በጣም ሊጠቅሙንና ከፍተኛ ትኩረትም ሊሰጣቸው የሚችሉት ነገሮች በዓይኖቻችን ብርሃን ሊታዩ የሚችሉት ነገሮች አይደሉም። ልብ ብለን ከታዘብን፡ ዓይናችን፡ አንዳንድ ጊዜ፡ ነጩን ጥቁር፡ ቀዩን ቢጫ እያስመሰለ ሊያታልለን፡ ሊያወናብደንና መስመሩን ሊያስተን ይችላል።
ብዙ ጊዜ እንደ ምሳሌነት የምናያቸው የፖለቲካ፡ የኃይማኖት እንዲሁም የተለያዩ ተቋማት መሪዎች የሕብረተሰቡን ታሪካዊ እጣ ተቀብለው ከሕዝቦች ጋር አብረው ለመጓዝ በ “እድል” የተመረጡና እንዲታዩ የተደረጉ አገልጋይ መሪዎች ናቸው እንጂ ከሌላው በልጠው የተለየ ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ ተደርገው የተፈጠሩ ልዩና ከጠፈር የተገኙ መሪዎች አይደሉም። ሃቁን ለመናገር፡ ለሕብረተሰቡ የሚኖራቸው አስተዋጽኦም ቢሆን ምናልባት እያንዳንዳችን የአዳም ልጆች ሊኖረን ከሚችለው አስተዋጽኦ ብዙም የተለየ አይሆንም። እንዲያውም አንዳንድ በተለያዩ ተቋማትና መንግሥታት በመሪነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች ለዓለማችን ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽኦ አንዲት የጓሯችን ቢራቢሮ ልታበረክተው ከምትችለው አስተዋጽኦ እምብዛም አይበልጥም።
ፈጣሪያችን በዚህች ምድር ላይ የሚታየውንና የማይታየውን ነገር ፈጥሯል። እኛ የአዳም ዘሮች በአይናችን በማየት፡ በአፍንጫችን በማሽተት ወይም በምላሳችን በመቅመስ፡ በአካባቢያችን የሚገኘውን ተፈጥሮአዊ ክስተት ምናልባት 5% የሚሆነው ነገር ላይ ብቻ ነው ልንደርስበት የምንችለው። ማለትም፤ የተቀረው 95% ነገር ሁሉ በተለየ መንግድ፡ ያለ ዓይናችን እርዳታ፡ ለምሳሌ፡ በመንካት፡ በመቅመስ፡ በማሽተት፡ ብሎም ህሊናችንን ለጸሎት በመጠቀም ብቻ ነው ሊደረስበት የሚችልው ማለት ነው።
የሰለጠኑ፡ የመጠቁና፡ የተመረጡ እንዲሁም ኃያላን ሆነው የሚታዩን ግለሰቦችና ማሕበረሰባት በዓለማችን ላይ ሊያመጡ የሚችሉት ተጽእኖ፡ ያልሰለጠነ፡ ኋላ ቀርና ያልታደለ እንዲሁም ደካማ እንደሆነ አድርገን ከምንቆጥረው የኢትዮጵያ ገበሬና ማሕበረሰብ የሚበልጥ ሆኖ ሊታየን ይችላል። ነገር ግን ይህ ትልቅ ስህተት ነው።
እነዚህ ሰለጠኑ ብለን የምናወድሳቸው ሕብረተሰቦች በርግጥ ለሰው ልጅ ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አምጥተው ሊሆን ይችላል። አብዛኛው ጥቅም ግን ዘላቂ የሆነ ጥቅም ሳይሆን በተወሰኑ ትውልዶች ሊጠፋ የሚችል ጥቅም ነው። ለምሳሌ ሁላችንም የምንገለገልበት ኮምፒውተር ለሁላችንም ብዙ ጥቅሞችን አምጥቶልናል፡ ኑሯችንና የሥራዎቻችንን ክብደት ኣቃሎልናል። አንዷ ትንሽ ኮምፒውተር አንድ አንጋፋ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን መጻሕፍት ሁሉ ገጽ በገጽ አካታ መያዝ ትችላለች። ስለዚህም፡ መረጃ ሰብሳቢ የሆኑ ወገኖች ሁሉ ታሪካዊ የሚባሉትን ጽሑፎች፡ ምስሎች ወይም ድምጾች፡ በ “Digital Archive” ውስጥ በማስገባት ወረቀት፡ እንጨት ወይም ድንጋይ ላይ ተቀርጸው የነበሩትን “ጥንታዊ” መረጃዎች በማጥፋት ላይ ይገኛሉ። ታዲያ ኮምፒውተራችን ውስጥ አንድ ችግር ከተፈጠረ፡ ወይም ከአንድ ተፈጥሮአዊ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ በኋላ ኮምፒውተራችንን ከፍተን ጭራሹን መገልገል ካልቻልን፡ እነዚህ መረጃዎች ሁሉ እልም ብለው ለዘላለሙ ይጠፋሉ ማለት ነው።
ከዚህ ሁሉ ጥፋት ይጠብቀን!
___________________________