በ አዮር ሰማይ ክልል ውስጥ የአሉት አሥራ ሁለት ዓለሞች
-
ሐመልማል
ይህ የምድር ሠራዊት እንሆን ዘንድ እኛ የተፈጠርንበት ዓለም ነው። ጠባቂውና እንዲሰለጥንበት እግዚአብሔር የፈቀደለት አድማኤል ኪሩብ ይባላል። የአዳም ነገድ ሁሉ ከእርሱ አብራክ ወጥቶአል።
-
ረሐም
የዚህ ዓለም ጠባቂ መልአክ ሳውራኤል ኪሩብ ነው። በዓለም ረሐም ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረቶች የበግና የፍየል መልክ የመሰለ ገፅ ሲኖራቸው የተሰጣቸው አእምሮ ከሰው ልጆች የላቀ የራቀውን የሚያውቁ የረቀቀውን የእግዚአብሔር ፍጥረትን ማየት የሚችሉ ናቸው። ከነርሱም ሌላ በረሐም ዓለም ውስጥ የተለያዩ ገጽ ያላቸው ቁጥራቸው ትእልፈተ–ትእልፊታት ፍጥረታቶች አሉ።
-
ገውዛ
የዚህ ዓለም ጠባቂው ኪሩብ መልአክ ሱርያኤል ነው። ገውዛውያን መልካቸው እንደ ሰው ልጆች መልክ ሁኖ ቀንድና ጅራት አላቸው። የጅንጆሮና የጉሬዛ መልክ የመሰለ የአላቸውም አሉ። ሁሉም ሁለት እጆችና ሁለለት እግር አሏቸው እንዲሁ ግዙፋንና እረቂቃን የሆኑ በራሪዎች ይኖሩባቸዋል። እርስ በእርሳቸው አይነካኩም የሳውራ አፈር ቅመው ይኖራሉ።
-
ሻርታ
የዚህ ዓለም ጠባቂው ኪሩብ መልአክ ስርጣጣኤል ይባላል። በሻርታ ዓለም የሚኖሩ ፍጥረቶች እንደ ዳሞትራ ስምንት እግሮች የአላቸው የአንበጣ ገጽ ያላቸው ምግባቸው እርስ በእርስ በመበላላት አንዳንዶችም እንደ እባብ የሚያሸቱበት አፍንጫ ባይኖራቸውም በምላሳቸው መካከል በአለ ቀዳዳ ያሸታሉ፡ በምላሳቸው ይነድፋሉ፡ ያያሉም፡ በየጊዜው ተፈጥረው የሚሞቱ ፍጥረቶች ናቸው።
-
ሰውድ
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ኪሩብ አዛዝኤል ይባላል፡ ሰውዳውያን ወደዚህ ዓለምና ወደ ሌላው ዓለም ለመንጠቅ እድል ተሰጥቷቸዋል። በሄዱበት ምድር ያለውን እፅዋት ያደርቃሉ፤ እሳተ ገሞራ ይፈጥራሉ፤ ተንቀሳቃሹን ሁሉ በነፋስ ያደርቁታል፤ እግዚአብሔር ለመቅሰፍት ያዘጋጃቸው ናቸው። ምግባቸው የሚቃጠል ዲንና ባሩድ የመሰለ ነው፡ ነገር ግን በሄዱበት ዓለም እንዲኖሩ እግዚአብሔር ስላልፈቀደላቸው ተመልሰው ወደተፈጠሩበት ዓለም ይሄዳሉ እንጂ
-
ሰንባላ
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአኩ ኪሩብ ስምስማኤል ይባላል። በሰንበላውያ ዓለም ትእልፊተ–ትእልፊታት የሚሆኑ በአየር የሚንሳፈፉና የሚበሩ በምድር የሚሽከረከሩ አእዋፋትና እንስሳት አራዊትም አሉ። እንደነዚህ ምድር ዓለም እርስ በእርሱ ይጣላል፤ ይበላላልም። ነገር ግን የማይበላሉ አሉ እነርሱም እድሜያቸው በእነሱ አቆጣጠር ከመቶ እስከ አራት መቶ ይደርሳል። ነገር ግን የእኛ ዘመንና የሰንበላውያን ዘመን የተለየ ነው።
-
ሚሳን
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ሚሳኤል ይባላል። የሚሳውያን መልካቸው የእንስሳና የአውሬ መልክ ይምሰል እንጂ የተፈጥሮ ባህሪያቸው ቅዱስ ነው። እግዚአብሔርን በክብር ያመሰግናሉ ይዘምራሉም። ከኤሮርያ ሰማይ ክልል ውስጥ ከሜምሮስ ዓለም ክበብ ውስጥ የሚኖሩትን ሮሃንያን ይመስላሉ /ረውሃንያ/ የተለያዩ የዜማ ድምፅ መሥሪያዎች አሏቸው።
አንዳንድ ግዜ ወደ እኛ ዓለም ምድር ይመጣሉ፤ የሚከለክላቸው የዓየር ጠባይ የለም፤ ግዙፋንም እረቂቃንም አሉአቸው። በባሕር ቢሄዱ አይሰጡም በእሳተ ገሞራ ቢገቡ አይቃጠሉም አለቱን ሰንጥቀው ቢገቡ የሚያግዳቸው የለም፡ የእግዚአብሔርን ፍጥረት ያከብራሉ የሰው ልጆችን ይወዳሉ እግዚአብሔርን ከማመስገን አፋቸው አይቋረጥም።
-
አቅራብ
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ አቅርናኤል ይባላል። በዓለም አቅራብ ውስጥ የሚኖሩት ፍጥረታት በባሕር ውስጥ ይኖራሉ። የመልካቸው ገጽ የዝሆንና የጊንጥ ቅርፅ አላቸው። የተለያዩ የፍጥረት ነገዶች አሉ ሁሉም በበሐር ውስጥ እንጂ ወደሌላ የአፈርና የእሳት ጠባይ ወደአላቸው አይሄዱም አይኖሩምም።
-
ቀውሳ
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ቀውቃሳኤል ኪሩብ ይባላል። በቀውሳ መሬት የሚኖሩ ከእሳት ተፈጥረው ከእሳት ፈሳሽ ውስጥ ስለሚኖሩ ብዛታቸው እንደሌሎች ዓለም ፍጥረት አይበዙም ቀውሳውያን የአገኙትን ይመገባሉ ያቃጥላሉ የእሳት ሕይወት ነው ያላቸው።
-
ዠዲ
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ አጂብጀማኤል ይባላል። በጀዲ ወይም በዠዲ ዓለም የሚኖሩ ፍጥረታት ከዚህች ምድር ዓለም የተፈጠሩትን እንስሳትና አራዊት አእዋፋትንም ይመስላሉ። በመልክ በግጽ እርስ በእርሳቸው የተለያዩም ቢሆን በልሳን ቋንቋ አንድ ናቸው በተለያየ የድምፅ መሳሪያ ይጠቀማሉ። ከሰው ልጆች የላቀ አእምሮ ስላላቸው የተጠበቡ መርማሪዎች ናቸው። በሰሩት የጥበብ መንኮራኵር ብዙ ዓለማትን ጎብኝተዋል ነገር ግን ከተፈጠሩበት ከዠዲ ዓለም ተለይተው ስለማይኖሩ ወደ መጡበት ተመልሰው ይሄሃሉ። ምግባቸውን እንደ ሰው ልጅ አብስለው የሚበሉና በመአዛው ብቻ የሚረኩ ነገዶች አሉአቸው እግዚአብሔርን በጣም ያመሰግናሉ።
-
ደለዋ
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ደለዋውኤል ኪሩብ ይባላል። ይህ ደለዋ ዓለም የክበቡ ጥልቀት በጣም የጠቆረ ጨለማ ከመሆኑ የተነሳ እንደበርባሮስ የሚያስፈራ ነው። ነገር ግን በውስጡ የሚኖሩ እልፍ አእላፋትና ትእልፊተ አእላፋት የሚሆኑ ፍጥረታት በትናጋቸውና በምላሳቸው በማሽተት የሚፈልጉትን መርጠው ይበላሉ።
በጆሮአቸው በዓይናቸው ፈንታ በምላሳቸው እንዲያዩና እንዲሰሙ እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ጨለማንና ብርሃንን ለይተው አያውቁም።
-
ሁት
የዚህ ዓለም ጠባቂው መልአክ ኩምኩማኤል ይባላል። በሁት ዓለም የሚኖሩ ፍጥረቶች እንደንብ መንጋ በአንድ ላይ የሚሰፈሩ እንደተራራም ይከመራሉ፤ ከመካከላቸው እንደንብ ወይም እንደምስጥ አንዲት እናት አላቸው። እናቲቱ እድሜዋ አልቆ ከሞተች ሁሉም በነው ያልቃሉ አፈር ይሆናሉ፤ ሕይወታቸው በእንስቲቱ ብቻ ነው ከነሱ ሌላ ሕይወት ያለው ፍጥረት የለም።
በኢዮር ክበብ ውስጥ ያሉት አስራ ሁለት ዓለማት እነዚህ ናቸው። የአእምሮ መንፈስ የአለው አስተውሎ ይመርምርና ይወቅ ጥበብ በዚህ አለ።
______________________________