Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

 • May 2023
  M T W T F S S
  1234567
  891011121314
  15161718192021
  22232425262728
  293031  
 • Archives

 • Categories

 • Recent Posts

Posts Tagged ‘The Universe’

The 7 Heavens – Part ll

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on March 11, 2010

2.ራማ – ራማየ ሰማየ

በዚህ በራማ ሰማይ ክልል

 • ትእልፈተ ምእላፋት የሆኑ ክዋክብትና

 • ሠላሣ ሦስት ዓለማት

አሉት።

ከሠላሣ ሦስት ዓለማት መካከል ደብረቅዱሳን የሆነው የሐዩቀዩ ዓለም ይገኝበታል። በዚህ በየሐዩቀዩ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ቅዱሳን ፍጥረት ከተፈጠሩ ጀምረው በዘለዓለም ያለመታከት እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፤ ለኃይሉም ክብር ያቀርባሉ። እንደማር ወለላና እንደወተት የመሰለ ጣፋጭና መአዛው ያማረ ባህር አለ ሁሉም በእርሱ ይረካሉ ይታደሳሉ።

3.ኢየሩየ (ኢሩያ) ሰማይ

በኢየሩይ ክልል ውስጥ በስምዋ ሰማያዊት

 • ኢየሩሳሌም

የምትባል ብሔረ ሕያዋን ዓለም አለች።

ከዚህች ዓለም ምድር የተፈጠረው አድማኤል ኪሩብ በእግዚአብሔር መልክና በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ በኢየሩይ ሰማይ ውስጥ በአድማኤል ስም ኦዶም ወደተባለች ዓለም ተወሰደ ከዚያም በክብር ሲኖር ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ከመውጣቱና ከመሳሳቱ የተነሳ ወደተፈጠረበት ዓለም ተጣለ ነገር ግን የተስፋ ዘር የሆነው ዳግማዊ አዳም ተነስቶ የአዳምን ነገድ ነፍሳት የሚሰበሰብበት የሕይወትና የምህረት ዓለም እንድትሆን አደረገ።

4.ውዱድ ዱዱያኤል ሰማይ

በዲዲያኤል ሰማይ ክልል

 • የረቀቁና የገዘፉ ታላላቅ ክዋክብቱና

 • ሃያ አንድ ዓለማት

ይኖሩበታል።

ያሬስያ የተባለው ፀሐይም በክልሉ በአሉ ፍጥረቶች ላይ ብርሃኑን ያበራል የጨለማም ጥላ ይታይበታል። ቅዱሳን መላእክትና እረቂቃን መናፍስት በሀያ አንዱ ዓለማት ውስጥ እንደንብ ሲራወዱ እንደመንጋ አእዋፍት ሲበሩና ሲንሳፈፉ ይታዩባቸዋል።

5.አርያአርያም ሰማይ

በዚህ በአርያም ሰማይ

 • የእሳት ፈሳሽ ፏፏቴ የሚፈስበት

 • የሚገለባበጥ የእሳት ነበልባል ቅጥር የተደረገበት

 • የነፋሳትና የውኃ ድምፅ የነጎድጓድም ድምፅ የመሰለ የቅዱሳን መላእክት ድምፅ የሚሰማበት

 • የብርሃናት መላእክት ለእግዚአብሔር ክብር የተሰለፉበት

 • በአንደበት በቃላት ሊነገር በምሳሌም ለማስረዳት ለመግለጽም በመጽሐፍ ሊጻፍ የማይሞክር የድንቅ የግሩም ልዩ ቅዱስ የሆነው መንበረ ፀባኦት

ይገኝበታል።

በአርያም ሰማይ የእግዚአብሔር መንግሥት ለሰው ልጆች ይታይ ዘንድ በክብርና በምስጋና ይመጣል። መንግሥቱም የዘለዓለም ሕይወት ነው። መንግሥተ ሰማይ ተብሎ ከሚጠራው ከሰማያቶች መካከል አንዱ የእግዚአብሔር መንግሥት በአርያም ነውና።

በዚህ በቅዱሱ መንበረፀባኦት ላይ የእግዚአብሔር የቃሉ ክብር ይገለጻል። ግዙፉን የሆኑ ሥጋ የለበሱና ረቂቃን የሆኑ ሁሉ ያዩታል። በፊቱም እየሰገዱ ከአንተ ከፈጣሪያችን በቀር ሌላ ቸር አባት ጌታ የለንም ለአንተ በአንተ አፍ እስትንፋስ ሁላችን ተፈጥረናል ስምህን በክብር እየጠራን እናመስግንህ ይሉታል ምህረቱና ቸርነቱ ለዘለዓለም እንደሆነ ታውቆአል።

