[መጽሐፈ ነገሥት ካልዕ። – ምዕራፍ 9]
1፤ ነቢዩም ኤልሳዕ ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው። ወገብህን ታጥቀህ ይህን የዘይት ማሰሮ በእጅህ ያዝ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድም ሂድ።
2፤ በዚያም በደረስህ ጊዜ የናሜሲን ልጅ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ታገኘዋለህ፤ ገብተህም ከወንድሞቹ መካከል አስነሣው፥ ወደ ጓዳም አግባው።
3፤ የዘይቱንም ማሰሮ ይዘህ በራሱ ላይ አፍስሰውና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ በለው፤ በሩንም ከፍተህ ሽሽ፥ አትዘግይም።
4፤ እንዲሁም ጕልማሳው ነቢይ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ።
5፤ በገባም ጊዜ፥ እነሆ፥ የሠራዊት አለቆች ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም። አለቃ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ነገር አለኝ አለ። ኢዩም። ከማንኛችን ጋር ነው? አለ። እርሱም። አለቃ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ነው አለ።
6፤ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ገባ፤ ዘይቱንም በራሱ ላይ አፍስሶ እንዲህ አለው። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ።
7፤ የባሪያዎቼን የነቢያትን ደም፥ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ።
8፤ የአክዓብም ቤት ሁሉ ይጠፋል፤ በእስራኤልም ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ ከአክዓብ አጠፋለሁ።
9፤ የአክዓብንም ቤት እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፥ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ።
10፤ ኤልዛቤልንም በኢይዝራኤል እርሻ ውሾች ይበሉአታል፥ የሚቀብራትም አታገኝም። በሩንም ከፍቶ ሸሸ።