ሰሙነ ሕማማት ረቡዕ የእንባ ቀን
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on April 20, 2022
❖❖❖ የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ስያሜዎች ❖❖❖
- † ሰኞ፤ መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ፤ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ሰኞ።
- † ማክሰኞ፤ የጥያቄና የትምህርት ቀን።
- † ረቡዕ፤ ምክረ አይሁድ፥ የዕንባ ቀን፥ የመልካም መዓዛ ቀን።
- † ሐሙስ፤ ጸሎተ ሐሙስ፥ ሕጽበተ ሐሙስ፥ የምሥጢር ሐሙስ፥ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፥ የነጻነት ሐሙስ።
- † ዐርብ፤ የስቅለት ዐርብ።
- † ቅዳሜ፤ ቀዳም ሥዑር (ሹር ቅዳሜ)፤ ለምለሚቱ ቅዳሜ፥ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፥ ሰንበት ዐባይ፥ ቅዱስ ቅዳሜ፡፡
🗣 ለምን የምክር ቀን ተባለ?
ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ፣ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ፣ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ [ማቴ. ፳፮፤፩፡፲፬፣ ማር. ፲፬፤፩፡፪፣ ቁ ፲፤፲፩፣ ሉቃ. ፳፪፤፩፡፮]
💐 የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል
ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ፣ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት፣ /ባለሽቱዋ ማርያም/፤ “ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ፣ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ” ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ፣ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ፣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ነው ረቡዕ የመዓዛ ቀን የተባለው፡፡
😢 የእንባ ቀንም ይባላል
ይህም ይህቸው ሴት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ፣ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በዕንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፣ በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ [ማቴ.፳፮፤፮፡፲፫፣ ማር.፲፬፤፫፡፱፣ ዮሐ.፲፪፤፩፡፰] ከዚህ ልንማር የሚገባው ነገር አለ፤ ይኸውም የራስን ኃጢአት በማሰብ ማልቀስና የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ነው፡፡ የማርያም እንተ ዕፍረትን ኃጢአት ይቅር ብሎ መብዓዋን የተቀበለ አምላክ ዛሬም በመካከላችን አለና፡፡
ለብርሃነ ትንሣኤው አምላካችን በሰላም ያድርሰን።
______________
Leave a Reply