ለዚህ ነው የአዳም ነገድ የሆነው ሁሉ እግዚአብሔርን የዘለዓለም መንግሥትህ ትምጣልንእያለ የሚጸልየውና በተስፋ የሚጠባበቀው፤ ለተመረጡት ቅዱሳን ንጹሐን ለጻድቃንም የተዘጋጀው የእግዚአብሔር መንግሥት በአርያም ሰማይ መሐልና ክልል ውስጥ በሚገኘው መንበረ ጸባኦት ስር በጽርሐ አርያም ነው። /አርያም አዳራሽ/

ጽርሐ አርያም የሕይወት ዓለም ነው፡ በአምስተኛው ሰማይ በአርያም ከመንበረፀጋኦትና ከጽርሐ አርያም በቀር ሌላ ዓለሞች የሉም።

የአዳም ዘር የሆኑት ሁሉ ፍጻሜ የሌለው ሕይወታችን በዚህ መንፈሳዊ ቅዱስ የሕይወት ዓለም ነው። የምንወርሰውም ሰማያዊ እርስታችን ብለን በተስፋ የምንጠባበቅ ትእዛዛቶቹን የፈጸምን ቅዱሳን የእግዚአብሔር ልጆች ብቻ ነን እሄውም በማይፈርሰው በመንፈሳዊ አካል እንጂ በሚፈርሰው በግዙፍ ሥጋ አካል አይደለም። በብፁዕ ሥጋዊና መንፈሳዊ አካል የሚወርሱ ከዚህ ዓለም ደስታና ጥቅም ያልተካፈሉ ብፁአን ንጹሐን የሆኑ ብቻ ናቸው እንጂ የዚህን ዓለም ኃጢአት የተካፈሉ ደምና ሥጋ ፈጽመው አይወርሱትም።

6. ኤረርኤሮርያ ሰማይ

በዚህ በስድስተኛው በኤሮርያ ሰማይ ክልል ውስጥ

 • አእላፋት ምዕልፋታት ክዋክብትና

 • ሠላሳ ሦስት ዓለማት

ይገኛሉ።

ከሠላሳ ሦስት ዓለማት መካከል እግዚአብሔርን ለካዱና እግዚአብሔርን ለማያውቁ ለአጋንንት መናፍስት ለተገዙና ለአምላኩ ሙታን ኃጥአን የተዘጋጁት የዳግመኛ ሞት ዓለሞች የጨለማ ዓለም ሲኦል የእሳት ዓለም ገሃነም የአጋንንት መናኽርያ መገናኛ በርባሮስ የፍዳና የስቃይ መፍለቂያ ዲያብሎስም የታሰረበት በርባሮስ ይገኝበታል።

እነዚሁ ከሠላሳ ሦስቱ ዓለማት መካከል አራቱ ዓለማት ለሰው ልጆች ሥጋ ለብሰው ለነበሩ አጸያፊና አስቀያሚ ነውና ከዚህ ከስቃይና ከፍዳ ዓለሞች ነጻ ለመሆን የእግዚአብሔር የቀኑ ትእዛዞችን መጠበቅ መልካም ሥራ / ስነ ምግባር እውነተኛ የሆነን እምነት መከተልና ማድረግ ነው። እውነተኛ ሃይማኖት የአለው ከሥራው ለአስተዋለው ይታወቃልና እሄውም ለሰው ልጆች ፍቅርና ሰላም የሚያመጣው ከእግዚአብሔር ነው። ከዚህ የወጣ ግን እስከፍርድ ቀን የጨለማ ዓለም ወደሆነው ወደሲኦል ይወርዳል። ከፍርድ ቀን በኋላ እንደየፍርዱና እንደየክፋቱ ለሥቃይና ለፍዳ ከሦስት ተከፍሎ ወደገሃነምና ወደ እንጦሮጦስ ወደ በርባሮስ ይጣላል። በዚያ የጩኽት የልቅሶ ብዛት ለዘለዓለም ይሆናልና ከመሆኑ በፊት የሰው ልጆች ሁሉ መልካሙን ሥታ ቢሰሩ እውነተኛውን ሃይማኖት ቢከተሉ የተሻለ እድል ነውና እግዚአብሔር በሰጠው ነጻ አእምሮ መምረጥና ማድረግ የራሱ የግሉ ውሳኔ ነው።

7. ሻዳያ ሰማይ

ይህ ሰባተኛው የሻድያ ሰማይ

 • የግዚአብሔር ግርማ መለኮት የሚገለጽበት

 • የብርሃናት ብርሃን የሆነ ክብሩ የሚይንጸባርቅበት

 • ባለሠረገላ መንኮራኩር መንበረ መንግሥተ ሰማይ (ጽርሐሰማይ) የተንሳፈፈበት በዙሪያውም እንደውኃ ጎርፍ የእሳት ማዕበል ድምፅ የሚሰማበት

 • የእሳት መንጦላዕት የተጋረደበት

 • እንደሚራወጹ የቀትር ንቦች ድምጻቸው እንደመብረቅ የሚያስደነግጡ መላእክት ብርሃናት በማህበር ዜማ ለእግዚአብሔር የክብር ምስጋና የሚያቀርቡበት

ሰማይ ነው።

እግዚአብሔር የዘለዓለም ሕይወት መንግሥቱን በሰማያት ያፀናበት የሰባቱም ሰማያት ጸጋ የገለጸበት የሰባቱ ምስጢር ይህ ነው።

እንዲሁ ለእኛ ለምድራውያን ሰባት ቀናትን የአዘጋጁልን ከሰባቱ ቀናትም መጨረሻ የሆነችውን እለት ማረፊያ ትሆነን ዘንድ እናከብራትም ዘንድ የሰባቱን ሰማያት ምሳሌ ምስጢር አደረገልን። ስለዚህ የእግዚአብሔር ምህረቱና ቸርነቱ በፍጡራኑ ላይ የበዛ ስለሆነ ስሙን በክብር እየጠራን እናመስግነው።

ሻዳይ በተባለው የምስጢር ዓለም ውስጥ የሚገቡ እርሱ ራሱ መርጦ ያዘጋጃቸው ንጹሐን ቅዱሳን ልጆቹ ብቻ ናቸው። ለዚህ የተመረጡ የዚህን ዓለም ደስታ ያልተካፈሉ ብሩሃን – ብሩካን ናቸው።

እግዚአብሔር በሰባቱ ብሩሃን ብሩካን ሰማያት ጠፈር ክልል ውስጥ መቶ ዓለማትን አእላፋተ ማእለፍታት ክዋክብትን ፈጥሮ ወደ እጣ ክፍሎቻቸው አሰፈራቸው። ለዘለዓለም በአሉበት እንዲጸኑ አደረጋቸው። ለሰባቱ ሰማያት ሠራዊቶቻቸው ይሆኑ ዘንድ ዓለማትንና ክዋክብትን እንደአደለ ሁሉ እንዲሁ ለዓለማት ሐብቶቻቸውና ሠራዊቶቻቸው ይሆኑ ዘንድ ልዩ ልዩ የሆነ የሚሳብና የሚንቀሳቀስ የሚዘልም የሚበረግግም አራዊትንና እንስሳትን በበሐርም ውስጥ የሚሳብና የሚንሳፈፍ ደማዊ ነፍስ ያለውም የበቀለም ፍጥረት በሰማይ በታች በአለ ጠፈርም የሚበሩ የአእዋፋትና የንስር ዓይነቶች እንደየወገኑ በመሬት የበቀለ በባሕርም የበቀለ የእፀዋት ዓይነት ፈጥሮ አደላቸው። ሁሉም እንደተፈጥሮው እንደየወገኑ እንደዘር ዓይነቱ ብዙ ተባዙ ብሎ ዘርን ሰጣቸው።

እግዚአብሔር በዓለማትና በከዋክብት መካከል አንዱ ፍጥረት ወደሌላው ክልልና ክበብ (ጠፈር) እንዳይተላለፍ ገደብ የአለው የተፈጥሮ ባህርይ ሰጣቸው። ስለዚህ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ደማዊ ነፍስና ለባዊ ነፍስ የአለው ፍጥረት ሁሉ ከተፈጠሩበት ዓለሞቻቸው እንዲፀኑ ተመልሰውም ወደተፈጠሩበት እንዲቀላቀሉ የእድሜ ገደብ አደረገባቸው። አንደኛው ፍጥረት ለሌላው ፍጥረት ምግቡ እንዲሆንም አዘጋጀው።

