ከ መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት የተገኝ
በዚህ ጽሑፍ የቅዱስ ሚካኤልን ጽላት ወደ መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባ ምክንያት የሆኑትን አባት የአቶ በለጠ ዘነበን ታሪክና ስለታያቸው ራዕይ የሰጡንን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፦
መንበረ ልዑል
በመጀመሪያ ለመጠይቅ ፈቃድዎን ስለሰጡን በእግፍዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። የት እና መቼ ተወለዱ?
አቶ በለጠ
የተወለድኩት ሰሜን ሸዋ ግድምና ኤፍራታ ወረዳ በምትባል አነስተኛ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ በ1921 ዓ.ም. ነው።
መንበረ ልዑል
ትምህርት መቼና የት ተማሩ?
አቶ በለጠ
በአስር ዓመቴ ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በመግባት የዲቁና ማእረግ ተቀብያለሁ። እንዲሁም መስተጋብዕ አርባዕት ተምሬ አርያም ላይ ስደርስ ልብስና ስንቅ ስላለቀብኝ ወደ እናትና አባቴ ተመለስኩ።
መንበረ ልዑል
ትምህርት ካቋረጡ በኋላ ህይወትዎ ምን ይመስላል?
አቶ በለጠ
ትምህርቴን ባቋረጥቁ በዚያው ወቅት ክረምት ላይ ቀኑ ነሐሴ ፲፮ ቀን ሰዎች መተት ሰርተውብኝ ለ፫ ዓመታት ያህል አእምሮዬ በመቃወሱ በእግር ብረት ታስሬ በደብረ ሊባኖስና ሚጣቅ አማኑኤል ፀበል ስጠመቅ ቆይቼ ትንሽ ተሻለኝ። ከህመሜ ካገገምኩ በኋላ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ በመሄድ ወደ ካራ ቆሬ የሚያደርሰኝ መኪና እየፈለግኩ ሳለ “አሥመራ አሥመራ” የሚል አዎቶብስ አገኘሁ። መኪናው ውስጥ ገብቼ አስመራ ምጽዋ ወደሚባለው ቦታ ደረስኩ፡ እዛም ከሠራዊቱ ጋር የምገኘውን ምግብ እየበላሁ እኖር ጀመር። ነገር ግን ህመሙ ስላገረሸብኝ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ። አዲስ አበባም ለ፯ ዓመት ቆይቼ ወደ ትውልድ ሀገሬ በመመለስ ትዳር መስርቼ ለ፪ ዓመታት ያህል ቆየሁ። ነገር ግን ህመሙ ስለተመለሰብኝ ወደ አዲስ አበባ በድጋሚ መጣሁ።
መንበረ ልዑል
አዲስ አበባ በሚኖሩበት ወቅት መተዳደሪያዎት ምን ነበር?
አቶ በለጠ
አዲስ አበባ እንደመጣሁ የካርታ ስራ ድርጅት በሚባል መስሪያ ቤት በቀን ሰራተኛነት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩ። እዚያ ትንሽ ጊዜ ከሰራሁ በኋላ የተሻለ ስራ በማግኘቴ ወደ መዘጋጃ ቤት በጥበቃነት ተቀጥሬ እየሰራሁ እያለ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ቻልኩኝ። ከመዘጋጃ ቤት በመውጣት በሹፌርነት መስራት ጀመርኩ። ነገር ግን ብዙም በስራው ሳልገፋበት ትቸው ወጥሁ። በዚህ መካከል አንድ ህልም አየሁ።
መንበረ ልዑል
በወቅቱ የታየዎት ህልም ምን ነበር?
አቶ በለጠ
ነገሩ እንዲህ ነው። በህልሜ ፃድቁ አባታች ኤዎስጣቴዎስ መቅደሳቸውን እንድሰራ ሲያዙኝ አየሁ። እኔም ቤተክርስቲያን የሚሆን ቦታ እየፈለኩ እያለ ስኔ12 2001 ዓ.ም. ምሽት ላይ ቅዱስ ሚካኤል በህልሜ ታየኝ። ህልሙም ምስካየ ግዙናን አስቀድሼ ስመለስ 6ኪሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ በር ላይ ሚዛንና ሰይፍ የያዘ ሰው ወደ አንደኛ በር ይጠቁመኝ ነበር። ብንን ስል ከሌሊቱ ዘጠኝ ሆኗል። ይህ ነገር ከዛን ጊዜ ጀምሮ በየወሩ3 ወይም 4 ጊዜ “ተናገር!“ እያለ ያዘኛል። እኔ ግን አቅም የለኝም ምን ብዬ ልናገር ስል፡ “ነፃ አውጣኝ መታሰሩ ይበቃኛል!“ እያለ እየመላለሰ ይነግረኝ ነበር።
እኔም ይረዱኛል ብዬ በማስባቸው ባለሀብቶችና ታዋዊ ሰዎች ብጠቁምም መፍትሄ ሳላገኝ ድካም ብቻ ሆኖ ቀረ።
መንበረ ልዑል
የዚህ ህልሞዎት መጨረሻ ምን ሆነ?
አቶ በለጠ
የሚረዳኝ ሰው ባጣሁበት ሰዓት አሁን በህይወት ለሌሉት ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ደብዳቤ ድፊእ ጉዳዩን ስከታተል እሳቸውም በህይወተ ሥጋ ስለተለዩ በዚህም ምክንያት ከ ፫ አመት በኋላ እንደገና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጉዳዩን አመለከትኩ። ወደ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ተመርቶ እየተመላለስኩ ጉዳዩን ስከታተል በ፪ሺ፱ ዓ.ም. መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ከ፱ ዓመታት በኋላ ጉዳዩ መስመር እየያዘ መሆኑን ሰማሁ። በስተመጨረሻም፡ ህዳር ፲ ፪ሺ፱ ዓ.ም. ማለዳ በክብር ወደ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ታቦተ ህጉ እንዲገባ ሆነ። በወቅቱም ከተሰማኝ ደስታ የተነሳ እያነባሁ ነበር።
መንበረ ልዑል
በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት አለ?
አቶ በለጠ
በመጨረሻ የማስተላልፈው መልዕክት ይህንን ነገር ሁሉ በዓይኔ ላሳየኝ ለፈጣሪ ክብር ምስጋና ይሁን፡ እንዲሁም በዚህ መንፈሳዊ ስራ የተራዱኝን ሁሉ አምላከ ቅዱስ ሚካኤል ዋጋቸውን ይክፈልልኝ እያልኩኝ አሁንም ለጊዜው የማልናገረው ብዙ ነገር አለኝ።
መንበረ ልዑል
አባታችን አቶ በለጠ ቅዱስ ሚካኤል በእርስዎ ላይ አድሮ የገለጠውን ተዓምር ስላካፈሉን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፤ እግዚአብሔር ይስጥልን።
ታላቁ ደብር መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ወቅት
የ ፺፫ አመታት ዕድሜ ባለጸጋ የሆነው ታላቁ ደብር መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በዘመናት ብዙ ታሪካዊ ሂደቶችን አልፎ ከአሁኑ ትውልድ ደርሷል። የቤተክርስቲያኑ ታሪክ እንደሚያስረዳው ወደ ቅጽረ ቤተክርስቲያኑ የሚመጡት የንጉሳውያን ቤተሰብ ብቻ በመሆናቸው ምዕመናኑ ደብሩን የሚያውቁበት እድል አልነበራቸውም። ለዚህም ይመስላል ለመጀመሪያ ጊዜ ታቦተ ህጉ ለክብረ በዓል የወጣው ከተተከለ ከ፶፫ አመት በኋላ ሚያዝያ ፴ ፲፱፻፷፱ ዓ.ም መሆኑ እንዲሁም የቅዱስ ሚካኤል በዓል ህዳር ፲፪ ፲፱፻፸ ዓ.ም መከበር መጀመሩ ከህዝቡ እይታ የራቀ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው። ቢሆንም በደብሩ የታሪክ ጉዞ ውስጥ በርከት ያሉ ጥቧን አባቶች የተገኙ ሲሆን እንዲሁ አሁንም በቀደሙት አባቶች መንፈስ የሚጓዙ ሥጋቸው ለነፍሳቸው የተገዛላቸው አንጋፋ አባቶች የሚገኙበት ታላቅ ደብር ነው።
ይህም ደብር ፻ኛ አመቱን በቅርብ አመታት ለማክበር በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ይገኛል።
በአመት ውስጥም ጥቅምት ፴ እና ሚያዝያ ፴ የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ አመታዊ ክብረ በዓል እና ህዳር ፲፪ ፣ጥር ፲፪ ፣ ሰኔ ፲፪ የቅዱስ ሚካኤል አመታዊ ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀት በደብሩ ይከበራል። በተጨማሪም ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉበት በዓለ ሃምሳ በጽርሐ ጽዮን እንደሆነ ይታወቃል። ይህም የሐዋርያውና የሰማዕቱ ወንጌላዊ ማርቆስ እናት ቤት መሆኑን የሊቃውንት መጽሐፍት ይመሰክራሉ። ይህንንም አብነት በማድረግ “በዓለ ሃምሳ” ከቅዱስ ማርቆስ ታሪክ ጋር በማስማማት በታላቅ ድምቀት በደብሩ ይከበራል።