Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • September 2022
    M T W T F S S
     1234
    567891011
    12131415161718
    19202122232425
    2627282930  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

Archive for September 4th, 2022

ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on September 4, 2022

😇 ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ የኾነው ቅዱስ ይሁዳ ታዴዎስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ፪/2ኛው ዓ.ም በገሊላ ከተማ ናዝሬት ተወለዶ በ፶፬/54 ዓ.ም በእኅት አገር አርመኒያ አረፈ✞✞✞

ለእኔ በግሌ ብዙ ጊዜ የሚረዳኝ ቅዱስ ይሁዳ ታዴዎስ አንድ ምዕራፍ ብቻ፤ ነገር ግን ብዙ ምስጢሮችን የያዘ ኃይለኛ መልዕክት አስተላልፎልናል። ለአባታችን ሔኖክና መጽሐፉም ምስክር ነው።

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት አስቀድሞ ቅዱስ ታዴዎስን እንደ መረጠው መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡ ቅዱስ ታዴዎስ አባቱ እልፍዮስ ይባላል (ማቴ. ፲፥፫)፡፡ ሐዋርያው – ‹ልብድዮስ›፣ ‹የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ› እየተባለም ይጠራል (ሉቃ. ፮፥፲፮፤ ዮሐ. ፲፬፥፳፪፤ ሐዋ. ፩፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ታዴዎስ በየአገሩ እየተዘዋወረ ወንጌልን በመስበክ ከአይሁድ እና ከአረማውያን ወገን ብዙዎችን በክርስትና ሃይማኖት አሳምኖ በክርስቶስ ስም አጥምቋል፡፡ አንድ ቀን ወደ ሀገረ ስብከቱ ወደ ሦርያ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሲሔድ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጐልማሳ አምሳል ተገልጦ ‹‹ወዳጄ ታዴዎስ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ›› በማለት ሰላምታ ሰጥቶት ወደ ሰማይ በክብር ዐረገ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም የሐዋርያት አለቃ ነውና እንደ አባትነቱ ወደ ሦርያ ለማድረስ ከቅዱስ ታዴዎስ ጋር ሔደ፡፡ ከከተማዋ አጠገብ ሲደርሱም አንድ ሽማግሌ በሮችን ጠምደው ሲያርሱ አገኙ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ሽማግሌውን ምግብ በለመናቸው ጊዜ ‹‹በሮቼን ጠብቁ›› አሏቸውና ምግብ ሊያመጡላቸው ወደ ቤታቸው ሔዱ፡፡ ሽማግሌው እስኪመለሱ ድረስም ቅዱስ ጴጥሮስ በሮችን ጠምዶ ሠላሳ ትልም አረሰ፡፡ ቅዱስ ታዴዎስም በዚያ የነበረውን የሥንዴ ዘር መዝራት ጀመረ፡፡ የተዘራው ዘርም ወዲያዉኑ በቅሎ፣ አድጎ፣ እሸት ኾነ፡፡ ሽማግሌው ምግብ ይዘው ከቤታቸው ሲመለሱም ቅዱሳን ሐዋርያት ያደረጉትን ተአምር አይተው ደነገጡ፡፡ ከእግራቸው ሥር ወድቀውም ለሐዋርያት ሰገዱላቸው፡፡ በኋላም ‹‹እናንተ ከሰማይ የወረዳችሁ አማልክት ናችሁን?›› አሏቸው፡፡ እነርሱም ‹‹እኛ የእግዚአብሔር ባሮች እንጂ አማልክት አይደለንም›› አሉ፡፡

ሽማግሌውም ‹‹ስላደረጋችሁልኝ በጎ ሥራ በምትሔዱበት ቦታ ዅሉ ልከተላችሁን?›› ባሏቸው ጊዜ ሐዋርያት ‹‹ይህንን ልታደርግ አይገባም፤ ነገር ግን በሮችን ለጌታቸው መልስና በቤትህ የምንበላውን ታዘጋጅልን ዘንድ ለባለቤትህ ንገራት፡፡ እኛ ወደዚህች ከተማ ገብተን እግዚአብሔር እስከሚጠራን ጊዜ ድረስ እንቆያለንና›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ሽማግሌውም የሥንዴውን እሸት ይዘው በሮችን እየነዱ ወደ ከተማ ሲሔዱ ወቅቱ የእርሻ እንጂ የእሸት ጊዜ አልነበረምና እሸት ይዘው በመመልከታቸው የከተማው ሰዎች ተገረሙ፡፡ ሽማሌውንም ‹‹ይህንን እሸት ከወዴት አገኘኸው?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸው ግን ምላሽ አልሰጧቸውም ነበር፡፡ ሽማግሌው ሐዋርያት እንዳዘዟቸው በሮቹን ለጌታቸው መልሰው ቤታቸውን አሰናድተው ራት እንድታዘጋጅላቸው ለሚስታቸው ነገሩ፡፡

ወሬውን የከተማው መኳንንት በሰሙ ጊዜም ‹‹በክፉ አሟሟት እንዳትሞት እሸቱን ከወዴት እንዳገኘኸው ንገረን›› ብለው በሽማግሌው መልእክተኞችን ላኩባቸው፡፡ ሽማግሌውም ‹‹ሕይወት ከእኔ ጋራ ሳለ ሞትን አልፈራም!›› አሉ፡፡ ከዚያም ሐዋርያት ያደረጉትን ዅሉ ነገሯቸው፡፡ መኳንንቱም ‹‹ሐዋርያቱን አምጣቸው›› አሏቸው፡፡ ሽማግሌውም ወደ እርሳቸው ቤት ሲመጡ ማግኘት እንደሚችሉ ነገሯቸው፡፡ ሰይጣን የልቡናቸዉን ዐሳብ ወደ ክፋት ለውጦታልና ከመኳንንቱ ከፊሎቹ ቅዱሳን ሐዋርያትን ለመግደል ተነሣሡ፡፡ ከፊሎቹ ግን ‹‹አምላካቸው ኢየሱስ የሚሹትን ዅሉ እንደሚያደርግላቸው ሰምተናልና ልንገድላቸው አንችልም፡፡ ነገር ግን አመንዝራ ሴት ወስደን በከተማው በር ርቃኗን እናስቀምጣት፡፡ እርሷን ሲያዩ ወደ ከተማችን አይገቡም፤›› አሉ፡፡ ይህን ማለታቸውም ቅዱሳን ሐዋርያት ንጹሐን እንደ መኾናቸው በዓይናቸው የሴት ልጅን ርቃን እንደማይመለከቱ መመስከራቸው ነበር፡፡

መኳንንቱ እንደ ተነጋሩት ሴትዮዋን በከተማው በር ርቃኗን አስቀመጧት፡፡ ሐዋርያው ታዴዎስ ባያት ጊዜም ‹‹ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ወደ ከተማው ገብተን በከበረ ስምህ እስክንሰብክ ድረስ ይህቺን ሴት በአየር ላይ ይሰቅላት ዘንድ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ላክልን›› ብሎ ጸለየ፡፡ ጌታችንም ጸሎቱን ተቀበለውና ሴትዮዋ አየር ላይ ተሰቀለች፡፡ በዚህ ጊዜ የከተማው ሰዎችና መኳኳንንቱ ዅሉ እያዩአት ‹‹አቤቱ ፍረድልኝ›› እያለች ትጮኽ ጀመር፡: መኳንንቱ ግን ሰይጣን ልቡናቸውን አጽንቶታልና የሐዋርያትን ትምህርት አልተቀበሉም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ታዴዎስ ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ የሰዎቹን ልቡና የማረኩ መናፍስትን ርኩሳንን አባረረላቸው፡፡

ሰዎቹም የሐዋርያትን ትምህርት ተቀብለው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡ ሐዋርያው ታዴዎስም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ካጠመቃቸው በኋላ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመላቸው፡፡ በአየር ላይ የተሰቀለችውን ሴትም አውርዶ ዲያቆናዪት አደርጎ ሾማት፡፡ በዚያች ከተማ በሐዋርያት እጅ ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተደረጉ፡፡ ዕውሮች አዩ፤ ሐንካሶች ቆመው ሔዱ፤ ዲዳዎች ተናገሩ፤ ደንቆሮዎች ሰሙ፤ ለምጻሞች ነጹ፤ አጋንንትም ካደሩባቸው ሰዎች እየወጡ ተሰደዱ፤ ሙታንም ተነሡ፡፡ የከተማው ሰዎችም ይህንን ተአምር አይተው በቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ በእግዚአብሔር አመኑ፡፡

አንድ ሰይጣን ያደረበትና ገንዘብ የሚወድ ጐልማሳ ባለ ጠጋም ወደ ሐዋርያው ታዴዎስ መጥቶ ሰገደለትና ‹‹የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆይ! እድን ዘንድ ምን ላድርግ?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ኀይልህ ውደደው፡፡ አትግደል፤ አትስረቅ፤ አታመንዝር፡፡ በአንተ ሊደረግብህ የማትሻውን በሌላው ላይ አታድርግ፡፡ ደግሞም ገንዘብህን ሸጠህ ለድኆችና ለምስኪኖች ብትሰጥ በሰማያት ለዘለዓለም የሚኖር ድልብ ታገኛለህ›› በማለት ሕገ ወንጌልን አስተማረው፡፡ ጐልማሳውም ትምህርቱን በሰማ ጊዜ ተቈጥቶ ሐዋርያውን አነቀው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹የክርስቶስን አገልጋይ እንዴት ደፍረህ ታንቃለህ?›› ባለው ጊዜ ጐልማሳው ቅዱስ ታዴዎስን ለቀቀው፡፡ የእግዚአብሔር ኀይል በይረዳው ኖሮ ሐዋርያው ከመታነቁ ጽናት የተነሣ ዓይኖቹ ሊወጡ ነበር፡፡

ያን ጊዜም ቅዱስ ታዴዎስ ‹‹ጌታችን ‹ሀብታም መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል› ሲል በእውነት የተናገረው እንዳንተ ላለው ሀብታም ነው›› አለው፡፡ ጐልማሳውም ‹‹ይህ ሊኾን አይችልም!›› ባለ ጊዜ ሐዋርያው ታዴዎስ በመንገድ ሲያልፍ ያገኘውን ባለ ግመል አስቁሞ መርፌ ገዝቶ ሊያሳየው ወደደ፡፡ መርፌ ሻጩ ሐዋርያውን ለመርዳት ፈልጎ ቀዳዳው ሰፊ የኾነ መርፌ አመጣለት፡፡ ቅዱስ ታዴዎስም ‹‹እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ፤ ነገር ግን በዚህች አገር የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥ ዘንድ ቀዳዳው ጠባብ የኾነ መርፌ አምጣልን›› አለው፡፡ ቀዳዳው ጠባብ የኾነውን መርፌ ቅዱስ ታዴዎስ ተቀብሎ ‹‹ኀይልህን ግለጥ›› ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እጁንም ዘርግቶ ባለ ግመሉን ‹‹በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከግመልህ ጋር በመርፌ ቀዳዳው ውስጥ እለፍ›› አለው፡፡ ሰውየውም እስከ ግመሉ ድረስ በመርፌ ቀዳዳው አለፈ፡፡

ዳግመኛም ‹‹ሕዝቡ የፈጣሪያችንን የክርስቶስን ኀይል ይረዱ ዘንድ ዳግመኛ ገብተህ እለፍ›› አለው፡፡ ሰውየውም እንደ ታዘዘው ሦስት ጊዜ በመርፌ ቀዳዳው አለፈ፡፡ ሕዝቡም ይህንን ተአምር አይተው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ‹‹ከቅዱሳን ሐዋርያት አምላክ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ በቀር ሌላ አምላክ የለም›› እያሉ ተናገሩ፡፡ ያ ጐልማሳ ባለ ጠጋም ከሐዋርያው ታዴዎስ እግር በታች ወድቆ ሰገደና ‹‹ኀጢአቴን ዅሉ ይቅር በለኝ፡፡ ገንዘቤንም ዅሉ ወስደህ ለድኆችና ለምስኪኖች አከፋፍልኝ›› ሲል ተማጸነው፡፡ ሐዋርያውም እንደ ለመነው አደረገለት፡፡ የክርስትናን ሃይማኖትን ሕግ አስተምሮ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጠመቀው፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ አከናውኖም ሥጋውን፣ ደሙን አቀበለው፡፡ በዚያች አገር አካባቢ የነበሩትን ዅሉንም በቀናች የክርስትና ሃይማኖት አጸናቸው፡፡ ከዚያ በኋላም ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ታዴዎስ ከዚያች ከተማ ወጡ፤ ሕዝቡም በሰላም ሸኟቸው፡፡

ቅዱስ ታዴዎስ በየአገሩ እየተዘዋወረ ወንጌልን ሲሰብክ ቆይቶ ከአይሁድና ከአረማውያን ዘንድ ብዙ መከራ ከደረሰበት በኋላ አገልግሎቱን ፈጽሞ ሐምሌ ፪ ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ዘመንም ሐምሌ ፳፱ ቀን የከበረ ዐፅሙ ከሦርያ ፈልሶ በቍስጥንጥንያ ከተማ በስሙ በታነጸች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክብር እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ ከዐፅሙም ብዙ ድንቆችና ተአምራት ተገልጠዋል፡፡ ዅላችንንም የሐዋርያው ጸሎት ይጠብቀን፤ በረከቱም ይደርብን፡፡

❖❖❖[የይሁዳ መልእክት ምዕራፍ ፩]❖❖❖

  • ፩ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤
  • ፪ ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ።
  • ፫ ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።
  • ፬ ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።
  • ፭ ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ።
  • ፮ መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።
  • ፯ እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።
  • ፰ እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ ጌትነትንም ይጥላሉ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ።
  • ፱ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር። ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም።
  • ፲ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፥ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ።
  • ፲፩ ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል።
  • ፲፪ እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፥ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፥
  • ፲፫ የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፥ ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው።
  • ፲፬-፲፭ ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ። እነሆ፥ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ።
  • ፲፮ እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፥ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል።
  • ፲፯ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤
  • ፲፰ እነርሱ። በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና።
  • ፲፱ እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው።
  • ፳ እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥
  • ፳፩ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።
  • ፳፪ አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥
  • ፳፫ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።
  • ፳፬ ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው
  • ፳፭ ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።

______________

Posted in Ethiopia, War & Crisis | Tagged: , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , , | Leave a Comment »

 
%d bloggers like this: