Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

 • January 2023
  M T W T F S S
   1
  2345678
  9101112131415
  16171819202122
  23242526272829
  3031  
 • Archives

 • Categories

 • Recent Posts

Posts Tagged ‘አባ ሳሙኤል’

ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው ፥ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on March 20, 2022

💭 በኤዶማውያኑ ምዕራባውያንና በእስማኤላውያኑ ምስራቃውያን ፍላጎትና ትዕዛዝ በኦሮማራ ቃኤላውያን ክሃዲዎች አማካኝነት ከዋልድባ ገዳም የተባረሩትን ፩ ሺህ አባቶቻችንን የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያጽናናቸው የእግዚአብሔር መላእክት ይጠብቋቸው፤ ይንከባከቧቸው!

✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፯፥፭፡፮]✞✞✞

“እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።”

✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፯፥፴፡፴፩]✞✞✞

“በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው። መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።”

✞✞✞ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ✞✞✞

✞✞✞በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!✞✞✞

አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፤ አባታችን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በረከታችውና ረድኤታቸው ይደርብንና በሰሜኑ የሀገራችን የኢትዮጵያ ክፍል በ ፬ /4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ እንደ ተመሰረተ በሚነገርለት በደብረ ዋሊ ወይም ዋልድባ ገዳም የተነሱ ስመጥር መነኩሴ መናኝና የጽድቅ መምህር ናቸው።

የገዳማዊ ሕይወት እጅግ ተስፋፍቶ በነበረበት በ፲፫/13ኛው እና በ፲፬/14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እነ አባ ኢየሱስ ሞዓ፣ ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሆኑ የእነዚህም የቆብ ልጅ በሆኑት በገዳመ በንኮል በአባ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኩስናን ተቀብለው ቤተ ክርስቲያንን በተሰጣቸው መንፈሳዊ ጸጋ አገልግለዋል።

ትውልዳቸውና ቤተሰቦቻቸው፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተወለዱት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ አክሱም በ፲፪፻፺፭/1295 ሲሆን አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተ ማርያም ይባሉ። እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ የተመሰገኑ ክርስቲያኖች እንደነበሩና በኋላም በምንኩስና ህይወት እንዳለፉ በአባታችን የገድል መጽሐፍና በስንክሳር ላይ በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል።

መንፈሳዊ ትምህርታቸውና ገዳማዊ ህይወታቸው እንዲሁም የተማሩበት ቦታ፤ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ አባታቸው ለአክሱም ቄሰ ገበዝ እንደሰጧቸውና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከፊደል ጀምረው የቅዱስ ያሬድን ጸዋትወ ዜማና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጠናቀው ለአገልግሎትም ዲቁናን ተቀብለው በንቃትና በልባምነትም ቤተ ክርስቲያንን ለሰባት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ጌታችን በወንጌል “ፍጹም ልትሆን ብትወድ…”ማቴ.፲፱፣፳፩፡፳፪ ያለዉን ለመተግበር ለአክሱም ከተማ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ሚገኘው ደብረ በንኮል ገዳም ገብተው ከገዳሙ ሊቃዉንት የብሉያትንና የሐዲሳትን ትርጓሜ እንዲሁም ስርዓተ ምንኩስናን ተምረዋል። ከዚያም ብፁዕነታቸው አባ ሳሙእል ዘዋልድባ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ቅዱስ ሄኖክ የመረጠውን ምናኔ፤ አባ እንጦንስና መቃርስ የተከተሉትን የምንኩስና ሕይወት በሰፊው ተጓዘበት።

ነፍሱን ነፍሴ ሆይ እነሆ ለክርስቶስ ታጨሽ የቅዱሳንን ቀንበር እነሆ ተሸከምሽ የመላእክትን ንጽህና ትጠብቂ ዘንድ ዛሬ በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ፊት ቃል ኪዳን ገባሽ ቃልኪዳንሽን ብትጥብቂ እግዚአብሔር ይደሰትብሻል ባትጠብቂ ግን አጋንንት ይዘብቱብሻል በማለት መከራን በራሱ ላይ ያበዛ ነበር የጣመ የላመም አይመገብም ነበር ይልቁንም ከገዳሙ የሚሰጠዉን መቁኑን ተቀብሎ ለሌሎች

ሰጥቶ የዱር ቅጠል ይመገብ ነበር። ትጋቱንና የምናኔ ሕይወቱን ያዩ መናንያን አበው መነኮሳት የእነሱን የምንኩስና አክሊል እንዲቀበል ፈልገው የገዳሙን አበ ምኔት /ኃላፊ/ አባ መድኃኒነ እግዚእን ይመክሩና ይለምኑ ነበር አባ መድኃኒነ እግዚእም የሚያየዉንና ከመነኮሳቱም የሰማዉን ተቀብሎ በጊዜው ለምንኩስና ከተዘጋጁት አስራ ሁለት ከዋክብት ደቀ መዛሙርት ዉስጥ አንደኛው እንዲሆን ወስኗል።

ከምንኩስና ሥርዓቱም በኋላ እነዚህ አስራ ሁለት ከዋክብት ለሁለት ተከፍለው አምስቱን ከዋክብት በወሎ፣ ትግራይ እና ኤርትራ ሲመድቧቸው ሰባቱን ከዋክብት ደግሞ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በበዛዉም በጎጃም በጎንደር እንዲሁም በጣና አካባቢ እንዲያገለግሉ እንዲያስተምሩ አሰማርተዋል። አባታችን አባ ሳሙኤል በገድላቸው እንደምንመለከተው “ፀሐይ ሳሙኤል ዘዋሊ” ይላል ‘ዋሊ’ የዋልድባ ገዳም የቀድሞ መጠሪያ ስሙ ነው ዋልድባ ገዳም በጣም ተዳክሞ በነበረበት ዘመን ተነስተው ዋልድባን ከጥፋት የታደጉ መናንያንን በማሰባሰብ እንደገና ያስፋፉ በመሆናቸው ዘዋሊ ይሏቸዋል፤ ሳሙኤል ዘደብረ ዓባይም ይሏቸዋል የደብረ ዓባይን ገዳም የመሰረቱት እሳቸው ስለሆኑ።

አባታችን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከዚህ ዓለም በምናኔ ተለይተው ግርማ ሌሊቱን ድምፀ አራዊቱን ፀብዓ አጋንትን የሌሊት ቁር የቀን ሐሩርን ታግሰው የጽድቅን ጎዳና ተከትለው ብዙ የብዙ ብዙ ገድል በመሥራት ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርገዋል ይህም በገድልና በተአምራት መጽሐፋቸው በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል። ከነዚሁም ጥቂቶቹን ብንጠቅስ አባታችን አቡነ ሳሙኤል፤ ባሕርን የከፈለበት ጊዜ አለ፣በጌታ መንበር ፊት እየቀረበ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋርም የሚያጥንበት ጊዜ አለ፣

በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ሆኖ ከእነ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ከሁሉ ቅዱሳን ጋር አንድ ላይ ማዕድ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፣ በእጆቹ የያዛቸው መጻሕፍትም ሳይርሱ ወንዝ የሚሻገርበት ጊዜ አለ፣ በተለይ በጸሎቱ ሰዓት የእምቤታችንን ምስጋና ሲጀምር ከምድር አንድ ክንድ ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ፣ በቤትም ሆኖ ምስጋናዋን ሲጀምር የቤቱ መሰረት እየተናወጠ ዝናብ እንደያዘ ደመና፤ ቤቱ ከምድር ከፍ ብሎ የሚቆምበት ጊዜ አለ፣ መንፈስ ቅዱስም በብርሃን ሰረገላ እየወሰደው ወደ ተለያዩ ገዳማት ያደርሰዉና የጌታን ሥጋ እና ደም እንዲቀበልና እንዲያቀብል ያደርገው ነበር።

ብፁእ አባታችን ዉዳሴዋን ቅዳሴዋን ሲያደርስ እመቤታችን የፍቅሯ ምልክት ይሆነው ዘንድ ነጭ እጣንና የሚያበራ እንቁ ሰጥታቸዋለች። አባታችንም እነዚህን ስጦታዋች የምትሰጭኝ ምን ስላደረግሁ ነው? ብለው በጠየቋት ጊዜ እጣኑ የምኡዝ ክህነትህ ዕንቁው የንጽህናህ የድንግልናህ የቅድስናህ ናቸው ብላ ተርጉማላቸዋለች።

መራሄ ብሉይ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም የሁል ጊዜ ጠባቂው ነዉና በሁሉም ነገር ይረዳዉና እንደ ጓደኛም ያማክረው ነበር።

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባን የዱር አራዊት ሁሉ ይገዙለትና ይታዘዙለት እንደነበረ በዚሁ በገድል መጽሃፋቸው በሰፊዉ ተተንትኗል ይልቁንም ሁለት አናብስት የሁል ጊዜ አገልጋዮቹ ነበሩ። ከአንዱ ገዳም ወደ አንዱ ገዳም ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ እሳቸው በአንዱ አንበሳ ተቀምጠው ጻሕፍቶቻቸውን በሌላው አንበሳ ላይ ጭነው እንደሚጓዙ ገድላቸው ያስረዳል። ሌሎቹም አራዊት አባታችንን ሲያዩአቸው እናቱን እንዳየ እንቦሳ በደስታ ይፈነጩ ነበር።

