የ
ጲላጦስ ዐደባባይ /ገበታ/
የመጀመሪያው ምዕራፍ፤ ጌታ ከጲላጦስ ፊት ለፍርድ የቆመበት ዐደባባይ ነው፡፡ ስሙም በዕብራይስጥ ገበታ፣ በግሪክ ሊቶስጥራ ይባላል፡፡
ጌታ የተገረፈበት
ሁለተኛው ምዕራፍ፤ ከሊቶስጥራ ወጥቶ ወደ ጌቴ ሴማኒ የሚወስደውን መንገድ ተሻግሮ ጲላጦስ ጌታን ገርፎ ያ ሰው ያውላችሁ ያለበት ነው፡፡ የቦታው ስም እስከ ዛሬ ጌታ የተገረፈበት ይባላል፡፡ በቦታው ላቲኖች ገዳም ሠርተውበታል፡፡
ጌታ በመጀመሪያ የወደቀበት ቦታ
ሦስተኛው ምዕራፍ፤ የቀደመውን ሥፍራ ወደኋላ ትቶ ወደ ምዕራብ የሚወስደውን መንገድ ይዞ በደማስቆ በር መግቢያ የአርመን ቤተ ክርስቲያን ያለበት በሩ በብረት የታጠረ ትንሽ ክፍል ነው፡፡ ጌታ ከዚህ ሲደርስ ከግርፋቱ ጽናት እና ከመስቀሉ ክብደት የተነሣ የወደቀበት ነው፡፡ ስለዚህ ቦታው ጌታ በመጀመሪያ የወደቀበት ይባላል፡፡
እመቤታችን እያለቀሰች ልጇን ያገኘችበት ቦታ
አራተኛው ምዕራፍ፤ ከሦስተኛ ምዕራፍ ትንሽ ዝቅ ብሎ ከአርመን ገዳም በስተግራ ካለው ማዕዘን ሲደርሱ እናቱ ድንግል ማርያም እያለቀሰች ከልጅዋ ጋር የተገናኘችበት ቦታ ነው፡፡
ቀሬናዊ ስምዖን የጌታን መስቀል የተሸከመበት ቦታ
አምስተኛው ምዕራፍ፤ ከአራተኛው ሃያ ሜትር ያህል ወደ ደቡብ አቅጣጫ ከተጓዙ በኋላ ወደ ቀኝ የሚታጠፈው መንገድ ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ስምዖን ቀሬናዊ የሚባል ሰው ከእርሻ ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ ወታደሮች አግኝተውት አስገድደው እየጎተቱ ወስደው የጌታን መስቀል ያሸከሙበት ቦታ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ተግባር በወታደሮቹ ዘንድ የተለመደ ነበርና፤ በዚህ ቦታ ላቲኖች ትንሽ መቅደስ ሠርተውበታል፤ የስምዖን መቅደስ ይባላል፡፡
ይህ ስምዖን የተባለው ሰው የእስክንድሮስና የሩፎን አባት ነው፡፡ ማር. 15፤21፡፡ ጳውሎስም በሮሜ መልእክቱ 16፤13 በሰላምታው ውስጥ ሩፎን ያነሣዋል፡፡ እነዚህ ሁለቱ ልጆቹ ቁጥራቸው ከሰባ ሁለት አርድእት ነው፡፡ ይህ ሰው ምንም እንኳን ተገድዶ ቢሆንም የጌታን መስቀል በመሸከሙ የበረከተ መስቀሉ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ ስለ ሆነም ዕድለኛ ሰው ነው፡፡
ቤሮና /ስራጵታ/ በመሐረብ የጌታን ፊት የጠረገችበት ቦታ
ስድስተኛው ምዕራፍ፤ ቤሮና /ስራጵታ/ የምትባል ሴት ከግርፋቱ ጽናት፣ ከመስቀሉ ክብደት የተነሣ ፊቱን የደም ወዝ አልብሶት ስታየው አዝና ፊቱን በነጭ መሐረብ ስትጠርግለት ወዲያውኑ አምላክነቱን የሚገልጥ፣ ለበጎ ሥራዋም ተስፋ የሚሰጥ፣ ሃይማኖቷን የሚያበረታታ የፊቱ መልክ
በመሐረቡ ላይ ተገኘ፡፡ እሷም በዚህ ምክንያት እምነቷ እጅግ የጸና ሆነ፡፡
