በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
ዘንድሮ የጰራቅሊጦስ (ጰንጠቆስጤ) በዓል በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ሰኔ ፭ ቀን በመላው አብያተ ክርስቲያናት ተከብሮ ይውላል። ከጌታ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንደኛው የጰራቅሊጦስ በዓል ነው። ይህ በዓል በኦሪቱ በዓለ ሠራዊት ይባላል። የእሸት በዓል ማለት ነው። ከፋሲካ ሰንበት በኋላ እሑድ በሃምሳኛው ቀን ላይ ስለሚውል በዓለ ሃምሳ ተብሎ ይታወቃል። ይህንን ዕለት ጽርአውያን በቋንቋቸው ጸንጠቆስጤ ይሉታል። የሃይማኖት ስም አይደለም። በዘመናችን በተለይም እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከ ፲፱፻፮ ዓ.ም ጀምሮ በዚህ ስም ራሳቸውን የሰየሙ ቡድኖች የሃይማኖታቸው መታወቂያ በማድረግ ሲጠሩ ይሰማል። በመጽሐፍ ቅዱሱም ሆነ በጥንታዊት ቤተክርስቲያን ታሪክ በጰንጠቆስጤ ስም የሚታወቅ የሃይማኖት ድርጅት አልነበረም አይታወቅም።
ቤተክርስቲያናችን ይህን በዓል የምታከብረው መጽሐፍ ቅዱስንና ትውፊተ ሐዋርያትን መሠረት አድርጋ ነው። በግብረ ሐዋ.፪፥ ፩ – ፳፪ ተጽፎ እንደምናገኘው አይሁድ ከመላው ዓለም ተሰብስበው በዓለ ሃምሳን ሲያከብሩ ጰራቅሊጦስ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ድምፁን እንደ አውሎ ነፋስ እያሰማ ጸጋውን እንደ ባዘቶ በእሳት ላንቃ አምሳል ከፍሎ ከፍሎ በጸሎት ጽሙዳን ለሆኑት መቶ ሃያ ቤተሰብ አድሏቸዋል። (ሐዋ.፪፥፲፬–፲፭) ሐዋርያትም ከሦስቱ ክፍላተ አህጉር ለመጡት አይሁድ መንፈስ ቅዱስ በገለጸላቸው ቋንቋ ለማስተማር በቅተዋል።
በሚያውቁት በአንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ላይ ሰባ አንድ ቋንቋ ስለተጨመረላቸው እንደ ልባቸው የክርስቶስን አምላክነትና ትንሣኤውን ያለ ፍርሃት መስክረዋል። በተገለጸላቸው ቋንቋ ለሰው ሁሉ ስላስተማሩ ሰሚዎቹ ተአምራቱን በማድነቅ “የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን” በማለት ተገርመዋል። የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የተጠራጠሩ ሰቃልያን ክርስቶስ አይሁድ ግን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ለጉሽ ጠጅ ሰጥተው ማፌዝ ስለጀመሩ ቅዱስ ጴጥሮስ ነቢዩ ኢዮኤል በምዕራፍ ፪ ከቁጥር ፳፰—፴፪ የተናገረውን ትንቢት በመጥቀስ በተግሳፅ አሳፍሯቸዋል። ኢዮኤል የተናገረው ትንቢት ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻው በዘመነ ሐዋርያት ተፈጽሟል። መንፈስ ቅዱስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቤተክርስቲያን አድሮ ለምእመናን እንደ ሃይማኖታቸው ጽናት፥ እንደ ምግባራቸው ቅንነት ጸጋውን ሲያድል ይኖራል። የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በጥምቀተ ክርስትና በሜሮን ሲሰጥ በመጠኑ ነው። ምዕመናን ጸጋው እየተጨመረላቸው እንዲሄድ በገድል በትሩፋት ተወስነው የክርስቲያንን ተግባር እየፈጸሙ ሲሔዱ ጸጋው እየተጨመረላቸው እንዲሄድ በገድል በትሩፋት ተወስነው የክርስቲያንን ተግባር እየፈጸሙ ሲሔዱ ጸጋው እየተጨመረላቸው ከነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ፥ ከከዊነ እሳት ማዕረግ ለመድረስ ይበቃሉ። በዚህን ጊዜ እንደሐዋርያት በጥላቸው በልብሳቸው ሕሙም መፈወስ፣ ጋኔን ማውጣት፣ ሙት ማንሳት
ይቻላቸዋል። ቤተክርስቲያናችን ጠቅለል ባለ መልኩ ስለ መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን እንዳልተሰጠ ተቆጥሮ አንዳንድ መናፍቃን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የሚሰነዝሩት ጉንጭ አልፋ ዘለፋ መሠረት የሌለው ስለሆነ አንደነቅበትም። “እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ።” መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸውና። (ይሁዳ ፩፥፲፱) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያይቱ የቆሮንቶስ ክታቡ የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት አምነው በተጠመቁ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ አድሮባቸው እንዳለ ገልጾልናል። በተጨማሪም የመንፈስ ቅዱስ አካሉ አንድ ሲሆን ጸጋው (ሀብቱ) ግን ልዩ ልዩ በመሆኑ ለምዕመናን ሁሉ አንድ አይነት ጸጋ የላቸውም ብሏል። (፩ቆሮ. ፲፪፥፩—፲፩) ጸጋውንም እነርሱ እንደወደዱት ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ እንደፈቀደ እንደሚጠቅማቸው አድርጎ ይሰጣቸዋል። ከመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ከእምነትና ከፍቅር የሚበልጥ ጸጋ አለመኖሩን ዐውቀን በየሰፈሩ እየተሹለከለኩ መንፈስ ወርዶብናል እያሉ ከሚያጭበረብሩ ቢጽ ሐሳውያን ሁሉ መጠበቅ ይገባናል።
እነዚህ ሰዎች የጵጵስናም ሆነ የቅስና ማዕረግ ክህነት ሳይኖራቸው ራሳቸውን በራሳቸው ሾመው እጆቻችንን እየጫንን መንፈስ ቅዱስ እናሳድራለን በማለት ብዙዎቹን የዋሆች የመንፈስ ርኩስ ቁራኛ ስላደረጉዋቸው ምዕመናን ሆይ በተዋሕዶ ሃይማኖታችሁ እስከመጨረሻው እንድትጠበቁ እንመክራችኋለን። (፩ቆሮ.፲፪፥፫፧ ፩ቆሮ.፲፫፥ ፩—፲፫) በጸሎተ ሃይማኖታችን ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለን እምነት እንደሚከተለው ይጠቃለላል፡
“በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን። እርሱም ጌታ ሕይወትን የሚሰጥ ከአብ የሠረፀ፣ ከአብና ከወልድ ጋራ በአንድነት እንሰግድለታለን እናመሰግነዋለን። እርሱም በነቢያት አድሮ የተናገረ ነው።” መንፈስ ቅዱስ እንዳይለየን በመናፍቅነትና በእልከኝነት ልባችን እንዳይደነድን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን አጽንቶ በክርስቲያናዊ ሕይወት ለመመላለስ ያብቃን፡ አሜን።
ምንጭ፡ ethiopianorthodox.org
Speaking In Tongues: An Orthodox Perspective
Fr. George Nicozisin