*ከማሞ ውድነህ*
“የእስበሳችን ነገር ያለ ማክረሩ ነው የሚሻለው። ጠንካራ ክንድና ብርቱ ትኩረት የሚገባው ግን እንደ አዞ ከውሀ ውስጥ ብቅ የሚለው ነው“ (አሉላ አባነጋ)
አፄ ዮሐንስ ከጉራዕ ጦርነት በኋላ ሐማሴን ውስጥ ሰነባብተው ወደ ዐደዋ ከመመለሳቸው በፊት የሰሜን ኢትዮጵያ በር የተከበረና የታፈረም እንዲሆን ሲሉ ደጃዝማች ኃይሉ ተወልደ መድኅንና ራስ ባርያውን በገዥነት ሲሾሙ፡ ስመ–ጥሩውን አዋጊያቸውን ሊጋባ አሉላን በራስነት ማዕረግ አስኮፍውሰና አስጊጠው ከመረብ ማዶ ያለውን አገር በጦር አበጋዝነት እንዲጠብቁ ሾሙዋቸው። ከዚያ በኋላም የአፄ ዮሐንስ ትልቁ የሥራ ምዕራፍ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ማደላደልና ማለሳለስ አንድነቷን ማጽናትና ሕዝቡ ፍትሕ አግኝቶ አርሶና ነግዶ እንዲተዳደር የማድረጉ ጉዳይ ነበር።
ይህን ዓላማቸውን ሊያደናቅፉባቸው እንደሚችሉ አሥግተዋቸው ከነበሩት ሁኔታዎችም ጋር መፋጠጡን ተያያዙት። በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል የውስጡን ተቀናቃኝ ቀርቶ የውጭውንም ወራሪ ጠላት ከአንዴም ሁለቴ ኃያሉ ክንዳቸውን ስለአሳረፉበት ለጊዜው ረጭ ብሎላቸዋል። በምዕራብና በመካከል ኢትዮጵያም በኩል የቤገምድር የወሎና የጐጃም ሁኔታ ጋብ ብሎላቸዋል። የጥርጣሬና የሥጋት ትኩረታቸውን የሳበባቸው ግን ሸዋ ሆነ። የወጣትነት ጓደኛቸውና ምስጢረኛቸው ምኒልክ “አፄ” ተብለው ቁጥሩ እስከ ሰባ ሺህ በሚደርስ ሠራዊት ጐልብተው፡ ከሸዋም አልፈው ወሎንና ጐጃምን ለመደረብ ከሚያስፈራሩበት ደረጃ ላይ ወጥተዋል።
አፄ ዮሐንስ ግን፡ የምኒልክን ሁኔታ አንሥተው ከመኳንንቶቻቸውና ከጦር አበጋዞቻቸው ጋር በሚወያዩበት ሰዓት ሁሉ ደጋግመው የሚያነሡት ጉዳይ ነበራቸው።
“ዋናው ሥጋቱና ችግሬ የሠራዊቱ ብዛት አይደለም። ለዚህ ለዚህስ እኔም ላቅ ያለ እንጅ ከእርሱ ዝቅ ያለ ሠራዊት የለኝም። ግን እንደዚያ ማሳያ እንደሚሉት የሰይጣን መልእክተኛ የመሰለ ፈረንጅ ከአጠገቡ አስቀምጦ፡ ከነሙንዚንገር ጋርም የሚያደርገው መላላክና መስማማት ነው።
ከዚያ ሌላ ደግሞ እነዚህ ሚሲዮኖችም በዚያ በኩል ገብተዋል፡. ዋናው ዓላማቸውም ምኒልክን አሳስተውና ጦር አስመዝዘው ከኔ ጋር ለማጋጨት መሆኑን አላጣሁትም። ግዴለም የማደርገውን ዐውቃለሁ” እያሉ ዛቻ አዘልና ትካዜ–ለበስ አነጋገር ያሰሙ ነበር። እርግጥም ነው በዚያ ዘመን ፒዬር አርኖ የተባለ ፈረንሳዊ በዘይላ በኩል ወደ ሸዋ ገብቶ የምኒልክ ባለሟል ሆኖ የእርሳቸውንም መልእክት ይዞ ወደ ግብጽና ፈረንሣይ እየሔደ ‘ዮሐንስን ለመጣል ትልቅ መሣሪያ ይሆናችኋል‘ እያለ ያሽቃብጥ ነበር። ከእርሱም ሌላ ደግሞ በምሕጻረ ቃል “አባ ማስያስ” እየተባለ የሚጠራው ሎሬንዞ ጉልየሞ ማሳያ የሚባለው የሮማ ካቶሊክ ሚሲዮን አባል በሸዋና በከፋ ውስጥ ድርጅቱን አቋቁሞ የምኒልክን ባለሟልነትም አትርፎ ከሚሲዮናዊነቱ ይልቅ በዲፕሎማቲክና በስለላው ሙያ ተሠማርቶ ዮሐንስንና ምኒልክን ለማራራቅና ለማጋጨት በመካከላቸው ገብቶ ነበር።
እነዚሁ ሁለቱ አውሮጳውያን የምኒልክን ጉልበት ከዮሐንስ ጉልበት የጠነከረ ለማድረግ ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት ሲከታተሉት የነበሩት ዮሐንስም ክንዳቸውን በቀላሉ የማይታጠፍ ለማድረግና ምኒልክንም ለማስገበር ሲሉ የሠራዊታቸውን ቁጥር እስከ አንድ መቶ ሺህ ከአደረሱት በኋላ፥ ክዚሁ ውስጥ እስከ ዐርባ ሰባት ሺህ
የሚደርሰውን ልዩ ልዩ መሣሪያዎች አስታጠቁት። ከጉንደትና ጉራዕ ጦርነቶች የተገኘው ቀላል መካከለኛና ከባድ መሣሪያም የበላይነታቸውን ያረጋገጡበት ዋናው ትጥቃቸው ነበር።
ከመሣሪያው ጥራትና ብዛትም ሌላ በአጼ ተክለ ጊዮርጊስና በግብጾች ላይ ያገኙት ድል ዝናቸውንና ጥንካሬያቸውን “አበሻ መሬት አውጥቶ በአፍሪቃ፡ በእስያና በአውሮጳ ውስጥ አስተጋብቶላቸው ነበር። በአሜሪካም ውስጥ ቢሆን፡ “የኛ የጦር መኮንኖች ያዘመቱትን የግብጽን ጦር ድል ያደረገ ብርቱ ንጉሥ” የሚል ጸጸት–ለበስ ታዋቂነት አትሮላቸው ነበር።
ታዲያ እንደዚያ ሆኖ ስሙ የገነነ ሠራዊት ሸዋ የገባ እንደሆነ ሊያደርስ የሚችለውን ብርቱ ጉዳት አስቀድመው የተረዱትና የተጠነቀቁበት ከጐልማሳው ምኒልክ ይልቅ አዛውንቱ አጐታቸው ዳርጌ ንበሩ። “ጉዳዩን በቀላሉ አትዩት፤ በየልቦናችሁ ምከሩበትና በእርቅ ይለቅ” ሲሉ አዛውንቱ “ጦር ጠማኝ” ይሉ የንበሩት የምኒልክ የጦር አበጋዝ ግን፤
“ወይ እሳቸው መጥተው፥ ያለዚያ እኛ ዘምተንባቸው ሳንሞካከር እንዴት አስቀድመን እንገብራለን” እያሉ ምኒልክን ይወተዉቱ ነበር።
በዮሐንስ ቤተ መንግሥት እንደአባት ይታዩ የንበሩት ራስ አርአያም በበኩላቸው፤
“የሁለት ወንድማማች ጠብ ማንን ጐድቶ ማንን ይጠቅም ይመስላችሁ? ኢትዮጵያን እኮ ነው የሚያዳክማት! ኢትዮጵያን እኮነው የሚያሳንሳት! ኢትዮጵያን እኮ ነው የጠላቶቿ መሳቂያ የሚያደርጋት! ታሪክ ይወቅሰናል፤ ትውልድ ያፍርብናል፤ ታቦትና መስቀል አስይዘን ካህናትን ወደ ምኒልክ እንስደድ እንጂ ጦር መምዘዙን አልስማማበትም” እያሉ የእህታቸውን ልጅ ከነጦር አበጋዞቻቸው ይቆጡ ነበር።
Continue reading…AtseYohannesNegusMenilik