ታሪኳን ወይም በጎ ሥራዋን የሚናገር ወንጌላውያን በጻፉት ወንጌል አይገኝም፡፡ ነገር ግን ታሪኳን የተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ይናገሩላታል፡፡ አንዳንድ አባቶችም ስለዚች ሴት ሲናገሩ ለዐሥራ ሁለት ዓመታት ያህል ደም ሲፈሳት ቆይታ የጌታን ልብስ ጫፍ በመዳሰሷ የዳነችው ሴት ናት ይላሉ፡፡ በዚህ በስድስተኛው ምዕራፍ ላይ ግሪኮች መቅደስ ሠርተውበታል፣ ዓርብ ዓርብ በየሳምንቱ ይከፈታል፡፡
የጎልጎታ መቃረቢያ
ሰባተኛው ምዕራፍ፣ ከስድስተኛው በግምት አንድ መቶ ሜትር ያህል ተጉዞ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በሚወስደው መንገድ ከሰሜን አቅጣጫ መጥቶ ወደ ጽርሐ ጽዮን በሚያሳልፈው መካከለኛ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ በጌታችን ዘመን የከተማው መጨረሻ የምዕራቡ በር ይህ ነበር ይባላል፡፡ በዚህም ቦታ ትንሽ መቅደስ አለበት፡፡ በውስጡ በቀድሞ ዘመን የነበሩ አዕማድ ናቸው እያሉ ያሳያሉ፡፡ መቅደሱ የላቲኖች ነው፡፡ እንደ ታሪኩ ቦታው ጥንት የከተማው በር ነበረ ይባላል፣ እንደዚህ ከሆነ ጎልጎታ ከከተማው በጣም ሩቅ አልነበረም፡፡
የጌታችንን ሥቃይ ሴቶች አይተው ያለቀሱበት ቦታ
ስምንተኛው ምዕራፍ፣ ከሰባተኛው ምዕራፍ በዐሥራ አምስት ሜትር ያህል ወደ ላይ ወጣ ብሎ ይገኛል፡፡ ጌታ መስቀሉን ተሸክሞ መከራ መስቀልን እየተቀበለ ሲሔድ ሴቶች አይተው እያለቀሱ ይከተሉት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ጌታችን ወደነሱ መለስ ብሎ፣ እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ለኔ ማልቀሳችሁ ቀርቶ ለራሳችሁ አልቅሱ ያለበት ቦታ ነው፡፡ ሉቃ.ሉቃ.23;27:: ጌታ ይህን ማለቱ ከአርባ ዘመን በኋላ የሚመጣባቸውን መከራ በትንቢት ሲነግራቸው ነው፡፡ በዚህ ቦታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሆኑ የመነኮሳት መኖሪያ አራት ቤቶች አሉ፡፡
መስቀል ይዞ የወደቀበት
በዘጠነኛው ምዕራፍ አንድ የቆመ የድንጋይ ዓምድ አለበት፡፡ በዚህ ቦታ ጌታ መስቀል ይዞ ወድቆበታል፡፡ ይህ ቦታ ወደ ጎልጎታ መውጪያ በር ሲሆን፣ ቦታው የኢትዮጵያ ገዳማት መግቢያ በር ነው፡፡
ልብሱን የገፈፉበት
ዐሥረኛው ምዕራፍ፣ የጌታችን ልብስ የገፈፉበት ቦታ ነው፡፡
ጌታን የቸነከሩበት
ዐሥራ አንደኛው ምዕራፍ ጌታን ልብሱን ገፍፈው ዕርቃኑን ካስቀሩት በኋላ እጆቹንና እግሮቹን በምስማር የቸነከሩበት ቦታ ነው፡፡
ቅዱስ ሥጋውን ያወረዱበት ቦታ
ዐሥራ ሦስተኛ ምዕራፍ እነ ኒቆዲሞስ ጌታን ከመስቀል ያወረዱበት እና ያሳረፉበት ቦታ ነው፡፡
ቅዱስ ሥጋውን የገነዙበት ቦታ
ዐሥራ አራተኛው ምዕራፍ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የጌታን ቅዱስ ሥጋ የገነዙበት ቦታ ነው፡፡
ቅዱስ ሥጋው የተቀበረበት ቦታ
ዐሥራ አምስተኛው ምዕራፍ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የጌታን ቅዱስ ሥጋውን በአዲስ መቃብር ያሳረፉበት ቦታ ነው፡፡ በአጠቃላይ የፍኖተ መስቀል ምዕራፎች እነዚህ ናቸው፡፡
ምንጭ
__
Like this:
Like Loading...