በመግቢያችን እንደገለጽነው የዋልድባ ገዳም የተመሰረተው በጥንታውያን አበው ቢሆንም አባታችን አባ ሳሙኤል ሲገቡ ገዳሙ ምድረ በዳ ሆኖ እስከ መጥፋት ደርሶ ቋያ በቅሎበት የወባ ትንኝ መፈልፈያ ሆኖ እንደ ነበረና ቅዱስነታቸው ሲገቡ ግን የተበተኑትን መነኮሳት ሰብስበው ዋልድባን እንደገና አደራጅተዉና አድሰው አቀኑት የተባህትዎ ኑሮንም አጠናክረው የመናንያን መነኮሳት አበው መሰባሰቢያና መፍለቂያ ከማድረጋቸውም በላይ ዋልድባን እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋታል።

ጻድቁ አባታችን ወንጌልን ለማስፋፋት በየሀገሩ ዞረው አስተምረዋል ብዙ የትሩፋትንም ሥራ ሠርተዋል ጣና ውስጥ በሚገኙ ገዳማትና ማን እንደአባ ያሳይ እንዲሁም ገሊላ ቦታዎች በምድር ዉስጥ ጉድጓድ ቆፍረው እየገቡ ከእህልና ዉሀ ተለይተው ሁለትና ሦስት ሱባኤ ይፈጽሙ ነበረ።

ከሁለት ቅዱሳን ወንድሞቻቸው ከአባ ሳሙኤል ዘወገግና ከአባ ብንያም ዘታህታይ በጌምድር ጋር በመሆን ምድረ ከብድና ዝቋላ በመሄድ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር በተገናኙ ጊዜ ብዙ ተአምራት እንደተደረገላቸው መጽሐፈ ገድላቸው ያስረዳል እንዲሁም ደግሞ በኤርትራ የሚገኘዉን ገዳም ከመሰረቱት ከአቡነ ፊልጶስ ጋር እንደተገናኙና የእግዚአብሔርን ክብር ይጨዋወቱ እንደነበር በገድላቸው ተጽፏል።

ጻድቁ አባታችን በሰኔ ፳፩/21 በእመቤታችን የእረፍት ቀን በመካነ ጸሎታቸው ላይ እያሉ ጌታችን መድኃኒታችን ተገለጸላቸው። ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ ሰላምታ ይገባሃል ። የሚል ድምጽ ሰሙና ደንግጠው ቆሙ። ጌታችን ቀረብ ብሎ የእናቴ የድንግል ማርያም በዓል ነውና እንድትቀድስ ብሎ አዘዛቸው። አባታችንም እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ለመቀደስ አልበቃሁም በማለት ነው ከቤተ መቅደስ አገልግሎት የተለየሁት ብለው መለሱለት። ጌታችንም ስለዚህ ትህትናህ ነው እንድትቀድስ የመረጥኩህ አላቸው። ወዲያዉኑ አባታችን ከፈጣሪያችን ሥርየትና ቡራኬ ተቀብለው ቅዳሴ ገቡ። ሥርዓተ ቅዳሴዉን አድርሰው ከፍሬ ቅዳሴው ደርሰው ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ፣ ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ፣ ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ባሉ ጊዜ የሚቀድሱበት ቤተ ክርስቲያን አንድ ክንድ ከስንዝር ከምድር ለቅቆ እንደ ደመና በአየር ላይ ቆመ። ቅዳሴው ተፈጽሞ እትው እስኪባልም ድረስ እንደቆመ ቆይቷል። ከቅዳሴው በኋላም ጌታችን ከሰው ልጆች የተወለዱትን ሁሉ ወደፊትም እስከ ምጽዓት ድረስ የሚወለዱትንም እልፍ አእላፋት መናንያን መነኮሳት ሰብስቦ በአምላካዊ ሥራው ሕያዋን አድርጎ አሳያቸው።አቡነ ሳሙኤልም በመገረም አምላኬ ፈጣሪየ ሆይ ይህንን ያህል ግዛት ያለው ሰው ከምን የመጣ ነው? ብለው ጠየቁት። እነዚህ እስከ እለተ ምጽዓት ድረስ የሚወለዱ ልጆችህ ናቸው።በአንተ እጅ እንዲባረኩም አምጥቻቸዋለሁ ባርካቸው በማለት ነግሯቸዋል። የአቡነ ሳሙኤልን ስም የሚጠራ መታሰቢያቸዉን የሚያደርግ በአማላጅነታቸው የሚያምን ሁሉ ተባርኳል።

የአባታችን በረከት ከሁላችን ጋር ይደር። የአባ ሳሙኤል ቃል ኪዳናቸው፣ እረፍታቸውና ዓመታዊ ክብረ በዓላቸው የአባታችን የእረፍት ጊዜ ሲደርስም በተወለዱ በአንድ መቶ ዓመት በምናኔ በተባህትዎ እና በምንኩስና ከዚህ ዓለም ተለይተው ግርማ ሌሊትን ድምፀ አራዊትን ፀብአ አጋንንትን የቀን ሐሩር የሌሊት ቁሩን ታግሰው ራቡን ጥሙን ችለው መላ ዘመናቸውን የተቀበሉትን ፀዋትወ መከራ አይቶ ገነት መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸው ዘንድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባታችን ካሉበት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማእታትን አስከትሎ መጥቶ በህይወት ሳሉ የሰጣቸዉን ቃል ኪዳን በእረፍታቸዉም

ደግሞ ስምህን የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በጸሎትህ በአማላጅነትህ ያመነ፣ በመቃብርህ በመካነ አፅምህ የተማፀነ የአንተ ቤተሰብ ሆኖ አንተ የገባህበት አገባዋለሁ። ርስት መንግሥተ ሰማይን አወርሰዋለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። ንጽሕት ጽዕድት ነፍሳቸው በእደ መላእክት በመዓዛ ገነት ከሥጋዋ ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በነብዩ በዳዊት ቃል መዝ.፻፲፮፥፲፭ “ክቡር ሞቱ ለጻድቅ

በቅድመ እግዚአብሔር” እያሉ በታላቅ ዝማሬ፣ በይባቤ፣ በእልልታና በሕይወት ወደ ዘለዓለም የእረፍት ቦታ አስገቧት። ጻድቁ አባታችን በተወለዱ በመቶ ዓመታቸው ታህሳስ ፲፪/12 ቀን ማክሰኞ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዋልድባ አብረንታንት አርፈዋል።

ስለ አባታችን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ይህንን አጭር ጽሁፍ ስናቀርብ አቅጣጫ ለማመላከት ያህል ሲሆን መላዉን በገድል መጽሐፋቸውና በስንክሳር ያገኙታል።

በመስከረም ፮/6 ፍልሰተ አጽማቸው ነው፤ ይህም ከአብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ነው፣ ታህሳስ ፲፪/12 እረፍታቸው ነው እንዲሁም ወር በገባ ፲፪/12 ደግሞ ወርኃዊ በዓላቸው ነው።

የጻድቁ አባታችን የአቡነ ሳሙኤል ረድኤት በረከት አማላጅነት አይለየን!!!

👉 ሙሉውን ለማንበብ

_______________

Posted in Ethiopia, Faith, War & Crisis | Tagged: , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , | Leave a Comment »

በታጣቂዎች የተከበቡት የአሰቦት ገዳም መነኰሳት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው፤ የወረዳው አስተዳዳሪ “ለቃችሁ ውጡ” በማለት ከታጣቂዎቹ ጋር አብሯል

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on October 26, 2018

 • + ከጥቅምት 7 ጀምሮ በየምሽቱ ከታጣቂዎቹ ጋራ የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ላይ ናቸው፤
 • + ታጣቂዎቹ፣“የኦነግ ወታደሮች ነን”ቢሉም ተከፋይ ሁከተኞች ሊኾኑ እንደሚችሉ ተነግሯል፤
 • + የወረዳው አስተዳደሪ፣ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው በዞኑ የተላለፈለትን ትእዛዝ አልፈጸመም፤
 • + በሶማሌ ክልል ወሰን በኩል የመከላከያ ድጋፍ ቢጠየቅም ኦሮሚያ መፍቀድ አለበት፤ተብሏል፤
 • + አንዱ በሌላው ሲያመካኝ፣ የግንቦት 1984 ዐይነቱ ወረራና እልቂት እንዳይደገም አስግቷል፤
 • + በስብሰባ ላይ ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በአስቸኳይ የኦሮሚያን ክልል እገዛ ሊጠይቅ ይገባል፤
 • + ፓትርያርኩ በመክፈቻቸው እንዳሉት፣ በተጽዕኖና በማፈናቀል የማዳከም ስልቶች አንዱ ነው፤
 • + ከጸጥታና ፍትሕ አካላት ጋራ በመቀናጀት፣ጥቃቱን ከወዲሁ ለማምከን መፍጠን ያስፈልጋል፤

ማንነታቸው በውል በማይታወቁ ታጣቂዎች የጥቃትና ወረራ ስጋት ውስጥ ቀናትን ያስቆጠሩት ጥንታዊው የአሰቦት ደብረ ወገግ ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል ገዳም ማኅበረ መነኰሳት፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለመንግሥት አካላት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በሜኤሶ ወረዳ የሚገኘው የገዳሙ መነኰሳት እንደተናገሩት፣ ታጣቂዎቹ ከጥቅምት 7 ጀምሮ በየምሽቱ ወደ ገዳሙ በመተኰስ ማኅበሩን ለማሸበር እየሞከሩ ሲኾን፤ የወረዳውና የዞኑ አስተዳደር ጥበቃ እንዲያደርጉላቸውና ከይዞታቸው እንዲያስወጡላቸው ያደረጉት ጥረት ውጤት ባለማስገኘቱ የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥሪ አሰምተዋል፡፡

