የታኅሣሥ ገብርኤል
“ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት” ከሚለው የንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደየሱስ መጽሐፍ የተወሰደ
ከከበረ ሰላምታ ጋር…
በታኅሣሥ ወር በ፲፱ነኛው ቀን የሚውለው የ “ታኅሣሥ ገብርኤል” በዓል የሚከበርበት ምክንያት እንዲህ ነው፦
እግዚአብሔር በሙሴ መሪነት የእሥራኤልን ሕዝብ በግብፅ አገር ይገኙበት ከነበረው የባርነት አገዛዝ ነጻ አውጥቶ ቤተ መቅደሳቸውንና ከተማቸውን በኢየሩሳሌም አድርገው በምድረ ከነዓን እንዲኖሩ አበቃቸው። እነርሱ ግን ባካባቢያቸው ያሉትን አሕዛብ እየተከተሉ አምልኮ ባዕድን በመፈጸም አምላካቸውን እግዚአብሔርን አሳዘኑት። በነቢያቱ ቢመክራቸውና ቢገሥፃቸውም በዚያ ኃጢአታቸው እየጨመሩበት ከመኼድ በቀር ከበደላቸው ተጸጽተው ሊመለሱ ጨርሶ የማይቻል ኾነ።
በዚህ መልክ በፈጣሪያቸውና ከእርሱ ጋር በተጋቡት ቃል ኪዳናቸው ላይ በሥውርና በገሃድ ያካሂዱት የነበረው ክህደት ዓመፅና አመንዝራነት፡ በመጨረሻ ጽዋው ስለሞላ እግዚአብሔር ለዚህ ድርጊታቸው ምስክር የሆነችው ታቦተ ጽዮን ከእሥራኤላዊው ንጉሥ፡ ከሰሎሞንና ከኢትዮጵያዊቷ ንግሥት፡ ከመከዳ በተወለደው፡ በቀዳማዊ ምኒልክ አማካይነት በቅድሚያ ወደ ኢትዮጵያ እንድትሄድ አደረገ። ከዚያ በኋላም ያወረሳቸውን አገርና ከተማ ወርሮ ይበዘብዝ ዘንድ አረማዊውን ንጉሥ፡ ናቡከደነፆርን ታላቅ የሠይፍ ኃይልን አስታጥቆ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፡ እርሱም በዚያ የቅጣት ተልእኮውን እንዲፈጽም ኃጢአተኛውንም የእሥራኤል ትውልድ ፈጅቶ የተረፉትን በምርኮ ወደምድሩ ወደ ባቢሎን እንዲወስዳቸው ለስደትም እንዲዳረጋቸው አሠለጠነው።
ለዚያ ስደት ከተዳረጉት እሥራኤላውያን መካከል በሃይማኖታቸው የጸኑና በምግባራቸው የተጠናከሩ፡ አካሄዳቸው ከነቢዩ ዳንኤል ጋር የሆኑ፡ አናንያ፥ አዛርያን ሚሳኤል የተባሉ መንፈሳውያን ወጣቶች ነበሩ። እነዚህ “ሠለስቱ ደቂቅ የተባሉት ሦስት ልጆች በእውቀታቸውና በብልህነታቸው ተመርጠው የንጉሡ ሹማምንት ኾነው ያገለግሉ ነበር።
የኋላ ኋል ግን የአገሩን አማልክት እንዲያመልኩ ንጉሡ ላቆመውም ጣዖት እንዲሰግዱ ያን ባያደርጉም በአዋጅና ባደባባይ እየነደደ ባለ አስፈሪ የእሳት ነበልባል ውስጥ የሚጣሉ መሆናቸውን የሚገልጽ የፈተና ጥያቄ ከንጉሡ ቀረበላቸው። እነርሱም ለገንዘብና ለሹመት ጓጉተው የንጉሡን ቍጣም ፈርተው አምላካቸውን የማይክዱ፡ ሃይማኖታቸውንም የማይለውጡ መሆናቸውን በመግለጽ “ንጉሥ ሆይ! የምናመልከው አምላካችን ፡ ከእጅህም ሆነ ከዚህ ከሚነድደው የእሳት ነበልባል ሊያድነን ይችላል፡ ባያድነንም እንኳ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ጣዖት እንዳንሰግድለት እወቅ!” ሲሉ በድፍረትና በቆራጥነት መልስ ሰጡት።
በዚህ ጊዜ ፍርዱ እንዲፈጸምባቸው ከንጉሡ ታዝዞ ሦስቱም ገድለኞች በሚነድደው እሳት ውስጥ ተጣሉ። ወደ እሳቱ ሊጥሏቸው የወሰዷቸው ኃያላንም በነበልባሉ ብርቱ ወላፈን እየተቃጠሉ ሞቱ።
ወደ እሳቱ ውስጥ ታሥረው የተጣሉት እኒህ መንፈሳውያን አርበኞች ግን የእግዚአብሔር መልአክ እሳቱን አቀዝቅዞላቸው በነበልባሉ መካከል ወዲያ ወዲህ ሲመላለሱ ከመታየት በቀር በአካላቸው ቀርቶ በልብሳቸው ላይ እንኳ አንዳችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከተፈረደባቸው የቃጠሎ ሞት ድነው በደህና ሊወጡ ችለዋል። ይህንም፡ “የዚያን ጊዜም፡ ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ፡ ፈጥኖም ተነሣ፡ አማካሪዎቹንም ሦስት ሰዎችን አሥረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? … እነሆ፡ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን አያለሁ ምንም አላቆሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል፡‘ ብሎ መለሰ።“
“የአራተኛው መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል” የተባለው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል መኾኑን ከትውፊታችን አግኝተነዋል።
በሃይማኖት ሳይወላውሉ በምግባር ተጠናክረው እስከመጨረሻው፡ ማለትም የሞት ጽዮን ለመቀበል ተዘጋጅቶና ቆርጦ እስከመቅረብ ድረስ በጅመሩት ገድል ጸንቶ መገኘት የሚያስከትለው ውጤትና የሚያስገኘው ፍሬ በነፍስ ብቻ ሳይኾን የሥጋ ሞትን ጭምር በማስቀረት፡ የምሕረት ሕይወትን በክፋት ኃይላትም ላይ ድልን የሚያቀዳጅ የመላእክት ተራዴነትን መኾኑን በዚሁ በታኅሣሥ ፲፱ ቀን የምናከብረው “የታኅሣሥ ገብርኤል” በዓል ያስታውሰናል፡ ያስተምረናልም።