Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • April 2024
    M T W T F S S
    1234567
    891011121314
    15161718192021
    22232425262728
    2930  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

Posts Tagged ‘ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ’

አቡነ ቴዎፍሎስ | ኮማንዶዎች በገመድ አንገታቸውን ሸምቀቅ አድርገው በማነቅ ከገደሏቸው በኋላ አስከሬናቸውን በርካታ ሬሳ በተጣለበት ጉድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on October 29, 2017

ጎፋ ገብርኤል አቅራቢያ የሚገኘውን አደባባይ በብጹዕነታቸው ስም ለመጥራትና ኃውልታቸውንም እዚያ ለማቆም ነበር ታቅዶ የነበረው። ለነገሩማ፤ ኃውልቱ እንዲያውም ከናፍጣ ጭስ ተገላግሎ በዚህች ንጹህና ውብ ቤ/ክርስቲያን ግቢ ውስጥ መተከሉ ሳይሻል አይቀርም።

የአገራችን፣ የወገናችንየአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጠላቶች እነማን እንደሆኑ ያው አሁን በግልጽ እየታየን ነው።

ለእነ “ቦብ ማርሊያ”፣ ለ “ካርል ሃይንስ ቡም” እና ለሌሎቹ ባዕዳውያን የአደባባዮች እና የመንገድ ስሞች ይሰጣሉ፣ ኃውልቶች ይቆማሉ፤ ለወገናችን ለአገራችን መስዋዕት ለከፈሉት ኢትዮጵያውያን ግን ቦታም አይሰጣቸውም።

አወይ ጊዜ አወይ ጊዜ
ጊዜ ነቃሽ ፤ጊዜ ወቃሽ
መንገደኛ ሁሉን ታጋሽ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ

ኢትዮጵያ ብዙ መከራዎችን አሳልፋለች ፤ ብዙዎቹ መከራዎች ከውጭ ወራሪዎች ቢደረሱም ከውስጥ ሀይሎችም ከደረሰው ጥቃት ያልተናነሰ መከራ በቤተክርስትያንና በሀገር ላይ ብዙ መከራ ደርሷል ፤ ይህች ቤተክርስቲያን ከዘመነ አክሱም ጀምሮ አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ ብዙ መንግስታትን አሳልፋለች ፤ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ነገስታት ለቤተክርስትያን እና ለህዝበ ክርስትያን በርካታ መልካም ተግባሮችን አከናውነው ወደማይቀረው አለም አልፈዋል ፤ ስማቸውም በየዘመኑ በመልካም እየተጠራ ትውልድም የሚዘክራቸው እስከ አሁን ድረስ አሉ ፤ ሌሎች ደግሞ የምትጠፋ መስሏቸው ጦር መዘውባታል ፤ በዘመናቸው ቤተክርስትያኒቷን ለማፍረስ ድንጋይ አንስተውባታል ፤ አሳት ለኩሰውባታል ፤ እርሷ ግን የመጣውን መከራ ተቋቁማ እጃቸውን ያነሱባትን ወደ ኋላ ትታ አሁን እኛ ትውልድ ላይ ደርሳለች፡፡

በሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ላይ የደረሰውን ነገር ማስትታወስ ይኖርብናል፡፡ ብጹዕነታቸው ስለ ቤተክርስቲያን በነበራቸው አቋም ምክንያት በግፈኞች ሕይወታቸውን በግፍ እንዲያልፍ ነበር የተደረገው፡፡

አቡነ ቴዎፍሎስ በእስር ቤት ደረሰባቸውን ፀዋትወ መከራ በዓይን ያዩ በታላቁ ቤተመንግስት አብረዋቸው ታስረው የቆዩ ፤ በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን በስልጣን ላይ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ የአይን ምስክሮች በተገኝው የቃል መረጃ መሰረት ቅዱስነታቸው መጀመሪያ የታሰሩት ለብቻቸው በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ነበር፡፡ በዚህ ቦታ ጥቂት ቀናት ከቆዩ በኋላ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ አስገብተው እጃቸውንና እግራቸውን ከአልጋ ጋር ጠፍረው አሰሯቸው ፡፡ ቀንም ሆነ ማታ ለሽንት ሲወጡ ካልሆነ በስተቀር ሰንሰለቱ አይፈታላቸውም ነበር በዚህ አይነት ለአራት ቀናት እንዲሰቃዩ ከተደረገ በኋላ ባለስልጣኖች ታስረውበት ወደነበረው ቁጠር አንድ እስር ቤት ወሰዷቸው።

ወቅቱ አብይ ፆም ነበር ከጎፋ ገብርኤል ተይዘው ከመጡበት ቀን ጀምሮ ለአርባ ቀናት ያህል እህል የሚባል ነገር አልቀመሱም ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጣታቸውን በውሀ ውስጥ በመንከር ከንፈራቸውን ከማርጠብ በስተቀር ጥም የሚቆርጥ ውሀ እንኳን አልጠጡም፡፡ ምግብ እንዲበሉ አንዳንድ ደርግ ባለስልጣናት እና አብረዋቸው ታስረው የነበሩ አዛውንቶች ለምነዋቸው ነበር ነገር ግን ለመብላት ፍቃደኛ አልነበሩም እስከ ፋሲካ ማግስት ድረስ ምንም ሳይቀምሱ ቆይተዋል ፡፡ ለፋሲካ ማግስት ግን እስረኞች መካከል አረጋውያኑ አጥብቀውና አስጨንቀው ስለለመኗቸው እህል ሊበሉ ችለዋል፡፡

በወቅቱ ከነበሩ ሰዎች መረጃ መሰረት ደርግ አቡነ ቴዎፍሎስን በእስር ቤት ስቃይ ካሳዩአቸው ሰዎች መካከል አንድ ሻለቃ የፈፀመባቸው ግፍ ሳይጠቀስ አይታለፍም ፡፡ ይህ ሰው እርሳቸውን የማበሳጨት ተልዕኮ ስለነበረው በንቀት ‹አባ መልአክቱ›› እያለ ይጠራቸው ነበር፡፡ ሞራልም የሚነካ አነጋገርም ይናገራቸው ነበር፡፡ ከወርቅ የተሰራ የእጅ መስቀላቸውን ቀምቶ እስከ መውሰድ ደርሶም ነበር፡፡ ከሚተኙበት ትንሽ ክፍል ውስጥ ሰቅለውት የነበረውን የጌታችን እና የመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስዕልም በስልጣኑ አውርዶ ወስዶባቸዋል፡፡ የዚህ ሰው ድርጊት ከበስተኋላው የሚገፋፋው ጠላት እንዳለ ያመላክት ነበር፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ የነበራቸው አነስተኛ ግላዊ ነፃነት እንኳን እስከዚህ ድረስ ተገፍፎ እንደነበር የሻለቃው ድርጊት ያሳያል፡፡

‹‹ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።›› የማቴዎስ ወንጌል 5(11-12)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በብዙ ስቃይ እያዩ በእስር ቤት የቆዩት እስከ ሐምሌ 7 1971 .ም ነበር፡፡ በዚህ ቀን እስረኛው እንዲሰበሰብ ታዞ ሲሰበሰብ አንድ ዘበኛ መጣና የሁለት እስረኞችንና የብፁዕነታቸውን ስም ጠርቶ ብርድ ልብሳቸውን እና የሽንት ቤት ወረቀታቸውን ይዘው እንዲወጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ወደ ክፍላቸው ገብተው አጭር ፀሎት ካደረጉ በኋላ ጥቁር ቀሚሳቸውን ለብሰው ነጠላ ጫማ አድርገው ቆባቸውን ደፍተውና ከእንጨት የተሰራ የእጅ መስቀላቸውን ይዘው እስረኞችን ካፅናኑ እና መስቀል ካሳለሙ በኋላ ‹‹ እግዚአብሔር ያስፈታችሁ›› በማለት ተሰናብተዋቸው ወጡ፡፡..

‹‹ጊዜው ክረምት ነበር አባታችን አቡነ ቴዎፍሎስ ተይዘው ወደ ራስ አስራት ካሳ ግቢ አዲስ አበባ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ተይዘው ሄዱ በወቅቱ የለበሱት ጥቁር የሐር ቀሚስ ጥቁር ነጠላ ጫማ ጥቁር የመነኩሴ ቆብ ነበር፡፡ እንደ ወትሮ በአንገታቸው ያጠለቁት ወይም በእጃቸው የያዙት መስቀል ግን አልነበረም ፡፡ በተጠቀሰው ግቢ ውስጥ ወዳለው ቤት እንዲገቡ ሲደረግ ከውስጥ የተደበቁ ኮማንዶዎች ባዘጋጁት ገመድ በድንገገት አንገታቸውን ሸምቀቅ አድርገው በማነቅ ገደሏቸው፡፡ወዲያውም አስከሬን የሚያነሱ ሌሎች ሰራተኞች አስከሬናቸውን አንስተው ከቤቱ ውጪ ባለው ግንብ ስር በስተ ምዕራብ በኩል በተቆፈረው እና በርካታ ሬሳ በተጣለበት ጉድጓድ ውስጥ ወርውረው ጣሉት›› (በጊዜው ከነበረ ወታደር የዓይን እማኝ የሰጠው ቃል)

ከዚህ በኋላ ቅዱስነታቸው የት እንደደረሱ ምን አይነት ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሳይታወቅ ለ13 ዓመት ተዳፍኖ ቆየ፡፡ ነገር ግን ‹‹ የማይገለጥ የተከደነ ፤ የማይታወቅ የተሰወረ ምንም የለም›› ማቴ 1626 እንደተባለው ጊዜ ሲደርስ በምን አኳኋን እንደሞቱና አስከሬናቸው የት ቦታ እንደተጣለ ሊታወቅ በመቻሉ በእንጦጦ አውራጃ ከፍተኛ 12 ቀበሌ 22 ከሚገኝው ከራስ አስራት ካሳ ግቢ አስከሬናቸው ተቆፍሮ ወጥቶ በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስትያን በክብር አረፈ፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ከአሜሪካ ቦስተን ዩኒቨርሲቲ በቴዎሎጂ የክብር ዶክትሬት ድግሪ አግኝተዋል ፤ 24 ሺህ ሰው በማሳመንና በማጥመቅ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች አድርገዋል ፤ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማቋቋም እንደ አንድ መምህር ከክፍል እየገቡ በማስተማር ምሳሌነታቸውን አሳይተዋል ፤ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ድርጅት መስርተዋል ፤ ቤተ ክርስቲያን ከዘመኑ ስልጣኔ ጋር ጎን ለጎን መራመድ ትችል ዘንድ ሰባኪያን ቀሳውስትና ዲያቆናት የሚሰለጥኑባቸው የካህናት ማሰልጠኛ ተቋማትን በየሀገረ ስብከቱ እንዲቋቋሙ አድርገዋል ፤ አሜሪካ ከሚገኝው ብሔራዊ የሰብአዊ ጥናቶች መርጃ ድርጅት የገንዘብና የመሳሪያ እርዳታ በመጠየቅ የብራና መጻህፍት የማይክሮ ፊልም ድርጅት አቋቁመዋል(አሁን በመንግስት የተወረሰ) ፤ የዘመን ጥርስ የበላቸው በርካታ በሺህ የሚቆጠሩ የብራና መጻህፍት ጨርሰው ሳይጠፉ ከየገዳማቱና ከየአድባራቱ በማሰባሰብ በማይክሮ ፊልም እንዲቀረጹ አድርገዋል ፤ ቤተክርስቲያን በራሷ ገቢ የምትተዳደርበት የሰበካ ጉባኤ ሃሳብ በማቅረብ አደራጅተው በቃለ አዋዲ እንዲመራ አድርገዋል ፤ የሕጻናት ማሳደጊያ ድርጅት እንዲቋቋም አድርገዋል ፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ በጠቅላላ ቤተክርስቲያን ያፈራቻቸው አለም አቀፋዊ ብቁ ዲፕሎማት መሆናቸውን ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡

______

Posted in Ethiopia, Faith, Infos | Tagged: , , , , , , , , , | Leave a Comment »