ዓርብ ስቅለት | ተፈጸመ! | ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ ወጣን
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on April 22, 2022
❖ ልክ አሁን የሕማማተ መስቀልን ፀሎት አንብቤ እንደጨረስኩ፤ ከጎረቤቴ ሕንጻ ጣራ ላይ ፲፫ ርግቦች ተነስተው በዙሪያዬ አንድ ጊዜና በአንድ ላይ ጅው ብለው በመብረር የተነሱበት ጣራ ላይ ተመልሰው አረፉ። ተገርሜ በመመሰጥ፤ “ምን የሚሉኝ ነገር ሊኖር ይችላል?” የሚለውን ጥያቄ ጠየቅኩ። ፲፫/13ቱ ሕማማተ መስቀል?
❖ ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ “የድኅነት ቀን” ይባላል።
✞ ፲፫ቱ ሕማማተ መስቀል
- ፩ኛ. ተአስሮ ድኅሪት (ወደኋላ መታሰር)
- ፪ኛ. ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መሳብ)
- ፫ኛ. ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይ መውደቅ)
- ፬ኛ. ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በእግረ አይሁድ መረገጥ)
- ፭ኛ. ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ (ከምሶሶ ጋር መላተም)
- ፮ኛ. ተጽፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)
- ፯ኛ. ተቀስፎ ዘባን (ጀርባን በጅራፍ መገረፍ)
- ፰ኛ. ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዱላ መመታት)
- ፱ኛ. አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል መድፋት)
- ፲ኛ. ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)
- ፲፩ኛ. ተቀንዎ በቅንዎት (በችንካር መቸንከር)
- ፲፪ኛ. ተሰቅሎ በዕፅ (በመስቀል ላይመሰቀል)
- ፲፫ኛ. ሰሪበ ሐሞት (መራራ ሐሞትን መጠጣት)
✞ ጌታችን ሲሰቅል የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤
- ፩. ፀሐይ ጨለመ፤
- ፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤
- ፫. ከዋክብት ረገፉ፤
- ፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤
- ፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤
- ፮. መቃብራት ተከፈቱ፤
- ፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡
✞ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤
- ፩. “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)”፤
- ፪. “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ”፤
- ፫. “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው”፤
- ፬. እመቤታችንን “ሴትዮሆይ፣እነሆልጅሽ”፤ ደቀ መዝሙሩንም “እናትህ እነኋት” በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤
- ፭. “አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ”
- ፮. “ተጠማሁ”፤
- ፯. “ዅሉተፈጸመ” (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡
ከሰድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ሁኖአል፡፡ “ወፍናሠርክይ በርህ ብርሃነ ፀሐይ” እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡
ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም “ንሴብሖለእግዚአብሔር” እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
______________
Leave a comment