Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • June 2023
    M T W T F S S
     1234
    567891011
    12131415161718
    19202122232425
    2627282930  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

Posts Tagged ‘እቴ ህንድኬ’

Apostle Matthew in Ethiopia | ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ በአክሱማዊቷ ኢትዮጵያ | በፍርድ ቀን፤ ከ፪ሺ ዓመት በኋላ፤ “ወንጌል አልተሰበከልንም” ማለት የለም

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on October 22, 2022

✞✞✞

ጥቅምት ፲፪/ 12፤ የሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ በዓለ ዕረፍቱ ነው፤ ከቅዱስ ማቴዎስ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡

💭 ፊልሙን ከዚህ ድንቅ ጽሑፍ ጋር እናነጻጽረው፦

👉 በ መሪራስ አማን በላይ

የዓለም መድኃኒት እየሱስ ክርስቶስ እኔን ማቴዎስን መርጦ ተከተለኝ አል እኔም ስላመነታ ተከተልኩት የመዳን ተስፋ የሆነውን የወንጌሉን ቃል እንድንሰማና ከእርሱ አፍ የሰማሁትንም ለዓለም እንዳሰማ ልኮኛል።

መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ሊያድን ከእግዚአብሔር አብ የመጣ ከእርሱም ሌላ አዳኝና መሐሪ ወደ እግዚአብሔር መንግሥትም የሚያገባ እንደሌለ የአየሁትን ልመሰክር የሰማሁትን ቃል ለእናንተ ለአሰማ ከቃሉ የተነሣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ትሆኑ ዘንድ በስሙም ትጠመቁ ዘንድ ልኮኛል። ከአብና ከልጁም ከእኛም ህብረት እንዳላችሁ ያንጊዜ ታውቃላችሁ፤ ዓለሙ ግን የፈጠረውን ተጣሪውን ትቶ ላልፈጠረው ምህረት የአደረገለትን ጌታውን ትቶ ሥቃይንና መአትን ለሚያመጣበት ለክፉ መንፈስ እየተገዛና የክፉ መንፈስ ባሪያ በመሆን የኃጢአትን ንጉሥ ዲያብሎስን እያገለገለ ይገኛል።

ይህ ክፉ መንፈስ በሰዎች ልብ ላይ መርዙን እንደረጨ ሁሉ እንዲሁ በእግዚአብሔር ልጆች ላይ ደጋኑን ወጥሮ ቀስቱን እንደቀተረ ነው። አንዳንዶች ወገኖች ለእርሱ ሲማረኩለት ጥቂቶችም የሆኑ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝቦች ከፍጹም እምነታቸውና ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተነሣ በጸሎት ድል ያደርጉታል፡ በጾምም ያሸንፉታል ያሳፍሩታልም። ወደ ሰማየ ሰማያት ለወጣው ለእግዚአብሔር ልጅ ለእየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ሠራዊቱ ናቸው። መንፈሱን ተላብሰዋል፣ ጸጋውን ተሞልተዋል፣ ኃይሉንም ታጥቀውታል። ሥልጣንም በአፋቸው ተሰጥቷል። እኒሁ እናንተም የእግዚአብሔር አብን ምህረት የልጁንም የእየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ልትቀበሉትና ልትለብሱት ለመጣችሁ ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁንላችሁ። የልጁም የእየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ይፅናላችሁ። አሜን።

እቴ ህንድኬ ዣን ንግሥተ ነገሥታት ዘኢትዮጵያ በሆነች በአሥራ አንደኛው ዘመነ መንግሥትዋ ከእየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ቅዱስ ማቴዎስ በመርዌ ከተማ የሚኖሩትን ህዝቦች ቃለ ወንጌል እየሰበከ አስተምሮ ማጥመቁን ሰማች፤ ይዘውት ወደ እርስዋ እንዲመጡ መልእክተኞችን ወደ ወንጌላዊ ማቴዎስ ላከች፡ ነገር ግን ስለክርስቶስ መወለድና ብዙ ታእምራትንና ድንቅ የሆኑ ሥራዎችን እየሱስ ክርስቶስ መሥራቱን ሰምታ ስለነበረ የእየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነው ሲሏት መልኩን ለማየት የሚያስተምረውንም ለመስማት ጓጉታ እርሱ የእግዚአብሔር አገልጋይ ከመምጣቱ እኔ መሄድ አለብኝ ብላ በብዙ ሺህ ሠራዊት ታጅባ ወደ መርዌ /መርዋ/ በ70 ዓ.ም. ሄደች።

በዚያም ቅዱስ ማቴዎስን አግኝታ እንዲህ አለችው፦

“እየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እኛ እንደተላከና የሰላም አለቃ የዘለዓለም አባት እንደሆነ ከነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት የተነሣ አምናለሁ፤ ነገር ግን በውኃ ጥምቀት ከእግዚአብሔር መወለድን የእግዚአብሔር ልጅ መባልን አላውቅም ነበር፡ አሁን ግን አንተን ወደ እኛ የላከህና ከአንተ ላይ የአለ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከስብከትህ የተነሣ ገለፀልኝ፡ የምትነግረን ቃለ ወንጌል ህይወት መድኃኒት እንደሆነ አወኩ በእርሱም አመንኩ ስለዚህ አጥምቀኝ።” አለችወ።

ቅዱስ ማቴዎስም እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንደላካት አውቆ በደስታ ከሠራዊትዋ ጋር ወደ ግዮን ወንዝ ወረዱ ከዚያም ከእርሱዋ ጋር የነበረው ሠራዊትና መኳንንት ሁሉ በእየሱስ ክርስቶስ ስም አጠመቃቸው። እንዲህ ሲል፦

“በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠቃችሁ አለሁ!” እያለ።

እቴ ህንደኬ ዣን እንደህዝብዋ ተጠመቀች፤ ፍጹም ክርስቲያን ሆነች፤ ከዚያም ቅዱስ ማቴዎስን ከደቀ መዛሙርቶቹ ጋር ወደ አክሱም አምጥታ አክሎስ የሚባለውን ባልዋን ልጆችዋን ቤተሰብዋን ሁሉ በእየሱስ ክርስቶስ ስም አስጠመቀች። ቅዱስ ማቴዎስ በአክሱም አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከበርቶሎሜዎስ ቀጥሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የኑብያን፣ የኢትዮጵያንና የናግራንን ሰዎች የአጠመቀ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ወንጌላዊ ማቴዎስ ነው።

እንደዚህም ሆነ እቴ ህንደኬ ዣን ክርስቲያን በሆነች በአሥራ ሦስት አመትዋ አቡሳውያን /አበሾች/ የሚባሉት የአክሱም የአዶሊስ ሕዝቦችና ፈላስያን /ፈላሾች/ በሌዋውያን ምክር ወንድሙዋን ንጉሠ ባህር ዘዝቃሌስ ተብሎ የነበረውን ከተብን አፄ ባህር ሰገድ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ብለው በበላዩዋ ላይ አነገሡት፤ እቴ ህንደኬን ዣንና አክሎስ ልጆቸዋን ገድለው አቃጠሏት። እርሷም በሰማእትነት በሰማንያ ሦስት /83/ በነገሠች በ24 ዘመነ መንግሥቱዋ አረፈች።

አፄ ባህር ሰገድ ተብሎ በነገሠው በከተብ ዘመነ መንግሥት እየሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ክርስቶስ ተወልዶአል ብሎ የሚያስተምርና የሚአምን ሰው ቢገኝ እንዲገደል በአዋጅ ተነገረ።

የእስራኤል ልጆች የሆኑ ሌዋውያን ካህናት እየሱ ክርስቶስም አይደለም ስሙንም መድኃኒት አይደለም ለማለት “ኢየሱስ” እንጂ “እየሱስ” ብላችሁ አትጥሩ ብለው በምኩራብ በአደባባይ በቢተ መቅደስ በገበያ አስተማሩ።

እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆችን ጥጦስ የሚባለውን አስነስቶ በጭካኔ እንደገደላቸው ሁሉ እንዲሁ የባህር ሰገድን መርከብ ሠራተኞችና በአዶሊስ በዳህቂቅ የሚኖሩትን ቤተ እስራኤል ሂክሶስ የሚባሉት የግሪኮችን ሰዎች አስነስቶ አስገደላቸው።

ንጉሠ ነገሥቱ ባህር ሰገድ ክርስቶስ እየሱስ በተወለደ 105 መታራ ከሚባለው አገር ላይ ከግሪኮች ከሮማውያን ጋር ጦርነት አድርጎ ተማርኮ በ81 ዓመት እድሜው በነገሠ በ22 ዘመነ መንግሥቱ ሞተ።

አንዳንድ ጎሣዎችና በጎሣዎች ውስጥ የሚገኙ ነገዶች ቃለ ወንጌል ያልተሰበከላቸው በጨለማ ዓለም ውስጥ ከመኖራቸው የተነሣ ከንቱ የሆነ አምልኮት ያመልኩና ለሚያመልኩት ነገር እንስሳና አእዋፍ ዶሮ ያርዱለት ነበር። ከዚያም አልፈው ሰውን አስረው እንደ እንስሳ የሚያቀርቡና የሚሰው ነበሩ። የሚያመልኳቸው ተራራዎች ዛፎች ሸለቆዎች ኮረብታዎች አራዊቶች ነበሩ። እንደዚሁ አስቀያሚ መልክ ያላቸው ቅርጾችን ያመልኩባቸው ነበር።

ነገር ግን የሰው ልጅ ክቡር ፍጥረት እንደሆነ ከሁሉም በላይ መሆኑን የሚያምኑና ሁሉን የፈጠረና ቻይ ጌታ እግዚአብሔር ብቻ አንድ አምላክ እንደሆነ በነቢያት ላይ አድሮ ለሰው ልጆች ህግና ሥረአት እንዲኖራቸው የፈቀደ ወይም የአዘዘ ትእዛዙንም የሚፈጽሙ የመልከ ጼዴቅ ካህን ዘሮች የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው የሚጠሩ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነበሩ። በኋላ ዘመን ደግሞ የአብርሃም ዘሮች በሙሴ አማካኝነት አንድ እግዚአብሔርን ማምለክ ጀመሩ። ከዚህ በኋላ ነው ሁለቱ ጎሣዎች አንድ እግዚአብሔርን በማምለክና በማመን ሲኖሩ የአለም መድኃኒት እየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ ሊሰግዱለት ሄደው ከሌላው ዓለም በፊት የተገኙትና ገጸ-በርከት አቅርበው ወደ ሀገራቸው በሰላም የተመለሱ።

አሁንም እኛ ኢትዮጵያውያን የክርስቶስን ትእዛዝና ትምህርት የተቀበልን እንደ ኃዋርያት ማለት ብሉያት መጽሐፍትን አስቀድመን እንደተቀበልን፡ መጽሐፍተ አዲሳትንም ወዲያውኑ ነው የተቀበልንና አምነን በጌታችን በእየሱስ ክርስቶስ ስም የተጠመቅነው፤ በስሙ ክርስቲያኖች የተባልነው እንጂ ሐዲሳትን መጻሕፍትን ብቻ እንደተቀበሉት እንደ አሕዛቦች አይደለም። ለዚህ ሁሉ ምስክራችን ፈጣሪያችን እግዚአብሔርና እግዚአብሔር ያዘዘው የአምልኮታችን ሥርአት ነው። እሄውም የማይታየው አምላክ በነቢያት ሰው እንደሚሆን አስቀድሞ መነገሩ በሐዋርያት ሰው መሆኑ መሰበኩን የሚያበስሩትን ብሉያትና ሐዲሳትን /በማስማማታችን/ በማዋሐዳችን እምነታችን ተዋሕዶ ሃይምንት ተብሏል። ምስጢሩም ቃል ሥጋ በመሆኑ የነቢያት ትንቢት በመፈጸሙ ተዋሕዶ ሃይማኖት አሰኝቶታል።

እሄን ክብርና ጸጋ ለሰጠን ለአንድ እግዚአብሔር የአምልኮት ምስጋናና ሥግደት ይገባዋል። እግዚአብሔር ለዘለዓለም ለሰው ልጆች ሰላምንና ፍቅርን ሕብረትንም ይስጠን። ምህረቱና ቸርነቱም በሰማይ እንደሆነ በምድርም ይሁን። አሜን።

______________

Posted in Ethiopia, Faith, Saints/ቅዱሳን | Tagged: , , , , , , , , , , , , , , , , , | Leave a Comment »

 
%d bloggers like this: