Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

 • June 2023
  M T W T F S S
   1234
  567891011
  12131415161718
  19202122232425
  2627282930  
 • Archives

 • Categories

 • Recent Posts

Posts Tagged ‘መጽሕፍ ቅዱስ’

ገነትን ፍለጋ

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on September 7, 2018

(በዶ/ር ሐዲስ ትኩነህ)

መግብያ

የቀደሙ አባቶች ገዳማውያን ገነትን ፍለጋ የፍየል ሌጦ ለብሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ድንጊያ ተንተርሰው በረሀ ለበረሀ ተንከራተዋል፡፡ ሰማዕታትም ገነትን ፍለጋ ተሰደዋል ፣ እንደእንጨት ተፈልጠው፣ እንደአትክልት ተከትፈው ደማቸውን አፍሰዋል፡፡ ከቀደሙ አባቶች መካከል እግዚአቤሔርን አገልግለው በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ወደ ገነት ተነጥቀው በገነት የሚኖሩ አሉ (ኄኖክ ፣ ኤልያስና ዕዝራ) (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ 212 ፣ ዕብ 115 ፣ ኄኖክ 41161)፡፡ አንዳዶቹ አባቶች ወደገነት ከተነጠቁ በኋላ የሀገሪቱን መልካምነት አይተው የተመለሱ ይገኙባቸዋል (2 ቆሮ 124)፡፡ ከገነትም ከተመለሱ በኋላ በፊት ይሠሩት ከነበረው መልካም ሥራ ይበልጥ ለመሥራት ይነሣሳሉ፡፡ በመሆኑም ይራባሉ፣ ይጠማሉ፣ ዓለም ሊሸከመው የማይችለውን ከባድ ሸክም ሁሉ ይሽከማሉ፡፡ ከሞትም በኋላ በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ወደአዩት ሀገር በክብር ይሄዳሉ፡፡ አንዳዶቹም አባቶች በሃማኖት ጸንተው የብዙ ገድል ባለቤቶች ይሆኑና በዕረፍታቸው ጊዜ ወደዚሁ ሀገር ይገባሉ፡፡

ገነት ማለት ምን ማለት ነው? ገነት ማለት የተክል ቦታ ፣ ብዙ ዛፍና ዕንጨት ያለበት ፣ ሽቱና ቅመማ ቅመም የሚበቅለበት ፣ ውሀ የሚገባበት የተከለለ ቦታ ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ 313)፡፡ ከዚህም ሌላ መጻሕፍት ስለገነት ብዙ ስያሜ ሰጥተዋት እናጋኛለን፡፡ ይህም ገነት ዕፁት (መሐ 412) ፣ ገነተ አቅማሕ (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ 219) ፣ ገነት ርውይት (በውሀ የረካች) (ሲራ 2430)፣ ገነተ ጽጌ (አባ ገብረ ማርያም) ፣ ገነተ ተድላ (አክሲማሮስ ገጽ 156)፣ ገነተ ትፍሥሕት (አክሲማሮስ ገጽ 157)፣ ገነተ እግዚእ ((አሪ ዘፍ 1310) ፣ ገነተ ኅሩያን ደቂቅ (ደራሲ) ፣ ምድረ ገነት (ድጓ ገጽ 407 ፣ ዕዝ ሱቱ 42) ፣ ኤዶም ገነት (ድርሳነ ማሕየዊ ገጽ 110) ፣ ሰማይ ሣልሲት (2 ቆሮ 12:2)፡፡ ገነት ኤዶም (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ 212)፡፡ የስሟ ትርጓሜ ይህ ይሁን እንጅ ገነት መልካም የሠሩ የሚኖሩባት ፣ ክፉ የሠሩ የሚከለከሉባት መንፈሳዊ ሀገር ናት፡፡

ገነት ዬትትገኛለች?

ገነት እንደመጽሐፈ ቀሌምንጦስ አገላለጽ ከቀራንዮ በላይ በአየር ላይ ትገኛለች፡፡ ገነት ከቀራንዮ በላይ ትገኛለች ስንል ከቀራንዮ ጋር የተያያዘች ሳትሆን በህዋ ላይ በመንሳፈፍ ያለችና መሬትነት ያላት ሀገር ናት (አክሲማሮስ ገጽ 73፣መጽሐፈ ቀሌምንጦስ)፡፡ ይህችም ገነት የመጀመሪያው ሰው አዳም በቀራንዮ በማእከለ ምድር ከተፈጠረና ለእንስሳት ሁሉ ስም ካወጣ በኋላ ሊኖርባት የተሰጠችው ቦታ ናት (ኩፋ 49 ፣ ዕዝ ሱቱ 16 መቃ ቀዳ 2714 ፣ አቡሻክር ፣ ጊዮርጊስ ወልደ ሐሚድ)፡፡ አዳም በምድር መካከል ተፈጠረ የሚለው ቃል የሚያስረዳው በዚህ በቀራንዮ ላይ አራቱ የዓለም ክፍሎች የሚገናኙ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ብዙ ነገር ተከናውኖበታል፡፡ ይህም አዳም ወደገነት በሚገባበት ዕለት እንስሳትና መላእክት ተሰባስውበታል፡፡ የኖኅ ልጅ ሤም የአዳም አባታችንን ዐፅም ቀብሮበታል፡፡ መልከጼዴቅ የልዑል እግዚበሔር ካህን ሆኖ ተቀምጦበታል፡፡ አብርሃም አባታችን ይስሐቅ ልጁን ለአግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦበታል፡፡ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ የሰው ዘርእ ለማዳን ተሰቅሎበታል (መዝ 7312)፡፡ ገነት አራት አቅጫዎችና ሦስት መንገዶች ያሏት ሀገር ናት፡፡ አንደኛው መንገድ በጎልጎታ፣ ሁለተኛው በደብረ ዘይት ፣ ሦሰተኛው በደብረ ሲና ላይ ነው፡፡ በገነት ክረምትና በጋ አይፈራረቁባትም፡፡ በውስጧም የሚገኙ እንጨቶች ያበራሉ (ኄኖክ 821)፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ዓለም ያሉ ረኀብ ፣ ጥም ፣ ሕማም ፣ ሞት ፣ ማጣት ማግኘት የለባትም፡፡ ገነት የምስጋና ፣ የደስታ ፣ የእውነትና የቅድስና ቦታ ብቻ ናት (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ)፡፡

ገነት በመጽሕፍ ቅዱስ

በመጽሐፍ ቅዱስ ኤድን የሚለው ቃል ከ17 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ከጥቅሶቹም ውስጥ አንዳዶቹ ኤድን ስለሚባል ሀገር የሚገልጹ ሲሆን አንዳዶቹ በኤድን ስለአለች የተክል ቦታ ይገልጻሉ፡፡ ኤድን የቃሉ ትርጉም ደስታ ፣ ለም ቦታ ፣ መልካም መዓዛ ያለበት አካባቢና ሰፊ ሜዳ ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ገነት ያለችና የምትኖር ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ስለገነት ስም ፣በውስጧ ስለሚገኙ ዕፀዋትና ወንዞች ፣ አዳምና ሔዋን ፣ ገነትን ስለሚጠብቅ መልአክ (ኪሩብ/ሱራፊ) ይገልጻል፡፡ ይህም እንደሚከተለው ይገለጻል፣ አንቺ የገነት የሕይወት ውሃ ጉድጓድ ከሊባኖስ የሚፈስ ወንዝ ነሽ (መኃል 415)፡፡ እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በኤድን ገነትን ተከለ፤ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው (ኦሪ ዘፍ 28)፡፡ ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ በኤድን ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ከአራት ይከፈል ነበረ (ኦሪ ዘፍ 210)፡፡ በእግዚአብሔር ገነት በኤድን ነበርህ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር (ሕዝ 2813)። በክብርና በታላቅነት በኤድን ዛፎች መካከል ማንን መስለሃል? ነገር ግን ከኤድን ዛፎች ጋር ወደ ታችኛው ምድር ያወርዱሃል (ሕዝ 3118)፡፡ አዳምንም አስወጣው፤ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በኤድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ (ኦሪ ዘፍ 324)። ኢየሱስም፦ “እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” (ሉቃ 2343)፡፡

እነዚህ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የገነትን መኖርና የአዳምን ከገነት መሰደድ ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ገነት የምትገኝበትን ኤድን ዬት አካባቢ እንደሆነች በግልጽ አያመለክትም፡፡ ነገር ግን መጽሐፈ ኩፋሌ ለእግዚአብሔር ሦስት የተቀደሱ ቦታዎች እንዳሉት ይገልጻል (ኩፋ 532)፡፡ እነዚህም ቦታዎች፣ አንደኛዋ ደብረ ሲና ፣ ሁለተኛዋ ደብረ ጽዮን ፣ ሦስተኛዋ ገነት እንደሆኑና ሦስቱንም አንጻራዊ አድርጎ ፈጥሯቸዋል ይላል (ኩፋ 98)፡፡ አንጻራዊ አድርጎ ፈጥሯቸዋል የሚለውን ቃል ስንመለከት ደብረ ሲና በምዕራብ ፣ ደብረ ጽዮን በመካከል ፣ ገነት በምሥራቅ እንደሆኑ እንረዳለን፡፡ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምልከታ እንደሚያሳየው ገነት ከደብረ ጽዮን በምሥራቅ በኩል ባለው አካባቢ ትገኛለች ማለት ነው፡፡ ገነት ከከነዓን ምድር በስተምሥራቅ ሁና ከደብር ቅዱስ ጋር ጎረቤት መሆኗ ነው፡፡

ደብር ቅዱስ

ደብር ቅዱስ (በአተ መዛግብት) (መጥርዮን) አዳምና ሔዋን ከገነት ከተሰደዱ በኋላ ይኖሩበት የነበረ ቦታ ነው (አቡሻክር)፡፡ ይህ ተራራ የገነት አጎራባች ሲሆን በዚህ ቦታ ይኖሩ የነበሩ አባቶች ሁሉ ገነትን አሻግረው ይመለከቷት ነበር፡፡ ይህም ማለት ገነት ለደብር ቅዱስ የቀረበች ቦታ ናት ማለት ነው፡፡ ደብር ቅዱስ በአሁኑ ጊዜ ኤርሞን (ሄርሞን) የሚባለው ተራራ ነው፡፡ ይህም ተራራ በ3ቱ ሀገሮች በእስራኤል ፣ በሶርያና በሊባኖስ መካከል የሚገኝ በበረዶ የተሸፈነ ተራራ ነው፡፡ ኤርሞን ወይም ሄርሞን ዋሻ የበዛበት ተራራ ሲሆን ትርጓሜው ደብረ መሐላ (የመሐላ ተራራ) ማለት ነው፡፡ የዚህም ተራራ ጫፍ ሰርዲን ይባላል፡፡ በዚህ በሰርዲን ጫፍ ላይ የሴት ልጆች እስከ ኖኅ ዘመን ድረስ ይኖሩበት ነበር (የመጽሐፈ ኅኖክ አንድምታ)፡፡ እነዚህም የሴት ልጆች ወደደብር ቅዱስ ተራራ ግርጌ ወደሚገኝ ምድረ ፋይድ ወደተባለ ቦታ ተጠቃለው ወርዋል (አቡሳክር ፣ ጊዮርጊስ ወልደ ሐሚድ)፡፡ ምድረ ፋይድ ማለት ምድረ ኀሣር ወመርገም ፣ ምድረ ድንፄ ወረዓድ ማለት ነው (የወንጌል አንድምታ ገጽ 19)፡፡ ይህም መከራ የሚፈራረቅበት ፣ ቀይና ጥቁር የሚወለድበት ፣ ሀብታምና ድሀ የሚኖርበት ቦታ ማለት ነው፡፡

የገነት ወንዞች

አራቱ የገነት ወንዞችን በተመለከተ የዘመናዊ ጸሐፊዎች የተለያየ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህም የሐሳብ መለያየት ያደረሳቸው የወንዞቹ ተራርቆ መገኘትና የፍሰት አቅጣጫቸው ነው፡፡ አንደኛው ኤፍራጥስ የተባለው ወንዝ ከቱርክ ተራራማ ሥፍራ ፈልቆ ከላይ የቱርክንና የሦርያን ደምበር ፣ ከታች የሦርያንና የኢራቅን ደምበር በማካለል ከጤግሮስ ወንዝ ጋር ተቀላቅሎ ወደፋርስ ባሕረሰላጤ ይገባል፡፡ የጤግሮስም ወንዝ ከቱርክ ተራራማ ቦታ ፈልቆ በባቢሎን (ኢራቅ) አድርጎ በመጨረሻ ከኤፍራጥስ ወንዝ ጋር በመደባለቅ ወደባሕረሰላጤው ይገባል፡፡ ኤፌሶን የታባለው ወንዝ በአሁኑ ጊዜ ውሀ ይዞ የሚፈስ ወንዝ ሆኖ አልተገኝም፡፡ ሆኖም በወንዙ ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎች እንደሚሉት ይህ ወንዝ ከመዲና አጠግብ ከሚገኝ ሂጃዝ ከሚባል ተራራ ተነሥቶ የዐረብያን ምድር አቋርጦ በኵየት ሰሜን ምሥራቅ አድርጎ ወደባሕረሰላጤው ይገባ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ድሮ ይሄድበት የነበረውን ደረቅ ወንዝ በማጥናት መጽሐፍ ቅዱስ ኤፌሶን የኤውላጥን ምድር ይከባል ከሚለው ሐሳብ ጋር ለማጣጣም ጥረት አድርገዋል፡፡ ግዮን የተባለው ወንዝ የሀገራችን ትልቁ ወንዝ ነው፡፡ ይህም ወንዝ በመጽሐፍ ቅዱስ የኢዮትዮጵን ምድር ይከባል (ኦሪ ዘፍ 213) እንደተባለው በርካታ የሀገራችንን አካባቢዎች በማዳረስ የሱዳንና የግብፅ ሀገሮች አቋርጦ ሚዲትራንያን ባሕር የሚገባ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሊቃውንት አራቱ ወንዞች በህልውናቸው እንዳሉና እያንዳደቸው ልዩ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይጽፋሉ፡፡ ይህም መልካም ሥራ የሠሩ ምእመናን ወንዞችን በርስትነት እንደሚወርሷቸው ነው፡፡ አናደኛው ወንዝ ኤፌሶን ፈለገ ሐሊብ ነው፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ሁለተኛው ወንዝ ግዮን ፈለገ ወይን ነው፤ ርስትነቱም መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወታቸውን የሚያሳልፉ ሰዎች ርስት ነው (በጾም ፣ በምጽዋትና በጸሎት የሚኖሩ ምእመናን ይውርሱታል)፡፡ ሦስተኛው ወንዝ ጤግሮስ ፈለገ መዓር ነው፤ ርስትነቱም ነገርን የሚታገሡ ሰዎች ነው (የወንድማቸውን ጥላቻ ታግሠው ፣ ክፉውን ነገር በመልካም ነገር ለውጠው የሚኖሩ ሰዎች ይወርሱታል)፡፡ አራተኛው ወንዝ ኤፍራጥስ ፈለገ ዘይት ነው፤ ርሰትነቱም ደማቸውን ያፈሰሱ ሰማዕታተ ክርስቶስ ርስት ነው (ስለቤተ ክርስቲያን ደማቸውን ያፈሰሱ ሰማዕታት ይወርሱታል) (የወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ገጽ 52)፡፡

ገነት በዘመናዊ ጸሐፊዎች

የዘመናዊ ጸሐፊዎች ገነትን በምድር የነበረችና በማየ አይኅ ጊዜ የጠፋች ሀገር ያደርጓታል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 241)፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኤድን የሚባለው ሀገር የመሶፓታሚያና የአካባቢው አገሮችን (አሦር ፣ አካድ ፣ ባቢሎን (ኢራቅ)ና ፋርስ (ኢራን) ያጠቃልላል ይላሉ፡፡ አንዳዶቹ ኤድን ገነት በደቡብ መሶፓታሚያ ማለትም በደቡብ ኢራቅና ኢራን ደንበር የጤግሮስና የኤፍራጥስ ወንዞች ወደባሕረሰላጤው ከሚገቡት ላይ ነበረች ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች ኤድንን በመካከል ያደርጉና በሰሜን አርመንን ፣ በሰሜን ምሥራቅ አዘርባይጃንን ፣ በሰሜን ምዕራብ ቱርክን ፣ በምሥራቅ የካስፒያን ባሕርን ፣ በምዕራብ ሦርያን፣ በደቡብ ምዕራብ ኢራቅን፣ በደቡብ ምሥራቅ ኢራንን አድርገው የኤድንን የድሮ ካርታ ያስቀምጣሉ፡፡ አንዳዶቹ ጸሐፊዎች ትክከለኛ የገነት ቦታ ሊባኖስ የሚባለው ሀገር ነው ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውም ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለጢሮስና ስለኤድን ገነት የተናገረው የትንቢት ቃል ነው (ሕዝ 28:11-19)፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎችም ሁለት አይነት ገነቶች እንዳሉ ይገልጻሉ (አንዷ ምድራዊት ፣ ሁለተኛዋ ሰማይዊት)፡፡ ምድራዊቷ ገነት አዳምና ሔዋን የነበሩባት የዛሬዋ መሶፓታሚያ እንደሆነች ያምናሉ፡፡ ሰማያዊቷ ገነት የነፍሳት ማደሪያና ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ የነፍሳት መቆያ ሀገር እንደሆነች ጽፈዋል (ሐና ማርቆስ (1996 ገጽ 41-42)፡፡

የቤተ ክርስቲያን ምንጮችንና የዘመናዊ ምንጮችን ስንመለከት የተራራቀ ሐሳብ አላቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ምንጮች እንደሚያስሩዱት ገነት ልዕልት ናት (ከፍ ያለች)፤ ምድርም ዝቅ ያለች ናት (ሕዝ 3118) ፣ ሥውርና የንጹሓን መኖሪያ ፣ የነፍሳት ማደሪያ ናት ይላሉ፡፡ በተጨማሪም በዚህ ዓለም ሰዎች ዐይን መታየት አትችልም የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው፡፡ በውስጧ ስለሚገኙት ወንዞች ሲናገሩ ወንዞቹ የገነትን ዕፀዋት ካጠጡ በኋላ ወደዚህ ዓለም መጥጠው የዓለምን አካቢቢዎች ያጠጣሉ ይላሉ፡፡

ገነት በቅዱስ ያሬድ አስተምህሮት

በቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ ገነት ያለችና የምትኖር ፣ የንጹሓን ማደሪያ ናት፡፡ ቅዱሳን ሰዎች በሩቅ ሁነው እንደሚመለከቷትና አገራቸው እንደሆነች እንደሚገነዘቡ ይገልጻል፡፡ ይህም፣እምርኁቅስ ርእይዋ ወተአምኅዋ ወአእመሩ ከመ ሀገሮሙ ይእቲ ገነት ይእቲ ነቅዐ ገነት አዘቅተ ማየ ሕይወት ማኅደር ለንጹሓን (ከሩቅ ሁነው አዩአት አይተውም ሰላም አሏት አገራቸውም እንደሆች አወቁ ገነት ናት የሕይወት ምንጭ ናት የንጹሓን ማደሪያ ናት) (ጾመ ድጓ ገጽ 110)፡፡ የገነት ምድር አፈጣጠርንም ሲያስረዳ ፣ እምሰማይ አውርደ ምድረ ገነት ዘሰይሰቅያ ለምድር በቃለ ሰላም (በፍቅር ምድርን የሚያጠጣት አምላክ የገነትን ምድር ከሰማይ አውረደ (ድጓ ገጽ 407)፡፡ አዳም በገነት ከኖረ በኀላ ከፈጣሪው ጋር በመጣላቱ ከገነት በተሰደደ ገዜ እንዳዘነ ፣ እንደተከዘና ንስሓ እንደገባና በኋላም ወደገነት እንደተመለሰ ሲገልጽ፣ ተማኅለለ አዳም ቀዳሜ ኵሉ ፍጥረት ወተነሢሖ ገብዐ ውስተ ገነት (የፍጥረት ሁሉ መጀመሪያ አዳም ምህላ ይዞ ንስሓም ገብቶ ወደ ገነት ተመለሰ) ብሏል (ድጓ ገጽ 420)፡፡

እግዚአብሔር ለወዳጆቹ በገነት መልካም ነገር እንደሚያደርጋለችው ሲጽፍ፣ ዘዐይን ኢርእየ ወእዝን ኢሰምዐ ዘአስተዳለወ ለእለ ያፈቅርዎ ኀበ አልቦ ደዌ ወአልቦ ሐማም ኀበ ኢመውቱ እምዝ ዳግመ ገነት ተርኅወ አክሊል ተደለወ ፍኖት ረትዐ ወፃማ ኀለፈ (እግዚአብሔር ለሚውዳቸው ያዘጋጀው ዐይን ያላየው ጀሮ ያልሰማው ነው ፣ ደዌ የሌለበት ሕማምም የሌለበት ነው ፣ ዳግመኛ የማይሞቱበት ነው ፣ ገነት ተከፈተ ፣ አክሊል ተዘጋጀ ፣ መንገድ ተጠረገ ፣ ድካምም አለፈ (ድጓ ገጽ 101) ብሏል፡፡ ገነት በዚህ ዓለም ከሚገኙ ተራሮች ከፍ አንደምትልና በርቀት የምትታይ መሆኗን ሲገልጽ፣እንተ ታስተርኢ እምአርስተ አድባር ርኁቅ ጻድቃን ኪያሃ አብደሩ እምወርቅ ሀገረ ክርስቶስ ሐዳስ ንድቅ ወበውስቴታ የኀድር ጽድቅ (ከታራሮች በላይ ከርቀት የምትታይ ጻድቃን ከወርቅ ይልቅ እሷን ወደዱ ፣ አዲስ ሕንፃ የክርስቶስ ሀገር ናት፤ በውስጧም እውነት ያድራል) ብሏል፡፡ ገነት በናግራን (ዐረብያ) አካባቢ እንደምትገኝ ሲገልጽ፣በሐኪ ኦ ዐባይ ሀገር ሀገረ ናግራን ሀገረ ነጐድጓድ ሀገረ እግዚአብሔር እንተ ተሰመይኪ ገነተ (አንች ትልቅ ሀገር የነጐድጓድ ሀገር ፣ የእግዚአሔር ሀገር ፣ ገነት ተብለሽ የተጠራሽ ናግራን (ናጅራን) ሆይ ሰላምታ ይገባሻል) ብሏል፡፡ ከዚህ ላይ እንተ ተሰመይኪ ገነተ የሚለው ሐረግ ገነት በናግራን አካባቢ መሆኗን ያመለክታል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በገነት ስለሚገኙ አራቱ ወንዞች ሲጽፍ፣ሀገር ቅድስት ሀገሩ ለንጉሥ ዐቢይ አፍላገ ሕይወት በየማና ወአፍላገ ሕይወት በፀጋማ ይውኅዝ ሐሊብ ወመዓር ውሉደ ሰላም የዋሃን ይበውኡ ውስቴታ (የገናና ንጉሥ ሀገር ልዩ ናት ፣ የሕይወት ወንዞች በቀኟና በግራዋ ናቸው ፣ በውስጧም ወተትና መዓር ይፍሳል ፣ የሰላም ልጆች የዋሃን ከውስጧ ይገባሉ (ድጓ ገጽ 140) ብሏል፡፡ ገነት የዕረፍት ቦታና የቅዱሳን ነፍሳት ማረፊያ እንደሆነችም ሲገልጽ ፣እስመ ለክሙ ተርኅወ ገነት ወተተክለ ዕፀ ሕይወት ኀበ ማየ ዕረፍት ውስተ ገነተ ትፍሥሕት ህየ ይበውኡ ነፍሳቲሆሙ ለጻድቃን (ገነት ተከፈተላችሁ፣ የደስታ ቦታ ከምትሆን ከገነትም የሕይወት ዛፍ ተተከለላችሁ እኮ) (ድጓ ገጽ 109) ባሏል፡፡

የገነት መዘጋትና መከፈት

አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠበቁ ገነት ተዘግታ ስትኖር በጌታችን ሞትና ትንሣኤ መከፈቷ የሁሉም ክርስቲያን እምነት ነው፡፡ በመሆኑም የገነትን መዘጋትና መከፈት ፣ የአዳምን ወደቀደመ ቦታው መመለስ የሚገልጹ ብዙ ድርሳናት ተጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም ጥቂቶቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል ፣ ፈቀደ እግዚእ ያግዕዞ ለአዳም ኅዙነ ወትኩዘ ልብ ወያግብኦ ኀበ ዘትካት መንበሩ (ጌታ ልቡ ያዘነና የተከዘ አዳምን ነጻ ያወጣው ዘንድና ወደቀድሞው ቦታው ይመልሰው ዘንድ ወደደ)፡፡ ተፈሥሒ ኦ ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት እስመ በኀቤኪ ተወልደ ክርስቶስ ዳግማይ አዳም ከመ ያግብኦ ለአዳም ቀዳሚ ብእሲ እምድር ውስተ ገነት (የነቢያት አገራቸው ቤተ ልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ ሁለተኛው አዳም ክርስቶስ ከአንች ዘንድ ተወልዷልና የመጀመሪያው ሰው አዳምን ከምድር ወደገነት ይምልሰው ዘንድ)፡፡ በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ (በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ ዳግመኛ በድንግል ማርያም ተከፈተልን)፡፡ ወገብረ ሰላመ ማእከሌነ በመስቀሉ ወበትንሣኤሁ ቅድስት አግብኦ ለብእሰ ዳግመ ውስተ ገነት (ለእኛም እርግማን አጠፋልን፤ በመካከላችንም ሁኖ በመስቀሉ አስታረቀን፤ በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው) (ቅዱስ ኤፍሬም)፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አመ ተለዐልከ እምድኅረ ፄዋ ለገነተ ጽድቅ ዘእደ ሱራፊ ዐፀዋ ቤዛ ኀጥኣን ኲሎሙ ደምከ አርኀዋ (ኢየሱስ ክርስቶስ ከምርኮ በኋላ ወደላይ ከፍ ከፍ ባልህ ጊዜ የኀጥኣን ሁሉ መድኃኒት ደምህ የሱራፊ እጅ የዘጋትን ገነት ከፈታት) (አባ ዘሐዋርያት)፡፡ወበውእቱ ደመ ርግዘቱ አርኀወ አናቅጸ ገነት ፫ተ ዘተዐፅዉ በእደ ኪሩቤል ወሱራፌል ዘቦሙ ሰይፈ እሳት ወኲይናተ እሳት ወበትረ እሳት (በዚህም በመወጋቱ በፈሰሰው ደም የእሳት ጦርና የእሳት ሰይፍ በያዙ በኪሩቤልና በሱራፌል እጅ የተዘጉ ሦስቱን የገነት በሮች ከፈተልን (ድርሳነ ማኅየዊ ገጽ 110 ፣ ሃይ አበ ሳዊሮስ ገጽ 339)፡፡ በመስቀሉ አርኀወ ገነተ (በመስቀሉ ገነትን ከፈተ) (ጾመ ድጓ ገጽ 73)፡፡

ሁሉም የቀረቡት ማስረጃዎች የሚያሳዩት ገነት በአዳም ጥፋት ምክንያት ተዘግታ ከኖረች በኋላ በክርስቶስ መስቀል ዳግመኛ መከፈቷን ነው፡፡

ማጠቃለያ

ገነት ዬት ትገኛለች የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በዙ ምንጮችን ለማየት ሞክሯል፡፡ ከምንጮችም ስለገነት አራት አይነት ሐሳቦች እንዳሉ ተመልክቷል፡፡ አንደኛው አይነት ሐሳብ ገነት ከመሬት በላይ በአየር ላይ ያለች ሀገር ሁና ከመሬት በጣም የራቀች እንደሆነች ይገልጻል፡፡ ሁለተኛው ሐሳብ ገነት በመሬት ላይ ነበረች ነገር ግን በማየ አይ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ ሰማይ አሳርጓታል የሚል ነው፡፡ ሦስተኛው ሐሳብ ገነት በማየ አይኅ ጊዜ እንደጠፋችና የነበረችበትም አካባቢ በመሶፓታሚያ አንደነበረና በአሁን ጊዜ ሀገሩ በሌላ ስም እንደሚጠራ የሚስረዳ ነው፡፡ አራተኛው ገነት ከመሬት ሁና ነገር ግን ከፍ ካለ አካባቢ ትገኛለች፡፡ ከፍ ባለ ቦታም በመገኘቷ ሰማይ ትባላለች የሚል ሆኖ ይገኛል፡፡ ገነት በሰማይ ናት ለሚለው ጥያቄ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ሲመልስ ገነት በሰማይ ያለች ብትሆን ኖሮ መልአኩ ለጥበቃ ባልተሾመ ነበር ብሏል፡፡ ምክያቱም ሰው ወደሰማይ መውጣት ባለመቻሉ ነው(መጽሐፈ ምሥጢር)፡፡ የቅዱስ ያሬድም ድርሰት ገነት ከተራሮች በላይ በርቀት እንደምትታይና ጻድቃን እርሷን ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ይገልጻል፡፡ ኄኖክም የገነትን አቅጣጫ ሲያመለክት፣ ወደኤርትራ ባሕር ሄድሁ፤ ከዚያም የራቅሁ ሆንሁ፤ ዙጡኤል በሚባል መልአክ በላይ አልፌ ሄድሁ፤ በቸርነቱም ወደምትወረስ ገነት መጣሁ ብሏል(ኄኖ 819-22)፡፡

የገነት መገኛ ግልጽ ባይሆንም በርካታ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ገነት ከሰማይ ሳትሆን ክምድር ላይ ናት የሚለውን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤም አላማ የተዘጋች ገነትን ለመከፈትና አዳምን ወደቀደመ ቦታው ለመመለስ በመሆኑ ገነት በማየ አይኅ ጠፍታለች የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ሰለዚህ ስለገነት መመራመር የሚፈልግ ሁሉ ገነት እግዚአብሔር በሥዉር ያስቀመጣትና ከመታየት የሠወራት ሀገር መሆኗን ተቀብሎ እንደቅዱሳን ሰዎች መልካም ሥራ በመሥራትና ከክፉ ነገር በመራቅ ገነትን መውረስ እንደሚቻል ማመኑ የተሻለ ይሆናል፡፡

ምንጭ

______

Posted in Ethiopia, Faith | Tagged: , , , , , , , , , | 1 Comment »

 
%d bloggers like this: