በመንግሥቴ አወቀ – ሪፖርተር ጋዜጣ 12 Aug, 2016
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 2013፣ በመቶ ቤት የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎችን የያዘ ጀልባ ጣሊያን ባህር ጠረፍ ማዶ ውስጥ ሰጥሞ ከ360 በላይ ሰው ሲያልቅ፣ አገሪቷ ጣሊያን የታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን የወሬ መተረማመሻ ሆኖ ነበር፡፡
በሰሜናዊው አፍሪካ በኩል የሜዲትራንያን ባህር አቋርጦ አውሮፓ ለመግባት እንደ ጐርፍ የሚፈሰውና ቁጥሩ እያደር የሚጨምረው ፈላሽ (መጣተኛ) ቁጥር፣ እነሆ እንደ ከሳምንት በፊት በደረሰው የ900 ሰዎች እልቂት አማካይነት ከቁጥጥር የወጣ ችግር መሆኑን በግድ እያስመዘገበ መጥቷል፡፡ ከዚህ እልቂት ሁለትና ሦስት ቀናት በፊት 550 መጣተኞች (ማይግራንትስ) ከያዘ ጀልባ ውስጥ ከ400 ያላነሱ ሰምጠው ሞተዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) መረጃ መሠረት፣ ሜዲትራንያን ባህርን አቋርጦ ወደ አውሮፓ የሚወስድ ዕድልና ሁኔታ እስኪመቻችላቸው ድረስ መከራ እየተቀበሉ የሚጠብቁና ሊቢያ ጠረፍ ላይ የሠፈሩ በግማሽ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በተለመደው ስቃይና መከራ ውስጥ ጣሊያን የደረሱት 20 ሺሕ ያህል ብቻ ናቸው፡፡
አብዛኞቹም የግዞት ካምፕ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከአፍሪካ በሜዲትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ የሚደረገው ጉዞ ሦስት ጎዳናዎች (መንገዶች) አሉት፡፡ አንደኛው የመንገደኞች ምንጭ ከሴኔጋል፣ ጊኒ፣ ማሊ አድርጎ ከዚህም አጋብሶ ወደ ሰሜን አፍሪካ የሚያቀናው የምዕራቡ መንገድ ነው፡፡ የናይጄሪያ፣ የጋናና የኒጀርን ወጣት እያግተለተለ በተመሳሳይ ሁኔታ ሽቅብ ወደ ትሪፖሊ አቅንቶ ወደ ላምፔዱዛ የተዘረጋው መንገድ ማዕከላዊ ይባላል፡፡ ከሶማሊያ፣ ከኤርትራ፣ ከኢትዮጵያና ከሱዳን (ዳርፉር) አሰባስቦ በሱዳን ካርቱም፣ ከዚያም በኩርፍ አጅዳቢያ ቤንጋዚ ወይም ትሪፖሊ በኩል ወደ ባህሩ የሚሄደው ደግሞ የእኛው ምሥራቃዊ መንገድ ነው፡፡ የገዛ ራሱ ገባር ወንዝ ያለው ይህ ሁሉና እያንዳንዱ መንገድ ራሱ የሜዲትራንያን ባህር ገባር ነው፡፡
ከመነሻው ከእያንዳንዱ ቤትና ጭስ ጀምሮ የሚያስመዘግበው መከራና ግፍ፣ ጭካኔና ዝርፊያ ደግሞ የእያንዳንዱ ስደተኛ ወይም መጣተኛ ‹‹ሕይወቴና የአገሬ ዕርምጃ›› ነው፡፡ አሁን ይህንን ስጽፍ ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ አቋራጭና አጭሩ የሜዲትራንያን ባህር በኩል ለማለፍ ተራ ወረፋና ዕድል የሚጠብቁ ከግማሽ ሚሊዮን የበለጡ መከረኞች አሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል ነው 900 ያህሉ በግፍ ሰምጠው የሞቱት፡፡ ከእነዚህ መካከል ነው 30ዎቹ በግፍ ታርደው የሞቱት፡፡ ሁለቱም ዓይነት ሞቶች ልዩ ልዩነት አላቸው እንጂ ከግድያና ከትራጀዲ በላይ ወንጀል ጭምር ናቸው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በ30ዎቹ አረመኔያዊ ግድያ ምክንያት ብሔራዊ ሐዘን ቁጭ ብላለች፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ግዛቱ በገፍ በግፍ የሚሞቱ ስደተኞችና መጣተኞች መቃብር መሆኑ አሳፍሮት ይይዘው ይጨብጠው አጥቶ የመከራ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ በዘጠኝ መቶ ሟቾች ውስጥ አጠራጣሪው ቁጥራቸው እንጂ ኢትዮጵያውያን ስለመኖራቸው አይደለም፡፡ ይህም ሌላ ያልተረዳነው ሐዘን ነው፡፡ በቅጡ ያላወቅነው መርዶ ነው፡፡
እንዲህ ያለ ሐዘን ወቅት ከሚያሳስቡን ጉዳዮች መካከል በዛሬው ጽሑፌ የማነሳቸው ሁለቱን ነው፡፡ የውጭ ጉዞና ሃይማኖት፡፡
- ጉዳዩ ከሚያነሳው ነገሮች መካከል አንዱ የውጭ ጉዞ ነው፡፡ ወደ ዓረብ አገሮች የሚወስደውን በሰሜናዊው አፍሪካ በኩል ሜድትራንያንን አቋርጦ አውሮፓ የሚያደርሰውን፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በህንድ ውቅያኖስ አድርጎ መካከለኛው ምሥራቅ የሚያስገባውን፣ በምሥራቅ አፍሪካ አድርጎ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚወስደውን፣ ወዘተ ይህን የውጭ ጉዞ ከነስያሜው እንኳን ገና አላወቅንበትም፡፡ አልተስማማንበትም፡፡ መንግሥትና የመንግሥት ባለሥልጣናት ራሳቸው ጭምር ሌላው ቢቀር መንግሥን ያሳጣል ብለው እንኳን ሳያጠራጥሩ ስደት ይሉታል፡፡ የመንግሥትን የፖለቲካ አጀንዳ የሚሸከም መልዕክት አክለው ማስተላለፍ ሲፈልጉ ደግሞ ሕገወጥ ስደት ይሉታል፡፡
ለነገሩ አማርኛውም በ‹‹ሬፊውጂና›› እና በ‹‹ማይግራንት›› መካከል በስያሜ ልዩነት ስለማያበጅ የመገናኛ ብዙኃን ራሳቸው ይምታታባቸዋል፡፡ ስለ “IOM” ያውሩ ስለ “UNHCR” አይታወቅም፡፡ በዚህ ረገድ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሚመስል ዕርምጃ ወስዶ ያየሁትና መሰንበቻቸውን ልዩነቱ ላይ አስምሮ ተደጋግሞ የሰማሁት የአማርኛው ቪኦኤ በስደትና በፍልሰት፣ በስደተኛና በፍልሰተኛ መካከል ልዩነት አበጅቶ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡
እንዲህ ያለ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰማና የማይደበቅ ችግር በመጣ ቁጥር ተደጋግሞ የሚሰማው፣ ሙዝዝ ተብሎ የተያዘውና በሊቢያው የሚያዝያ 2007 ዓ.ም. ቁጣ ውስጥ አደባባይ የወጣው የውጭ ጉዞ ጉዳይ፣ ‹‹አገር ውስጥ ሠርቶ መለወጥ›› ሲቻል የሚል አዝማች ያለው የመንግሥት ዜማ ነው፡፡ መንግሥትና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ምክንያት መንግሥትና ፓርቲው የተነካካባቸውና የተሸነፈባቸው የሚመስላቸው ደጋፊዎች፣ እንዲህ ያለ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር በመንግሥት የኢኮኖሚ፣ የዕድገትና የልማት ፖሊሲ ወይም በተከታታይ በሚመዘገበው የዕድገት ውጤት ላይ ተፈጥሮና ታሪክ ከመደብ ጠላት ጋር ተረባርቦ የማይካድ የግፍ ማስረጃ ያቀረበባቸው ስለሚመስላቸው፣ የውጭ ጉዞን ጨርሶ የሚያወግዝ፣ እንዲከለከል የሚያደርግ፣ ከዚህ ጋር የተያያዘውን ሁሉ ለችግሩና ለወንጀሉ ጭምር ካበረከተው አስተዋጽኦና ድርሻ በላይ የሚያወግዝ፣ የሚዝትና የሚረግም መከላከያቸውን በዘመቻና ‹‹በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ›› መልክ ሲለፍፉ እናያለን፡፡
ኢትዮጵያዊ በገፍ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ውጭ የሚጎርፈው የኢሕአዴግን መንግሥት ለማሳጣት አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ የዕድገትና የልማት ፖሊሲ ላይ የሕይወትና የአካል ማስረጃ ለማቅረብ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ያስመዘገበው ባለሁለት አኃዝ ዕድገትም ሙሉ በሙሉ ለማስተባበል አይደለም፡፡
የተለያዩ ጉዳዮች እየተጋገዙ የውጭ ጉዞውን የግፊት ኃይል ሲበዛ ከፍ አድርገውታል፡፡ የመንግሥት ዲስኩርና የሃይማኖት መሪዎች ስብከት ‹‹የአገር ፍቅር ስሜት›› ቅስቀሳ የፈለገውን ቢሉም፣ ግፊቱና ፈተናው ከሚታገሱት በላይ ሆኖ በየቤቱ የአዲስ ዘመን ምኞት ቃል ማሰሪያ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥት የዚህን ችግር አተያዩን ግልጽና የጠራ ማድረግ አለበት፡፡ በተለይም ደግሞ የውጭ አገር የዜጎች ጉዞን የፖሊሲው ውድቀት ማስረጃ ሆኖ ይቀርብብኛል ብሎ እየተደናገረና እየተወናበደ የአገርን አጠቃላይ ችግር ከማየት ወደሚከለከለው ደመነፍሳዊ ራስን የመከላከል ስትራቴጂው መውጣት አለበት፡፡ እናም ኢሕአዴግ ራሱ እንደሚለው ልማት የአገር የህልውና መሠረት መሆኑን እየተገነዘበ፣ በተግባርም እያስገነዘበና እያስመዘገበ ልማቱ የሚያስመዘግበው ዕድገትና ውጤት የሥራ ሥምሪቱን እያስፋፋና እያፋፋመ መሆኑን ከማረጋገጥ ጋር፣ የውጭ ጉዞን አታንሱብኝ ከማለት አባዜው መውጣት አለበት፡፡ ‹‹በአገር ውስጥ ሠርቶ መሻሻል ሲቻል›› ማለት መፈክሩንም ‹‹የደመኛ ጠላቶቹ›› (ወደ ውጭ ሄደው በሚደርስባቸው ችግር ‹‹የሚያሳጡትን››) እና ደጋፊዎቻቸው መምቻ ከማድረግ ተራ ጨዋታ መውጣት አለበት፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው የ2007 ዓ.ም. የሊቢያ ጭፍጨፋም ሆነ ማንኛውም አጋጣሚ ደግሞ በውጭ ጉዞና በሌሎችም አርዕስቶች ላይ (ለምሳሌ አሸባሪነት፣ ሃይማኖት ወዘተ) የሚቀርቡትን አስተያየቶች ከውይይት በላይ ማድረግ የለበትም፡፡ ከውይይት በላይ የሆነ፣ አላናግርም፣ ሐሳብን መግለጽ አልፈቅድም የሚል ምንም ዓይነት የመንግሥትም ሆነ የማንም አቋምና እምነት የለም፡፡ የውጭ ጉዞው አሁን የሊቢያው ጉዳይ በቀረበበት መልክ የሚጠይቀውንና የሚያስከፍለውን የገንዘብ ወጪ እያነሱና እየጣሉ፣ ከፍተኛነቱን እያሳዩ (ይህ የቀበጡ ወይም የደላቸው ሰዎች በገዛ ራሳቸው ያመጡት ችግር ነው ዓይነት) የመንግሥትን አቋምና መከላከያ ብቻ እየወቀጡ ዜና መሥራት፣ የዚህ ተቃራኒ መከራከርያ፣ ከዚህ የተለየ ሐሳብ እንዳይቀርብ መከልከል፣ አገር ሌላው ቀርቶ የጋራ ሐዘን እንዳይኖራት የሚከለክል አለማወቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ የውጭ ጉዞን ራሱን የዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ ዋነኛ ምክንያት ማድረግ፣ በጉዞው ውስጥ የሚከሰከሰውን (ገና ልክና መልኩ ተዘርዝሮ ያልታወቀውን) ገንዘብ አንፃራዊ መጠን እያወሱ (ሲሉ የሰሙትን) የ‹‹ካልጠገቡ አይዘሉ፣ ካልዘለሉ አይሰበሩ›› መከራከሪያና ብያኔ መስጠት፣ በየአቅጣጫው ከኢትዮጵያ አንድ ወረዳ ወይም ዞን እስከ ሊቢያ የባህር ዳር ድረስ ያለውን የውጭ ጉዞ የደላላ መዓት ብቸኛው የወንጀል ድርጊቱ ተካፋይ አድርጎ ማሳየት፣ በሕጋዊው የውጭ ጉዞ ሰንሰለትና ፌርማታ ውስጥ በመላ መንግሥት የተዋጣለት ሥርዓት የዘረጋ ይመስል፣ መደበኛ ያልሆነውን የጉዞ መስመር ብቻ የችግራችን ምንጭ ማድረግ ሕመማችንን የሚያሳይ አካሄድ አይደለም፡፡
የውጭ ጉዞ ሲባል ሁልጊዜም የሚነሳው ይህ ዘፈኖች ሁሉ ተባብረውና ተረባርበው የሚዘምርለት፣ በጅምላ ‹‹ስደት›› የሚባለው ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ለምሳሌ ወደ ውጭ አገር የሚፈልሱት ለ‹‹ስደት›› አይደለም፡፡ በቃሉ ትክክለኛ ትርጉም አገር ወይም የፖለቲካ ሥርዓቱ አላስቆም አላስቀምጥ ብሏቸው፣ ‹‹አሳዷቸው›› አይደለም፡፡ ሲሉ እንደምንሰማው እንደ ቦትስዋና ባሉ አገሮችም በተግባር እንደሚታየው፣ የኢትዮጵያ የሕክምና ባለሙያዎች በውጭ አገር ገበያ ውስጥ ተፈላጊ ናቸው፡፡ እንደዚህ ያለና ከዚህ ዓይነት ፍላጎት የተነሳ የባለሙያ ፍልሰትም በተለይ መንግሥትን ያሳስበዋል፡፡
በዚህም የተነሳ መንግሥት ከባለሙያዎች ጋር ቢያንስ ቢያንስ የሚያሻክር፣ ከመብት ጋር አልገጥም የሚል ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ጀምሮ እስከ የሥራ ውል ይዘት ድረስ የማራዘም የመከላከያ ዕርምጃ ሲወስድ ይታያል፡፡ የክልከላ ዕርምጃውም፣ የዕርምጃውም ዓላማ ግን ከአገር ልማት አጠቃላይ ግብ ጋር አይጣጣምም፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ መፍለሳቸው ማስፈራትም ማሳሰብም የለበትም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሙያተኛ በውጭ በመፈለጉ ተደስተን በተሻለ የችሎታና የሥነ ምግባር ብቃት ገበያውን ለመሙላት፣ እንዲሁም ለማስፋፋት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ፍላጎትም ለመሸፈን የሚችል የሰው ኃይል በየጊዜው ማፍራት፣ ኢትዮጵያ ልትረባረብበት የሚገባ አንድ የልማት ዕቅድ መሆን አለበት፡፡
በአሪቱ ውስጥ ያለውን የባለሙያ ፍላጎት ለመሸፈን የሚችል የውስጥ የሰው ኃይል ፍላጎት ሲባል መታሰብ ያለበት የኢትዮጵያ ዜጋ ወይም የኢትዮጵያ ሕዝብ የውስጥ ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡ ጥራትና ደረጃቸው ከለሙት አገሮች ጋር የተመጣጠኑ የሕክምና ወይም የመዝናኛ አገልግሎቶችን በቀላል ዋጋ ማቅረብ አንዱ የውጭ ምንዛሪ መሳቢያ ነው፡፡
የተሻለ የሥራና የገቢ ዕድል ወዳለበት አገር ሄዶ መሥራትም ነውር የለበትም፡፡ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ አገሮችም በሥራ አጥነት ማስተንፈሻ ይጠቀሙበታል፡፡ ወደ መካከለኛም ምሥራቅ ለሥራ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እዚህ ውስጥ መንግሥት ሥራውን፣ ሥራው ካልሆነው ለይቶ ማወቅ አለበት፡፡ የመንግሥት ሥራ ከውጭ የሥራ ዕድሎች ዕውቀት ጋር ባህልና ሕግ ነክ መረጃዎችና የምክር አገልግሎት ተሟልተው የሚገኙበትን ሕጋዊ መንገዶች ማመቻቸት ነው፡፡
በውጭ በሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንበአግባቡ ለመከላከልና ለመጠየቅ የሚያስችል (እዚህ አገር ቤትም ሆነ በውጭ) ሥርዓት አለመዘርጋትና ለዚህም ዝግጁና ብቁ ሆኖ አለመገኘት፣ አስጊ ወይም ጠንቀኛ ሁኔታዎች ሲኖሩም ከማሳወቅ እስከ ጉዞ ማገድና ዜጎችን እስከመጥራት የሚደርስ ዕርምጃ አለመውሰድ ማስጠየቅ አለበት፡፡
በዚህ ዘርፍ ያለው የመንግሥት ግዴታ ገና ያልተነካ መሆኑን የግል ሥራና ሠራተኛ ኤጀንሲ የሚባለው ሕግ ራሱ የተጓዘበትን ውጣ ውረድና አሁንም ድረስ የታገደ መሆኑን ማየት ብቻ ይበቃል፡፡
2. አሁን ያጋጠመው አረመኔያዊ የወንጀል ድርጊት በተፈጸመበት መልክ ‹‹በጥንቃቄ››ም ቢሆን ያነሳው የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ ሃይማኖትን ከጉዳዩ ጋር ያያያዘው ደግሞ በጭራሽ የውጭ ጉዞ አይደለም፡፡ በ30ዎቹ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን የግፍ አገዳደል ወንጀል በጥንቃቄ ከሚነሳ ሃይማኖት ጋር ያገናኘው አሸባሪነት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይህን ጉዳይ እየፈሩና እየቸሩ ሳይሆን በግልጽና አፍታቶ መጋፈጥ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
‹‹አገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው፤›› ማለት ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ውስጥ የነበረ መዳከር የሌለባቸውን ሁለት መብቶች ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ፣ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ሲጠብቅና ሲፈጠሩም መፍቻ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ቁልፍ የአብሮነት መመርያ ነው፡፡ ዛሬም ይህ መመርያ በዜጎች ግንኙነት ንቃተ ህሊና ውስጥ ያለው ዋልታነት መጠናከር አለበት፡፡ ክርስትናና እስልምና ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ በተቀዳዳሚ ጊዜ ውስጥ የገቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የሃይማኖቶች አገባብ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥንተ አመጣጥ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ይህ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ የመጣ›› የሚለው አባባል ለሁለቱም ሃይማኖቶች ማገልገል ይችላል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያን ከአንድ ሃይማኖት ጋር የማዛመድም ሆነ በአካባቢ ደረጃ ያለን የቋንቋና የሃይማኖት ሥርጭታዊ ክምችትን መሠረት በማድረግ አናሳውን እንደ ባይተዋር የመቁጠር አመለካከት፣ እንዲሁም በቅርቡ የገቡ እምነቶችን ተከባሪነት ከኦርቶዶክስ ክርስትናና ከእስልምና አሳንሶ ማሰብ የተሳሳተና የሚያሳስት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የክርስቲያኖች፣ የሙስሊሞች፣ የሌሎች እምነት ተከታዮችም አገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ የጋራችን እምነት የግል
ከደርግ በፊት ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት ስለነበር እስልምና በ‹‹ክርስትያኗ›› ኢትዮጵያ ውስጥ ውሱን ሥፍራ ያለው እምነት ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ደርግ ሃይማኖትንና መንግሥትን ከመለየት ዘሎ ሃይማኖትን የማፈንና የማዳከም ፖሊሲ ነበረው፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ከደርግ በፊትና በደርግ ጊዜ የነበረውን ችግር ለማስወገድ ሞክሯል፡፡
ነገር ግን የፖለቲካ ድርጅቶች ሃይማኖቶችን በደጋፊ ማሰባሰቢያነት ወይም በማስጠሊያንት ሊገለገሉባቸው መሞከራቸው ገና አልቀረም፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት በ1997 ምርጫ ጊዜ የግል መብቶችን ያጠበቀውን ወገን በመቃረን ኢሕአዴግ ስለቡድን መብት አስፈላጊነት ሲያስረዳ፣ ከብሔር መብት ሌላ ሙስሊሙ ወገን ያገኘውን የእምነት እኩልነት ጠብቆ የማቆየትን ጉዳይ መጠቃቀሱ፣ እንዲሁም የተቃዋሚዎች ወገኖችም ኢሕአዴግ በሙስሊሙ ላይ አደረሰ የሚሉትን በደል መቁጠራቸው ይታወሳል፡፡ ይህን የመሰለ ሃይማኖቶችን ምርኩዝ ያደረጉ ግልጽና ስውር የፕሮፖጋንዳ ቅስቀሳዎች በተለይ በሥልጣን ላይ የተቀመጠውን ፓርቲ ላንዱ ወይም ለሌላው ሃይማኖት ልዩ ተቆርቋሪነት ያለው የሚያስመስል ግንዛቤ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ መንግሥት ለዚህም ሆነ ለዚያ ሃይማኖት ያደላል የሚል አስተሳሰብ እንዳይፈጠርበት ተጠንቅቆ መሥራቱ ለተስሚነቱም ሆነ ለሃይማኖቶቹ ጤናማ ግንኙነት፣ ብሎም ለአገሪቱ ሰላም መሠረታዊ ነው፡፡ አንደኛውና ሃይማኖትን የሚመለከተው አጠቃላይ ጉዳይ ይኼው ነው፡፡
ይህን የሚደግፉ ሌሎች ዝርዝር ነጥቦችም አሉ፡፡ ሃይማኖትን መስበክ መብት ቢሆንም የሌላው መብት የሚነካበትን ወሰን አበክሮ ማወቅና ማክበር ደግሞ የግድ ነው፡፡ አንድ ሰው በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ረግቶ የሚቆየው ከሎጂክ ይልቅ በእምነት ፅናት ነው፡፡ ዛሬ ባለንበት የመቻቻልና የመከባበር ባህል ዝቅተኛነት ደረጃ የሃይማኖት ክርክር መግጠም ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊበልጥ መቻሉን አውቆ መቆጠቡ ይመረጣል፡፡
በእምነት ተቋምም ውስጥ ሆነ በጽሑፍና በሌላ የመገናኛ ዘዴ የሌላውን እምነት እየተቹ እምነትን ማስተማር አደገኛ ትንኮሳ አለበት፡፡ አንድ ሃይማኖት ማስተማር ያለበት ለእምነቱ ምሰሶ በሆኑ በራሱ መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ እንጂ፣ ከሌላው የእምነት መጻሕፍት እየመዘዘ መሆን የለበትም፡፡
የትኛውም ወገን ማንኛውንም እምነት የማረምና የመተቸት መብት የለውም፡፡ እምነቴ ስህተት ነው የሚል ሃይማኖተኛ በዓለም ላይ የለም፡፡ የእኔ ሃይማኖት ልክ ነው ባይነት ግን የሌላውን ልክ ነኝ ባይነት ከማክበር ጋር መጣመር አለበት፡፡
ስለዚህም አሁንም ‹‹አገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው፤›› የሌላውን ሃይማኖት ሳያከብሩ የራስን ማስከበር ያዳግታል፡፡ ሌላም ተጨማሪ መጤን ያለበት ጉዳይ አለ፡፡ ዛሬ፣ ‹‹ሃይማኖት›› የተለያየ ፍላጎት መሸፈኛና ማራመጃ ሆኖ የሚያገለግልበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ የዘንድሮ ሌባ ሳይቀር ሃይማኖት አጥባቂ መስሎ በመቅረብ ሙሉ ለሙሉ እስኪታመን ድረስ ጠብቆ በገፍና በእጅጉ ማጭበርበር አምጥቷል፡፡
በዓለም ውስጥ የተደራጀ ቡድንን ጥቅም ለማሟላትና ፖለቲካዊ ጥላቻንና በቀልን ለመወጣት፣ ሃይማኖት ሲያገለግል ብሎም የአዕምሮ ቀውሶች መጫወቻ ሲሆን ማየት አዲስ አይደለም፡፡
በተለያዩ ጊዜያት እንደ ክርስቶስ ሞተን እንነሳለን በማለት ራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን በመርዝ የጨረሱ ወፈፌዎች ተከስተዋል፡፡ በኡጋንዳ ውስጥ በሕዝብ ላይ ግፍ ሲውል፣ የቆየው ሎርድ ሬዚስታንስ አርሚ (LRA) ራሱን የጌታ አምላክ ሠራዊት ብሎ የሰየመና ለኦሪት ሥርዓት ቆሜያለሁ ባይ ሆኖ ነው፡፡
በእስልምናም በኩል ታሪክን ወደኋለኛው ዘመን ሊመልሱ የሚሞክሩና የሚጥሩ አሉ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በቅርቡ ሊቢያ ውስጥ የተፈጸመው ወንጀል ለእስልምና እምነት ከመቆም ጋር ፊጽሞ የማይዛመድ የታመመ ተግባር ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ለእምነቱ ከመገዛትም ሆነ ከመቆም ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ይልቁንም የሚቃረን አደጋና ጥቃት ሲያጋጥም፣ በስሙ የተነገደበት የትኛውም ሃይማኖት ተከታዮች እንደ ‹‹ተከሳሽ›› የሚቆጠሩበት ይቅርታ የመጠየቅ ያህል ለተለያዩ ሥነ ሥርዓታዊ ግርግር የሚዳረጉበት አሠራር የትም ቦታ ጤናማ አይደለም፡፡
እስካሁን ያሳነው በመንግሥት በኩል አለ ያልነውን ነው፡፡ የመንግሥት ተቃዋሚዎችም ከደሙ ንፁህ አይደሉም፡፡ አንዳንዴ ሲታሰብ የሚያስደነግጥ ነገር የሚደገስ መሆኑ ይሸታል፡፡ ሐዘን በተቀመጠች ኢትዮጵያ ‹‹ድንኳን›› ውስጥ ድንገት ከሰላሳ በላይ ሰው ሞቶ፣ ይህን ያህል ሕዝብ አልቆ በዚህም መንግሥት ቢሳጣ፣ ቢከሰስና ቢወገዝ ተብሎ ለዚህ ውጤት የሚከናወን ሥራ ያለ ይመስላል፡፡ ይህ የጤነኛ ፖለቲካ አካሄድ አይደለም፡፡ ጨርሶ ፖለቲካም አይሆንም፡፡ ፖለቲካ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከማውረድና ከመተካት በላይና ከዚህ የተለየ ዓላማና ግብ አለው፡፡ መንግሥትን መቃወምና ማሳጣት ወንጀልም ነውርም አይደለም፡፡ መቃወምንና ማሳጣትን በተለይም በሕዝብ ሕይወትና ደም ዋጋ፣ ዓላማና ግብ ማድረግ ግን በጭራሽ ፖለቲካ አይደለም፡፡