መጥምቁ ዮሐንስን የምናከብረው ከስጋና ከደም ጋር ስለተጋደለ አይደለም
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on September 12, 2022
😇 የቅዱስ ዮሐንስ ክብር እና መዓርጋት
ቅዱስ ዮሐንስ ክብሩ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ የክብሩ ምስክሮችም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ናቸው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል የመጥምቁን ክብር ተናግሯል፡፡
«ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጥታችኋል? ከነፋስ የተነሣ የሚወዛወዛውን ሸንበቆ ነው? ወይስ ምን ልታዩ መጥታችኋል ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን ነውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የሚለብሱማ በነገሥታት ቤት አሉ? ምን ልታዩ መጥታችኋል ነቢይ ነውን? አዎን እርሱ ከነቢያት እጅግ ይበልጣል፤ እነሆ በፊትህ መንገድህን የሚጠርግ መልእክተኛዬን እልካለሁ ተብሎ ስለ እርሱ የተጻፈለት ይህ ነውና፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም» [ማቴ.፲፩÷፯፡፲፩]
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም እንዲህ ሲል ክብሩን ተናግሮለታል፡– «እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናል» [ሉቃ.፩÷፲፭]
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ «የቅዱስ ዮሐንስ ክብር እና ከፍ ከፍ ማለት ምንጮች ሁለት ናቸው፡፡» ይላሉ፡፡
፩. በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ስለሆነ
ከመጥምቁ ዮሐንስ በፊት የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ብዙ ሰዎች መምጣቱ ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ ያህልም
❖ ሳሙኤል ሳኦልን ቀብቶ ባነገሠው ጊዜ «የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ወረደ» ተብሏል [፩ኛሳሙ. ፲፥፲]፡፡
❖ ሳሙኤል ዳዊትን በንግሥና በቀባው ጊዜ «የእግዚአብሔር መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ» ተብሏል፡፡ [፩ኛ ሳሙ. ፲፮÷፲፫]
❖ “የእግዚአብሔር መንፈስ ከሶምሶን ጋር ይሄድ ነበር» ተብሎም ተጽፏል፡፡[መሳ.፲፫÷፳፬]
ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር መንፈስ «ሞልቶታል» የተባለ ግን ማንም አልነበረም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ግን በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነበር፡፡ የከበረ እና ታላቅ በመሆኑ አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ግን መቼ ነበር? በመንፈስ ቅዱስ የተሞላው ገና በማኅፀን ሳለ እናቱ ኤልሳቤጥ የእመቤታችንን የሰላምታ ድምፅ በሰማችበት ቅፅበት ነው፡፡
«ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ፤ ፅንሱ በማኅፀኗ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ መላባት» [ሉቃ.፩÷፲፬]
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል» ብሎ የተናገረው በዚህን ጊዜ ተፈጽሟል፡፡
፪. ተጋድሎው
የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በእኛ ሕይወት ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው እኛ በድርጊታችንና በተጋድሎአችን ስንጠብቀው፣ ስንንከባከበውና ስንሠራበት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ይህንን በሚገባ አድርጓል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ያደገው በበረሃ ውስጥ፣ በብሕትውና /በብቸኝነት/፣ የግመል ጠጉር እየለበሰ፣ አንበጣ እና የበረሃ ማር ብቻ እየተመገበ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ እንዲህ ብለዋል «እርሱ በበረሃው ውስጥ ጸሎትና ተመስጦን፣ ድፍረትን እና ፍርሃት አልባነትን፣ ጥንካሬን እና እምነትን ተምሯል፡፡ እግዚአብሔር እመቤታችንን አምላክን ፀንሣ ለመውለድ በቤተ መቅደስ እንዳዘጋጃት እርሱን ደግሞ ለመንገድ ጠራጊነት ተልእኮው በበረሃ አዘጋጅቶታል፤ እኛም የእነዚህ ነገሮች ባለቤት ለመሆን የብቸኝነትና የትህርምት ጊዜ የምናሳለፍበት የየራሳችን በረሃ ያስፈልገናል፡፡»
😇 መጥምቁ ዮሐንስን የምናከብረው ከስጋና ከደም ጋር ስለተጋደለ አይደለም

❖❖❖[ወደ ኤፌሶን ሰዎች ምዕራፍ ፮፥፲፪]❖❖❖
“መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።”
እያንዳንዳችን ከጥምቀታችን ቀጥሎ በሚፈጸምልን ምሥጢረ ሜሮን አማካኝነት መንፈስ ቅዱስ ያድርብናል፡፡ ይህንን ተጠቅመን ሥራ ለመሥራት እኛም እንደ መጥምቁ የራሳችን በረሃ ያስፈልገናል፤ በትህርምትና ራስን በመግዛት መኖር አለብን፡፡
ይህንን ማድረግ የሚገባቸውና የሚችሉት በገዳም ያሉ ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በዓለም የምንኖር ሰዎችም ብቻችንን የምንሆንበትና በጸሎት፣ በተመስጦ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ራሳችንን በመመርመር የምናሳልፈው ጊዜ በመመደብ መኖሪያ ቤቶቻችንን ገዳማት ማድረግ እንችላለን፡፡ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ወደተለያዩ ገዳማት እየሄድን ጊዜ ማሳለፍም ጠቃሚ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ምግባችንን፣ መጠጣችንን እና ልብሳችንን በልክ እያደረግን መጥምቁን ባለ ብዙ ፍሬ በሆነበት ጎዳናው ልንከተለው ያገባናል፡፡
ሲሰርቁ፣ ሲያመነዝሩ፣ በዝሙት ሲወድቁ፣ ሲሰክሩ፣ ሲዘሉ፣ ሲያብዱና ሲያጨበጭቡ ከመሞት እግዚአብሔር ሁላችንንም ይጠብቀን!
😇 የቅዱስ ዮሐንስ ጸሎቱና በረከቱ ይደርብን! አማላጅነቱ ይደረግልን
______________
Leave a Reply