ለሕይወት እግዚአብሔር ለነፍስም ሕይወት ለአካልም ነፍስ ለደምና ለሥጋ ለአጥንትም ለተገጣጠሙት ብልቶች ሁሉ አካል እንደሚያስፈልጋቸውና በአካል አንድ ሁነው ፍላጎታቸውን እንደሚያከናውኑ ሁሉ እንዲሁ ከእግዚአብሔር ዘንድ በእግዚአብሔር ቃል ለተፈጠሩት ለመቶ ዓለማት በውስጣቸውና በውጭ የሚርመሰመስ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱትንም ሁሉ ፈጥሮ እንዲበዙም በውስጣቸው ዘርን ሰጣቸው። ሁሉም እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ሆኑ።

እግዚአብሔርም የፈጠረው ሁሉ መልካም እንደሆነ አየ። ፍጥረቱንም ብሩህ ብሩክ ሁን ብሎ ባረከው። እስትንፋስንና ሕይወትን የሚሰጠው የእግዚአብሔር መንፈስ የህይወት እስትንፋስ ተሞሉ። የስነልቦና የአእምሮ የስነቃልን ድምጽ እንደየወገናችው ተሰጣቸው። በተሰጣቸው ስነ አእምሮና ስነቃል ፈጣሪያችን አንድ አምላክ እግዚአብሔር እንደሆነ ስሙን አውቀው በክብር አመሰገኑት።

ከመጀመሪያው ከፍጥረቱ አስቀድሞ ከእርሱ ዘንድ ጥበብ ተወለደ። ወላጅና ተወላጅ በፍጥረቱ ዘንድ ታወቀ፤ ከበረ ከፍ ከፍም አለ።

ጥበብም በእውቀት ከበረ በማስተዋልም ሰማያትን ዘርግቶአልና በውስጣቸውም ዓለማትን ፈጥሮ አፅንቶአልና የፈጠረው ሁሉ ከእርሱ ሰለተፈጠረ ለእርሱ ሆነ። ለእርሱ የሆነውን የመረጠውን ብሩህ – ብሩክ ቅዱስ ሲለው ፈጣሪውን በራሱ ድምጽና ቃና የሚያመሰግንበት የልሳን አንደበት አደለው። የፈለገውንም የሚመርጥበት አእምሮ ክፉንና ደጉን የሚለይበት ህሊና እርሱ ማን ወይስ ምን እንደሆነና የአለበትን ሠፈር ቦታ ወይም የአቅሙን ገደብ የሚለካበት ስነ ልቡናን ሰጠው።

በተሰጠው ስጦታ የማይጠቀም ፍጥረት ካለ የከንቱ ከንቱ ኢምንት ነው። የእጣው እድልም ጥፋትና ስህተት ነውና እሄውም ሰይጣን ሆነ ማለት ተሳሳተ ጠፋ ማለት ነውና።

__________________________________________________________________

የሰባቱ ሰማያት ስም ዓለሞቻቸው
1 ኢዮር (አየር) አሥራ ሁለት 12
2 ራማ ራማየ ሠላሳ ሦስት 33
3 ኢየሩይ (ሰማያዊት ኢየሩሳሌም/ጌልጌል) አንድ 1
4 ውዱድ ዲድያኤል ሃያ አንድ 21
5 አርያ – አርያም (መንበረ ጸባኦት ያለበት) 0 0
6 ኤረር ኢሮርያ ሠላሣ ሦስት 33
7 ሻዳይ ኤልሻዳይ (የሕይወት ምንጭ የአለበት፡ ስሙም ጔልጔል ይባላል) 0 0

___________________________________________________________________

Posted in Ethiopia | Tagged: , , , , , , | Leave a Comment »

The 7 Heavens: The 12 Worlds of Eyor Heaven

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on January 22, 2010

አዮር ሰማይ ክልል ውስጥ የአሉት አሥራ ሁለት ዓለሞች


 1. ሐመልማል

  ይህ የምድር ሠራዊት እንሆን ዘንድ እኛ የተፈጠርንበት ዓለም ነው። ጠባቂውና እንዲሰለጥንበት እግዚአብሔር የፈቀደለት አድማኤል ኪሩብ ይባላል። የአዳም ነገድ ሁሉ ከእርሱ አብራክ ወጥቶአል።

