ኢትዮጵያ ሆይ፥ ሀገራችን! ረስቼስ እንደኾነ፡ ቀኜ ትርሳኝ፣
ያላሰብሁሽ እንደኾን፡ መላሴ ትናጋዬን ሰልቶ ይውጋኝ።
አቤቱ ፈጣሪያችን፡ በኢትዮጵያ ቀን፡ ጠላቶቿን ኹሉ አስብ፤
አፍርሷት፡ ኢትዮጵያን፡ እስከመሰረቷ ድረስ፡ የሚሉትንም ሕዝብ።
እናንት ትምክህተኞች፡ የኢትዮጵያ ጸሮች፥ የተነኰላችሁን ብድራት፤
የሚመልስ ነው አምላካችን፡ በፍትሕ በተአምራት፤
በሚጠሉሽ ላይ፡ በእውነት፥
በቅን ለሚፈርደው ንጉሥ፡ ምስጋናችን ይብዛለት።
ኢትዮጵያ ሆይ፥ ሀገራችን! ረስቸሽ እንደኾነ ቀኜ ትርሳኝ።
“ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት“(የተደበቁ የኢትዮጵያ ምስጢሮች)ከሚለው የንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ ሦስተኛ መጽሐፍ የተወሰደ።
ከታላቅ አክብሮትና ምስጋና ጋር።
ዛሬ ባሉትም ሰዎች ዘንድ፡ እንደጥንቱ እየተፈጸመ ከመቀጠል በቀር፡ ሌላ ዕድል ሊኖረው አይችልም! ምክኒያቱም እውነታ፡ እርግጥ በበለጠ እየጨመረና እየተጠናከረ የኼደ መኾኑን፡ ይኸው፡ እየረሳችን ምስክር በመኾን፡ በገሃድና በግዘፍ እናየዋለን፡ ይኹን እንጂ፡ እየራሳችን ምስክር በመኾን፡ በገሃድና በግዘፍ እናየዋለን፡ ይኹን እንጂ፡ ከሰነፎችና በሰነፎች የሚቀርበው፡ እንዲህ ያለው ምክንያት፡ እዚያው፡ ለሰነፎች የሚያገለግል፡ የሰነፎች፡ ከንቱና ፍሬቢስ አሳብ ሰለሆነ፡ በእኛ፡ በቀዱሱ ኪዳን ኢትዮጵያውያን ዘንድ፡ ፈጽሞ ቦታ የለውም።
በሓሰተኞችና በእምነተቢሶች ዘንድ፡ ክፉው ኹሉ እንደሚቻል፡ እንዲሁ፡ በእውነተኛና ሃይማኖት ባለው፡ በቆራጥ ሕዝብ ዘንድ፡ መልካሙ ኹሉ ይቻላል! አንድ ቆራጥ ሕዝብ ከፈለገ ኹሉን ማድረግ የሚቻለው መኾኑን ለማመልከት ባመኑበት እምነታቸውና በፈለጉት ሥርዓታቸው ማንነታቸውን አኩርተው፥ መሪዎቻቸውንም አቅፈው፡ የኃያላን ተቃዋሚዎቻቸውን ጥቃት ተቋቁመው፥ በውጭ ተፅዕኖም ሳይበገሩ፡ ይህን እውነታ፡ በግብር ያረጋገጡ ሕዝቦችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
ከእነዚህም መካከል የዛሬውን ትውልዷን አያድርግባትና ከቀደሙት ታማኞቹ ኢትዮጵያውያን ልጆቿ፡ ምግባርና ገድል የተነሣ፡ ቀንደኛ ኾና በመልካም ምሳሌነት የምትጠቀሰው፡ ኢትዮጵያ መኾኗ፡ በባለጋራዎቿ ዘንድ ሳይቀር የተመሰከረ እውነታ ነው። ለዚህ ቆራጥነት ስለሚያበቃው፡ ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር፡ በዓለም ላይ የሚኖሩት ሕዝቦች፡ የተለያየ ግምት፡ እንዳላቸው፡ ከዚህ የሚከተለው፡ የጊዜያችን ኹነት በቀላሉ ሊያስረዳ ይችላል፦
ከጥቂት ዓመታት በፊት፡ በመካከለኛው ምሥራቅ፡ ኢራቅ ኩዌይትን በወረረች ጊዜ፡ አሜሪካውያንና ምዕራባውያን አገሮች፡ በነዳጅ በኩል ያላቸውን ጥቅም ለመጠበቅ ሲሉ የቃል ኪዳን ጦር አደራጅተው ኩዌይትን በመርዳት ጎረቤቲቱን ሳዑዲ ዓረቢያን ጭምር፡ ከወረራው ማትረፋቸው ይታወሳል። ይህን በመሰለው እርዳታቸው፡ ሊዋጉላቸው፡ ወደእነዚሁ የእስልምና አገሮች የኼዱትን፡ አሜሪካንና የጦር ጓደኞቿን፡ ሳዑዲ ዓረቢያ፡ በቅድሚያ ካስገባቻቸው ግዴታዎች መካከል አንደኛውን ልጥቀስላችሁ! እርሱም ለእርዳታ የደረሱላት ክርስቲያኖቹ ምዕራባውያን የጦር ጓደኞቿ፡ በሳዑዲ ዓረቢያ ምድር ላይ፡ ሃይማኖታውያን የኾኑ፡ የጸሎትም ኾነ የሰንደቅ ዓላማ፥ ወይም የበዓል ሥርዓቶቻቸውን፡ በምንም መንገድ እንዳይፈጽሙ የሚከለክለው ነበር።
ይህም ማለት፡ “እናንተ ክርስቲያኖች፡ የክርስትና ሥርዓታችሁን፡ በእስልምና ምድራችን ላይ ከምትፈጽሙ ይልቅ፡ እስላሙ ጠላታችን ኢራቅ ወርራን፡ አገራችንን ብትይዝ ይሻለናል!” በማለት፡ ቅድሚያውን ለሃይማኖቻቸው መስጠታቸው ነው። በተቃራኒው ደግሞ አሜሪካና ምዕራባውያን ተባባሪዎቿ፡ “እናንተን ሳንረዳ፡ ሃይማኖታችንን ከምናስከብር ይልቅ፡ ለገንዘብ ጥቅማችን ስንል ሃይማኖታችን ቀርቶ እናንተን ብንረዳ ይሻለናል!”ማለታቸው ነው።
ምሥራቃውያንና ምዕራባውያን፡ ስለሃይማኖት ያላቸው አስተሳሰብና ግምት እንግዴህ በዚህ ተለይቶ ይታወቃል። ኢትዮጵያ፡ ከእግዚአብሔር ያገኘችው፥ ጥንታዊ፥ ቀዳሚና የራስዋ የኾነ ሕዝባዊ የአስተዳደር አቋም የሌላት ይመስል፥ እነርሱም ዛሬ እየሠሩበት ያለው ከዚሁ ከእርሷ የወረሱት መኾኑን ለማዘናጋት በመሞከር በአሜሪካና በቀሩት ምዕራባውያን አገሮች ግፊት፡ “በኢትዮጵያ የሕዝባዊ አገዛዝ ሥርዓት (democracy/ዲሞክራሲ) መስፈን አለበት!” ተብሎ ለዚህ ትውልድ ይህን ያህል ነጋሪት የሚደለቅለት ለምን እንደኾነ በቀላሉ መመልከት ነው።
የሳዑዲ ዓረቢያ ሕዝብ፡ ከአሜሪካውያንና በጠቅላላ ከምዕራባውያን ጋር ያለው ግንኙነት ያው በገንዘብ ላይ የተመሠረተ ኾኖ፡ የቱን ያህል የጸናና የተንሰራፋ እንደኾነ በይፋ ይታወቃል። ይኹን እንጂ ግንኙነቱ እንዲህ እጅግ የተቀራረበና የተጠናከረ እንደመኾኑ፥ አገሩም በፈረንጆቹ የሥልጣኔ ምርት እንደመጥለቅለቁ መጠን ሕዝቡ በሃይማኖቱ ላይ የተመሠረተውን ሥነ ምግባሩን ቋንቋውንና ፊደሉን፥ አለባበሱንና ሌላውን ባህሉን በይበልጥ አጠናከረ እንጂ በምንም መንገድ አልለወጠም።
እንዲያውም ዐረቦች፡ የዘመኑን ትውልዳቸውን በእስላማዊው ሃይማኖታቸው ሥርዓተ ትምህርት እያነፁ በማሳደግ እያዘጋጁት ያሉት በክርስቲያኖቹ ምዕራባውያን ላይ በጠላትነት እንዲነሣ መኾኑ በይፋ የሚታወቅ ከመኾኑ ጋር፡ በአሁኑ ጊዜ፡ ከምዕራቡ የክርስቲያን አህጉር ላይ በእስልምና አክራሪዎች ታውጆ እየተካኼደ ያለው ዓለም አቀፍ የ”ሽብር” ጦርነት በቂ ማስረጃ ነው።
ኢትዮጵያም እኮ እስከዚህ እስከዛሬው ትውልድ ድረስ እንደዚህ ነበረች። ያውም በ፯ሺሆች ዓመታት ለሚቆጠር ዘመን። ዛሬ ግን ይህ ትውልድ ከላይ የተጠቀሱትን የአባቶቹንና የእናቶቹን ምሳሌያዊ ምክር ባለማጤንና ባለማስተዋል ወይም ቸል በማለት ወይም በመናቅ እንኳንስ ዓበይት የኾኑትን የተከበሩ ውርሶቹን ሊንከባክብ ይቅርና፡ ጥቃቅንና ተራ የኾኑትን እንኳ መጠበቅ አቅቶት ይኸው፡ ጨርሶ ለመውደቅ፡ ሲፍገመገም ይታያል።
የኢትዮጵያውያን አንዱ የጨዋነታቸው መገለጫ የኾነው የመከባበር ባህላችን በዚህ ትውልድ እየተዳከመ በመኼድ ላይ ይገኛል፤ ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ ቀደም አድርጎ የማያውቀውንና በዕድሜው ከእርሱ ላቅ ያለ መስሎ የሚታየውን ማንንም ሰው፥ ወንድ ኾነ ሴት፡ “እርስዎ” በማለት ወደ “አንቱታ” ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፥ ወይም ያደርጋታል እንጂ፡ እንዲያው ተነሥቶ ወንዱን “አንተ!” ወይም ሴቷን፡ “አንቺ!” አይልም ነበር። ዛሬስ፡ ይህ ባህል፡ በምን ኹኔታ ላይ ይገኛል ይህስ የመከባበሩ ባህላችን እየቀረ መኼዱን አያመለክትምን?
የሥጋ ወላጆችን፥ ወንድሞችንና እኀቶችን ብቻ ሳይኾን፡ አዛውንቶችን ወንዶች፡ “አባባ” ወይም ታላላቆችን፡ “ጋሼ” ፥ አዛውንቶችን ሴቶች ደግሞ “እማማ” ወይም ታላላቆችን “እትዬ” ብሎ የመጥራቱ መልካም ባህላችን ደብዘው ሳይቀር፡ እየጠፋ መኼዱን ይኸው እየተመለከትን ነው። እንዲያውም በዚህ ፋንታ በባዕዳን ቋንቋ፡ Father! Mother! Brother! Sister! እያሉ መጥራት በኅብረተሰቡ ዘንድ ሙሉ ተቀባይነትን አግኝቶ ተጠሪዎቹም፡ በደስታ፡ ወንዶቹ “ወይ!” ወይም “አቤት!”፥ ሴቶቹ፡ “ወይ!” ወይም “እመት!” እያሉ ፈጥነው መልስ በመስጠት ተባባሪነታቸውን ሲያረጋግጡ ይታያል። በነገራችን ላይ “አቤት!” የሚለው ምላሽ የሚሰጠው፡ ጠሪው ወንድ ሲኾን ብቻ እንጂ ለሴት ጠሪ ፈጽሞ “አቤት!” አይባልም፤ ነውር ነው። ለሴት ጠሪ፡ ተጠሪው ምላሹን መስጠት ያለበት “እመት!”ብሎ ነው።
ለዚህም፡ ለኹለተኛው ቁም ነገር፥ በቂ ምክንያት አለ፤ ይኸውም “አቤት!” “አብ የት?” ማለት ሲኾን፡ በግእዝ፡ “አቡየ” አባቴ፥ “አይቴ” የት ማለት ስለኾነ፡ “አባቴ! የጠራኸኝ፡ ወደየት (ወዴት)ልትልከኝ ነው?” ፥ እንደዚሁ ኽሉ “እመት!” “እም የት? ማለት ሲኾን በግእዝ “እምየ” እናቴ፥ “አይቴ”፡ የት ማለት ስለኾነ “እናቴ! የጠራሽኝ፡ ወደየት (ወዴት)ልትልኪኝ ነው?” ማለት ነው ተብሎ ይተረጎማል።
የአለባበሳችን ባህል ስለሚገኝበት ሁኔታ ስንነጋገር በጣም የሚያሳዝነን ነገር ይኖራል። ይኸውም ይህ የዛሬው የኢትዮጵያ ትውልድ በአለባበሱ ረገድ የራሱን ባህል ጨርሶ ትቶ፡ ፈጽሞ አውሮጳዊ፥ ወይም ምዕራባዊ ወይም ፈረንጅ በመኾኑ ነው።
ዘመናዊውን ትምህርት ከተማረው፥ ከጥራዝ ነጠቁና ከከተሜው መካከል በአኹኑ ጊዜ የአገራችንን ልብስ ለዓውደ ዓመት እንኳ የሚለብሰው ስንቱ ነው? እጅግ ጥቂቶች ናቸ፤ ምናልባት የመልበስ ፍላጎት ኖሮአቸው የሚለብሱ ቢኖሩ እንኳ እነርሱ አለባበሱን ስለማያውቁበት አንድ ባዕድ የኾነ ሰው፡ “እንዲህ አድርገህ ልበሰው!” እየተባለ እንደሚናገረው ተዋናይ መስለው እንደሚለብሱት የሚታወቅ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ከጥንታውያኑ የዓለም አህጉር መካከል በዘመኑ ትውልዷ ምክንያት በአጠቃላይ ኹለንተናዋ “ባለቤቱ፡ በቤቱ ባይተዋር፡ ባይተዋሩ በሰው ቤት ባለቤት” የኾነባት አገር ቢኖር ኢትዮጵያ ኾና ትገኛለች። ይህ ዝቅጠት አያሳዝንምን? አያሳፍርምንስ?
የዘመኑን ዓለማዊ ሥልጣኔ እንደሃይማኖት በተከተለው ወገን ዘንድ ከአገር ልብሱ ብቻ ሳይኾን ከለባሹም ሰው ይልቅ የክብሩን ቦታ የያዘው የባዕዳኑ ልብስ ስለኾነ የኢትዮጵያዊነት አንዱ ምልክት የኾነውን “ነጠላ” ወይም “ኩታ” ደርቦ መታየት ለዚያ ሰው በዘመናዊ ትውልድ ዘንድ የመጨረሻውን የውርደትና የንቀት ምልክት ተጎናጽፎ እንደመታየት የሚያስቆጥር ከመኾን ደረጃ ተደርሷል። ይህን እውነታም፡ “ባለኩታ”፥ ወይም “ኩታ ለባሽ” የኾነው ኢትዮጵያዊ የዚህ መጽሓፍ አዘጋጅ በራሱ አገር፥ በራሱ ወገኖች ሳይቀር ሲናቅና ሲዋረድ አይቷል። አዎ! በነገራችን ላይ “በራሱ አገር በራሱ ወገኖች”አያስብልም ምክኒያቱም በባዕዳኑ ዘንድማ እየተደነቀና እየተከበረ ነው ያለው። የተናቀውና የተዋረደው እኮ በራሱ አገር፥ በራሱ ወገኖች ዘንድ ብቻ ነው።
ይህ ኹኔታ የደረሰው በኩታውና በባለኩታው አገር በኢትዮጵያ ከዚያም ይባስ፡ በአገሩ በኢትዮጵያ ስም በሚጠራው አየር መንገድ ነው። ባለኩታው ኢትዮጵያዊ ወደባሕር ማዶ የሚበርበትን የጉዞ ወረቀቱን (Ticket)ለማስቆረጥ፡ በመናገሻዪቱ ከተማ ውስጥ ካሉት የአየር መንገድ ጽሕፈት ቤቶች መካከል በአንዱ እንደተገኘ በተራው የተቀበለችው ጸሓፊ ባለጉዳዩ ባልጠበቀው መልክ አነጋግራና የጉዞ ወረቀቱን አዘጋጅታ እስከሰጠችው ጊዜ ድረስ ለአንድም አፍታ ቀና ብላ ዓይን ለዓይን ሳታየው ከእርሱ ለቀረበላት የምስጋና ሰላምታም እንኳ አጸፋውን በአግባቡ ሳትመልስለት አሰናበተችው።
Continue reading in PDF>EthioBahel
_______________________________________