መዝሙር ዘደብረ ዘይት፦ እንዘ ይነብር እግዚእነ
ምስባክ፦ እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ
ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ (መዝ. 49፥2-3)።
‹‹ጌታችሁ በየትኛው ሰዓት በይትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤››
(ማቴ 24፥42)
‹‹የሰው ልጅ(ክርስቶስ) በማታስቡበት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤›› (ማቴ 24፥44)
ይህ ዓለም ኃላፊ፣ ረጋፊ፣ ጠፊ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ታስተምረናለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም ይህ ዓለም ዘለዓለማዊ አለመሆኑን፤ አንድ ጊዜ የሚያልፍና የሚጠፋ መሆኑን ቢያንስ በዓመት ሁለት ጌዜ ለምእመናን ልጆችዋ
1ኛ/ በደብረ ዘይት (በግማሽ ጾም ላይ)
2ኛ/ በዓመቱ የመጨረሻው እሑድ ላይ አጽንኦት ታሳስባለች
ዓለም ስንል መላውን የዓለምን ሕዝብ ጭምር ነው። ታዲያ ሁላችንም ለመጨረሻው ቀን ሁልጊዜ ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ ቅደስት ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ጌታችሁ በየትኛው ሰዓት በይትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤›› (ማቴ.24፥42) እያለች ዘወትር ታሳስበናለች።
ደብረ ዘይት ይህ የዛሬው ሰንበት ደብረ ዘይት ይባላል። ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም ከተማ ባሻገር በስተምሥራቅ በኩል የሚገኝ ኮረብታማ ቦታ ነው። በመካከሉ የቄድሮስ ወንዝና ሸለቆ ይገኛሉ። ቦታው የወይራ ዘይት ዛፍ በብዛት የሚገኝበት ስለሆነ ደብረ ዘይት ተባለ። የዘይት ዛፍ የሞላበት ተራራ ማለት ነው። ጌታ የጸለየበትና እመቤታችን የተቀበረችበት ጌቴሴማኒ የተባለውም የአትክልት ቦታ በዚሁ ኮረብታ ስር ነው የሚገኘው። ደብረ ዘይት የሚያስታውሰን ጌታ ስለ ዳግም ምጽአቱ በቦታው ያስተማረው ትምህርት ነው።
አንድ ቀን የጌታ ደቀ መዛሙርትና ፈረሳውያን ስለ ጌታ መምጣትና የዓለም መጨረሻ መቼ እንደሚሆን በዚሁ ኮረብታማ ስፍራ (ደብረ ዘይት) ጌታችንን ጠየቁት። የጌታም መልስ ‹‹ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ አታውቁምና ተግተቃችሁ ጠብቁ›› እንዲሁም ‹‹የሰው ልጅ በማታስቡት ሰዓት ስለሚመጣ ተዘጋጅታችህ ኑሩ፤›› (ማቴ 24፥24፣44) የሚል ነበር።
ዳግም ምጽአት፦ ምጽአት ምንድን ነው? ምጽአት ሲባል እጅግ ያስደነግጣል፣ ያስፈራልም። ምጽአት ማለት ጌታችን ወደዚህ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ ማለት ነው። ይኸውም አንደኛ የጌታ ምጽአት፣ ሁለተኛ የጌታ ምጽአት በመባል ይታወቃል። ‹‹ወአውሥአ ወይቤሎሙ ዑቁ ኢያስሕቱክሙ» ኤፌ 5፥6 ያንጊዜ ክርስቶስ ከወዲህ አለ ከወዲያ የለም ቢላችሁ አትመኑ እነሆ አስቀድሜ ነገርኳችሁ ከቤተ አለ ከበርሐ አለ ቢላችሁ አትውጡ እነሆ በምኩራብ ይስተምራል ቢላችሁ በጀ አትበሉ ›› ማቴ. 25-23
የመጀመሪያው የጌታ ምጽአት፦ ነቢያትና የጥንት አባቶች በተነበዩትና ተስፋ በአደረጉት መሠረት ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከቅዱስት ድንግል ማርያም ተወልዶ እኛ ሕዝቦቹን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ አድኖናል። ጌታ ቀድሞ የመጣው ለምሕረት፣ ለቸርነት፣ ለይቅርታና ሰውን ለማዳን፣ ሰውን ይቅር ለማለት፣ ለማስተማር ትሑት ሆኖ፣ በፈቃዱ ክብሩን ዝቅ አድርጎ፣ የሰውን ሥጋ ለብሶ ነው የመጣው። ይህንንም ፈጽሞ እኛ በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን የምንገኝበትን ቤተ ክርስቲያንን መሥርቶልናል። ይህ የጌታችን የመጀመሪያው ምጽአት ይባላል።
ሁለተኛው ምጽአት፦ ወደፊት ክርስቶስ የሚመጣበት ሁለተኛው ምጽአት ይባላል። ክርስቶስ ወደፊት የሚመጣው ከፍ ባለ ግርማና በታላቅ ክብር፣ በአስፈሪነት፣ በእምላክነቱ ክብርና በግርማ መለኮቱ በመላእክት ታጅቦ ነው። ዛሬ በቅዳሴ ጌዜ የተነበበው የማቴዎስ ወንጌል ‹‹የሰው ልጅም በኃይልና በታላቅ ክብር በደመና ላይ ሆኖ ይመጣል፤›› (ማቴ. 24፥30) ሲል አስረድቶናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ የሚመጣው ለምሕረትና ለይቅርታ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ሰው በዚህ ዓለም እንደ ሠራው ሥራ መሠረት ዋጋውን ለመስጠት፣ ዋጋውን ለመክፈል እንደ ሠራው ሥራ መሠረት ዋጋውን ለመስጠት፣ ዋጋውን ለመክፈል እንደ ታላቅ ዕለተ ዕለት (የክብር ዕለት) ወይንም ዕለተ ፍዳ ወደይን (የፍዳና የመከራ ዕለት) ትባላለች። ዕለተ ክብር (የክብር ዕለት) የምትባልበትም ምክንያት ጌታ ጌትነቱን፣ ከብሩን የሚገልጥባት፣ ለወዳጆቹ ለጻድቃን፣ ለሰማዕታትና በአጠቃላይ ሕጉን ትእዛዙን አክብረውና ፈጽመው ለኖሩት ለተቀደሱት ምእምናን ክርስቲያኖች ዋጋቸውንና የሚገባቸውን ክብር የሚሰጥባተ ዕልት ስለሆነች ነው። እነዚህ ቅዱሳን በዚህ ጊዜ ታልፋልች የምትባለውን መንግሥተ ሰማያት የሚወርሱባት ቀን ስልሆነች ነው።
ስለ ሰው ልጅ ትንሣኤ፦ ሰው ከሞተ በኋላ አንድ እንስሳትና እንደ አራዊት ፈርሶ በስብሶ አፈር ትብያ ሆኖ የሚቀር ፍጥረት አይደለም ነገር ግን ሰዎች ቢሞቱም በመጨረሻው ጊዜ በዕለተ ምጽአት ሕይውትን አግኝተው ለዘለዓልም ለመኖር በሥጋ ይነሣሉ። የሰው ልጅ ትንሣኤ ሁለት ዓይነት ነው፦
(ሀ). የከብር ትንሣኤ፤
(ለ). የሐሳር (የመከራ) ትንሣኤ
ይባላል።
የክብር ትንሣኤ የሚባለው ሰዎች በምድር ሕይወታቸው ሳሉ በሚሠሩአቸው መልካም ሥራ ሁሉ እንዲሁም ሕጉን ትእዛዙን አክብረውና መፈጽመው ስለኖሩ ከልዑል እግዚአብሔር የክብር ዋጋ ጽድቅን መንግሥተ ሰማያትን የሚያገኙበት ስለሆነ ነው። የመከራ ትንሣኤ የሚባለው ደግሞ ሰዎች በምድር ሕይወታቸው ሳሉ በሚሠሩተ ክፉ ሥራ ሁሉ በጌታ ዘንድ ፍዳና መከራ፤ ሐሳርና ኵነኔ የሚያገኙበትና ወደ ገሃነመ እሳት የሚወርዱበት ስለሆነ ነው።
የሰው ልጀ በምድር ላይ ሲኖር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ከሞተ በኋላ ክልዑል እግዚበሔር ዘንድ ተገቢውን ፍርድ ያገኛል። የሚሰጠውም ፍርድ በሁለት ይከፈላል፤
1ኛ/ ጊዜያዊ ፍርድ
2ኛ/ የመጨረሻ ፍርድ ይባላሉ
ጊዜያዊ ፍርድ፦ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየ በሠራው ሥራ መሠረት ጊዜያዊ ፍርድ አግኝቶ ወደ ጊዜያዊ ማረፊያወደ ገነት ወይም ወይም ሲኦል ይገባል።
የመጨረሻው ፍርድ፦ የመጨረሻው ፍርድ የሚባለው ደገሞ ሰዎች በምድር ሕይወታቸው መልክም ሥራ የሠሩ፤ የእግዚብሔርን ሕግን ትእዛዝ ጠብቀው የኖሩ በመጨረሻው ጊዜ በሥጋ ተነሥተው ዓለም ሲፈጠር ጀምቶ የተዘጋጀውን መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ የሚሰጣቸው ፍርድ ነው። ማቴ. 25፥41-46 ያለውን አንብብ።
ገሀነመ እሳት፦ ገሃነመ እሳት የሚባለው ደግሞ ሰዎች በዚህ ዓለም ሕይወታቸው ክፉ ሥራ ሲሠሩ የቆዩ፦ ሕጉንና ትእዛዙን ሳይፈጽሙ የኖሩ ሁሉ በመጨረሻው ፍርድ ጊዜ እነሱም በሥጋ ሥቃይና መከራ ቦታ ገሀነመ እሳት ይገባሉ። ማቴ 25፥ 41 -46 ያለውን አንብብ ።
ምስጋና ወቀሳ፦ በመጨረሻው ፍርድ ጊዜ ጌታ ለጻድቃን የሚሰጠው ምስጋናና ኃጥአንን የሚወቅስበት የተግሣጽ ቃን የማኀበራዊ አገለግሎትን የሚመለከት ነው።