❖❖❖ መዝሙረ ዳዊት ከ ምዕራፍ ፻፩ እስከ ምዕራፍ ፻፭ ❖❖❖
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻፭]
፩ ሃሌ ሉያ፤ ቸር ነውና፥ ምህረቱም ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ።
፪ የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማን ይናገራል? ምስጋናውንስ ሁሉ ማን ያሰማል?
፫ ፍርድን የሚጠብቁ፥ ጽድቅንም ሁልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው።
፬ አቤቱ፥ በሕዝብህ ሞገስ አስበን፥ በመድኃኒትህም ጐብኘን፤
፭ የመረጥሃቸውን በጎነት እናይ ዘንድ፥ በሕዝብህም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ፥ ከርስትህም ጋር እንጓደድ ዘንድ።
፮ ከአባቶቻችን ጋር ኃጢአትን ሠራን፥ ዐመፅንም፥ በደልንም።
፯ አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትህን አላስተዋሉም፥ የምሕረትህንም ብዛት አላሰቡም፤ በኤርትራ ባሕር ባለፉ ጊዜ ዐመፁብህ።
፰ ኃይሉን ግን ለማስታወቅ። ስለ ስሙ አዳናቸው።
፱ የኤርትራንም ባሕር ገሠጸ እርሱም ደረቀ፤ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው።
፲ ከሚጠሉአቸውም እጅ አዳናቸው፥ ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው።
፲፩ ያሳደዱአቸውንም ውኃ ደፈናቸው፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም።
፲፪ በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ፥ ምስጋናውንም ዘመሩ።
፲፫ ፈጥነውም ሥራውን ረሱ፥ በምክሩም አልታገሡም።
፲፬ በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ፥ በበረሃም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት።
፲፭ የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።
፲፮ ሙሴንም እግዚአብሔር የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኙአቸው።
፲፯ ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው፥ የአቤሮንንም ወገን ደፈነች፤
፲፰ በማኅበራቸውም እሳት ነደደች፥ ነበልባልም ኅጥኣንን አቃጠላቸው።
፲፱ በኮሬብም ጥጃን ሠሩ፥ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ።
፳ ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ።
፳፩-፳፪ ታላቅ ነገርንም በግብጽ፥ ድንቅንም በካራን ምድር፥ ግሩም ነገርንም በኤርትራ ባሕር ያደረገውን ያዳናቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ።
፳፫ እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ።
፳፬ የተወደደችውን ምድር ናቁ፥ በቃሉም አልታመኑም፥
፳፭ በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም።
፳፮-፳፯ በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ፥ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ፥ በየአገሩም ይበትናቸው ዘንድ፥ እጁን አነሣባቸው።
፳፰ በብዔል ፌጎርም ተባበሩበት፥ የሙታንንም መሥዋዕት በሉ።
፳፱ በሥራቸውም አስመረሩት፥ ቸነፈርም በላያቸው በዛ።
፴ ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፥ ቸነፈሩም ተወ፤
፴፩ ያም እስከ ዘላለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።
፴፪-፴፫ በክርክር ውኃ ዘንድም አስቈጡት፥ መንፈሱን አስመርረዋታልና፤ ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ፤ በከንፈሮቹም በስንፍና ተናገረ።
፴፬ እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም፤
፴፭ ከአሕዛብም ጋር ተደባለቁ፥ ሥራቸውንም ተማሩ።
፴፮ ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ፥ ወጥመድም ሆኑባቸው።
፴፯ ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠው፤
፴፰ የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻቸን ደም፥ ለከነዓን ጣዖቶች የሠውአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ፥ ምድርም በደም ረከሰች።
፴፱ በሥራቸው ረከሱ፥ በማድረጋቸውም አመነዘሩ።
፵ የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፥ ርስቱንም ተጸየፈ።
፵፩ ወደ አሕዛብም እጅ አሳለፋቸው፥ የሚጠሉአቸውም ገዙአቸው።
፵፪ ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው፥ ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ።
፵፫ ብዙ ጊዜ አዳናቸው፤ ነገር ግን በምክራቸው አስመረሩት፥ በኃጢአታቸውም ተዋረዱ።
፵፬ እርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ፤
፵፭ ለእነርሱም ኪዳኑን አሰበ፥ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ።
፵፮ በማረኩአቸውም ሁሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው።
፵፯ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን።
፵፰ ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ ሕዝብም ሁሉ አሜን ይበል። ሃሌ ሉያ።
________________________