 2. ረሐም

  የዚህ ዓለም ጠባቂ መልአክ ሳውራኤል ኪሩብ ነው። በዓለም ረሐም ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረቶች የበግና የፍየል መልክ የመሰለ ገፅ ሲኖራቸው የተሰጣቸው አእምሮ ከሰው ልጆች የላቀ የራቀውን የሚያውቁ የረቀቀውን የእግዚአብሔር ፍጥረትን ማየት የሚችሉ ናቸው። ከነርሱም ሌላ በረሐም ዓለም ውስጥ የተለያዩ ገጽ ያላቸው ቁጥራቸው ትእልፈተትእልፊታት ፍጥረታቶች አሉ።

 3. ገውዛ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው ኪሩብ መልአክ ሱርያኤል ነው። ገውዛውያን መልካቸው እንደ ሰው ልጆች መልክ ሁኖ ቀንድና ጅራት አላቸው። የጅንጆሮና የጉሬዛ መልክ የመሰለ የአላቸውም አሉ። ሁሉም ሁለት እጆችና ሁለለት እግር አሏቸው እንዲሁ ግዙፋንና እረቂቃን የሆኑ በራሪዎች ይኖሩባቸዋል። እርስ በእርሳቸው አይነካኩም የሳውራ አፈር ቅመው ይኖራሉ።

 4. ሻርታ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው ኪሩብ መልአክ ስርጣጣኤል ይባላል። በሻርታ ዓለም የሚኖሩ ፍጥረቶች እንደ ዳሞትራ ስምንት እግሮች የአላቸው የአንበጣ ገጽ ያላቸው ምግባቸው እርስ በእርስ በመበላላት አንዳንዶችም እንደ እባብ የሚያሸቱበት አፍንጫ ባይኖራቸውም በምላሳቸው መካከል በአለ ቀዳዳ ያሸታሉ፡ በምላሳቸው ይነድፋሉ፡ ያያሉም፡ በየጊዜው ተፈጥረው የሚሞቱ ፍጥረቶች ናቸው።

 5. ሰውድ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ኪሩብ አዛዝኤል ይባላል፡ ሰውዳውያን ወደዚህ ዓለምና ወደ ሌላው ዓለም ለመንጠቅ እድል ተሰጥቷቸዋል። በሄዱበት ምድር ያለውን እፅዋት ያደርቃሉ፤ እሳተ ገሞራ ይፈጥራሉ፤ ተንቀሳቃሹን ሁሉ በነፋስ ያደርቁታል፤ እግዚአብሔር ለመቅሰፍት ያዘጋጃቸው ናቸው። ምግባቸው የሚቃጠል ዲንና ባሩድ የመሰለ ነው፡ ነገር ግን በሄዱበት ዓለም እንዲኖሩ እግዚአብሔር ስላልፈቀደላቸው ተመልሰው ወደተፈጠሩበት ዓለም ይሄዳሉ እንጂ

 6. ሰንባላ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአኩ ኪሩብ ስምስማኤል ይባላል። በሰንበላውያ ዓለም ትእልፊተትእልፊታት የሚሆኑ በአየር የሚንሳፈፉና የሚበሩ በምድር የሚሽከረከሩ አእዋፋትና እንስሳት አራዊትም አሉ። እንደነዚህ ምድር ዓለም እርስ በእርሱ ይጣላል፤ ይበላላልም። ነገር ግን የማይበላሉ አሉ እነርሱም እድሜያቸው በእነሱ አቆጣጠር ከመቶ እስከ አራት መቶ ይደርሳል። ነገር ግን የእኛ ዘመንና የሰንበላውያን ዘመን የተለየ ነው።

 7. ሚሳን

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ሚሳኤል ይባላል። የሚሳውያን መልካቸው የእንስሳና የአውሬ መልክ ይምሰል እንጂ የተፈጥሮ ባህሪያቸው ቅዱስ ነው። እግዚአብሔርን በክብር ያመሰግናሉ ይዘምራሉም። ከኤሮርያ ሰማይ ክልል ውስጥ ከሜምሮስ ዓለም ክበብ ውስጥ የሚኖሩትን ሮሃንያን ይመስላሉ /ረውሃንያ/ የተለያዩ የዜማ ድምፅ መሥሪያዎች አሏቸው።

  አንዳንድ ግዜ ወደ እኛ ዓለም ምድር ይመጣሉ፤ የሚከለክላቸው የዓየር ጠባይ የለም፤ ግዙፋንም እረቂቃንም አሉአቸው። በባሕር ቢሄዱ አይሰጡም በእሳተ ገሞራ ቢገቡ አይቃጠሉም አለቱን ሰንጥቀው ቢገቡ የሚያግዳቸው የለም፡ የእግዚአብሔርን ፍጥረት ያከብራሉ የሰው ልጆችን ይወዳሉ እግዚአብሔርን ከማመስገን አፋቸው አይቋረጥም።

 8. አቅራብ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ አቅርናኤል ይባላል። በዓለም አቅራብ ውስጥ የሚኖሩት ፍጥረታት በባሕር ውስጥ ይኖራሉ። የመልካቸው ገጽ የዝሆንና የጊንጥ ቅርፅ አላቸው። የተለያዩ የፍጥረት ነገዶች አሉ ሁሉም በበሐር ውስጥ እንጂ ወደሌላ የአፈርና የእሳት ጠባይ ወደአላቸው አይሄዱም አይኖሩምም።

 9. ቀውሳ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ቀውቃሳኤል ኪሩብ ይባላል። በቀውሳ መሬት የሚኖሩ ከእሳት ተፈጥረው ከእሳት ፈሳሽ ውስጥ ስለሚኖሩ ብዛታቸው እንደሌሎች ዓለም ፍጥረት አይበዙም ቀውሳውያን የአገኙትን ይመገባሉ ያቃጥላሉ የእሳት ሕይወት ነው ያላቸው።

 10. ዠዲ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ አጂብጀማኤል ይባላል። በጀዲ ወይም በዠዲ ዓለም የሚኖሩ ፍጥረታት ከዚህች ምድር ዓለም የተፈጠሩትን እንስሳትና አራዊት አእዋፋትንም ይመስላሉ። በመልክ በግጽ እርስ በእርሳቸው የተለያዩም ቢሆን በልሳን ቋንቋ አንድ ናቸው በተለያየ የድምፅ መሳሪያ ይጠቀማሉ። ከሰው ልጆች የላቀ አእምሮ ስላላቸው የተጠበቡ መርማሪዎች ናቸው። በሰሩት የጥበብ መንኮራኵር ብዙ ዓለማትን ጎብኝተዋል ነገር ግን ከተፈጠሩበት ከዠዲ ዓለም ተለይተው ስለማይኖሩ ወደ መጡበት ተመልሰው ይሄሃሉ። ምግባቸውን እንደ ሰው ልጅ አብስለው የሚበሉና በመአዛው ብቻ የሚረኩ ነገዶች አሉአቸው እግዚአብሔርን በጣም ያመሰግናሉ።

 11. ደለዋ

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ደለዋውኤል ኪሩብ ይባላል። ይህ ደለዋ ዓለም የክበቡ ጥልቀት በጣም የጠቆረ ጨለማ ከመሆኑ የተነሳ እንደበርባሮስ የሚያስፈራ ነው። ነገር ግን በውስጡ የሚኖሩ እልፍ አእላፋትና ትእልፊተ አእላፋት የሚሆኑ ፍጥረታት በትናጋቸውና በምላሳቸው በማሽተት የሚፈልጉትን መርጠው ይበላሉ።

  በጆሮአቸው በዓይናቸው ፈንታ በምላሳቸው እንዲያዩና እንዲሰሙ እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ጨለማንና ብርሃንን ለይተው አያውቁም።

 12. ሁት

  የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ኩምኩማኤል ይባላል። በሁት ዓለም የሚኖሩ ፍጥረቶች እንደንብ መንጋ በአንድ ላይ የሚሰፈሩ እንደተራራም ይከመራሉ፤ ከመካከላቸው እንደንብ ወይም እንደምስጥ አንዲት እናት አላቸው። እናቲቱ እድሜዋ አልቆ ከሞተች ሁሉም በነው ያልቃሉ አፈር ይሆናሉ፤ ሕይወታቸው በእንስቲቱ ብቻ ነው ከነሱ ሌላ ሕይወት ያለው ፍጥረት የለም።

  በኢዮር ክበብ ውስጥ ያሉት አስራ ሁለት ዓለማት እነዚህ ናቸው። የአእምሮ መንፈስ የአለው አስተውሎ ይመርምርና ይወቅ ጥበብ በዚህ አለ።

______________________________

Posted in Curiosity, Ethiopia | Tagged: , , , , , , , , | Leave a Comment »

 
%d bloggers like this: