እኛ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ዓለም ጨለማ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ቀድመን ያወቅንና የሰለጠን፤ ጥሩን ከመጥፎው፤ ጽድቁን ከኃጢአት ለይተን የተረዳን፤ ከአምስት ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለን ሰብአዊ ክብራችን የጠበቅን ሕዝቦች፤ ለፈጣሪያችን ተገዥ፤ ሰውን አክባሪ፤ ሃይማኖተኞች መሆናችንን ለመረዳት ጥንታዊ ታሪካችንን ማየት ይገባል፡፡ ለምሳሌ፡– ዓባይ (ናይል) ግዮን ወንዝን በተመለከተ፤ ከቀይ ባህር በተያያዘ መልኩ ከውጩ ዓለም ጋር የነበረን ግንኙነት፤ ሀገራችን የመን ድረስ የነበራትን የይዞታ ስፋትና የሕንድ ውቅያኖስን በመጠቀም ከህንድና ከሌሎች ዓለማት ጋር የነበረንን የጠበቀ ትስስር መመልከቱ በቂ ማስረጃ ሊሆነን ይችላል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ ጸሐፍትና በፈላስፎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስም የታወቀች አገር ናት። የሕዝቧም ማንነት በቅዱስ መጽሐፍ (በብሉይ ኪዳን) እና በሐዲስ ኪዳን ተገልጧል። ሙሴ የሥነ ፍጥረትን ታሪክ በተናገረበት በመጀመሪያው መጽሐፍ ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ የተከበበች አገር መሆኑዋን ተናግሯል። “የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም ኢትዮጵያን ምድር ይከበዋል” የሚል ማስረጃ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ዘፍ 2÷13
እስራኤልን ከግብፅ ነጻ ያወጣው ታላቁ ነቢይ ሙሴ የዮተር ኢትዮጵያዊ ልጅን ያገባ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ዘኁ. 12÷1
መጽሐፍ ቅዱስ የኢትዮጵያን ሕዝብና ምድር ሁልጊዜ ከግብፅ ጋር በማያያዝ ይናገራል፡፡ ኢሳ. 20÷3-6፣ ሕዝ. 20÷4-51፣ ዳን. 11÷43፤ ናሆ. 3÷9
በጂኦግራፊ አቀማመጥም ኢትዮጵያ ከግብፅ ደቡብ የምትገኝ አገር መሆኑዋ በቅዱስ መጽሐፍ ተነግሯል ሕዝ. 29፣10፣ ዮዲ .1÷10
ሱዳንንና ግብፅን ሲያጠጡ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ወንዞች ዐባይና ተከዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የታወቁ ታላላቅ ታሪካዊ ወንዞች ናቸው ኢሳ. 18÷1
ኢትዮጵያ በማዕድን የከበረች አገር እንደመሆንዋ አልማዟና ወርቋም በዓለም ተደናቂ ነበር፡፡ኢዮ. 28÷19
ሕዝቧም በንግድ ሥራ በዓለም የታወቁ ነበር። በንግዳቸውም በልጽገውና ተደስተው ይኖሩ ነበር። ኢሳ. 43÷3
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ድንክ አጭር፣ እንደ አዛሔል ረዥም ሳይሆኑ ልከኛና መጠነኛ ናቸው። ኤር. 13÷23
የኢትዮጵያ ግዛትም እጅግ በጣም ሰፊ እንደ ነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይመሰክራል። በዜና መዋዕል ካልዕ እንደተገለጸው ኢትዮጵያውያን በጦር ስልትና በጀግንነት ከጥንት ጅምሮ የታወቁ ናቸው ዜራህ (ዝሪ) በሚባለው ንጉሣቸው እየተመሩ ዘምተው ምድረ ይሁዳን ያዙ 2ኛ ዜና መዋ. 14÷9-15፣ 16÷8
ኢትዮጵያውያንን ያለ ፈቃደ እግዚአብሔር በኀይላቸው ተመክተው በሚሠሩት ሥራ ነቢያት ይገሥፁአቸው ነበር። ሶፎ. 2÷12
በእግዚአበሔርና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የማያቋርጥ ፍቅርና ግንኙነት ሲገልጡ ደግሞ “ኢትዮጵያ እጆቹዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” እያሉ በግልፅ ተናግረዋል። መዝ. 68÷31
ከዚህ ሌላ እንደ ባጅ ያሉ ታዋቂ ታሪክ ጸሐፊዎች ኢትዮጵያ ያለ ሃይማኖት የኖረችበት የታሪክ ዘመን እንደሌለ ጽፈዋል። ይህም ያገር ውስጥ ታሪክ ጸሐፊዎች ከሚሰጡት የምስክርነት ቃል ተጨማሪ ነው።
ኢትዮጵያ ከክርስትና በፊት ስለነበራት ሃይማኖት ስንናገር የአቅኒዎቹዋን የሕይወት ታሪክ በመመርመር ነው። ኢትዮጵያን ያቀኑ ሰዎች የመምለኬ እግዚአብሔር የኖኅ የልጅ ልጆች የአያታቸውን አምላክ አንድ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር።
በተጨማሪም በሐዲስ ኪዳን ክርስትናን በ34 ዓ.ም እንደተቀበለች እነዚሁ ብሔራውያን ሊቃውንት፦ ኢትዮጵያውያን የቅዱስ ፊልጶስን ትምህርትና ስብከት ከጃንደረባው ሰምተው ክርስቶስን መቀበላቸውንና ማመናቸውን ሲገልጡ እንዲህ ብለዋል።
“…. መጥምቁና የወንጌል ሰባኪው ሐዋርያ ፊልጶስ ሆይ! ኢትዮጵያውያን ትምህርትህን ከብልሁ ጃንደረባ ሰምተው ለድንግል ማርያም ልጅ ይሰግዳሉ…..”
ወይም መባቸውን ይዘው ለተወለደው ሕፃን ሊሰግዱለት ቤተልሔም ከተገኙ ሰብአ ሰገል አንዱ ኢትዮጵያዊ ከባዜን ንጉሥ የተላከ መሆኑ ግልጽ ነው።
ይህ አገላለጥ ጃንደረባው በመንፈስ ቅዱስ ከተላከለት አስተማሪው ከቅዱስ ፊልጶስ የተማረውን ትምህርት ለኢትዮጵያውያን በማስተማሩ ዳዊት በመዝሙሩ 72÷9 “በፊቱም ኢትዮጵያውያን ይሰግዳሉ” ሲል የተናገረው ትንቢት እንደተፈጸመ ያሳያል።
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ” ብሎ እምነቱን በመግለጡና በማረጋገጡ “ኢየሱስ የእግዚብሔር ልጅ እንደሆነ በሚያምን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል፤ እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል” (1ኛ ዮሐ. 4÷15) የሚለው አምላካዊ ተስፋ የተፈጸመለት እውነተኛ አማኝ ነበር።
ጃንደረባው የጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን በምታጠምቅበት ጊዜ ትጠቀምበት ለነበረው ሥርዐተ ተአምኖ ጀማሪ መሆኑ ይነገርለታል። ሥርዐቱም የሚከተለው ነው።
አጥማቂው ካህን፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ታምናልህን? ተጠማቂ ምእመን፡– አዎ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ።
ይህ ሥርዐት ከወንጌላዊው ፊልጶስና ከጃንደረባው ንግግር ጋር ስለሚተባበር ከዚሁ እንደተወሰደ ይታመናል። የሐዋ. ሥራ 8÷37
ወንጌላዊው ፊልጶስና ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በምን ቋንቋ እንደተነጋገሩ የግብረ ሐዋርያት አንባቢዎች ሁሉ ለማወቅ እንደሚፈልጉ ግልጥ ነው። ድርጊቱ የተፈጸመው በ34 ዓ.ም በተከበረው በበዓለ ሐምሳ ሰሞን እንደሆነ በሐዲስ ኪዳን ተገልጧል። ስለሆነም ወንጌላዊው ፊልጶስ በበዐለ ሐምሳ ዕለት ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ የመናገር ስጦታን መቀበሉ የታመነ ንው። ስለሆነም ጃንደረባው በራሱ ቋንቋ በግእዝ መጽሐፈ ኢሳይያስን በሚያነብበት ጊዜ ፊልጶስ ሊሰማውና ሊያነጋግረው ችሏል። በመሆኑም ፊልጶስና ጃንደረባው የተነጋገሩበት ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ግእዝ ነበር።
በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ክርስትናችን ሁሉ በተለይ ሰብአዊ ክብራችንና ጤናማ ሕይወታችን በጠበቀ መልኩ ለመምራት የነበረን አሁንም ያለን ጥሩ ትውፊት በቀላሉ የሚለካና የሚታይ አይደለም፡፡ ሊቃውንቱ ሰዎች ሰላማዊና ጤናማ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ ለምርምር የጻፏቸው መጻሕፍት፤ ለመድኃኒትነት የዕፀው ቅመማ፤ የግብረ–ገብ (መልካም ሥነ ምግባራት ትምህርት) ጽሑፎቻችንን በዘረፋ እና በስርቆት ወደ ውጭ ሀገር ቢሄዱብንም አሻራቸው ግን አሁንም አለ፡፡ በጥንት ጌዜ ሰዎች ከልዩ ልዩ ዕፀው መድኃኒት እየቀመሙ በሽተኞችን ይፈውሱ ነበር ኢሳ. 38÷21 ኤር. 8÷22 ሕዝ. 47÷12 ኩፋሌ. 10÷7 እግዚአብሔር አምላክ ለኖኀ መድኃኒትነት ያላቸውን ዕፀው አሳይቶታል።
ጥበብ፣ ማስተዋል፣ ዘዴ ማንኛውንም ነገር ለማግኘት የመመርመር ችሎታ፣ የሥራ ችሎታ የሕክምና ችሎታ የአስተዳደር ችሎታ ያላቸው ሁሉ ጥበበኞች ይባላሉ፡፡ ዘፍ. 31÷2-5 ሕዝ. 27÷8-9
ሰው እግዚአብሔርን በመፍራት ጥበብን ያገኛልና በእግዚአብሔር መንገድም ይራመዳልና መዝ.111÷10፣ ያዕ. 1÷5 ሆኖም ተማርን የሚሉ ሰዎች ጥበብ ከእግዚአብሔር ጥበብ ጋር ሲመዛዘን እንደ ምንም ወይም እንደ ኢምንት ነው።
ሰው ጥበበኛ ነኝ ቢልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ባዶ እንደ (አላዋቂ) ነው። ምክንያቱም አወቅሁ ተፈላሰፍኩ መጠቅኹ የሚል ሰው በእግዚአብሔር ከሃሊነት የተፈጠረ እና ሙሉ ሕይወቱም በእግዚአብሔር ሥልጣን የተወሰነ ስለሆነ እያንዳዱ ሰው እንደ ወቅቶች ታይቶ የሚሔድና የሚያልፍ መሆኑን ማወቅና መመራመር በራሱ ጥበብ ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አንዱ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ 1ቆሮ. 12÷8፣ ሮሜ 1÷22፣ 1ቆሮ. 1÷19፣ ያዕ 3÷13
ይህን እውቀታችንና ጥንታዊነታችንን መነሻና መሠረት በማድረግ አሁን ዓለም በግሎቫላይዜዥን ከደረሰበት ስልጣኔ ጋር እንዴት አድርገን በማጣጣም የሚበጀንን ብቻ መጠቀም እንዳለብን ቆም ብሎ በማሰብና በማስተዋል ሊሆን ይገባል፡፡ ሁሉም ነገር ከውጭ የመጣውና ጊዜ የወለደው ፍልስፍና ሁሉ ጥሩ ነው ብለን የምናምንና የምንቀበል ከሆን ወይም ዘመናዊነትን ብቻ የምንከተል ከሆነ አደጋው በትውልድና በሀገር እንዲሁም በነፍስም ሆነ በሥጋ የከፋ ይሆናል፡፡
አሁን በቀላሉ የምናያቸውና የምንሰማቸው ከጊዜ በኋላ ዋጋ ሊያ ስከፍሉን ይቸላሉና ነው።
ጥሩ ማስተዋል የተሞላበት ዕውቀት ምን ጊዜም ቢሆን ሰውን ወደ እግዚአብሔር ይመራዋል እንጂ ከእግዚአብሔር አያርቀውም። ከእግዚአብሔር የሚያርቅ ሃይማኖታዊ ያልሆነ ሥጋዊ ዕውቅት ብቻ ነው።
ሀ. ሳይንስና ሐኪሞቹ
ብዙዎችን ሰዎች በተለይ በሕክምና ሙያ ባሉ ክፍሎች ከሃይማኖት እንዲርቁ የሚያደርጉዋቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ሙያቸው ሳይሆን የአምላክን ሥራ ተመራምረው መድረስ ባለመቻላቸው ነው። ይህ ደግሞ ክህደቱ የብስጭት ይመስላል፡፡ ዛሬ የምናየው የሳይንስ ዕድገት በሚያደርገው ምርምርና (መፈላሰፍ) ለብዙዎች ሰዎች የዕውቀት ዳርቻ ሆኖ ታይቷቸው ሊሆን ይችላል። ከዚህ በፊት ያልታዩና የማይታወቁ የነበሩት ነገሮች ሁሉ ዛሬ በልዩ ልዩ መሣሪያዎች ርዳታ በመገለጻቸው ምክንያት ብዙ ሰዎች የፍጥረት ምስጢር እንደተገኘ አድርገው ቈጥረውታል። ስለዚህ ዛሬ ከመታየትና ከዕውቀትም ውጭ የሆነ ነገር ሁሉ በብዙዎች ዘንድ እንደሌለ ያህል እስከ መቈጠር ደርሷል። ነገር ግን በእውነቱ ከሆነ እነዚህ ሰዎች ምንኛ ተሳስተዋል? ዛሬ የሰው ልጅ የደረሰበት የዕውቀት ደረጃ ምንም እንኳ ካለፈው ዘመን ጋራ ሲነጻጸር ከፍ ያለ ሁኖ ቢታይም ቅሉ እውነቱ ሲታይ የምናውቀው ነገር ከማናውቀው ነገር ጋር ሲነጻጸር ከዕውቀት ጫፍ መድረሳችን ቀርቶ ገና ከመጀመሪያው (ከመነሻው) ትንሽ ፈቀቅ እንኳ እንዳላልን ለምን አንረዳም። አንዳንድ ሰዎች በሃይማኖት እግዚአብሔርን ከማመን የሚርቁት ስለ ሰው የዕውቀት ደረጃ እንዲህ ዐይነት አስተያየት ስለሌላቸው ነው። ይኸውም የሰው ልጅ ሊኖር የሚቻለውን ነገር ሁሉ እንዳገኘና እንደ ተረዳው አድርገው ያስባሉ። በመሆኑም ከዕውቀት ውጭ የሆነውንና ሊታይ ወይም ሊዳሰስ የማይቻለውን ሁሉ ሊቀበሉት ያዳግታቸዋል። ግን ይህ ሁሉ መሳሳት ነው። ለዚህ ጉዳይ ታላላቅ ሳይንቲስቶችንም ሆነ ሊቃውንትን መጠየቅ ያስፈልጋል። መጻሕፍቶቻቸውንም ወስደን ብንመለከት እንዲህ ያለው አመለካከት ስሕተት መሆኑን ያረጋግጡልናል። ለመሆኑ ሳይንስ ገና ከዚህ መቼ ደረሰና! ገና ልናውቀው የሚገባን የዚህ ዓለም ምስጢር የትና የት! ሳይንስ ስለ ዓለም የመጨረሻውን ጥበብ ሰጥቷል ብለን ስንደመድም በማግስቱ እንደገና አዳዲስ ነገሮችና በሽታዎች ሲፈጠሩ እናያለን። በዚሁ ጉዳይ ተመራማሪዎች በየበኩላቸው የሚያቀርቡትን ሐሳብ ብንሰማ በእውነቱ ከዚህ በላይ ስለ ሳይንስ ከፍተኛ ግምት ባልደረስን ነበር።
ዛሬ ስለምንመካበትና ሁሉንም ነገር እንዳወቅን አድርገን ስለምን መለከተው፣ ስለምናስበው ስለዚሁ ሳይንስ ስለ ተባለው ነገር BOUTROUX የተባለ ሊቅ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ቃል ለማስረጃነት ይሰጠናል።
ሳይንስ ተብሎ ስለሚነገረው ነገር ዛሬ ባለንበት ዘመን የተፈጠረውን ሐሳብ መመልከት ዋጋ ያለው ነገር ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ሳይንስ ሲባል የፍጥረትን ልዩ ልዩ ነገሮች በትክክል አድርጎ የሚፈታና የሚያስረዳ ፍጹምነት ያለው የዕውቀት ዐይነት ሁኖ ይታሰብ ነበር። ይህም የሆነበት ምከንያት ይህ ትምህርት ብዙ ርምጃዎችን በማድረጉ የሱ ኀይል የማይደርስበት ምንም ስፍራ እንደማይገኝ ታስቦ ከፍ ያለ ግምት ተጥሎበት ስለ ነበር ነው። ግን ይህ ሁሉ ዛሬ ሳይንስ ያስገኘው ጥቅም አለ፤ ነገር ግን ያልተደረሰበትም ሌላ ጥበብና እውቀት አለ።
LE COMTE DE NOUY የተባለ ምሁር ሲናገር እንዲህ ብሏል።
ተረድቸዋለሁ ደኀና አድርጌ ዐውቀዋለሁ ብለን ዛሬ ስለ ምንም ነገር ለመናገር አንችልም። ይህ እንዲህ ዓይነቱ አፍን መልቶ መናገር ከብዙ ዓመታት በፊት ነበር እንጂ ዛሬ እንዲህ ለማለት የማይቻል መሆኑ በሊቃውንት ሁሉ ፊት የጸደቀ ሐሳብ ሁኗል። ምክንያቱም ቀድሞ ማንኛቸውንም ነገር በርግጥ ባሕርዩን ለይተን ምስጢሩን የምንረዳው አድርገን እናስብ ነበር።ነገር ግን ዛሬ እንዲህ ያለው ዘመን አልፎ ያለነው የኀይላችንን ትንሽነት መገንዘብ ማስተዋል ግዴታ ከሆነብን ዘመን ላይ ነን ያለነው። ከዚህ በፊት በሰው ዕውቀት ላይ የነበረው እምነትና ከፍተኛ ግምት ዛሬ የለም። ይህ በፊት የነበረው እምነትም ተመልሶ ሊመጣ የሚችልበት ዘመንም ያለ አይመስልም።
የዚህን ሰው ሐሳብ የመሰለ ዛሬ እንዲሁ ሌላም PRINCIPLE OF INDETERMINTION በሚል ዐይነት አነጋገር የታወቀ በሳይንቲስቶች በኩል አንድ ዐይንት ሐሳብ ተፈጥሯል። በዚህም ሐሳብ መሠረት ስለ ምንም ነገር ከዚህ በፊት ይደረግ እንደ ነበረው ሁሉ አንድም ርግጠኛና ስሕተት የሌለበት ሆኖ የሚታሰብ ዕውቀት ለማግኘትና ወስኖ ለመናገርም የማይቻል መሆኑ የተረጋጋጠ ሁኗል። ይህም በብዙዎች ታላላቅ ምሁራን ዘንድ የጸደቀ ሐሳብ ነው።
እንደዚህም አንድሬይንክ የተባለ ሊቅም ሲናገር የምናውቀው ነገር መጠኑ ካንድ ከማይታወቅ ትልቅ የውቅያኖስ ባሕር ውስጥ እንደ ሁለት ያኸል ጠብታዎች ነው። የበለጠ ባወቅንም ቁጥር ሌሎች ብዙዎች የማይታወቁ ልዩ ልዩ ከባድ ጥያቄዎች ይፈጠሩብናል ሲል አመልክቷል። ስለሆነም ብዙ ምሁራን እንዳላችሁ አውቀናል ሰዎች ከየት እስከ የት ነው እውቀታችሁ?
አንድሬ ብሎንዴል የተባለ ምሁርም እንዲህ ብሏል። የዛሬዎቹ ሊቃውንት ከፍጥረት ምስጢር ፊት ስለ ራሳቸው ከፍ ያለ ትሕትና ይሰማቸዋል። ዛሬ ሁላቸውም ደካማነታቸው ታውቋቸዋል።
ባንድ ከፍተኛ አእምሮ ይኸውም የዓለሙ ፈጣሪና አቀናባሪ በሚኾን ኀይል ማመንም ከማናቸውም ከማቲሪያሊስቲክ ሐሳብ ሁሉ የበለጠ አጥጋቢነት ያለው ነው ብለዋል።
እንዲሁም ኬ.ሙሬ የተባለ ሊቅም ከዚህ የሚከተሉትን ቃላት ተናግሯል።
ዓለሙ ከአእምሮ ኀይል በላይ ነው። በዓለሙ ፊት አእምሮ ተሸንፎ የሚወድቅ ነው። ከዓለሙ ትልቅነትና ግርማም ፊት አእምሮ የራሱን ትንሽነት ስለሚገነዘብ ትሕትና ይሰማዋል።
ዶክተር ሮምበር ሚልካነ የተባለ አንድ ሌላም ሊቅ እንዲህ ሲል ተናግሯል።
በ፲፱ነኛው መቶ ዓመት ይደረግ እንደነበረው አንድ ፊዚስት የዓለሙን መሠረታዊ ነገር እንዳወቀ ዐይነት አድርጎ ያስብ የነበረበት ዘመን አልፚል። ዛሬ ሊቃውንት የሰው አእምሮ እንኳንስ እንዲህ ያለ ዕውቀት ሊያገኝ ይቅርና ጥቂት እንኳ እንዳልተራመደና እንደ እውነቱም ያለው መንገድ በመጀመር ላይ መሆኑን ተገንዝበዋል።
ሰር ጄስም ጂንስ የተባለ አንድ የከዋክብት ተመራማሪ ሊቅም የሰውን አእምሮ ደካማነት ሲጠቅስ የዓለሙን እውነተኛና ቀጥተኛ ባሕርይ እናገኛለን ብለን ምንጊዜም የዚህ ተስፋ ሊኖረን አይችልም ሲል ተናገሯል።
አሁን ይህን ሁሉ የጠቀስንበት ምክንያት ብዙ ሰዎች የአምላክንም መኖር ሆነ የሃይማኖትን እውነተኛነት በአእምሮ ወይም በስሜት አውታሮች በኩል እንደ ሌላው ሁሉ ነገር በግልጽ ለመረዳት ያስቡና ይህ ሳይሆንላቸው ሲቀር ወደ ክህደት የሚያደርጉትን ርምጃ ለመውቀስ ነው።
ዶክተሮች በምትሠሩት የሕክምና ሙያ ሥራና በምታክሙት ታማሚ እውነተኛው ሐኪም አምላክ መሆኑን በእናንት ምክንያት፣ በእናንተ ጥበብ እግዚአብሔር ገብቶበት ሰውን ያህል ትልቅ ፍጡር ታድኑበት ዘንድ በእምነትና በጸሎት ሥራችሁን ጀምሩት።
እንዲሁም መልካም ስነ ምግባርን በመጠበቅና በማስተላለፍ በኩል በሀገራችን ቅዱስ ባህል መሠረት ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት መደሰት ባለባቸው ጊዜያት ሰብአዊ ክብራቸውን፤ ባህላቸውን፤ ሃይማኖታቸውን፤ ታማኝነታቸውን በጠበቀ መልኩ ይበላሉ ይጠጣሉ ይደሰታሉ እንጂ ከእንስሳት በአነሰ መልኩ የረከሰ ተግባር አይፈጽሙም፡፡ ስለዚህ የሀገር መሪዎችና የሃይማኖት አባቶችም ጥሩና ቅዱስ ባህላችን የማስከበርና ከመጥፎና ጐጂ ልማዶች ሕዝቡን የመጠበቅ ከእግዚአብሔርም ሆነ ከሰው ታላቅ አደራና ኃላፊነት አለብን፡፡ በቃልም የምናስተምረውንና የምንናገረውን በተግባር የማንገልፀው ከሆነ መልእክታችን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነትን አያገኝም።
ለምሳሌ ያለፈው አንድ አራተኛ ክፍለ ዘመን ሳይንስ ብዙ ዕውቀትን አምርቷል፡፡ ከዚህ ክፍለ ዘመን በፊት ካለፉት በሙሉ ዐራቱ ክፍለ ዘመናት ይልቅ በጣም ጨለምተኛ የሆነው የቅርብ ጊዜ የታሪክ ንባብ ሁሉም አዳዲስ እውቀቶችን ለክፉ ነገር ዓላማ የተጠቀምንባቸው መሆኑ የግድ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም ሲባል የእኛ የሆነው የተረበሸ ወይም በጫጫታ የተሞላ እና የተደባለቀ ስሜት እንዲሁም እዚህም እዚያም በጣም የተጨናነቀ ነው፡፡ ነገር ግን ምዕራባዊው ዓለም በሰላማዊ ሰልፍ ብቻ የተሻለ ዓለም ነው፡፡ በአጠቃላይ እኛ በታዋቂ አዳዲስ ንቃት ዕውቀት ወደ ከበሩ ሀብቶችና ውስጣዊ ምጣኔዎች እየተወስድን ነው፡፡ በእያንዳንዱ የሰው ልጅ ኅሊና የማይገመቱና ሊጠኑ የሚገባቸው፤ሊያድጉ የሚገባቸውና በምርምር ሊጣሩ የሚገባቸው አመራጮች አሉ፡፡
ማን ነው ይህን ሊል የሚችል? ሰንበር ያለበትን ሕፃን፤ ፊቱ በለቅሶ ቀይ ሆኖ ባየ ጊዜ ይህ ልጅ አንድ ቀን የታላቅ ሕንፃ ዲዛይን የሚያደርግ መሆኑን እንዲሁም የትልቁ ካቴድራልን ዲዛይን የሚያደርግ መሆኑን፣ በማርስ የመልክዓ ምድር ገጽታ ላይ እግሩን የማያሳርፍ መሆኑን ደፍሮ የሚናገር ማን ነው? ገዳይ ለሆነ በሽታስ መድኃኒት የማያገኝ መሆኑን፤ በብቸኛ ሁኔታ በጥበብ የተሞላ መጽሐፍ ትውልድን አስተማሪ የሆነ የማይጽፍ መሆኑንስ? ታላቅ ኃይል ያላትን ሀገር የማይመራ መሆኑን ወይም ብቸኛ የሆነች ነፍስን የማያድን መሆኑን ደፍሮ የሚይናገር ማን ነው?
ይህ ሁኔታ እኛ የእኛን ሰብእና ብቻችንን ሁነን እንድናሳድገው የተሰጠ አስተያየት አይደለም፡፡ የዚህ ተቃራኒው ግን ይሠራል፡፡ ከእኛ ውጭ በሆኑት ከሰዎች ጋርና ከክስተቶችም ጭምር ይህ የእኛ ሰብእና ጥልቅ የሚሆነውና የሚሰፋው በዚህ ትርጉም ባለው ግንኙነት ብቻ ነው፡፡ ማንም ሰው ብቸኛ ደሴት አይደለም፡፡ ይህ ተቀባይነት ያለው በዓለም ላይ ያለ እውነት ነው፡፡ የእኛ የራሳችን ተሞክሮዎች በመመሪያ የሚከናወኑ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ በሌሎች ሰዎች ልምዶች በጉጉት በተቃራኒ ጊዜ የእኛ ስስ ስሜት ወይም መነቃቃትና አረዳድ በታላቅ ሁኔታ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ሲባል ከሚሰቃዩት ጋር ለመሰቃየት ፤ከሚደሰቱት ጋር ለመደሰት፤ በሌሎች ሰዎች ሕመምና ጭንቀት ለመግባት በጎዳና የሚኖሩት ሁሉ የድረሱልን ጥሪ የሚጣሩትን ታላቅ ቦታ ግምት መስጠት ይገባል፡፡
እኛ የወጣቶችን አስደሳች የሆነ ሕይወት፤የታላላቆችን ቅን የሆነ ጥበብ ፤የወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን በጉጉት መነሳሳት ለመጋራት በምንችለው መጠን፤ እንተባበር፡፡ የተለያዩ ወጣቶች የሱስ ሰለባዎች እንዳይሆኑ ለሕይወታቸው መበላሻት ምክንያት የሚሆኑትን የተስፋ ቢስነት ወይም ሙሉ በሙሉ ተስፋ በመቁረጥ በአልባሌ ቦታ የሚውሉና በሱሰኝነትና በሌብነት ሥራ የተጠመዱ ወገኖች እንዳይኖሩብን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ለ. ስለ ሕክምና አገልግሎት የቤተ ክርስቲያን መልእክት
ሐኪምና ሕክምና (ሐከመ፡– አከመ ፈወሰ አዳነ) ከሚለው የግዕዝ ቋንቋ የወጣ ስያሜ ነው፡፡ በሌላም አገላለጽ ጠቢብ አቃቤ ሥራይ ተብሎ በብዙ መጻሕፍት ላይ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ ጠቢብ አቃቤ ሥራይ ማለትም ጥበበኛ ፈዋሽ አዳኝ ባለ መድኃኒት የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ሕክምናን ጥንታዊ ወይም ባሕላዊ ሕክምና ዘመናዊ ወይም ሳይንሳዊ ሕክምና ብለን በ2 ምዕራፍ ልንከፍለው እንችላለን፡፡
ሕክምና ማለት በእግዚአብሔር ልግሥና በሰዎች ፍልስፍና የተገኘ እና የሚገኝ በሽተኛ ሰውን ወይም የታመመ እንስሳን የመፈወስ ጥበብና የማዳኛ ዘዴ ማለት ነው፡፡ የሕክምናውና የጥበቡ ባለቤትም ፈዋሴ ድውያን መንሥኤ ሞውታን የተባለው ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት የሚፈውሰው ዶክተሩ ጠቢበ ጠቢባን እግዚአብሔር ነው፡፡
በመጽሐፈ ሰሎሞን መጽሐፈ ምሳሌ 9 ላይ የተጠቀሰውን ኃይለ ቃል (ጥበብሰ መድኃኒነ ውእቱ) ጥበብ ወይም ጠቢብ የተባለው በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ያዳነን መድኅኒታችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው በማለት ሊቁ እንደተረጐመው፡፡ (ቅዳሴ ኤጴፋንዮስ) የመጀመሪያውም ሐኪም ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ሲሆን በሽተኛውና ታካሚውም አባታችን አዳም ነው፡፡ ለሰው ልጅ ጤንነት መድኃኒት ምክንያት ሕይወት የሚሆኑትም ለምሳሌ ያህል የተጠቀሱትን ከቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ እናነባለን፡፡ (እምኩሉ እፅ ዘውስተ ገነት ብላዕ ወእምእፅሰ ዘሀሎ በማዕከለ ገነት ዘያሌቡ ሠናየ ወእኩየ ኢትብላዕ እሞኔሁ) (መልአከ ሕይወት) ጌታ የሕይወት ባለቤት ጌታ በገነት መካከል ካለው አትክልት አዝርዕት ሁሉ ለጤንነትህ ይጠቅምሃልና ብላ ነገር ግን ለጤንነትህ የማይጠቅም ጐጂና መርዛማ የሆነውን ፍሬ ዕፅ ግን አትብላ ስንኳን መብላት ቅጠሉን ወይም ግንዱን በእጅህም አትንካው፡፡ ምክንያቱ ከዚያ መርዛማ ዕፅ ከበላህ ድውየ ሥጋ ድውየ ነፍስ ያደርግሃልና ሲል መርዛማውን ዕፅ ከነምክንያቱ በመግለጽ እንዳይበላው አስጠንቅቆታል፡፡ ከዚህም ኃይለ ቃል መርዛማና አደንዛዥ የሆኑ እፀዋት መጠቀም እንደሌለብን እንገነዘባለን፡፡ ይህን የመሰለውንም መርዛማ እና አደንዛዥ ለሰዎች ሕይወት ጠንቅ የሆነውን ዕፅ ይዞ የተገኘም ሰው በሕግ ፊት ተጠያቂ እንደሚሆን በዓለም አቀፉ ሕገ መንግሥት ተደንግጓል፡፡ ዘፍ.2 ÷17
ዳግመኛም በትርጓሜ መጽሐፈ ሲራክ ምዕራፍ 39÷ከቁ.26 ጀምሮ ለሕይወታችን ገንቢ ለጤንነታችን ጠቃሚ የሆኑትን እንደምሳሌ ሁነው ተጠቅሰው የምናገኛቸው እህልና ውኃ ወይንና ስንዴ ማርና ቅቤ እንዲሁም ጨው እና ነጭ ሽንኩርት የመሳሰሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ (ጥበበ ሲራክ ንባብና ትርጓሜው) ደዌ ሥጋው በጸናበት ቸነፈሩና ወረርሽኙ በተስፋፋበት ወቅትም ለቀደሙት ቅዱሳን አበው ለሄኖስ ለሄኖክና ለኖኀ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም በርካታ ፈዋሽ መድኃኒቶችን ነግሯቸዋል (አሳይቷቸዋል)፡፡ ከቀደሙት አበው ሲያያዝ በመጣውም አምላካዊ መመሪያ መሠረት በሊቀ ነቢያት ሙሴ አማካይነት ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ከተጻፈበትም ጊዜ ጀምሮ አበው ነቢያት በቈጽለ ወይን፤ በፍሬወይን፤ በሐረገ ወይን፤ በቈጽለ በለስ፤ በፍሬ በለስ፤ በማየ ዮርዳኖስ ሕዝብንና አሕዛብን ሳይለዩ በእኩልነት በሽተኞች የሆኑትን የሰው ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር ስም ይፈውሷቸው እንደነበርና መርዛማውንና መራራውንም ውኃ በጨው ያጣፈጡት እንደነበር ከታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ አንብበን መረዳት እንችላለን፡፡ መጽሐፈ ነገሥት ለምሳሌ፡– የእስራኤል ንጉሥ ሕዝቅያስ በታመመ ጊዜ የተላኩት አሽከሮች ለጌታቸው ደዌ መፍትሔ ሲጠይቁት ቅዱሱ ነቢይ ኢሳይያስ ቈጸለ ወይኑን ሐረገ ወይኑንና ፍሬ ወይኑን ቈርጦ በመስጠት (ሑሩ ቅብዕዎ ኀበ ሕበጡ ለእግዚእክሙ በስሙ ለእግዚአብሔር ጸባኦት አምላከ እስራኤል ወየሐዩ) ሂዳችሁ በአሸናፊው በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም የጌታችሁ የሕዝቅያስ አካሉን በዚህ ፍሬወይን ቈጽለ ወይን ቀቡት እርሱም ይድናል በማለት አሽከሮቹን እንደመከራቸውና ንጉሥ ሕዝቅያስም በዚሁ የፈውስ አገልግሎት እንደተፈወሰ እንረዳለን ( 2ነገሥ. ም. 20 ቁ. 1-7) በተመሳሳይ ሁኔታ ታላቁ ነቢይ ኤርምያስም በቈጽለ በለስ በፍሬ በለስ ምክንያት በሽተኞችን በመፈወስ ይረዳቸው እንደነበረ አንብበን መረዳት እንችላለን፡፡
በተለይ ጥበብ ሥጋዊ ጥበብ መንፈሳዊ የተገለጸለት ነቢዩ ንጉሠ እስራኤል ሰሎሞን የእያንዳንዳቸውን የዕፀዋት አገልግሎት ያውቅ ስለነበር በእፀዋቱ ምክንያት በእግዚአብሔር ስም ለሕሙማኑ የፈውስ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ከፈውሱ ተጠቃሚዎችም መካከል አንዷ የኢትዮጵያ ንግሥት ሳባ እንደሆነች በትርጓሜ መጻሕፍት ተገልጿል፡፡ (ትርጓሜ ወንጌል)
ጥበበኛው ሰሎሞንም ከእርሱ በፊት የነበሩት አባቶቹ እስራኤላውያን በግብጻውያን ላይ ከተከሰተው ቸነፈር በሲና በረሃም ሳሉ ከወረደባቸው ደዌ ሥጋና መቅሰፍተ ሥጋ የጸኑት በእርሱም በሰሎሞን ዘመን የነበሩዋት ወገኖቹ ድውያን እብራውያን የተፈወሱት ሕያው ማሕየዊ በሆነው በእግዚአብሔር ቅዱስ ስም እንደሆነ እና እፀዋቱና አፍላጋቱ ግን ምክንያተ ሕይወት መሆናቸውን እንዲህ በማለት አስረድቷል፡፡
አኮ ዘድኀነ በዘርዕየ አላ በእንቲከ ድኀነ ኦ መድኃኔ ኩሉ ትርጉም የሁሉ መድኃኒት ጌታ ሆይ ድውያነ ሥጋ እስራኤል አርዌ ብርቱን በማየት የጸኑ አይደሉም አንተን በማመን ጸኑ እንጂ ወዝንቱ ትእምርት ኮኖሙ መድኃኒተ ያዘክሮሙ ትዕዛዘ ቃልከ ይህ አርዌ ብርት አዘህ ያሠራኸውን ሕገ ሕይወት መጽሐፍ ያሳስባቸው ዘንድ ምክንያተ ሕይወት ሆናቸው እንጂ፡፡
ግዕዝ አኮ እፅ ዘይሰትይዎ ወኢሥራይ ዘይቀብእዎ ዘፈወሶሙ አላ ቃለ ዚአከ እግዚኦ ዘኩሎ ይፌውስ ፈውሶሙ እስመ ለሞት ወለሕይወት ሥልጣን ብከ፡፡
ትርጉም ሕሙማኑን ድውያኑን የሚጠጡት እንጨት የሚቀቡት አስማት ያዳናቸው አይደለም አቤቱ ሁሉን የሚያድን ቅዱስ ቃልህ አጸናቸው እንጂ ለሕይወትና ለሞት ሥልጣን አለህና በማለት ለፈውስ አገልግሎት የሚውሉት እፀዋቱ አዝርዕቱ፣ አትክልቱና ማያተ አብሕርቱ ምክንያተ ሕይወት ናቸው እንጂ ፈዋሹ እግዚአብሔር ስለሆነ በእግዚአብሔር ፈዋሽነት አምነን ቅዱስ ስሙን ጠርተን እፀዋቱን ወይም ክኒኑንና መርፌውን ብንጠቀም የፈውስ አገልግሎት ማግኘት የምንችል መሆኑን በጥንቃቄ አስረድቶናል፡፡ ትርጓሜ መጽሐፈ ጥበብ ም10 ከቁ. 29-36፡፡
በመቀጠል ጥበበኛው ሰሎሞን ፈዋሽ ከሆኑ ዕፀዋትም መካከል አንደኛውን እፀ ሕይወት ጠቆም አድርጐ አልፏል፡፡ ግዕዝ ሐረገወይን ዘእምሐሢሦን ይትገዘም ወበጐልጐታ ይተከል ኮነ መድኃኒትየ ትርጉም፡– ከገነት የተቈረጠው በጐልጐታ የተተከለው ሐረገወይን ጉንደ ወይን (ቅዱስ መስቀል) መድኃኒቴ ሆነኝ በማለት እርሱ ሰሎሞን ንግሥት ሳባና ሌሎችም ድውያን በጉንደ ወይን (በጉንደ መስቀል) ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የተፈወሱበት መሆኑን መስክሯል መሐልየ ሰሎሞን
በመጨረሻም ጥበበኛው ነቢይ ሰሎሞን ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የሚያድኑ መምህራን እንዲሁም የፈውሰ ሥጋ አገልግሎት የሚሰጡ ጠበብት ሐኪሞች በየኅብረተሰቡ መካከል በብዛት እየተገኙ ለዓለሙ ኅብረተሰብ አገልግሎት ቢሰጡ ጠቃሚ መሆናቸውን ሲገልጽ እስመ ብዝኃ ጥበብት መድኃኒተ ዓለም ውእቱ ትርጉም የጥበበኞች (የመምህራን የሐኪሞች) መብዛት የዓለም መድኃኒት ነው በማለት የባለሙያዎች እጥረት መኖር እንደሌለበት መልእክቱን አስተላልፏል፡፡ መጽ. ጥበብ 4÷25
ከደዌ ሥጋ የሚፈውስ ሐኪም (ወጌሻ) ከደዌ ሥጋና ከደዌ ነፍስ የሚያድን ካህን ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ መሆኑንና አምላካችን እግዚአብሔርም በዚህ ዓለም ፈዋሽ መድኃኒትን (አንድም) ሥርየተ ኃጢአትን እንደፈጠረና እንደአዘጋጀ ተገልጋዩ ኅብረተሰብም ሐኪሙን ካህኑን አክብሮ መገልገል እንደአለበት እንዲህ በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ሲራክ አባታዊ ምክሩን ይለግሰናል፡፡ ግዕዝ አክብሮ ለአቃቤ ሥራይ እስመ በከመ እዴሁ ከማሁ ክብሩ እስከ ሎቱኒ እግዚአብሔር ፈጠሮ
ትርጉም ባለመድኃኒቱን ሐኪሙን አክብረው በአገልግሎቱ መጠን መከበር ይገባዋልና እርሱንም እግዚአብሔር ለዚህ አገልግሎት ፈጥሮታልና አንድም ካህኑን አክብረው በመስቀሉ (በእጁ) ባርኮ በጸበሉ ረጭቶ (አጥምቆ) በቃሉ ናዝዞ ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ በማዳኑ ሊከበር ይገባዋልና እርሱንም እግዚአብሔር ለዚህ ለክህነት አገልግሎት ሹሞታልና፡፡ ግዕዝ፡– እስመ እግዚአብሔር ፈጠረ ሥራየ እምነ ምድር ወብእሲ ጠቢብ ኢይሜንኖ ትርጉም እግዚአብሔር መድኃኒትን ከምድር ፈጥሯልና ብልህ ሰውም አይንቀውም (እግዚአብሔር ካህኑን ከሰው መርጦ ሹሞታልና) ብልህ ሰውም አይንቀውም ግዕዝ፡– አኮኑ በእፅ ጥዕመ ማይ ከመ ያዕምሩ ኃይሎ ትርጉም መድኃኒት መናቅ እንደሌለበት ይታወቅ ዘንድ መራራው ውኃ በእንጨት የጣፈጠ አይደለምን? ነቢዩ ሙሴ ዞጲ በሚባል እንጨት መራራውን ውኃ እንደ አጣፈጠው ዘፀዓት. 15÷25
ነቢዩ ኤልሳዕም መራራውንና መርዛማውን ውኃ በጨው አጣፍጦታል፡፡ እፀዋቱ በእግዚአብሔር ስም ከተጠቀሙባቸው ፈዋሽነት እንደአላቸው ለማጠየቅ ጌታ ለኖኅ ሺህ መድኃኒት ነግሮታል (አሳይቶታል)፡፡ ከሺሁ ሦስቱን መቶ ይህ ለዚህ ይበጃል ብሎ ቃል በቃል ነግሮታል፡፡ ሰባቱን መቶ (፯፻ን) ግን ከዕፀዋት ውጤቶች ከሆኑት ከማር እና ከቅቤ ታገኘዋለህ ብሎታል (ኩፋሌ 42÷8-10)
በመቀጠልም ነቢዩ ሲራክ ሐኪሙና እፀዋቱ ካህኑና ጥምቀቱ ለፈውሰ ሥጋና ለፈውሰ ነፍስ ምክንያቶች ናቸው እንጂ ሕይወተ ሥጋንና ሕይወተ ነፍስን የሚያድለው የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር ነውና ደዌህን ያርቅልህ ችግርህንም ያስወግድልህ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ በማለት መልክቱን በማስተላለፍ መልእክቱን ይቋጫል፡፡
ግዕዝ፡– ወልድየ ኢትጸመም ሕማመከ ጸሊ ኀበ እግዚአብሔር ወውእቱ ይፌውሰከ
ትርጉም ልጄ ሕማምህን ቸል አትበል አድነኝ ብለህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ እርሱም ይፈውስሃል (ትርጓሜ መጽሐፈ ሲራክ ም. 38 ከቁጥር 1-15) ይመልከቱ፡፡
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዓለም ስለሚገኙት ፈዋሽ እፀዋት እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ ወተከለ እግዚአብሔር ሠለስተ ዕፀወ ሕይወት በዲበ ምድር
ትርጉም እግዚአብሔር በምድር ላይ ሦስት የሕይወት እንጨቶችን ተከለ (አበቀለ) በማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተነገረው ጋር አያይዞ ተናግሯል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ሲል ተርጉሞታል፡፡ ግዕዝ፡– ከፈለነ ንብላዕ እምእፀ ሕይወት ዘውእቱ ሥጋሁ ቅዱስ ወደሙ ክቡር
ትርጉም ከእፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ ነው በማለት በከፊል ተርጉሞታል፡፡ ሠለስቱ እፀወ ሕይወት የተባሉት ሁለቱ ቅዱስ ኤፍሬም እንደተረጐመው እፀ ሥርናይና እፀ ወይን ሲሆኑ ሦስተኛው ለልጅነት ለሥርየተ ኃጢአት ምክንያት የሚሆነው እፀ ዘይት ወይም እፀ በለሳን ነው፡፡ በለሳነ ኮነ ሐፈ ሥጋሁ በቁሎ ሜሮን ቅብዕ ዘይቄድስ ኩሎ እንዳለው ደራሲ በመቀጠልም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ስለ እፀ ሕይወት ሲያብራራ ወላዲተ አምላክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያምን ባመሰገነበት አንቀጽ እንዲህ በማለት ዘምሯል፡፡ ግዕዝ፡– አንቲ ውእቱ እፅ ቡሩክ ዘኮንኪ እፀ ሕይወት በዲበ ምድር ህየንተ ዕፀ ሕይወት ዘውስተ ገነት
ትርጉም በገነት መካከል ስላለው እፀ ሕወት ፈንታ በምድር ላይ እፀ ሕይወት የሆንሽ የተባረክሽ እፅ አንቺ ድንግል ማርያም ነሽ በማለት እመቤታችንን በቃል ኪዳኗ ለሚማጸንባት በአማላጅነቷ ለሚተማመንባት ሁሉ ምክንያተ ሕይወት መሆኗን አስረድቷል፡፡ (ድጓ አንቀጸ ብርሃን) ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሥጋችን ለብሶ ባሕርያችን ባሕርይ አድርጎ ሰዎችን በሚያስተምርበት ጊዜ አንድ አንዶችን ፈቀድኩ ንጻሕ በቃሉ ብቻ ያለምንም ምክንያት እኔ ፈቅጃለሁና ንጻ እያለ ድውያንን የፈወሰ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ ለፈውሱ ምክንያት በመፈለግ የዓይነ ሥውሩን ዓይን በምራቁ ጭቃ ለውሶ በመቀባትና ሂደህ በሰሊሆም በፈሳሹ ወንዝ ውኃ ተጠመቅ በማለት ይፈውሳቸው እንደነበር በቅዱስ ወንጌል ተጠቅሷል፡፡ ዮሐ. 9÷1
ዳግመኛም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕክምና አገልግሎት መጠቀም ተገቢ መሆኑን ጥንቁልና ወይም እንደ በደል የሚቆጠር አለመሆኑን እንዲህ ሲል በቅዱስ ወንጌል አስረድቷል፡፡ግዕዝ፡– ሕሙማን ይፈቅድዎ ለዐቃቤ ሥራይ
ትርጉም በሽተኞች ሐኪሙን ወይም ባለመድኃኒቱን ይሹታል በማለት ያስተማረ ሲሆን በሉቃስ ወንጌል እንደተመዘገበው ወንበዴዎች ደብድበው የጣሉትን ቁስለኛ ሰው ደጉ ሣምራዊ መጥቶ ለጊዜው ቁስሉን የሚያለዝብ ዘይትና የሚያደርቅለት ወይን ቀብቶ በአህያውም ላይ ጭኖ ወደተሻለ ሐኪም እንደወሰደውና እንደአሳከመው በምሳሌነት ጠቅሶ እንደአስተማረበትና ደጉ ሳምራዊም የነፍስ አድን ሥራ በመሥራቱ በሽተኛውን በወቅቱ ባለው ባሕላዊ ሕክምና በመርዳቱ እንደ አመሰገነው እንረዳለን፡፡ ሉቃስ 10÷30
ምንጭ፡ አቡነ ሳሙኤል