- “ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት“ ከሚለው የንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ መጽሐፍ የተወሰደ…
በአረማዊነት ባህል፡ በክዋክብት ሥነ እውቀት ላይ የተመሠረተው የምዕራባውያን የዘመን አቆጣጠር፡ ከኢትዮጵያውያኑ የዘመን አቆጣጠር፡ የሚለይበት ባሕርይና አኹን ያለበት ቀውስ የደረሰበት ለምን ይሆን?
ኢትዮጵያውያን፡ በቅዱሱ ኪዳን ሃይማኖታቸው ላይ የመሠረቱትን፡ ይህን የጊዜ አቆጣጠር ሥርዓት፡ ምዕራባውያን፡ ኦርቶዶክሳውያን የተባሉት አብያተ ክርስቲያናት ጭምር፡ በአረማዊው፡ ዮልየስ ቄሣርና ጎርጎርዮስ (ግሬጎሪ) ፩፫ኛ በተባለው፡ በካቶሊካዊው ጳጳስ ስሞች እየሠየሙ፥ በየጊዜው እየለዋወጡና በመጨረሻ፡ ፰ ዓመታት ከ፲ ቀናት ያህል አክለውበት መቆየታቸው ይታወቃል። በዚህ የአቆጣጠራቸው ስልት፡ የጌታችን የኢያሱስ ክርስቶስን የልደት ቀን፡ ከ፬ እስከ፯ ዓመታት ለሚደርስ ዘመን፡ ከፍ አድርገው እንዲጨምሩ በመገደዳቸው፡ ይህን፡ ሰው ሠራሽ ቀውስ አስተካክለው ለማስታረቅ አቅቷቸው፡ እነሆ፡ እስካሁን ሲባዝኑ ይገኛሉ። በዚህ፡ በእነርሱው አቆጣጠር፥ ጌታ፡ የተወለደው፡ “በ፬፥ በ፮ ዓመተ ምሕረት ላይ ሳይኾን አይቀርም” ከማለት በስተቀር፡ እርግጠኛውን ቀን፡ በቁርጥ ሊወስኑ ሳይቻላቸው ቀርቷል።
ይህ ቀውስ የተፈጠረባቸው፡ የጌታን የልደት ዓመት፡ አንድ ብለው መቁጠር ከጀመሩ በኋላ፡ ያ፡ የዓመተ ምሕረት መነሻ ዘመን፡ በአረማዊነት ዘመናቸው፡ “ጁልያን” በሚል ስምና በተለያየ ስልት ይጠቀሙበት በነበረው የአቆጣጠር ሥርዓታቸው፡ በ፬፥ በ፯ ዓመታት ላይ ውሎ ስላገኙት ነው።
ሌላው፡ ይህን ችግር የፈጠረባቸው ምክንያት፡ የምዕራባውያን የጊዜ አቈጣጠር፡ እንደ ኢትዮጵያውያኑ፡ በአንድ መሠረት ላይ ታንጾና በአንድ በተስተካከለ ሥርዓት ተቀምሮ የሚመራ ባለመኾኑ ነው። ይህንም፡ ከዚህ የሚከተለውን ማነጻጸሪያ ሓተታ በመመልከት መረዳት ይቻላል።
ኢትዮጵያውያን፡ “የእግዚአብሔር ገነት” ተተከለባት፡ አዳምና ሔዋን የተፈጠሩባት አገራቸው የምትገኘው፡ በምድር ማዕከል ወይም መቀነት ክልል ውስጥ ስለኾነ፡ የጊዜ አቈጣጠራቸው ሥርዓት፡ መዓልቷና ሌሊቷ፡ ዓመቱን ሙሉ፡ በ፲፪፡ በ፲፪ ሰዓታት፡ እኩል በተከፈለበት የአሠፋፈር ስልት ላይ ተመሥርቶ፡ የባሕረ ሓሳቡ ቅመራ፡ ሥርዓቱን ጠብቆ፡ ያለችግር ይካኼዳል። ይኽውም፡ ወደኋላ፡ ወደረቂቃኑ ሳንኼድ፡ ከሣልሲት ተነሥተን፡ እስከ ዓመት ብንቈጥር እንኳ፡ ቀመሩ፡ የተስተካከለ ኾኖ እናገኘዋለን። ማለትም፡ ፷ (ስድሳ) ሣልሲታት፡ ፩ (አንድ) ካልዕት (second)፥ ፷ ካልዕታት፡ ፩ ደቂቃ፥ ፷ ደቂቃት፡ ፩ ሰዓት፡ ፳፬ ሰዓታት፡ ወይም ፷ ኬክሮስ፡ ፩ ዕለት፡ ፩፪ ሰዓታትን የያዘው፡ የብርሃን ጊዜ፡ “መዓልት“፥ ጨረቃ እንድትሠለጥንበት የተፈጠረችበት፡ ፩፪ ሰዓታትን የያዘው፡ የጨለማ ጊዜ፡ “ሌሊት” ይባላል።
የመዓልቱ የጊዜ አቆጣጠር፡ የተፈጥሮውን ሥርዓት በመከተል፡ “ከቀትር በፊት” እና “ከቀትር በኋላ” ተብሎ፡ ፀሓይ፡ ጮራዋን በምትፈነጥቅበት፡ በንጋቱ ፩ ሰዓት ይጀምርና፡ በምትጠልቅበት፡ በምሽቱ ፲፪ ሰዓት ያበቃል፡ የሌሊቱም ጊዜ፡ እንደዚሁ፡ እስከእኩለ ሌሊት ድረስ፡ “ከማታው“፥ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ደግሞ፡ “ከሌሊቱ” እየተባለ፡ ጨረቃ ከምትታይበት፡ ወይም ጨለማው ከሚጀምርበት፡ ከምሽቱ፡ ፩ ሰዓት ይነሣና፡ ጎህ በሚቀድድበት፡ በንጋቱ ፲፪ ሰዓት ይቆማል።
በዚህ መሠረት የተደለደለችው፡ አንዲቱ ዕለት፡ ሰባት ስትኾን፡ ፯ቱ ዕለታት፡ ፩ ሳምንት ይኾናሉ።
የምዕራብውያኑ ግን፡ እንዲህ አይደለም። ምዕራባውያን፡ የሰሜኑንና የደቡብን የመሬት ዋልታ ተከትለው፡ በሰሜንና በደቡብ ክፍላተ ዓለማት፡ የሚኖሩ በመኾናቸው፡ ኢትዮጵያውያን፡ ክረምት፥ መፀው፥ በጋ፥ ጸደይ እንደሚሉት፡ የእነርሱም ዓመት፡ Winter(ዊንተር) Spring (ስፕሪንግ) Summer (ሰመር) Autumn (ኦተምን) በተባሉ፡ በአራት የተለያዩ ወራት ተከፋፍሎ፡ በክረምቱ፡ ሌሊታቸው፡ እስከ ፭ ሰዓታት የሚጨምርበት፥ እንዲያውም፡ ወደሰሜኑም ኾነ ወደ ደቡቡ የመሬት ዋልታ ጫፍ እይተጠጉ በኼዱ መጠን፡ የሚቀነሱት፡ ወይም የሚጨመሩት ሰዓታት እያደጉ ይኼዱና፡ ወደ መጨረሻው ጽንፍ ላይ ሲደርስ፡ ከናካቴው፡ ፮ ወራት ሙሉ፡ ሌሊት ብቻ፥ ወይም መዓልት ብቻ ይኾናል።
ይህም ማለት፡ ይህ ኹኔታ፡ በሰሜኑና በደቡቡ ክፍላተ ዓለም፡ በዓመቱ ውስጥ፡ እንዲህ ስለሚፈራረቅ፡ የክረምቱ ብርዳማ ጠባይ፡ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው፡ የሰሜኑን ክፍል በሚያጠቃበት ጊዜ፡ በደቡቡ ክፍል ደግሞ፡ የበጋው ፀሓያማ ጠባይ ይሰፍናል ማለት ነው።
ይህ ብቻ ሳይኾን፡ በዓመት፡ ሁለት ጊዜያት፡ በየ፮ ወሩ፡ የሰዓት አቆጣጠራቸውን፡ እንደየክፍለ ዓለማቸው አቀማመጥ፡ በ፩ ሰዓት ያሳድጉታል፡ ወይም በ፩ ሰዓት ይቀንሱታል።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ፡ ፯ቱ የሳምንቱ ቀኖች፡ የእግዚአብሔር፡ የሥነ ፍጥረት ሥራው፡ በተራና በቅደም ተከተል የተካሄደባቸውንና በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡትን የዕለታት ስም እንደያዙ፡ የአዳምና ሔዋን ቋንቋ በሆነው፡ በግእዝ፡ “አሐዱ“፡ “አንድ“፡ ወይም፡ “መጀመሪያ ቀን” ለማለት፡ “እሑድ“፥ ቀጥሎ፡ “ሁለት“፥ ወይም፡ “ሁለተኛ ቀን” ለማለት፡ “ማግሰኞ“፡ ቀጥሎ፡ “አራት“፥ ወይም፡ “የሰንበት መግቢያ” ፥ ወይም፡ “የሳምንቱ ጊዜ፡ የሚጠልቅበት ቀን” ለማለት፡ “ስድስተኛው ቀን“፡ “ዓርብ“፥ በሰንበት ጌታ፡ በኢያሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፡ “ወደዘለዓለማዊነት” ከመለወጧ በፊት፡ ቀድሞ የነበረችበትን ሁኔታ ለማስታወስ፡ “ሰባተኛዪቱን የሰንበት ቀን“፡ “ቅዳሜ” ብለው ይጠርዋቸዋል።
ምዕራባውያን ግን፡ ለእነዚሁ የሳምንት ቀኖች፡ የሰጧቸውን የአረማውያን ጣዖታት አማልክቶቻቸውን ስም እንመልከት!
-
Sunday: Sun’s day (ሳንዴይ) ማለት የፀሓይ ቀን፥
-
Monday: Moon’s day (ማንዴይ) የጨረቃ ቀን፥
-
Tuesday: Tui’s day (ቱዩስዴይ)፡ ማለት፡ የጦርነቱ አምላክ፡ የቲዩ ቀን፥
-
Wednesday: Woden’s day (ዌድንስዴይ)፡ ማለት፡ የታላቁ አምላክ የውድን ቀን፥
-
Thursday: Thor’s day (ተርስዴይ)፡ ማለት፡ የነጎድጓዱ አምላክ፡ የቶር ቀን፥
-
Friday: Frigg’s day (ፍራይዴይ)፡ ማለት የታላቁ አምላክ፡ የዎድን ሚስት፡ የፍሪግስ ቀን፥
-
Saturday: Saturn’s day (ሳተርዴይ)፡ ማለት፡ የሰማዩ ኮከብ፡ የሳተርን ቀን።