ከ አማረ አፈለ ብሻው
በትንቢተ አሞጽ ምዕራፍ9 ቁ. 7፡ “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን ልጆች አይደላችሁምን?” ሲል የተናገረው ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሔርን የሚያከብሩ መሆናቸውን በመረዳት ነው። በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስ በትንቢቱ መሠረት በቤተልሔም ሲወለድ የሰገዱለት ሰብዓ ሰገል ኢትዮጵያውያን ናቸው። ቀደም ሲል ኢትዮጵያውያን እንደሚሰግዱለት በታሪክ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይቀር ተጠቅሶ ይገኛል።
መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 72 ቁ. 9፡ “በፊቱም ኢትዮጵያውያን ይሰግዳሉ ጣላቶቹም አፈር ይልሳሉ፤ የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዐረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻ ያቀርባሉ” ተብሎ የተጻፈው ይፈጸም ዘንድ ከኢትዮጵያውያን የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? እያለ ወደ እስራኤል ተጓዙ። ኢትዮጵያውያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ ይጠባበቁ ስለነበር መወለዱን ሲያውቁ ከርቤ፡ ወርቅና ዕጣን አበርክተው ሰግደውለታል። ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ጀምሮ የዓለም ንጉሥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብስረዋል። ቀደም ሲል የአውሮፓ ደራስያን ሊቀበሉ አልፈለጉም ነበር። አሁን ግን ቀስ እያሉ ወደ እውነቱ በመምጣት ላይ ናቸው። ከሦስቱ ሰብዓ ሰገል አንደኛው (ባልታዛር) ኢትዮጵያዊ መሆኑን መናገር ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ዛሬስ እንዲያውም እስከ ጋሻ ጦሩ ሥለው አውጥተውታል።
“The Lost Book of The Bible” የተባለው መጽሐፍ ገጽ 40 ላይ የሚያመለክተው ሥዕል አንዱ ብቻ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ሲሆን ሁለቱ ግን ኢትዮጵያዊ ለዛ ያላቸው አይደሉም። ከዚህ ታሪክ ጋር ሊመሳሰል የሚችል ሌላ ታሪክ መኖሩን ደግሞ ልገልጽ ፈለግሁ። ምክኒያቱም ሁለቱንም መጽሐፍ ያላገኘው ሰው በዚያው መተማመን እንደሌለበትና ተመሳሳይ የሆነ ሌሎችን ሊያሳስት የሚችል በመሆኑ አብሮ ማቅረቡን ትክክል መስሎ ስለታየኝ ይህን ለመጥቀስ ወሰንኩ።
“ተውፊታዊ ሐሳብ ዘመንና ታሪክ” ገጽ 37 “ለጌታ ልደት ወደ ቤተልሔም ከሄዱት ከነገስታተ ፋርስ መካከል ከጥበብ ሰዎች አንዱ ኢትዮጵያዊ እንደነበረ ከኢትዮጵያውያን ደራሲያን ጽሑፎች እናገኛለን” ሲሉ ጽፈዋል። ምናልባት የእኚህ ደራሲ አባባል ከውጭ አገር የታሪክ መጽሐፍት ጋር በተለይም ከላይ ከተጠቀሰው መጽሐፍ ጋር ተቀራራቢ ነው እንጂ በኢትዮጵያውያን ደራሲያን ግን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለው ነው የሚያስተምርቱ። ስለዚህ አንዱ ብቻ ሳይሆን ሦስቱም ንጉሦች ኢትዮጵያውያን ናቸው።
የጥንት ኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ የተባለው መጽሐፍ ገጽ 126 “ከኢትዮጵያ ከሚወለዱ የእግዚአብሔር ካህናት በየጊዜው በመንፈስ ተናገሩ። ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ በምሥራቅ በኩል እግዚአብሔር ምልክትን እሳየ ስለዚህ ነው ሁሉም በየራሱ ከሶስት ላይ ወደ ኢየሩሳሌም የወረዱ” ይሉና “በኮከብ ብርሃን እየተመሩ ከተወለደበት ደረሱ። ወደ ቤት ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት። ወድቀውም ሰገዱለት ሣጥናቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና እጣን፡ ከርቤ ከወርቅ ሃመልማል የተሰራ እጅ ጠባብ አቀረቡለት። ለእናቱም አንቆአርያውን ዮጵን ሉል የከበረ ድንጋይ ከወርቅ ሃመልማል የተሰራ መጎናጸፊያ ሰንደል እንጨት አድርገው ሰጧት” ሲሉ ጽፈዋል።
ገብረ ዮሐንስ ገብረ ማርያም፡ ክርስትና በኢትዮጵያ በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 52 “ጌታ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ከምሥራቅ መምጣታቸው በአዲስ ኪዳን የተነገረላቸው ሰብዓ ሰገል ከኢትዮጵያ እንደሄዱ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በትውፊታዊ አባባላቸው ይተርካሉ” ሲሉ ጽፈዋል። ሱባኤ የተገባለት ትንቢት የተነገረለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ኢትዮጵያውያን ሰግደውለታል።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኢትዮጵያዊ መዐሆናቸውን አልጻፈም። እነርሱ የጻፉት ማቴዎስ ወንጌል ም. 2 ቁ. 1 “የከዋክብት ተመራማሪዎች ከምስራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ” የሚል ነው። ከኢየሩሳሌም ምሥራቅ ኢትዮጵያ እንጂ አውሮፓ ወይም ሕንድ አሊያም አሜሪካን አይደለም።
መሪራስ አማን በላይ በጉግሣ መጽሔት ቅጽ. 3 ቁጥር 1 ሐምሌ 1993 ዓ.ም ገጽ 29 “በዚህን ጊዜ በደሽት ከተማ በንጅ ጎጃም የሚቀመጠው በተስፋ ሲጠባበቅ የነበረው ‘እጎጃ ጃቦን ዮጵ‘ የሚባለውን ሉል ድንጋይ፡ የወርቅ ሐመልማል ማለት ወርቁን እንደ ሰፌድ ሆኖ የተሰራውን ይዞ በበፉ ሶስት ንጉሶች አስከትሎ፡ ከጣና ደሴት ተነስቶ ኮከቡ ወደሚያመለክትባት ምድር ጉዞአቸውን ቀጠሉ።
“አጎጅ የዳቦ አማኣአናቱ የአማራ ጎሳ። ከአናርያ ዙባ ከተማ የሚቀመጠው የመደባይ ጎሣ የደርጊያ የሰገል የማጂና የአራመን ንጉሥ መጋል ከኤውላጥ ንጉሥ መካድሼ ከአቢል ንጉሥ አውር ከአፈር አፍሪካ ንጉሥ ሙርኖ ጋር ሆኖ ከወርቅ ሐመልማል የተሰራ መጎናጸፊያ እጀጠባብ የሰንደል እንጨትና ዕጣን ከርቤም የከበረውን ሉል ወርቅ ይዞ ኮከቡ ወደሚያመለክተው ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም በጥንቱ ናግራ ኤደን በዛሬው የመን አድርጎ ጉዞውን ቀጠለ።
የገዳዲ ልጅ ዲዳ ስፍ የኦሮሞ ጎሳ፡ ከዋይዝ ከተማ በቀርሴስ ደሴት በዛሬው አፋር የሚቀመጠው የአዜባውያን አዛል–አዳኣዓል የአፍርሴካውያን ንጉሥ አጋቦን በኢንኤ ጊዜር ከአውባው ንጉሥ ሳዱንያ ባል ሜሌኩ አቡል ሰላም ከሳባ ከተማ የሚቀመጠው አርስጣ ጋር ሆነው ወርቅና ዕጣን ከርቤም ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ቀይ ባሕርን ተሻግረው በምሥራቅ በኩል ወጦ ብርሀኑ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገውን ኮከብ አየተው ጉዞአቸውን ቀጠሉ።
“አፍርስካ አፍርስካውያን የሆኑ እነዚህ ንጉሦች ሁሉም ዘውድ የደፉ ናቸው። ለእነዚህ ለአስራ ሁለቱ ንጉሦች የበላያቸው በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አክሱም የሚቀመጠው ንጉሥ ነገሥት አጤ ባዜን ነው። እነዚህ ንጉሦች በግመሎቻቸውና በፈረሶቻቸው በምድራቸው የእህል የወርቅ የከርቤና የዕጣን ዓይነቶችና ልዩ ልዩ ልብሶች ገፀ በረከቶች ይዘው የንጋቱ ኮከብ ብርሃኑን ለሚያመለዐከታቸው የሰላም ንጉሥ ጋዳ ገፀ–በረከት ለማቅረብ ጉዞ ቀጠሉ” ሲሉ ጽፈዋል። ይህ ታሪክ ትክክል መሆኑ የዓለም ሕዝብ ሁሉም ያውቃል ባይባልም አልፎ አልፎ የማያውቅ ያለ አይመስለኝም። በተለይም የአፍሪካ ምሁራኖች ሰብዓ ሰገል አፍሪካዊ መሆናቸው በቅኔ ድርሰታቸውና በየአደባባዩ ታሪኩን ሲናገሩ መኖራቸውን አይካድም።
ፀጋዬ ገብረ መድህን ኣርኣያ ጦቢያ መጽሔት ቁጥር 4፡ 1995 ዓ.ም ገጽ 5 “የሴኔጋል ፈላስፋ፣ ዲፕሎማትና ባለቅኔ፡ ሴዳር ሲንጎር፡ የአፍሪካ ልደት ሲከበርና አህጉራዊ ድርጅታቸው ሲፈጠር ሰብዓ ሰገል ከምሥራቅ የመጡ ብልህ ሰዎች “The Wisemen of Africa” እስከመባል ደርሰው እንደነበር እናስታውሳለን” ሲሉ ጽፈዋል። ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ብዙ የምንይዝላቸው ያልተጻፈ ታሪክ አላቸው። እኛ የሩቅ አድናቂዎች የቅርብ ናቂዎች ሆንን እንጂ ሰብዓ ሰገል 12 ንጉሦች ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ቃለ ዓዋዲ የተባለው መጽሔት ቁጥር 2 ሚያዝያ 1990 ዓ.ም ገጽ 5 “ኢትዮጵያ በኮከብ እየተመራች ኢየሩሳሌም ድረስ ሄዳ ከፈጣሪዋ ተዋውቃ በአይነ መንፈስ ታየው፡ ትናፍቀው የነበረውን አምላክ በዓይነ–ሥጋ ለይታ መመለሷ ነው” ይልና “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወደየት ነው ብላ የጠየቀቻት ኢየሩሳሌም ወደ ቤተልሔም ሄደሽ ፈልጊ ብላ የተዘባበተችበትን ያህል በበረት የተኛውን አምላክ ሳትንቅ ሳታቃልል ከስግደት ጋር የተፈቀደላትን እጅ መንሻ በማቅረብ ሞቱን መንግሥቱን አምላክነቱን መስክራ ጠላቶቹን አሳፍራ ሃይማኖቷን አድሳ ታሪኩን ቀድሳ” ሲል ተጽፎ የሚነበበው ትልቅ ማስረጃ ነው።