👉 ገብርኤል 👉 ማርያም 🌞 ኡራኤል 👉 ጊዮርጊስ 👉 ተክለ ሐይማኖት 👉 ዮሴፍ 👉መድኃኔ ዓለም
❖❖❖ ድርሳነ ዑራኤል ❖❖❖
ምድረ ኢትዮጵያ ፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሴፍና ሰሎሜ በደመና ተጭነው ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ናግራን ከተባለ ሀገር ደረሱ። በናግራን ሳሉ ጌታ እንዲህ አለ። ከቀኝ ጎኔ የሚፈሰው ደሜ በብርሃናት አለቃ በዑራኤል እጅ ተቀድቶ በቅድሚያ በዚች ሀገር ይፈሳል ወይም ይረጫል። እናቱንም እንዲህ አላት አንቺ በድንግልና ጸንሰሽ በድንግልና እንደወለድሽኝ አምነው የሚያከብሩሽ በእኔም የሚያምኑ ብዙ የተቀደሱ ሰዎች በዚህ ሀገር ይወለዳሉ። ከናግራን ተነስተው ለትግራይ ትይዩ ከሚሆን ሐማሴን ከሚባለው ሀገር ሲደርሱ በምሥራቅ በኩል ከፍተኛ ተራራ ተመለከቱና ወደ ተራራው ሄዱ። ጌታም በተራራው ላይ ሳሉ እናቱን እንዲህ አላት ይቺ ተራራ ምስጋናሽ የሚነገርባት ቦታ ትሆናለች። የተራራዋም ስም ደብረ ሃሌ ሉያ ወይም ደብረ ዳሞ ይባላል። ትርጓሜውም የአምላክ ልጅ የመስቀሉ ቦታና የስሙ መገኛ ወይም አደባባይ ማለት ነው።ከዚያም በኋላ ታቦተ ጽዮን ወደምትኖርበት ወደ አክሱም ደረሱ። ታቦተ ጽዮን ባለችበት ቦታ ሳሉ ባዚን የተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ታቦተ ጽዮንን ለመሳለም መጣ። የካህናቱ አለቃ አኪን ለንጉሡ የኢሳይያስን መጽሐፍ አነበበለት። የተነበበውም የመጽሐፍ ክፍል ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች የሚል ነበር። ስደተኞቹ ግን ለንጉሡም ሆነ ለካህናቱ ሳይገለጡ የመጽሐፉን ቃል ከሰሙ በኋላ በደመና ተጭነው ወደ ደብረ ዐባይ ሄዱ ። ጌታም እናቱን እንዲህ አላት ይህች ሀገር እንደአክሱም ለስምሽ መጠሪያ ርስት ትሁን በኋላ ዘመን በቀናች ሃይማኖት ጸንተው ሕጌን የሚያስተምሩ አንቺን የሚወዱ ሰዎች ይኖሩባታል። ከዚያም በኋላ ከደብረ ዐባይ ተነስተው ዋሊ ወደ ሚባለው ገዳም /ወደ ዋልድባ / ሄዱ። በዋልድባ በረሃም ሳሉ በራባቸው ጊዜ ጌታ በዮሴፍ ብትር የአንዱን ዕንጨት ስር ቆፈረ። ሦስት መቶ አስራ ስምንት ስሮችን አወጣና ለእናቱ ብይ ብሎ ሰጣት። እናቱም ይህን የሚመር ዕንጨት አልበላም አለችው። ጌታም በኋላ ዘመን ስምሺን የሚጠሩ አንቺን የሚያከብሩ ብዙ መናንያን ይህን እየበሉ በዚህ ቦታ ይኖራሉ። ዕንጨቱም የሚጣፍጥ ይሆንላቸዋል አላት። ከዚህ በኋላ በደመና ተጭነው ከዋልድባ ወደ ጣና የባሕር ወደብ ሄዱ። በጣና ደሴትም ደጋግ ሰዎች ተቀብለዋቸው ሦስት ወር ከአስር ቀን ተቀመጡ። የኢትዮጵያ ሰዎች በደስታ ተቀብለዋቸዋል እንደ ግብፃውያን አላሰቃዩአቸውም ። በጥር አስራ ስምንት /18/ ቀን ዑራኤል መጥቶ የሄሮድስን መሞት ነገራቸው ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ በደመና ከተጫኑ በኋላ ጌታ እናቱን እንዲህ አላት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎች ሁሉ ለስምሽ መታሰቢያ ይሆኑሽ ዘንድ አሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ ። ብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎችን ሜዳዎችን ኮረብታዎችን አሳያት። እመቤታችን ሁሉንም ቦታዎች እየተዘዋወረች እንድታይ ልጅዋን ጠየቀችው። ልጅዋም የሚመለሱበት ጊዜ እንደደረሰ ነገራት። በብሩህ ደመና ላይ ተቀምጠው ክፍላተ አህጉር እየተዘዋወሩ ተራራዎችን ወንዞቸን አስጐበኛት የኢትዮጵያን ምድር ከጐበኙ በኋላ በደመና ተጭነው ጥር 29 ቀን ምድረ ግብፅ ደረሱ። ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው። ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ታሪክ በድርሳነ ዑራኤል ላይ በስፋት ተጽፏል።
የቅዱስ ኡራኤል በረከት ረድኤቱ ይደርብን ! ምልጃ ጥበቃዉ አይለየን!
❖❖❖ ቅዱስ ኡራኤል ኢትዮጵያን የጽዮንን ልጆችን አደራ፤ በእሳት ሰረገላ በነበልባል ታጅበህ ለተልዕኮ የምትፋጠን የአምላካችን አገልጋይ ወራዙተ ኢትዮጵያን በብርሐናዊ ክንፍህ ሸፍነህ ከመርዘኞች የሞት ቀስት ከቀሳፊ ነገር ሁሉ ሰውረን! ❖❖❖
✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻፰]✞✞✞
፩ አምላክ ሆይ፥ ምሥጋናዬን ዝም አትበል፥
፪ የኃጢአተኛ አፍና የተንኰለኛ አፍ በላዬ ተላቅቀውብኛልና፤ በሽንገላ አንደበትም በላዬ ተናገሩ፤
፫ በጥል ቃል ከበቡኝ፥ በከንቱም ተሰለፉብኝ።
፬ በወደድኋቸው ፋንታ አጣሉኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ።
፭ በመልካም ፋንታ ክፉን በወደድኋቸውም ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ።
፮ በላዩ ኃጢአተኛን ሹም፤ ሰይጣንም በቀኙ ይቁም።
፯ በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፤ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት።
፰ ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ።
፱ ልጆቹም ድሀ አደግ ይሁኑ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን።
፲ ልጆቹም ተናውጠው ይቅበዝበዙ ይለምኑም፥ ከስፍራቸውም ይባረሩ።
፲፩ ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት።
፲፪ የሚያግዘውንም አያግኝ። ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር።
፲፫ ልጆቹ ይጥፉ፤ በአንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ።
፲፬ የአባቶቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ፤ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ።
፲፭ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ፤ መታሰቢያቸው ከምድር ይጥፋ።
፲፮ ምሕረትን ያደርግ ዘንድ አላሰበምና ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ሰው ይገድል ዘንድ አሳደደ።
፲፯ መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች፤ በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች።
፲፰ መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች።
፲፱ እንደሚለብሰው ልብስ። ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ይሁነው።
፳ ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚያጣሉኝ በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ነው።
፳፩ አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ ምሕረትህን በእኔ ላይ አድርግ፤ ምሕረትህ መልካም ናትና አድነኝ።
፳፪ እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።
፳፫ እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥ እንደ አንበጣም እረገፍሁ።
፳፬ ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ።
፳፭ እኔም በእነርሱ ዘንድ ለነውር ሆንሁ፤ ባዩኝ ጊዜ ራሳቸውን ነቀነቁ።
፳፮ አቤቱ አምላኬ፥ እርዳኝ፥ እንደ ምሕረትህም አድነኝ።
፳፯ አቤቱ፥ እጅህ ይህች እንደ ሆነች፥ አንተም ይህችን እንዳደረግህ ይወቁ።
፳፰ እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ባርክ፤ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ፥ ባሪያህ ግን ደስ ይበለው።
፳፱ የሚያጣሉኝ እፍረትን ይልበሱ፤ እፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት።
፴ እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ፤
፴፩ ነፍሱን ከሚያሳድዱአት ያድን ዘንድ በድሀ ቀኝ ቆሞአልና።
________
_______
Like this:
Like Loading...