ገዳማውያኑ እንዳስረዱት፣ በቁጥር ከ25 ያላነሱ ታጣቂዎቹ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ የገዳሙ ይዞታ ወደኾነው ደን ውስጥ ገብተው ድንኳን ተክለው ተቀምጠዋል፡፡ ስለማንነታቸው ሲጠየቁ፣ የኦነግ ወታደሮች እንደኾኑና የመጡበትም ምክንያት፣ “የሶማሌ ወታደሮች ወደዚህ ይገባሉ ተብለን ወደ እነርሱ ነው የምንሔደው፤” ብለዋል፡፡ ቀደም ሲልም ጫካ ውስጥ ገብተው ወደ ገዳሙ በዘፈቀደ የሚኩሱ፣ ዐጸዶቹን የሚቆርጡ ሁከተኞች እንደነበሩ ያወሱት ገዳማውያኑ፣በኦነግ ስም ቢጠሩም በብጥብጥ ለመጠቀም የፈለጉ ተከፋዮች ሊኾኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ባለፉት ሦስት ቀናት በየምሽቱ በተኩስ ለማሸበር የሚያደርጉትን ሙከራ አጠናክረው እንደቀጠሉና መሰል አጸፌታ ከመስጠት ውጭ ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ መነኮሳቱ አስረድተዋል፡፡ ባለፈው ሰኞ ምሽት ከምሽቱ 2 እስከ 4 ሰዓት የቀለጠ የተኩስ ልውውጥ እንደነበርና በትላንትናው ዕለት ሌሊትም ኹለት አብሪ ጥይቶችን ወደ ገዳሙ በመተኰሳቸው መጠነኛ አጸፌታ እንደሰጡ አክለዋል፡፡

የችግሩ ምልክት እንደታየ መነኰሳቱ ጥያቄያቸውን ያቀረቡለት የሜኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪ፣“የያዛችሁት የሰው ቦታ ነው፤ ለምን ለቃችሁ አትወጡም” በማለት እንደሚያመናጭቃቸው ገዳማውያኑ ተናግረዋል፤ ለዞኑ ባቀረቡት አቤቱታ፣ ጥበቃ እንዲያደርግላቸውና መፍትሔ እንዲሰጣቸው ቢታዘዝም ሓላፊነቱን ለመወጣት ፈቃደኛ እንዳልኾነ አስታውቀዋል፡፡

ገዳሙ ከሶማሌ ክልል በሚዋስንበት አቅጣጫ ለሚገኘው የመከላከያ ኃይል ድጋፍ መጠየቃቸውን መነኰሳቱ ጠቅሰው፣“የኦሮሚያ ክልል በመኾኑ ፈቃድ ካላገኘን መግባት አንችልም፤ክልሉን ደጋግማችሁ ጠይቁ፤ የሚል ምላሽ ብቻ ነው የሰጡን፤” ብለዋል፡፡ አንዳችም ጥበቃ እየተደረገላቸው ባለመኾኑ የክልሉ መንግሥት እና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ለድረሱልን ጥሪያቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጧቸው ተማፅነዋል፡፡

ከጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ ዘኢትዮጵያ ደቀ መዛሙርት አንዱ በነበሩት ጻድቁ አቡነ ሳሙኤል በ13ኛው መ//ዘ የተመሠረተው ገዳሙ፣ በግራኝ ወረራ ጊዜ ከጠፉት ገዳማት አንዱ ነበር፡፡ እንደገና የቀናው እጅግ ዘግይቶ በ1911 .. ሲኾን፣ አቅኝውም የታወቁት ሊቅ አለቃ ገብረ መድኅን ናቸው፡፡ በ1912 .. የጻድቁ አቡነ ሳሙኤልን ቤተ ክርስቲያን በሣር ክዳን ሠሩ፡፡ በ1918 .. ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን መሥራት ጀምረው፣ ፍጻሜውን ሳያዩ ቢያርፉም በ1919 .. የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ተጠናቋል፡፡

1929 .. በሶማልያ በኩል በገባው የፋሽስት ኢጣልያ ጦር ገዳሙ ተዘርፏል፤ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንም ፈርሷል፡፡ በወቅቱ በገዳሙ ከነበሩት 500 መነኮሳት መካከል ከፊሉ ታቦቱን ይዘው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሲሸሹ ከፊሎቹ ደግሞ ወደ ሞቃዲሾ ተወስደው ታስረዋል፡፡ ወራሪው ከተባረረ በኋላ መነኮሳቱ በ1936 .. ተሰባስበው ወደ አሰቦት መጡ፡፡ ከ22 ዓመት በኋላ ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ በ1952 .. ተሠራ፡፡ ግንቦት 16 ቀን 1984 ..፣ የኦሮሚያ ነጻነት እስላማዊ ግንባር (ጃራ) የተባለ አክራሪ ኃይል፣ ገዳሙን ወርሮ በዙሪያው የሚኖሩ መነኮሳትንና 16 ክርስቲያን አባወራዎችን አርዷል፡፡

ካህናትንና ክርስቲያኖችን በተጽዕኖና በጥቃት ማፈናቀል፣ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም አንዱ ስልት እንደኾነ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግራቸው የጠቀሱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በየአካባቢው ከሚገኙ የፍትሕ እና ጸጥታ አካላት ጋራ በመቀናጀት ጥቃቶችን አስቀድሞ የማምከንና ሲደርሱም የመከላከል አሠራር እንደሚቀየስ ጠቁመዋል፡፡ የታጣቂዎቹ ፍላጎት፣ ድምፃቸውን አጥፍተውና መነኮሳቱን አጋዥ አሳጥተው ገዳሙን ማጥፋት እንደኾነ መነኮሳቱ እየተናገሩ በመኾኑ፣ ከክልሉ መንግሥትና ከወረዳው አስተዳደር ጋራ በመነጋገር ለድረሱልን ጥሪያቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው መፍጠን ያስፈልጋል፡፡

ምንጭ

______

Posted in Ethiopia, Faith, Infos | Tagged: , , , , , , , , , , | Leave a Comment »

Leaders & Leadership — መሪና አመራር

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on February 15, 2013

EthioCoronationአባ ሳሙኤል፡ መሪና አመራርበሚለውና በ2003 .ም የወጣው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ወቅታዊ ኹኔታ ያገናዘቡ ብልህነት የተሞላባቸውን ነጥቦች ለአንባቢው አቅርበዋል።

ከአድናቆትና ክብር የተሞላበት ምስጋና ጋር ከመጽሐፉ ቀንጨብ አድርጌ የሚከተሉትን ሓሳቦቻቸውን እንሆ አቅርቤአለሁ።

ምናልባት ለቤተክርስቲያናችን መሪነት በእጩነት ከቀረቡት አባቶች መካከል አባ ሳሙኤል አንዱ ከሆኑ የኔን ድምጽ አግኝተዋል።

6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ የሚካሄድበት ሣምንት ለእናት ኢትዮጵያ ልዩ ጸሎት የምናደርግበት የ ነነዌ ጾም ወቅት ስለሆነ መንፈስ ቅዱስ ስራውን እንዲሰራ፡ አባቶችንም እንዲረዳ በአንድነት ልባችንን ልናርገበግብ ይገባናል። ኢትዮጵያ የ6ኛውን ፓትርያርክ ፍለጋ በጀመረችበት ወቅት የሮማ ካቶሊክ ጳጳስም 112 ኛውን (100 + 6 + 6) ጳጳስ ለመምረጥ በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች። አጋጣሚ? የሮማው መብረቅ፡ የሩሲያው በራሪ ኮከብ ምን እየነገሩን ይሆን? አባታችህ ሔኖክ በመጽሐፉ ላይ አሁን ጎርፍ ሳይሆን እሳት ነው ከላይ የሚመጣውያለን የመጨረሻው ዘምን ደርሶ ይሆን? እግዚአብሔር ይጠብቀን! የሚገርመውና የማይገርመው ግን ሊቃውንቱ አውቀነዋል፣ ዓይተነዋል፣ አግኝተነዋል በማለት ምድራችንን በ20ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ዛሬ ማታ እንደሚያልፍ የተነበዩልንን ተለቅ ያለ በራሪ ኮከብ (Meteor > Metéora Eastern Orthodox Monasteries) በኩራት ሲጠባበቁ ይህ ያልታየው ሌላ ኮከብ ሹልክ ብሎ በሩስያ አረፈ። ይህም የሚያሳየው ምንም እውቀት የሌለን ግብዞች መሆናችን ነው። 10% ብቻ የሚሆነውን ነገር በዙሪያችን ማየት እንደምንችል ይህ ሌላ ትልቅ ማስረጃ ነው።

ለማንኛውም፡ ወደ መጽሐፉ፦

እግዚአብሔር አምላክ ታላላቅ ሥራዎችን ለማስፈጸም መሪዎችን እንዲመርጥና በእነርሱም አማካይነት ሥራውን እንደሚያስፈጽም ግልጽ ነው።

የማናቸውንም መሪ ተግባር በግልጽና በቀላል ኹኔታ ለመረዳት አገልግሎትን ለመስጠትና ሓላፊነትን ለመቀበል ዝግጁና ፈቃደኛ መሆንን መሠረት ማድረግ ይጠይቃል።

መሪነት ካለፈው ትውልድ ወደ አዲሱ ትውልድ መተላለፍ አለበት። ይሁን እንጂ የሽግግሩ ሒደት አባት ለልጁ የሚያደርገውን የሓላፊነት ሽግግር ዝግጅትና ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል። የሚሴና የኢያሱ የመሪነት ቅብብሎሽም ለዚህ አባባል ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። ንገር ግን እኛ ሰዎች ታሪክ እንማራለን እንጂ ከታሪክ አንማርም!” … መሪነት ማለት ሰዎች በፈቃደኝነት ለአንድ ዓላማና ግብ ለማሰለፍና የማግባባት ችሎታ ያላቸው ማለት ነው።

ኅይልና ሥልጣን

የመሪነትን ተግባር በአግባቡ ለማወቅ ኅይልና ሥልጣን (Power & Authority) የተባሉትን ጽንስሐሳቦች መገንዘብ ያስፈልጋል።

ኅይል (Power)

አንድ ሰው ሌሎችን ለመምራት ያለው ዕምቅ ችሎታ የሚታወቅበት (የሚገለጽበት) ሲሆን ዋና ዋና ዘዴዎቹም፦

 • በሕግ መሠረት በሚሰጡ ሓላፊነቶች
 • ግለሰቡ ለመግባባት የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች
 • ለማስፈጸም በሚፈጥራቸው ጤናማ የሆኑ ጫናዎች
 • ከችሎታው፣ ከልምዱና ከእውቀቱ በሚመነጩ ኹኔታዎች

የመሳሰሉትን የሚያጠቃለል ነው።

. ሥልጣን (Authority)

አመራር ለመስጠትና በሥሩ ባሉት መሠረታዊ ሀብቶች ለመጠቀም የሚሰጥ ሕጋዊ መብት ማለት ነው።

ስለሆነም አንድ መሪ ተገቢውን የመሪነት ሚና ለመጫወት ኅይልና ሥልጣንን በየዐውዳቸው መጠቀም ይጠበቅበታል ማለት ነው። ሐዋርያው እንዳለው የእግዚአብሔርን ቤት እንዴት እንደምታስተዳድር ታውቅ ዘንድ እጽፍልሀአለሁ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤት ናት። (1. ጢሞ. 315)

የቤተ ክርስቲያን ኅልውና በሥራ የሚገለጥ ሃይማኖት ነው፤ የሃይማኖት ፍሬም እውነተኛ የአስተዳደር ፍቅር ነው። በቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርንና ሰውን ሊያስደስት የሚችለው ሥልጣንና ገንዘብ አይደለም። ሊሆን የሚገባውን ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው በእውነት በተመደበበት የሓላፊነት ሥራ በታማኝነት ሲያገለግል ብቻ ነው።

ውጤታማ የኾነ አመራር መስጠት የሚቻለው የሰዎችን ፈቃደኝነት በተመረኮዘ ኹኔታ በመግባባት በመሆኑ ለማግባባት ደግሞ ጤናማ ግንኙነትን መፍጠር ግዴታ ይሆናል።

ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር መሪዎች ምን ማድረግ አለባቸው?

 • ኅይልና ሥልጣናቸውን በተገቢው አኳኋን መጠቀም፣
 • ተከታዮቻቸውን ከከፍተኛ ደረጃ ማብቃትና ማዘጋጀት፣
 • በተከታዮቻቸው ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት የበለጠ ማሳደግና ማስፋፋት፣
 • ከሥነምግባር ውጭ የሆኑ የማግባባት ዘዴዎችን አለመጠቀም፣
 • መነሻቸውን ከሰዎች መልካም ነገር እንደሚጠበቅ አድርጎ ግንኙነት መፍጠር (Positive expectation)
 • ራስን ለለውጥና ለአዳዲስ ነገር ዝግጁ አድርጎ መጠበቅ፣
 • የሕዝብን አስተያየት ለአመራር ተግባር ሊኖረው የሚገባውን ድርሻ መገንዘብ፣
 • ከሰዎች ጋር ለሚኖር ግንኙነት ተገቢውን ዝግጅት ማድረግና ውጤታማና ማራኪ
 • በሆነ አቀራረብ ለመቅረብ መጣር
 • ከስሜታዊ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ እንደሚገባ ያስረዳል።

መሪና ትሕትና

ለመንፈሳዊ መሪ ትሕትና የማዕር ልዩ ምልክት ነው ወይም ኒሻኑ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ከመታበይ አሮጌ እርሾ ይርቁ ዘንድ ይመክራቸው ነበር። ከዚህ ይልቅ ትሕትናን የተላበሱ ባርያን ይመስሉ ዘንድ ያሳስባቸው ነበር (ማቴ. 2025)። ትሕትና፡ በፖለቲካው እና በንግዱ ዓለም ጥቂት ብቻ አድናቆት የሚቸረው ጉዳይ ነው። ይህ ግን ትክክለኛ አይደለም። አንድ መንፈሳዊ መሪ ከእይታ ስውር የኾነውን እና መሥዋዕትነትን የሚጠይቀውን አገልግሎት የሚመርጥ፣ ከሌሎች ልቆ ለመገኘት እና በሁሉ ላይ የሠለጠነ ጌታ መኾኑን ለማረጋገጥ ሲል ራሱን ከመጠን በላይ የሚያስታጅረውንና ልታይ ልታይ የሚለውን ሰው ሊመስል አይገባውም።

መንፈሳዊ መሪ እና ትዕግሥት

መንፈሳዊ መሪ ጤና የኾነ ትዕግሥትን ገንዘቡ ሊያደርግ ይገባዋል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ትዕግሥትን የመልካም ሥራ ሁሉ እናት ናትያላታል። ሁልጊዜ ትዕግሥትን ስናስብ አንዴ ተከውኖ ድጋሚ የማይፈጸም አድርገን ልንቆጥረው አይገባንም። ትዕግሥተኛ ሰው ግማሽ በማንቀላፋትና እንደ መሩት እንደሚመራ ሰዎ አድርገን እንመስለዋለን። ነገር ግን እንዲህ ዐይነት ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል። (2ጴጥ. 16)

ቃሉ ፈጽሞ እጅን አጣጥፎና ነገሮችን ዝም ብሎ ለመቀበል መንፈስ ታስቦ መተርጎም የለበትም። ይልቁኑ ሁሌም አሸናፊ ኾኖ ለመዝለቅ መከራን ተቋቁሞ የማስፈን ትርጉም የሚሰጠን ቃል ንው።

ይህ አንድ ክርስቲያን በቆራጥነትና በእልህ በዚህ ዓለም የሚገጥሙትን የኑሮ ፈተናዎችን ትቋቁሞ የሚያልፍበት፣ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመለወጥ ደስታ ወዳለበት ከፍታ እንዲደርሱ የሚያግዝ መሳሪያ ነው።

ነገሮችን ተቋቁሞ በሰው ያልተደፈሩትን ሰብሮ ለመግባት፤ ጽናትን እና ድል አድራጊነትን ሊያሰጥ፤ አቅምን ሊፈጥር የምችል እና የማይታየውን በመናፈቅ በደስታ ለመቀበል የሚናፍቅ ነው።

ትዕግሥት በማኅበራዊ ቁርኝታችን በእጅጉ የሚፈተን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ማርቆስ ከሚባለው ዮሐንስ ጋር ባደረገው ክርክር ትዕግሥቱ አልቆ ነበር።

መንፈሳዊ መሪ ትዕግሥትን ከተከታዮች በመራቅ ሊገልጸው አይገባም። ይህ እንዲያዝኑ ያደርጋቸዋል። ነገር ግን የመሪነቱን ቦታ ሳይለቅ ከጎናቸው ሲቆም ራሱን ብቻ ከመመልከት እና ከመስማት በመቆጠብ ሊመላለስ ይገባዋል። ለተከታዮች ማሰብን አጠንክሮ መያዝ ካልቻለ ራሱን በጽናት ማቆም የሚቻለው የለም። እኛ ኅይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንን ደስ እንድናሰኝ ይጋብዘናል፤” (ሮሜ. 151)

አንድ ሰው የሰውን ድካም ሊታገሥ የማይችል ከኾነ መሪ ለመኾን የተገባ አይደለም። የእኛ ጥንካሬ የሚለካው ከፊታችን ቀድመው በሚሮጡት እና በእኛና በእነርሱ መካከል ባለው ርቀት መጠን ሳይሆን ከእኛ አጠገብ ባሉት ጎን ፈጥነን በመሄዳችን ስለእነርሱ ስንል ቀስ ብለን ርምጃችንን በእነርሱ ፍጥነት ያደረግን ከኾነ ነው። የእኛ እርዳታ እነርሱን ከውድቀታቸው የሚያነሣ፣ መንገዱን ያሳየናቸውና ያሻገርናቸው እንደ ኾነ ብቻ ነው።

ይህ መነበብ ያለበት መጽሐፍ ባጠቃላይ የሚከተሉትን ጉዳዮች ይመለከታል፦

 • ምዕራፍ አንድ፡ መሪ እና አመራሩ
 • ምዕራፍ ሁለት፡ የተፈጥሮአዊ እና መንፈሳዊ መሪነት እይታዎች
 • ምዕራፍ ሦስት፡ የመሪነት አእምሮ መመዘኛዎች
 • ምዕራፍ አራት፡ የመሪነት ዐበይት ተምሳሌታዊ ምክሮች
 • ምዕራፍ አምስት፡ የአለመግባባት ዐበይት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
 • ምዕራፍ ስድስት፡ ሙስና እና መሪነት
 • ምዕራፍ ሰባት፡ ጽናትና መሪ
 • ምዕራፍ ስምንት፡ ብልህነት እና ዲፕሎማሲ
 • ምዕራፍ ዘጠኝ፡ ከሁሉ በላይ የሆነው ጉዳይ የመሪዎች መንፈሳዊነት
 • ምዕራፍ ዐሥር፡ መሪ እና ጊዜ
 • ምዕራፍ ዐሥራ አንድ፡ የመሪነት ክህሎት ማሳደግ

__

Posted in Curiosity, Ethiopia, Faith | Tagged: , , , , , , , | Leave a Comment »

 
%d bloggers like this: