Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • June 2023
    M T W T F S S
     1234
    567891011
    12131415161718
    19202122232425
    2627282930  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

Posts Tagged ‘P’

ኢትዮጵያ የተስፋው ቃል ሕዝብ

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on November 24, 2011


የነብዩ ኤርምያስ ምስክርነት

ኢትዮጵያ የተስፋው ቃል ሕዝብ” በሚል ርዕስ ከታተመው የ ዶ/ር ዘላለም እሸቴ መጽሐፍ የተወሰደ።

ከታላቅ አክብሮትና ምስጋና ጋር

ነብዩ ስለ ተስፋው ቃል ሕዝብ እንዲህ ሲል ይመሰክራል።

በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” (ኤርምያስ 1323)

ይህን የትንቢት ቃል በጥልቀት ከማየታችን በፊት ነብዩ ኤርምያስ ስላለበት ሁኔታና ነብዩ ስለ ኢትዮጵያ የነበረውን ግንዛቤ ከእግዚአብሔር ቃል እንመልከት።

በመጀመሪያ በኤርምያስ 387-13 ያለውን ታሪክ እናጥና። ኤርምያስ የፍርድን ቃል ለእስራኤል ከእግዚአብሔር ያስተላልፍ ነበር። በዚህም የፍርድ ቃል ያልተደሰቱት ሕዝብ ኤርምያስ እንዲገድል ንጉሡን ለመኑት። ንጉሡም ኤርምያስን “እነሆ በእጃችሁ ነው” ብሎ አሳልፎ ሰጣቸው። ሕዝቡም ኤርምያስን በጉድጓድ ውስጥ እንዲሞት ጣሉት።

በዚህን ጊዜ በባዕድ አገር ይኖር የነበረ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ስለ ኤርምያስ ማለደ። ወደ ንጉሡም ገብቶ ሕዝቡ በነብዩ ላይ ክፉ እንዳደረጉና ኤርምያስ በረሃብ ሊሞት እንዳለው በማስረዳት ጠበቃ ቆመለት። ንጉሡም በኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ምክንያት ሀሳቡን ለውጦ ኤርምያስን እንዲታደገው ፈቀደለት።

ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው ነብዩ ስለ ኢትዮጵያዊው መልካም ምስክርነትን በሕይወቱ እንዲሰርፅ እግዚአብሔር በር እንደከፈተለት ነው። ታሪኩ የአጋጣሚ ሳይሆን እግዚአብሔር እንኳን ለራሳችን ለሌላም ለመትረፍ የሚያስችል ሞገስ ከጌታ የተሰጠን ሕዝብ እንደሆነ ያመለክታል። በተጨማሪም ከሁለቱ ኢትዮጵያውያን ጃንደረቦች ታሪክ የምንረዳው በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ከጌታ የተቀበልነው ጥሪ (መልክ) ሊለውጥ እንደማይችል ነው።

መልካችንን መለወጥ አለመቻላችን አንድም ተለዋዋጭ ሕዝብ አለመሆናችንን ያሳያል። ስለዚህም ይሆናል በስደት ለረዥም ዓመታት ስንኖር ኑሯችንና ነገራችንን ያየ ሁሉ እዚያው አገር ቤት እንዳለን ያህል ሳንለወጥ የሚያገኘን። ታዲያ ይህ ባህሪያችን ለጎጂ ባሕል ቢያጋልጠንም ለበጎ ነገር ዓይነተኛ ጎናችን ነው። ስለሆነም ጊዜው ሞልቶ እጃችንን ያነሳንለት ወደ ኋላ የሚመልሰን (መልካችንን የሚለውጥ) ነገር አይኖርም። ያኔም ለጌታ የምንመች ባስቀመጠን ቦታ የምንገኝ ሕዝብ እንሆንለታለን።

ቀጥሎ የምናየው ነብዩ ለኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ከእግዚአብሔር ያመጣለት የተስፋ ቃል ነው። እንዲህ ይነበባል፦

ፈጽሜ አድንሃለሁበእኔም ታምነሃልና፤ ይላል እግዚአብሔር” (ኤርምያስ 3918)

ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ለበጎ ሥራ የተነሳሳው በእግዚአብሔር ላይ ስለታመን ነው። ኢትዮጵያም እጆቿን የምትዘረጋው በጌታዋ ላይ ስለምትታመን ነው። ይህ በአምላክ የመታመን ባህርያችንን ምን ጊዜም (መልካችንን) ሊለውጥ የሚችል ነገር አይደለም።

በመጨረሻ ኤርምያስ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን ግንዛቤ በቃሉ እንዲህ ተገልጧል፦

ጋሻንም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና ኃያላን” (ኤርምያስ 469)

ይህ ኢትዮጵያውያን የያዙት የጦር መሳርያ ጋሻ ለመከላከያ የሚያገለግል ሲሆን በቃሉ ውስጥ እንዲህ የሚል ትርጉም እናገኛለን፤ “በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን ፍራፃዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነት ጋሻ አንሱ” (ኤፌሶን 616)

በኢትዮጵያ ላይ ያለውን መለኮታዊ ጥሪ ለማኮላሸት ለዘመናት የተዋጋን ክፉ የሆነው አንዱ ዲያብሎስ ነው። በዚህም አጥፊያችን በሆነው ጠላት ላይ የእምነት ጋሻችንን እንድናነሳ ይናገረናል። ለኢትዮጵያ መጐብኘት ቁልፉ ያለው ድል የምንነሳበትን የእምነት ጋሻን መታጠቃችን ላይ ነው። በገሀዱ ዓለም ደም እያፈሰሰ እርስ በርስ የሚያዋጋን ጠላታችን ላይ ሰማያዊ (መንፈሳዊ) ጦርነት ማካሄድ እንጀምራለን። በጦር ሜዳ የታወቅንበት ጀግንነታችንን (መልካችንን) ዕውቅ እንደነበረ ሁሉ በሰማያዊውም ፍልሚያ ልናሳየው ያለው የእምነት አርበኝነታችንን (መልካችንን) እንዲሁ ሳይለወጥ ይቀጥላል።

መልካችን” በቀጥታ ሲተረጎም – አንድም ጥቁርነታችንን ያሳያል። በአንዳንድ የእንግሊዘኛው መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ኩሽ የኢትዮጵያን መልከዓምድርና ዳርድንበር የሚያዋስኗትን ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚጨምር እንደሆነ ይገልጻሉ። ትርጉሙም ጥቁር ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ወርድና ስፋት በየጊዜው እየተለዋወጠ በዙሪያዋ አዳዲስ መንግሥታት መመስረታቸው እርግጥ ነው። ይሁን እንጂ

  1. ቃሉ መልካችንን (መለኮታዊ ጥሪያችንን) ሊለውጥ የሚችል ነገር እንደሌለ ይናገረናል።

  2. እጃችንን ስንዘረጋ መልካቸውን የለወጡ ሁሉ ከእግዚአብሔር የሚለቀቅልንን በረከት ተካፋይ ለመሆን ይሰበሰባሉ።

  3. እጃችንን ስንዘረጋ ከዘራችን ወጥተን በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ መመካት እንጀምራልን።

  4. በዚያም ሳንረካ ከጥቁር ሕዝብነታችን ባሻገር የእግዚአብሔር ሰው በመሆናችን ሀሴትን እናደርጋለን። ለዓለምም ብርሃን እንሆናለን። ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቆረጠልን መልካችን ነውና ይህን ሊለውጥ የሚችል ማንም የለም።

በድክመቶች ፈንታ መልካም ፍሬዎችን በመተካት ንስሀ እንገባለን። ሌላውን ከራሳችን ይልቅ የተሻለ አድርጎ በመቁጠር ዘረኝነትን እንገድላለን። የሌላውን የልብ ትርታ እናዳምጣለን። በአባቶቻችን ያጣነውን የሌላውን አመኔታ እናገኛለን።

በፍቅር ላይ የተመሠረተ እውነተኛ አንድነት ለማግኘት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል ራሳችንን እናዘጋጃለን። የሌላውን ወገናችንን ቋንቋና ባህል ችላ ብለን ብለን በመኖራችን እናፍርበታለን። እጃችንን ወደ እግዚአብሔር አንስተን በቅን ልቡና ብንጠቀምበት ጌታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ተነጥቀው ከሰው በታች ተቆጥረው ለዘመናት የተሰቃዩት ወገኖች የሚታሰቡበትን መልካም ዘመን ያመጣል።

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔርና ብሔረሰብ የጋራ ርስት እና ቤት ነች። ኢትዮጵያ የተጠራችው አንድ ትልቅ በፍቅር የተሳሰረ ቤተሰብ እንድትሆን ነው። ይሁን እንጂ እጆቻችንን ስንዘረጋ ነው ከእግዚአብሔር በታች ያለ አንድ ቤተሰብ የምንሆነው። ያን ጊዜም የኢትዮጵያ ገጽታ ይለወጣል። ገጽታውም ለእኛም ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ይታያል።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ

እግዚአብሔር ስለ ተስፋው ቃል እንዲህ ሲል ይናገራል።

አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጥቅጠህ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።” (መዝሙር 7414)

ምድራችን የመሪዎቻችንን ክብር ስታስተናግድ ለዘመናት ኖራለች። እጃችንን ስንዘረጋ ደግሞ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔርን ክብር ታስተናግዳለች።

የኤደን ገነት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በምድር ያዘጋጀው በረከት ነበረች። ኢትዮጵያም ከኤደን ጋር ተያይዛ በቃሉ ውስጥ ትገኛለች (ዘፍጥረት 213)። ዲያብሎስ ግን በኤደን የነበረውን በረከት ወደ መርገም ለወጠው።

ልናስተውለው የሚገባን ጉዳይ እሥራኤል እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያዘጋጀው ዘላለማዊ በረከት መንገድ መሆንዋን ነው። ለዚህም ምስክር የሚሆነን ከአብራሃምና ከዳዊት ዘር የወጣውና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ለሰው ልጅ ሁሉ መዳን ሆነ (ሐዋ. 412)

ኢትዮጵያ ደግሞ እግዚአብሔር በምድር ለሰው ልጅ በመጨረሻው ዘመን ያዘጋጀውን መነቃቃት ልታሳይ የተጠራች ምድር ብትሆንስ? ያለነገር ጌታ ዘንዶውን እየቀጠቀጠ ምግባቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሰጣል ተብሎ አይፃፍም። ደግሞስ እጃችንን ማንሳታችን ለዚሁ በረከት ቢሆንስ? ይህም የሚሆነው ኢትዮጵያውያን ለበረከት የተጠራን የተለየን ሕዝብ ስለሆንን ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቸርነት የተነሳ አምላክ አስቀድሞ ቃሉን ስለሰጠን ነው። ዘንዶው በአሸነፈበት ምድር ይጋለጥ ዘንድ አለውና ኢትዮጵያ እጆቿን እንድትዘረጋ ተጠራች።

በኤደን ገነት ዘንዶው (ጠላት) የእግዚአብሔርንና የሰውን ልጅ ግንኙነት አበላሸ። እግዚአብሔርም ለሰው ልጅ የዘንዶውን ራስ የሚቀጠቀጥ መሲህ እንደሚልክ ቃል ገባላት (ዘፍጥረት 315)። የጌታ ቀንም ሲደርስ አዳኙ ወደ ገዛ ወገኖቹ (እስራኤል) በመምጣት የዘንዶውን ራስ ቀጠቀጠ። ነገር ግን እስራኤል ንጉሧን አልተቀበለችም።

ከአህዛብ ወገን የሆንነው የጠላትን ተሸናፊነት ያስመሰከረ በሕዝብ ደረጃ በምድር ላይ አልተገኘም። ሌላው ቀርቶ በሃይማኖት ላይ የተመሰረቱ መንግሥታት እንኳን ለሕዝባቸው መንፈሳዊና ሥጋዊ ችግር መፍትሔ ለማምጣት ለዓለም እንደ ሞዴል ሲሆኑ አልታዩም።

ስለዚህም ዓለም መንግሥትን ከሃይማኖት ነጥላ “ሴኩላር/secular” መንግሥትን መመስረት መረጠች። ይህም አዲሱ ምሪት በመባል ይታወቃል። ታዲያ እነዚህ ሴኩላር (ዓለማዊ) መንግሥታት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ላለመግባት ሲሸሹ እግዚአብሔርንም አብረው ደህና ሰንበት አሉት። ስለሆነም የዘንዶው አሠራር እስከዛሬ በዓለም ተንሰራፍቶአል (መዝ. 10426)

እጆቻችንን ስንዘረጋ ግን ከምድር መጨረሻ በሆነችው ምድረ ኢትዮጵያ መንፈስ ቅዱስ የተሰበረችውን የጌታ አካል ተጠቅሞ በሙላት ይገለፃል።

ሁሉም በየቤተ ሃይማኖታችን እግዚአብሔር ወደ እውነት እንዲመራን እጆቻችንን ወደ እግዚአብሔር እንዘረጋለን። አንዳችን አንዳችንን ወደ የግል እምነታችን ለመቀየር ከመሮጥ ይልቅ ሁላችንንም በያለንበት ወደራሱ ወደ እግዚአብሔር ልብ እንዲያቀርበንና እንዲቀይረን እንጸልያለን። ሁላችንም በያለንበት ሁኔታ ለያለንበት ሥፍራ ብርሃን ሆነን እንቆማለን።

እግዚአብሔር የሰጠን ተስፋ ዓይናችንን ከራሳችን ላይ አንስተን ጌታችን ላይ እንድናደርግ ይጠራናል። የሚያስተሳስረንም በእግዚአብሔር ያለን እምነት ብቻ ነው። አምላክ የለሹ “ሴኩላሪዝም” ዓይናችንን ጨፍነን ከመነዳት እግዚአብሔር ለኛ ያለውን ጥሪ እናስተውላለን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያ የማንኛውም አንድ ሃይማኖት አገር ሳትሆን የአንዱ እግዚአብሔር አገር ትሆናለች።

ከላይ ባነበብነው ምንባብ ውስጥ የተጠቀሰው የዘንዶው ራሶች በእየሩሳሌም ከተቀጠቀጠው ከዘንዶው ራስ ይለያል። የዘንዶው ራስ በቀራንዮ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በክርስቶስ ደም የአንዱን ጠላት ሽንፈት ሲያመለከት የዘንዶው ራሶች ደግሞ በተለያየ መልክ የሚከሰተውን የጠላት አሰራሮች ሽንፈት በታላቅ መንፈስ ቅዱስ መነቃቃት ይታያል።

የእስራኤል ሕዝብ ጥሪ በአንድ ሰው ያውም በአብርሃም ላይ የተመሰረት ነው። ስለሆነም ያዕቆብ እስራኤል በመሆን የቃል ኪዳኑን ሕዝብ መሰረተ። ከእስራኤልም ሕዝብ አንድ አዳኝ የሆነ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ። እስራኤል ግን አዳኙን አልተቀበልችም። ስለዚህም እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ልትቆም አልተቻላትም።

የኢትዮጵያ ጥሪ ግን በሕዝብ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ እጆቿን በመዘርጋት የተስፋው ቃል ሕዝብ ትሆናለች። ጌታም በዚህ ሕዝብ በመጠቀም የጠላትን አሰራር በሕዝብ ደረጃ በማጋለጥ በመንፈሱ ይቀጠቅጠዋል። ለሕዝቡም ምግባቸውን ይሰጣቸዋል። ይህም ተጽፏል። ስለተጻፈው ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው።

በርግጥ በመንግሥተ ሰማይ እግዚአብሔር ይከበራል። ሰይጣንም ይጣላል። ነገር ግን በኤደን ገነት ነገርን ሁሉ ያበላሸው ዛሬ ደግሞ ዓለምን የሚገዛው ዘንዶ እንዲሁ እንደንተሰራፋ የዓለም ፍጻሜ አይሆንም። ስለዚህ በምድር ሰይጣን ዓይኑ እያየ እግዚአብሔርን በድል እንድታከብር ኢትዮጵያ ተጠራች። ዘንዶው ራሱ እየተቀጠቀጠ ሕዝቡ ግን ምግባቸውን ከአምላካቸው ሲቀበሉ ፍጥረት ያያል። ትልቁ ድግስም ወንጌል እንደሆነ አንዘንጋ።

ዳዊት በእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “በፊቴ ገበታን አዘጋጃለህኝ። በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ። ጽዋዬም የተረፈ ነው ይላል (መዝ 235)። ስለዚህም ጠላታችን እያየ በፊት ለፊቱ ምግባችንን እረኛችን የሆነው እግዚአብሔር እንዲሰጠን እጆቻችንን ወደ እርሱ ለማንሳት እንፍጠን።

ኮሚኒዝም አምላክን ክዶ አገር አጥፍቶ እርሱም ተሰባብሮ ከዓለም ጠፉ። በምትኩም በምድር ላይ የገነነው ሴሉላሪዝም አማራጭ ስለጠፋ ተቀባይነትን በዓለም አገኘ። ይሁን እንጂ በተራው የጌታን ፍርድ የሚጠብቅ ነው። ምድራችን በዘንዶው ሴራ የሚከሽፍበትና የጌታ ኃይል የሚገለፅበት አዲሲቷ ኢትዮጵያ ትሆናለች።

የማታ ማታ አምላክ የተሻለውን ክብርና በጎነት በምድራችን ሊገልጥ እንዳለው እንመን።

በችግርና በስደት ሕዝባችን በዓለም ዙሪያ ተበትኗል። ዓለምም እጇን ከፍታ አስተናግዳናለች። በጌታ ስንጎበኝ ግን ታሪክ ይቀየራል። ያኔ አምላክ ዘንዶውን እየቀጠቀጠ ምግባችንን ስለሚሰጠን እንጀራ ፍለጋ አንሰደደም፡ ይልቁንስ በምድራችን የተለማመድነውን ክብር እንድናካፍላቸው ዓለም ትለምነናለች። እኛም ያኔ ሃያል አምላክ ለሆነው እግዚአብሔር ምስክር አብሳሪ ለመሆን ወደ ዓለም ሁሉ ቃሉን ይዘን እንወጣለን።

ሁላችንም የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በዓለም ዚሪያ ተበትነናል። በሀገር ቤትም ያለው መውጫ ቀዳዳ ይፈልጋል። በሌላ በኩል ስናየው በውጭ ያለውም ሕዝብ በሥጋ ቢመቸውም ልቡ ያለው ሀገር ቤት ነው። ለመመለስ የፈለገም የኑሮ አባዜ አስሮት በምኞት ብቻ እየዋለለ ይገኛል። አገር ቤት በሥራችም ስንፍናን ያሳየን በስደት ስንኖር ሠራተኝነታችን በገሀድ ወጣ። ወንዞቻችን ለዓለም ሲሳይ እንጂ ለምድራችን እንዳልታደሉ ሁሉ ጉልበታችንም ለዓለም ሲሳይ እንጂ ለኢትዮጵያ እንዳልታደለ በሁሉም መስክ የተረጋገጠ ሆኗል።

እጃችንን ስናነሳ ይህ መርገም ከምድራችን ላይ ይነሳል። የጌታ ሞገስ በምድራችን ስለሚገን ሰዎች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ይፈጥኑ ዘንድ ታሪክ ይቀየራል። በስደት ያለነውም እስራታችን ተፈቶ ለአገራችን ልማት ወደ አገራችን እንመለሳለን። መኖር ማለት በኢትዮጵያ ነው እስኪባል ድረስ ስለምትባረክ ዓለም ዓይኑን ወደ ኢትዮጵያ ያቀናል። በምድረ ኢትዮጵያ አምላክን ስንከተል ምህረቱና ቸርነቱ ይከተለናል።

ዓይናችን ተከፍቶ ከእስራት ተፈተን እጆቻችን ለተገለጠልን ስጦታዎች በሥራ ሲበረቱ እግዚአብሔርም ሰምተንም አይተንም በማናውቀው ሥጦታዎች ይባርከናል። በአምላክ ጥሪ ጥላ ሥር ያለችው ምድራችን በውስጧ አምቃ የያዘችውን ድብቅ በረከት ማን አውቆት? በፊታችን የሚፈሱትን ወንዞችና ጅረቶች በመጠቀም ታማኝነታችንን ካሳየን በበለጠ ቸርነት ሊያስደንቀን አምላክ የታመነ ነው።

ኢትዮጵያ የዓለም ሞዴል

እግዚአብሔር ስለተስፋው ቃል እንዲህ ሲል ይናገራል።

የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?”

ይላል እግዚአብሔር (አሞጽ 97)

ይህ ቃል የተገላቢጦሽ የተጻፈ ይመስላል። ምክኒያቱም እስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ በመባል ሲታወቅ፦ ኢትዮጵያ ደግሞ እንደ አህዛብ ስለምትታወቅ ነው። ሲሆን ሲሆን ኢትዮጵያውያን እናንተ እንደ እስራኤል ልጆች አይደላችሁምን? ማለት በተገባው ነበር። ለምንድንነው ታዲያ እዚህ ላይ ኢትዮጵያን ከእስራኤል ይልቅ ወደራሱ ጌታ ያቀረበው? ደግሞስ ለምንድነው እስራኤል እንደ ኢትዮጵያ መቆጠሯ የሚያፅናናት?

ጥቅሱ የተወሰደበት አጠቃላይ ዐውድ ስንመረምረው እስራኤል በብዙ መከራ በምትገኝበት ወቅት ነው። የእስራኤል ሰላም አሁንም መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ነው። እስራኤልም ለእየሩሳሌም መጐብኘት መልስ የሚያመጣለትን የሰላም አለቃ አልተቀበለችውም። ስለዚህም ሰላምን ለኢየሩሳሌም ሊያመጣ የሚችል ሰው ሊመጣለት አይችልም።

ስለዚህም የተስፋ ቃሉ ተፈጽሞ ኢትዮጵያ እጆቿን አንስታ ከጌታ ስትባረክ እስራኤል በኢትዮጵያ ትደነቃለች። ጌታ ረሃብና ጦርነት ያጠቃትን የኢትዮጵያን ታሪክ ቀይሮ ለዓለም ብርሃንና ሞዴል ሲያደርጋት እስራኤል ስለ ሰላሟ ትጮሃለች። ያኔ ጌታ እናንተስ እንደ ኢትዮጵያ ልጆቼ አይደላችሁምን? የተባለው ቃል ትርጉም ይሰጣል። እነሱም ወደ ልባቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ በረከት ትሆንላቸዋለች።

አርማችን

ባንዲራችን እኛን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ኩራት እንደሆነ ይታወቃል። በባንዲራችን ላይ ያለው አርማችን ግን መንግሥት በተቀየረ ቁጥር እየተቀየረ ፈተና ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ በታሪክ የበለፀገች አገር ብትሆንም አርማችን ዕድሜው በመንግሥታት ዕድሜ ልክ ብቻ የሚቆጠር መሆኑ ይታወቃል።

እጆቻችንን ስንዘረጋ ግን ኢትዮጵያ ከጥሪዋ ጋር የሚሄድ አርማ እንዲኖራት ዕድል ቢሰጣት የተዘረጉ እጆች እንዲያርፍባት ታደርጋለች የሚል ምኞት አለን።

ይህ ዓርማ ታሪካዊ በሆነው ባንዲራችን ላይ ቢቀመጥ ሊሰጠን ያለውን በረከት በጥቂቱ እንመልከት።

1. የተሰጠን ዓርማ ከአምላክ የተወሰነልንን የበረከት ጥሪ ለመቀበል እሺ በማለት እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እንዲባርካት ፍቃደኝነታችንን ያሳያል።

2.የተሰጠን ዓርማ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንነት ያንፀባርቃል። የሰዎች ምኞት የሚያንፀባርቅ ሳይሆን የተስፋው ቃል ሕዝብ ለመሆናችን ምስክር ይሆናል።

3. የተሰጠን ዓርማ ከማናቸውም መንግሥታት ጋር ስለማይወግን ዘላቂነት ይኖረዋል።

4. የተሰጠን ዓርማ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ሃሳብ እንጂ ኢትዮጵያዊ ሰው የፈጠረው አይደለም። ስለዚህም ከአምላክ የተሰጠን ስጦታ ነው።

5. የተሰጠን ዓርማ በሺህ የሚቆጠር ዘመን ታሪክ ያለው ታሪካዊ ነው። ስለዚህም ታሪካዊ በሆነው ባንዲራችን ላይ ታሪካዊ ለሆነችው አገራችን ምቹ ነው።

6. የተሰጠን ዓርማ ለኢትዮጵያ ብቸኛ መለያ ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የብዙ አገሮች ባንዲራ ኮከብ አለበት።

7. የተሰጠን ዓርማ ከማናቸውም ሃይማኖት ጋር አይወግንም። ከማናቸውም ሃይማኖት ምልክቶች ጋር አይያያዝም።

8. የተሰጠን ዓርማ በፊት ለአፍሪካ ኩራት የነበረውን ባንዲራችንን ለዛሬ የአፍሪካ ተስፋ በማድረግ ይበልጥ ያከብረዋል።

9. የተሰጠን ዓርማ በዓለም የሰለጠነውን አዲሱን የሴሉላሪዝምን ምሪት እያጋለጠ የእግዚአብሔር ምሪት ምን እንደሚመስል ለዓለም ያበስራል።

10. የተሰጠን ዓርማ እግዚአብሔር አዲሲቷን ኢትዮጵያ ገፅታ ለውጦ የዓለም ሞዴል ሲያረጋት ለእግዚአብሔር ታማኝነትና ታላቅነት መታሰቢያ ይሆናል።

ጥቁር ሕዝብ

ቃሉ ሰይጣን የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል ይላል (2ኛ ቆሮንቶስ 1114)። ዓለም ግን ሰይጣንን ቀንድ ያወጣ ጥቁር ሰው አድርጎ ይስለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ቃሉ ስለ ክርስቶስ እንዲህ ሲል ይናገራል፤ “መልክና ውበት የለውም ባየነውም ጊዜ እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም (ኢሳያስ 532)። ዓለም ግን ክርስቶስን ቆንጆ ፈረንጅ አድርጎ ይስለዋል። እኛም በራሳችን ተስፋ ቆርጠን እግዚአብሔር ፈረንጅን እጁን አጥቦ ነው የፈጠረው ብለን እንድንደመደም አድርጐናል።

አፍሪካ የጨለማው አህጉር ተብላ ትታወቃለች። ጨለማነቷ በቆዳዋ ጥቁረት ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ነው። በቅኝ አገዛዝ ዘመን እንደ ዕቃ በብር ተሽጠናል ተለውጠናል። ጥቁር ሕዝብ በሰይጣን መልክ የወጣን ይመስል ጨልሞብናል።

ኢትዮጵያ የተጠራቸው ለብቻዋ ብርሃን ሆና በጨለማው አፍሪካ አህጉር እንድትኖር አይደለም። ኢትዮጵያ ኩሽ ስለሆነች የአፍሪካና የጥቁር ሕዝብ ተስፋና ፋና እንድትሆን እንጂ። እጆቻችንን ስንዘረጋ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር በእርግጥ እንዳለ ብርሃናችን ይታያል።

ዓለም ከፍልስፍናዋ የተነሳ ሰዶማዊነትን በፀጋ ተቀብለዋለች። መንግሥታት ወንድና ወንድን ወይም ሴትና ሴትን ሲያጋቡ አይተን ተገርመን ሳንጨርስ የምዕራቡ ዓለም አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ሰዶማዊነትን ሲቀበሉ እያየን ነው። ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም እንዲሉ ነገ በአደባባይ ልናይ ያለው የትዳር ዓይነቶች ገና ጉድ ያሰኘናል።

ዓለም ተፈጥሮ ሰልችቷት በራሷ ፍልስፍና ኢተፈጥሯዊ ነገርን ስታበራ ኢትዮጵያ የእግዚአብሔርን ክብር በመግለጥ የጥቁር ሕዝብን ታሪክ ፋና በመሆን ትለውጣለች። ዓለም ያረጀውንና ያፈጀውን የጠላት አሰራር እንደ አዲስ በመቁጠር ደስ ተሰኝተንበት ይሆናል። ኢትዮጵያ ደግሞ ጆሮ ያልሰማውን ዓይን ያላየውን የጌታ ድንቅ ሥራ ታስተናግዳለች። በኢትዮጵያ የጀመረውም ይህ ብርሃን አፍሪካን ሁሉ ያበራል።

ዓለም ከጥበቧ የተነሳ እንደባቢሎን ዘመን የፈጣሪን ሥራ እየተገዳደረች ነው። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን ሰውን “ክሎን” ለማድረግ መነሳሳታቸው ነው። በምናለበት ዛሬ ይህ ተጀመረ እንጂ የነገውን ጉድ ማን አውቆት። ባቢሎንን ንግግሯን ደባልቆ በምድር እንደበተናት ሁሉ ዛሬም ዓለም ራሷን ለሌላ ለፍርድ እያዘጋጀች ናት።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እጆቿን በመዘርጋት ለእግዚአብሔር የተሰጠች ናት። ዕድል ፈንታችንን በእግዚአብሔር ችሎት ላይ መጠቅለላችን እንደ መሃይምነትና ተስፋ መቁረጥ በዓለም ዘንድ ችሎት ላይ ይቆጠር ይሆናል። በሰዎች አቅምና መላ ላለመመርኮዝ ተስፋ መቁረጣችን እውነት ነው። የእግዚአብሔርን ጥበብ ለመውረስ ሞኝነትን መርጠናል። በዚህ የተነሳም የሰለሞን ጥበብን ለመስማት ፍጥረት ሁሉ ኢየሩሳሌም እንዳልተጓዘ ሁሉ የክርስቶስን ክብር ለማየት ወደ ምድራችን የሚፈጥንበት ዘመን በደጅ ነው።

መፍትሔ

ዓለም በየጊዜው በብርና ወርቅ እንዲሁም በሃይልና በጥበብ ገናና ለመሆን በመጣር ላይ ትገኛለች። ገንዘብንም አምላክ አድርጋ ታመልከዋለች። ይሁን እንጂ በዓለም አንድ ክፍል የሚገኙ ህፃናት በረሃብ ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ ስንዴ ተርፏቸው ባህር ውስጥ እንደሚጥሉ እንሰማለን። በርካታዎች በበሽታና በረሃብ ተይዘው መንገድ ዳር በሚተኙበት ምድር ባንዲራ ማርስ ላይ ለመስቀል ትሯሯጣለች። ዓለም ጥበቧም ሆነ ሀብቷ ለችግረኞች ጩኸት መልስ እንድትሰጥ ግድ ሲላት አላየንም። ምክንያቱም ለድሃ መድሃኒት ለመሆን የድሃ አምላክ ልብና ሃይል ያስፈልጋልና ነው። ለዚህም ነው የድሃ አደግ አባት ለሆነው አምላክ እጆቻችንን በፍጥነት መዘርጋት ያለብን።

በችግረኛነት በዓለም የምትታወቀው ኢትዮጵያ እጆቿን ስትዘረጋ ለዓለም እንቆቅልሽ የሆነ ፍትህን በምድሯ በማስፈን ሞዴል እንድትሆን ተጠርታለች። መሃይምነትና ኋላ ቀርነት የገነነባት ኢትዮጵያ ስትጎበኝ ለፍጥረት መፍትሔ ማፍለቂያ ምንጭ ትሆናለች።

እግዚአብሔር በዘመን መጨረሻ ሊሰራው ስላለው ድንቅ ሥራ ኢትዮጵያን አስቀድሞ የተስፋ ቃል በመስጠት ወደ ራሱ ጠርቷታል። በሥጋዊ አስተሳሰብ ካየን ኢትዮጵያን ለሞዴልነት የሚያበቃት ምንም ነገር የለም። እንዲያውም ከሰልፉ የመጨረሻ ጭራ ሆና ትገኛለች። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ግን የራሱን ክብር ለማሳየት የዓለም ዝቃጭ ሆና የምትቆጠረውን ኢትዮጵያን መርጧል።

የኤርትራ ባህር አምላክ እስራኤልን ከውጭ ጠላት የታደገበት ምስክር ነው። ዛሬ ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ መሰበር ዓይነተኛ ምስክር ነው።

የዛሬ የኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጋር በመልከዓምድር የተለያየች ብትሆንም ልቧ ግን አሁንም አንድ እንደሆነ ጌታ ያውቃል። የዓለም አስታራቂዎች ወጥተው ወርደው ሊያደርጉ ያልቻሉትን ነገር ወደ እግዚአብሔር ከኤርትራውያን ጋር ወንድማማች ስለሆንን በጥሪያችን መሰረት እጃችንን እናነሳለን።

የኤርትራ ሕዝብ ከጥሪያችን የተነሳ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የአምላክ በረከትና ሞገስ ያስተውላሉ። ለብቻቸውም ከአምላክ ፍቃድ ውጭ ሆነው መኖሩ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንባቸው ይገነዘባሉ። ከጥሪያችን በረከት ለመካፈልና ለኢትዮጵያ አንድነት ራሳቸው ኤርትራውያን በጌታ ሃይል ይነሳሉ። ቀይ ባህርም ዳግም የአምላክ ክንድ የሚታይበትና የኢትዮጵያ አንድነት በፍቅር የሚታደስበት ምስክር ይሆንልናል።

እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ታላቅነቱን ሊያሳይ አስቀድሞ ራዕይን ሰጥቶናል። ይህንንም ለመረዳት ቅዱስ ቃሉን በጥሞናና በተከፈተ ልብ እናያለን።

ኢትዮጵያ የተስፋው ቃል ሕዝብ ናት። ስለሆነም የተሰጠንን መለኰታዊ ጥሪ በሙሉ ልብ እንቀበላለን። የእግዚአብሔር ዓላማ በምድራችን እንዳይከናወን እንቅፋት የሚሆን ሰይጣናዊ አሠራር ሁሉ በጌታ ኃይል ይሻራል። አምላክም ክብሩን በምድራችን በመግለጥ ኢትዮጵያን ለበረከት ያደርጋታል።

ወሳኝ ምርጫ

ታዲያ ይህ ሁሉ በረከት ከአርያም ታዞልን ምድራችን ለምን በጦርነትና ችግር ደቀቀች ብለን ብንጠይቅ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ይመሰክራል፦

እናንተ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በሰይፌ ትገደላላችሁ” (ሶፎንያስ 212)

ቁጣውንስ አየን። ተስፋችን ግን ወዴት አለ ብለን ስንጠይቅ ያ የእኛ ወሳኝ ምርጫ እንደሆነ ቃሉ ያስረግጥልናል። እግዚአብሔር በቃሉ ሁልጊዜ ታማኝ ነውና።

ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔርእሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፥ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና” (ኢሳያስ 118-20)

የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው። ዛሬም ምርጫችንን ካላስተካከልን በረከቱ አባቶቻችንን እንዳለፈ ሁሉ እኛንም ያልፋል። ሰይፉን በበረከት ለመለወጥ ምርጫው የእኛ ፈንታ ነው። አንድ ቀን ኢትዮጵያ የጌታን አሸናፊነት ልታሳይ ተጠርታለችና ይህ መሆኑ አይቀሬ ነው። ዘመኑን ለመዋጀት ብንነሳ የበረከቱ ተካፋይ ሆነን ክብሩን ባየን ነበር። የጌታ ቃል እንዲህ ይነበባልና፦

በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢፀልዩ ፊቴንም ቢፈልጉ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ ኃጢያታቸውንም ይቅር እላለሁ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ።” (2ና ዜና 714)

ኢትዮጵያ ሆይ! ዛሬስ ምርጫሽ የቱ ይሆን?

Please download the fileEthiopiaYetesfauAger to read in PDF

___________________________________

Posted in Faith | Tagged: , , , , , , , | 1 Comment »

 
%d bloggers like this: