[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፵፬]
፩ አቤቱ፥ በጆሮአችን ሰማን፥ አባቶቻችንም በዘመናቸው በቀድሞ ዘመን የሠራኸውን ሥራ ነገሩን።
፪ እጅህ አሕዛብን አጠፋች፥ እነርሱንም ተከልህ፤ አሕዛብን ሣቀይኻቸው አሳደድኻቸውም።
፫ በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸው፤ ቀኝህና ክንድህ የፊትህም ብርሃን ነው እንጂ ወድደሃቸዋልና።
፬ አምላኬና ንጉሤ አንተ ነህ፤ ለያዕቆብ መድኃኒትንህ እዘዝ።
፭ በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን።
፮ በቀስቴ የምታመን አይደለሁምና፥ ሰይፌም አያድነኝምና፤
፯ አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን፥ የሚጠሉንንም አሳፈርሃቸው።
፰ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን፥ ስምህንም ለዘላለም እናመሰግናለን።
፱ አሁን ግን ጠላኸን አሳፈርኸንም፥ ከሠራዊታችንም ጋር አትወጣም።
፲ ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ኋላችን መለስኸን፥ የሚጠሉንም ተነጣጠቁን።
፲፩ እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን።
፲፪ ሕዝብህን ያለ ዋጋ ሰጠህ፥ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም።
፲፫ ለጎረቤቶቻችን ስድብ፥ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን።
፲፬ በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ፥ በሕዝብም ዘንድ የራስ መንቀሳቀሻ አደረግኸን።
፲፭ ጕስቍልናዬ ሁልጊዜም በፊቴ ነው፥ የፊቴም እፍረት ሸፈነኝ።
፲፮ ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ፥ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው።
፲፯ ይህ ሁሉ በእኛ ላይ ደረሰ፥ አልረሳንህም፥ ኪዳንህንም አልወነጀልንም።
፲፰ ልባችን ወደ ኋላው አልተመለሰም፥ ፍለጋችንም ከመንገድህ ፈቀቅ አላለም፤
፲፱ በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና፥ በሞት ጥላም ሰውረኸናልና።
፳ የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢሆን፥ እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢሆን፥
፳፩ እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን? እርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና።
፳፪ ስለ አንተ ሁልጊዜም ተገድለናል፥ እንደሚታረዱም በጎች ሆነናል።
፳፫ አቤቱ፥ ንቃ፤ ለምንስ ትተኛለህ? ተነሥ፥ ለዘወትርም አትጣለን።
፳፬ ለምንስ ፊትህን ትሰውራለህ? መከራችንንና ችግራችንንስ ለምን ትረሳለህ?
፳፭ ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና፥ ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለችና።
፳፮ አቤቱ፥ ተነሥና እርዳን፥ ስለ ስምህም ተቤዠን።