❖ ዛሬ በብቸኛነት ለፍትሕ እና ለሕልውናቸው እየታገሉ ካሉት ከጽዮናውያን ተጋሩ፣ አገው እና ቅማንት ኢትዮጵያውያን ጎን ያልቆመ በጭራሽ ክርስቲያንም፣ ኢትዮጵያዊም፣ የእግዚአብሔር ልጅም ሊሆን አይችልም!
✞✞✞ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የምትላቸው እነማንን ነው? ✞✞✞
😇 ቅዱሳን መላእክት፡– ቅዱሳን መላእክት ከማንኛውም ነገር የራቁ፣ ሥርዓታቸውን የጠበቁ፣ እግዚአብሔርን ያወቁ፣ እግዚአብሔርን የሚቀድሱ ስለሆኑ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
“አንዱም ለአንዱ፣ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡” [ኢሣ. ፮፥፫]ስለዚህ በባህሪዩ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔርን ስለሚያመሰግኑ፣ ስለሚቀድሱ ቅዱሳን ተብለዋል፡፡
😇 ቅዱሳን አበው፡– መጻሕፍት ሳይጻፍላቸው መምህራን ሳይላኩላቸው በሕገ ልቡና በቃል ብቻ የተላለፈላቸውን ይዘው እንዲሁም በሥነ ፍጥረት በመመራመር ፈጣሪያቸውን አምነው እርሱ የሚወደውን ሥራ የሠሩና በጣኦት አምልኮ ራሳቸውን ያላረከሱ አባቶች ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ትላቸዋለች፡፡ ለምሣሌ አበው ብዙኃን አብርሃም ኩፋሌ [፶፥፵፪፡፵፬፣ ፲፩፥፩]
😇 ቅዱሳን ነቢያት፡– እግዚአብሔር ከማኅፀን ጀምሮ ጠርቶ መርጧቸው ሀብተ ትንቢትን አጐናጽፏቸው ያለፈውንና ወደፊት የሚሆነውን በእርግጠኝነት እየተናገሩ ሕዝቡን ይመክሩትና ይገስጹት የነበሩ ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ማዕረግ የምትጠራቸው አባቶች ናቸው፡፡
“ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎችበ መንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” [፪ኛጴጥ ፩፥፳፭] እንዲል፡፡
😇 ቅዱሳን ሐዋርያት፡– በነቢያት የተነገረውን ቃለ ትንቢት መድረሱንና በዘመናቸው መፈጸሙን ለዓለም እንዲያስተምሩ ጌታችን ራሱኑ ተከተሉኝ ብሎ የጠራቸውና የመረጣቸው ናቸው፡፡
“በእውነት ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው፡፡ወደ ዓለም እንደላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንደሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ“[ዮሐ. ፲፯፥፲፯፡፲፱]
😇 ቅዱሳን ጻድቃን፡– ቅዱሳን ጻድቃን ጌታን አርአያ አድርገው መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ ዓለም ተለይተው ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳዋው አስገዝተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምናኔ ጸንተው ድምጸ አራዊትን፣ ጸብአ አጋንንትን፣ ግርማ ሌሊትን ሳይሳቀቁ ዳዋ ጥሰው፣ ደንጊያ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው የኖሩ አባቶችን ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ማዕረግ ታከብራቸዋለች፡፡
“ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል“[ማቴ ፲፥፵፪] እንዲል፡፡
😇 ቅዱሳን ሰማዕታት፡– ቅዱሳን ሰማዕታት ጌታችን በጲላጦስ ፊት “እኔ እውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ“[ዮሐ ፲፰፥፴፯] ያለውን ምስክርነት በመከተል እግዚአብሔርን አንክድም ለጣኦት አንሰግድም በማለት በዓላውያን ነገስታት ፊት ሳይፈሩና ሳያፍሩ ቆመው የመሰከሩትን ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ትጠራቸዋለች፡፡
😇 ቅዱሳን ነገሥታት፡– እንደ አሕዛብ፣ ዓላማውያን ነገሥታት በሥልጣናቸው በሀብታቸው በሠራዊታቸው ሳይመኩ ኃይማኖት ይዘው ምግባር ሰርተው የተገኙ እንደ ዳዊት ያሉ ቅዱሳን አባቶችናቸው፡፡
😇 ቅዱሳን ሊቃውንት፡– ቅዱሳን ሊቃውንት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያልተመሰለውን መስለው የተመሰለውን ተርጉመው በማስተማር መጻሕፍትን በመተርጐም መናፍቃንን ጉባኤ ሰርተው ረትተው ያስተማሩ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
“መልካሙን የምስራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው” [ሮሜ. ፲፥፲፭]
😇 ቅዱሳን ጳጳሳት፡– ቅዱሳን ጳጳሳት የካህናትና የምዕመናን፣ የሰማያውያንና የምድራውያን አንድነት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በኃይማኖት በመምራት መንጋውን ከተኩላ በመጠበቅ የክርስቶስን ትዕዛዝ የፈጸሙ ቅዱሳን ናቸው፡፡
😇 ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል)፡– ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል) ከሕገ እንስሳ ሕገ መላእክት ይበልጣል ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አጭተው ከሴት ወይም ከወንድ ርቀው ስለ መንግሥተ ሰማያት ብለው ራሳቸውን ጃንደረቦች ያደረጉ ናቸው፡፡
😇 ቅዱሳት አንስት፡– ጌታችን መርጦ ካስከተላቸው ፻፳/120ው ቤተሰብ ፴፮/36ቱ ቅዱሳት አንስት ጌታ ሲሰቀል ሳይሸሱ፣ በመቃብሩም በመገኘት፣ የትንሳኤው ምስክርም በመሆን መከራ በበዛበትና በጸናበት የክርስትና ጐዳና የተጓዙ እናቶች፣ እህቶች ሁሉ ቅዱሳት አንስት ይባላሉ፡፡
😇 ቅዱሳት መካናት፡– ማለት የተለዩ፣ የተከበሩ ሥራዎች ቦታዎች እግዚአብሔር በመዝሙር፣ በቅዳሴ፣ በማኅሌት ይገለገልባቸው ዘንድ የመረጣቸው ገዳማትና አድባራት ቅዱሳት መካናት ይባላሉ፡፡
“የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ኢያሱን፡– አንተ የቆምክባት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው” [ኢያሱ ፭፥፲፭]
😇 ቅዱሳት መጻሕፍት፡– ቅዱሳት መጻሕፍት የሚባሉት የብሉያትና ሐዲሳት፣ የመነኮሳትና ሊቃውንት፣ እንዲሁም አዋልድ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስንል የተመረጡ፣ የተከበሩ የተወደዱና የተመሰገኑ መጻሕፍት ማለት ነው፡፡
😇 ቅዱሳን መጻሕፍት ቅዱስ መሰኘታቸው የሰውን ልጅ መነሻና መድረሻ ታሪክ በሦስቱም ሕግጋት የተነሱ ቅዱሳን ጥንተ ክብራቸውን ገድላቸውን ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ጸጋ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ልጅ ለማዳን ያደረገውን ጉዞ የማዳን ሥራውን ስለያዙ ቅዱሳን ተባሉ፡፡
😇 ቅዱሳትሥዕላት፡– በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፈቃድ ተስለው የእግዚአብሔር ስም በሚጠራበት ቦታ የሚቀመጡና ከስዕሉ ባለቤት ተራዳኢነትና በረከትን ለማግኘት የሚጠቅሙ የእግዚአብሔር ልዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡ [ዘፀ. ፳፭፥፲፰፡፳፪፣ ዘኁ.፯፥፹፱]
ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለማውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው ነው፡፡ የቅዱሳኑ ቅድስና ሥዕላቱንም ቅዱሳት አሰኝቷቸዋል። ሥዕላቱ በራሳቸው የሚያደርጉት ገቢረ ተአምራት ቅዱሳት አሰኝቷቸዋል፡፡
😇 ቅዱሳት ንዋያት፡– በእግዚአሔር ቤት ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ንዋያት ሁሉ የተቀደሱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱ የሚፈፀመው ቅድስና የባህሪይ ገንዘቡ ለሆነ ለእግዚአብሔር ነውና፡፡
✞ ቅዱስ መስቀል፡– የጌታችን ቅዱስ መስቀል ሕያው፣ አማናዊ በሆነው በክርስቶስ ደም ከመክበሩ የተነሳ ቅዱስ ተብሏል፡፡ (ቅዱስ ያሬድ ስለመስቀሉ በድጓ ዘክረምት ላይ እንዲህ ብሏል) “የቅዱሳን ክብራቸው የጻድቃን ሞገሳቸው የዕውራን ብርሃናቸው እነሆ ይህ መስቀል ነው” ብሏል፡፡
✞ ታቦት፡– ቤተክርሲያን ቅዱስ ብላ ከምታከብራቸው አንዱ ታቦተ ሕጉን ነው፡፡
ታቦት ማለት በግእዝ ቋንቋ ማዳሪያ፣ ማዳኛ ማለት ሲሆን በዚህ ታቦት ላይ እግዚአብሔር የሚያድርበትና የሚገለጥበት የጽላት ሕጉ ማዳሪያ ነው፡፡ [ዘፀ. ፳፭፥፳፪]
________________