ ከኢትዮጵያ ጦር ዋና መሪዎች አንዱ እንደነበሩና በእያንዳንዱ የውጊያ ውሎ ግምገማ ላይ እንደሚሳተፉ እንዲህ ሲሉ ይጠቅሱታል/Jonas, Raymond; Jonas, Raymond Anthony. Battle of Adwa : African Victory in the Age of Empire, p.139/
“On the ninth, Ras Meconen forces launched a major assault on the fort (Mekeles fort), taking heavy casualities. The loss of life pained Ras Meconnen, but the reaction from Ethiopian leadership was pitliess. Taitu, Menelik, Tekle Haymanot and Abune Matewos turned on Meconnen and accused Ras Meconeen.”
ከዚህ መረዳት የምንችለው “Ethiopian leadership” ብሎ በአራተኛነት ያስቀመጣቸው አቡነ ማቴዎስን ነው:: አቡኑ ከሠራዊቱ ጋራ ኾነው የሚያጽናኑ ብቻ አልነበሩም::የኢትዮጵያ ጦር አመራር አካል ውስጥ አንዱ ነበሩ:: ውጊያ ሲበላሽ ይገሥጹ ነበር:: ራስ መኰንን ከፍተኛ ባለሥልጣን ቢኾኑም አቡኑ ሥልጣናቸውን ፈርተው ዝም አላሉም:: በውጊያ ውሎ ግምገማ(post combat evaluation) ላይ ተገኝተው ወቅሰዋቸዋል::
ዐፄ ምኒልክም ከባድ ውሳኔ ሲያጸኑ አቡነ ማቴዎስን አማክረው ነበር፤
ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ኢጣልያን ድል ካደረጉ በኋላ ምርኮኞችን በተመለከተ በኢትዮጵያ አመራሮች መካከል ከፍተኛ ክርክር ተደርጎ ነበር:: የመጨረሻውን ውሳኔ ንጉሡ የወሰዱት አቡነ ማቴዎስን አማክረው ነበር:: አሁንም ዝነኛው ፕሮፌሰር ሬይመንድ ጆናስ በዚያው መጽሐፋቸው ገጽ 234 ላይ እንዲህ ይላሉ፡–
“By all accounts, Menelik represented the voice of moderation. As Paul Lairbar put it, ” his natural goodness inclined him toward forgiveness. In the end Menelik took counsel of ABUNE MATEWOS, who sides with Taitu, Alula, Mengesha and the others.”
በጦርነቱ ወቅት በተከናወኑ ሌሎችም በርካታ ውሳኔዎች አቡነ ማቴዎስ ኹነኛ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡
እና ምን ለማለት ነው? በቅድመ ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ፣ አንዷ ዲፕሎማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነበረች፡፡ ዲፕሎማሲው ፈርሶ ጦርነት ሲታወጅ አንዷ ዘማች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነበረች:: የቀረ የለም:: ጽላቱ፣ ካህኑ፣ መነኩሴው፣ ጳጳሱ ዘምቷል፡፡ ጦርነቱን በበላይነት ሲመሩ፣ የውጊያ ውሎውን ሲገመግሙና በከፍተኛ ውሳኔዎችም ጠቅላይ አዛዡን ሲያማክሩ ከነበሩ አካላት አንዱ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ነበሩ፡፡
ዘማች ሠራዊቱን ያሰፍሩና ቦታ ያስይዙ ከነበሩት ካህናትም ነበሩ፤
የዐድዋ ዘማች ሠራዊት አሰፋፈር ዕቅዱ የወጣውም የተካሔደውም በቤተ ክህነቱ ፕላን ነበር፡፡ ከሰባ ሺሕ በላይ የነበረውን የዐድዋን ጦረኛ ያሰፍሩና ቦታ ያስይዙ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና መነኰሳት ነበሩ፤ ይሉናል– በቦታው ተገኝተው የነበሩት የታሪክ ጸሐፍት – ሐበሻውም ፈረንጁም::
በጦርነቱ በቦታው ተገኝተው ያዩትን የጻፉት ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ – “ታሪክ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒሊክ” በሚለው መጽሐፋቸው (ገጽ 225) – የጦሩን አሰፋፈር በካርታ ሥለውታል:: እዚህ ላይ የለጠፍኩትም እርሱን ነው:: አረንጓዴ ቀስቶቹንና ቀዩን ክበብ የጨመርኩበት እኔ ነኝ:: ቀይዋን ክበብ ውስጧን በደምብ ይመልከቱት – ታቦት ይላል:: ታቦቱ የሰፈረው ቦታ ላይ ነበር:: በደንብ እንዲታይ ብዬ ነው በቀይ የከበብኩት::
ጸሓፌ ትእዛዝ ያስቀመጡት ካርታ ብዙ ይናገራል:: መጀመርያ ይህ አሰፋፈር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክብ የቤተ ክርስትያን ሥሪት(ዲዛየን) ነው:: ዲዛየኑ ወይም ፕላኑ ሙሉ ለሙሉ ይመሳሰላል:: ቤተ ንጉሥ በመባል የሚታወቀው ክቡ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ነው:: መቅደስ፣ ቅድስት እና ቅኔ ማሕሌት:: በስተምሥራቅ በኩል ታቦት ይቀመጣል:: ቤተ መቅደሱ መሀል ላይ መቅደሱ አለ:: መቅደስ ውስጥ የሚገቡት ሥልጣነ ክህነት ያላቸው አገልጋዮች ብቻ ናቸው:: ኹለተኛው ዙር ቅድስት ላይ ደግሞ ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የወሰኑና ወደ እግዚአብሔር የቀረቡ ወገኖች ቦታ ነው:: ቅኔ ማሕሌት የመዘምራን ሊቃውንቱ ቦታ ነው:: ከዐድዋ ዘማች አሰፋፈር አንጻር ካርታውን በጥሞና ይመልከቱት::
የመጀመርያው መሀል ላይ ያለው ክበብ – የንጉሠ ነገሥቱ፣ የንግሥቲቱና የሚራዷቸው የአገልጋዮቻቸውና የጠባቂዎቻቸው ቦታ ነው:: ኹለተኛው ክበብ ደግሞ፣ ዋና ዋና የጦር አበጋዞች ሙሉ ክብ ሠርተው ሰፍረውበታል:: እነዚህ ለንጉሠ ነገሥቱ በጣም የቀረቡ አዋጊ መኰንኖችና ጭፍሮቻቸው ናቸው:: ሦስተኛውና የመጨረሻው ዙር ክበብ ደግሞ የተለያዩ ራሶችን ይዟል:: እዚህ ዙር ላይ ያለው ጦር እጅግ ብዙ ነበር፡፡ ምናልባትም የዘማቹ 60 በመቶ እዚህ ዙር ላይ እንደነበረ ተጽፏል:: የቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦት ደግሞ ጊዜያዊ ማደርያ ድንኳን ተሠርቶለት በስተምሥራቅ በኩል ተተክሏል::
ይህን በሚመለከት ያገር ውስጥ ታሪክ ጸሓፊዎችና እነበርክሌይን የመሰሉ የውጭ የታሪክ ጸሓፍትም ተባብረው የመሰከሩት ነገር ደግሞ እንዲህ ይላል፡–
“የዐድዋን ዘማች የአሰፋፈር ንድፍ አውጥተው ወታደሩን ቦታ ሲያሲዙ የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መነኰሳትና ካህናት ነበሩ፤” ይሉናል:: ዲዛየኑ ከነአሰፋፈሩ ራሱ እኮ ይናገራል:: መቅደስ፣ ቅድስት፣ ቅኔ ማሕሌት – ቤተ ንጉሥ ዲዛየን እንደኾነ::
የኢትዮጵያ ሠራዊትም ሲዋጋ የነበረው በዚህ አሰላለፍ ነበር:: ሦስተኛው ዙር ላይ ያለው የራሶች ዙር የመጀመርያውን ጥይት ይተኩሳል ወይም የመጀመርያውን ማጥቃት ያከናውናል:: ይህ ዙር ሲሳሳ ቀጣዩ ዙር ወደ ውጊያው ይገባል:: ከዚያ ደግሞ በወቅቱ የተሻለ ትጥቅና ልምድ የነበረው የንጉሠ ነገሥቱ እና የንግሥቲቱ ጦር እና ፈረሰኞች ይከተላሉ:: የኢትዮጵያ ጦር ብዛት ቢኖረውም በመልክ በመልኩና የተቀመጠውም በዙር ስለነበር ንጉሠ ነገሥቱ ለማዘዝ አላስቸገራቸውም:: ጣልያንም ይሄን ሦስት ዙር ሰብሮ መግባት አልቻለም::
ለጥቁር ሕዝብና በቅኝ አገዛዝ ሥር ለነበሩ ወገኖች ኹሉ የተስፋ ብርሃን የኾነው የዐድዋ ጦርነትና ድል አንዷና በዘመኑ ቋንቋ ወሳኟ መሐንዲስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን! የነጻነታችን እናት! የኢትዮጵያ ባለውለታ! ተገቢው ክብር ይሰጣት:: ውለታዋ አይዘንጋ! ዕዳ አለብን ጎበዝ!
ያለምክኒያት አይደለም ኢጣልያ በዛሬው እለት አዲሱን መሪዋን ለመምረጥ መወሰኗ። እንደገና እንደሚመረጡም የሚጠበቁት ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ናቸው። እሳቸውም 500ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ከኢጣልያ ለማባረር ቃል ገብተዋል። ብዙ ኢትዮጵያውያን (ኤርትራውያን) ይገኙበታል።
Leave a Reply