VIDEO
💭 በኤዶማውያኑ ምዕራባውያንና በእስማኤላውያኑ ምስራቃውያን ፍላጎትና ትዕዛዝ በኦሮማራ ቃኤላውያን ክሃዲዎች አማካኝነት ከዋልድባ ገዳም የተባረሩትን ፩ ሺህ አባቶቻችንን የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያጽናናቸው የእግዚአብሔር መላእክት ይጠብቋቸው፤ ይንከባከቧቸው!
✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፯፥፭፡፮]✞✞✞
“እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።”
✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፯፥፴፡፴፩]✞✞✞
“በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው። መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች። እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው። እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።”
✞✞✞ጻድቁ አባታችን አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ✞✞✞
✞✞✞በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!✞✞✞
አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፤ አባታችን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በረከታችውና ረድኤታቸው ይደርብንና በሰሜኑ የሀገራችን የኢትዮጵያ ክፍል በ ፬ /4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ እንደ ተመሰረተ በሚነገርለት በደብረ ዋሊ ወይም ዋልድባ ገዳም የተነሱ ስመጥር መነኩሴ መናኝና የጽድቅ መምህር ናቸው።
የገዳማዊ ሕይወት እጅግ ተስፋፍቶ በነበረበት በ፲፫/13ኛው እና በ፲፬/14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እነ አባ ኢየሱስ ሞዓ፣ ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሆኑ የእነዚህም የቆብ ልጅ በሆኑት በገዳመ በንኮል በአባ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኩስናን ተቀብለው ቤተ ክርስቲያንን በተሰጣቸው መንፈሳዊ ጸጋ አገልግለዋል።
ትውልዳቸውና ቤተሰቦቻቸው፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተወለዱት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ አክሱም በ፲፪፻፺፭/1295 ሲሆን አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተ ማርያም ይባሉ። እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ የተመሰገኑ ክርስቲያኖች እንደነበሩና በኋላም በምንኩስና ህይወት እንዳለፉ በአባታችን የገድል መጽሐፍና በስንክሳር ላይ በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል።
መንፈሳዊ ትምህርታቸውና ገዳማዊ ህይወታቸው እንዲሁም የተማሩበት ቦታ፤ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ አባታቸው ለአክሱም ቄሰ ገበዝ እንደሰጧቸውና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከፊደል ጀምረው የቅዱስ ያሬድን ጸዋትወ ዜማና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጠናቀው ለአገልግሎትም ዲቁናን ተቀብለው በንቃትና በልባምነትም ቤተ ክርስቲያንን ለሰባት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ጌታችን በወንጌል “ፍጹም ልትሆን ብትወድ…”ማቴ.፲፱፣፳፩፡፳፪ ያለዉን ለመተግበር ለአክሱም ከተማ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ሚገኘው ደብረ በንኮል ገዳም ገብተው ከገዳሙ ሊቃዉንት የብሉያትንና የሐዲሳትን ትርጓሜ እንዲሁም ስርዓተ ምንኩስናን ተምረዋል። ከዚያም ብፁዕነታቸው አባ ሳሙእል ዘዋልድባ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ቅዱስ ሄኖክ የመረጠውን ምናኔ፤ አባ እንጦንስና መቃርስ የተከተሉትን የምንኩስና ሕይወት በሰፊው ተጓዘበት።
ነፍሱን ነፍሴ ሆይ እነሆ ለክርስቶስ ታጨሽ የቅዱሳንን ቀንበር እነሆ ተሸከምሽ የመላእክትን ንጽህና ትጠብቂ ዘንድ ዛሬ በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ፊት ቃል ኪዳን ገባሽ ቃልኪዳንሽን ብትጥብቂ እግዚአብሔር ይደሰትብሻል ባትጠብቂ ግን አጋንንት ይዘብቱብሻል በማለት መከራን በራሱ ላይ ያበዛ ነበር የጣመ የላመም አይመገብም ነበር ይልቁንም ከገዳሙ የሚሰጠዉን መቁኑን ተቀብሎ ለሌሎች
ሰጥቶ የዱር ቅጠል ይመገብ ነበር። ትጋቱንና የምናኔ ሕይወቱን ያዩ መናንያን አበው መነኮሳት የእነሱን የምንኩስና አክሊል እንዲቀበል ፈልገው የገዳሙን አበ ምኔት /ኃላፊ/ አባ መድኃኒነ እግዚእን ይመክሩና ይለምኑ ነበር አባ መድኃኒነ እግዚእም የሚያየዉንና ከመነኮሳቱም የሰማዉን ተቀብሎ በጊዜው ለምንኩስና ከተዘጋጁት አስራ ሁለት ከዋክብት ደቀ መዛሙርት ዉስጥ አንደኛው እንዲሆን ወስኗል።
ከምንኩስና ሥርዓቱም በኋላ እነዚህ አስራ ሁለት ከዋክብት ለሁለት ተከፍለው አምስቱን ከዋክብት በወሎ፣ ትግራይ እና ኤርትራ ሲመድቧቸው ሰባቱን ከዋክብት ደግሞ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በበዛዉም በጎጃም በጎንደር እንዲሁም በጣና አካባቢ እንዲያገለግሉ እንዲያስተምሩ አሰማርተዋል። አባታችን አባ ሳሙኤል በገድላቸው እንደምንመለከተው “ፀሐይ ሳሙኤል ዘዋሊ” ይላል ‘ዋሊ’ የዋልድባ ገዳም የቀድሞ መጠሪያ ስሙ ነው ዋልድባ ገዳም በጣም ተዳክሞ በነበረበት ዘመን ተነስተው ዋልድባን ከጥፋት የታደጉ መናንያንን በማሰባሰብ እንደገና ያስፋፉ በመሆናቸው ዘዋሊ ይሏቸዋል፤ ሳሙኤል ዘደብረ ዓባይም ይሏቸዋል የደብረ ዓባይን ገዳም የመሰረቱት እሳቸው ስለሆኑ።
አባታችን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከዚህ ዓለም በምናኔ ተለይተው ግርማ ሌሊቱን ድምፀ አራዊቱን ፀብዓ አጋንትን የሌሊት ቁር የቀን ሐሩርን ታግሰው የጽድቅን ጎዳና ተከትለው ብዙ የብዙ ብዙ ገድል በመሥራት ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርገዋል ይህም በገድልና በተአምራት መጽሐፋቸው በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል። ከነዚሁም ጥቂቶቹን ብንጠቅስ አባታችን አቡነ ሳሙኤል፤ ባሕርን የከፈለበት ጊዜ አለ፣በጌታ መንበር ፊት እየቀረበ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋርም የሚያጥንበት ጊዜ አለ፣
በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ሆኖ ከእነ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ከሁሉ ቅዱሳን ጋር አንድ ላይ ማዕድ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፣ በእጆቹ የያዛቸው መጻሕፍትም ሳይርሱ ወንዝ የሚሻገርበት ጊዜ አለ፣ በተለይ በጸሎቱ ሰዓት የእምቤታችንን ምስጋና ሲጀምር ከምድር አንድ ክንድ ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ፣ በቤትም ሆኖ ምስጋናዋን ሲጀምር የቤቱ መሰረት እየተናወጠ ዝናብ እንደያዘ ደመና፤ ቤቱ ከምድር ከፍ ብሎ የሚቆምበት ጊዜ አለ፣ መንፈስ ቅዱስም በብርሃን ሰረገላ እየወሰደው ወደ ተለያዩ ገዳማት ያደርሰዉና የጌታን ሥጋ እና ደም እንዲቀበልና እንዲያቀብል ያደርገው ነበር።
ብፁእ አባታችን ዉዳሴዋን ቅዳሴዋን ሲያደርስ እመቤታችን የፍቅሯ ምልክት ይሆነው ዘንድ ነጭ እጣንና የሚያበራ እንቁ ሰጥታቸዋለች። አባታችንም እነዚህን ስጦታዋች የምትሰጭኝ ምን ስላደረግሁ ነው? ብለው በጠየቋት ጊዜ እጣኑ የምኡዝ ክህነትህ ዕንቁው የንጽህናህ የድንግልናህ የቅድስናህ ናቸው ብላ ተርጉማላቸዋለች።
መራሄ ብሉይ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም የሁል ጊዜ ጠባቂው ነዉና በሁሉም ነገር ይረዳዉና እንደ ጓደኛም ያማክረው ነበር።
አባ ሳሙኤል ዘዋልድባን የዱር አራዊት ሁሉ ይገዙለትና ይታዘዙለት እንደነበረ በዚሁ በገድል መጽሃፋቸው በሰፊዉ ተተንትኗል ይልቁንም ሁለት አናብስት የሁል ጊዜ አገልጋዮቹ ነበሩ። ከአንዱ ገዳም ወደ አንዱ ገዳም ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ እሳቸው በአንዱ አንበሳ ተቀምጠው ጻሕፍቶቻቸውን በሌላው አንበሳ ላይ ጭነው እንደሚጓዙ ገድላቸው ያስረዳል። ሌሎቹም አራዊት አባታችንን ሲያዩአቸው እናቱን እንዳየ እንቦሳ በደስታ ይፈነጩ ነበር።
በመግቢያችን እንደገለጽነው የዋልድባ ገዳም የተመሰረተው በጥንታውያን አበው ቢሆንም አባታችን አባ ሳሙኤል ሲገቡ ገዳሙ ምድረ በዳ ሆኖ እስከ መጥፋት ደርሶ ቋያ በቅሎበት የወባ ትንኝ መፈልፈያ ሆኖ እንደ ነበረና ቅዱስነታቸው ሲገቡ ግን የተበተኑትን መነኮሳት ሰብስበው ዋልድባን እንደገና አደራጅተዉና አድሰው አቀኑት የተባህትዎ ኑሮንም አጠናክረው የመናንያን መነኮሳት አበው መሰባሰቢያና መፍለቂያ ከማድረጋቸውም በላይ ዋልድባን እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋታል።
ጻድቁ አባታችን ወንጌልን ለማስፋፋት በየሀገሩ ዞረው አስተምረዋል ብዙ የትሩፋትንም ሥራ ሠርተዋል ጣና ውስጥ በሚገኙ ገዳማትና ማን እንደአባ ያሳይ እንዲሁም ገሊላ ቦታዎች በምድር ዉስጥ ጉድጓድ ቆፍረው እየገቡ ከእህልና ዉሀ ተለይተው ሁለትና ሦስት ሱባኤ ይፈጽሙ ነበረ።
ከሁለት ቅዱሳን ወንድሞቻቸው ከአባ ሳሙኤል ዘወገግና ከአባ ብንያም ዘታህታይ በጌምድር ጋር በመሆን ምድረ ከብድና ዝቋላ በመሄድ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር በተገናኙ ጊዜ ብዙ ተአምራት እንደተደረገላቸው መጽሐፈ ገድላቸው ያስረዳል እንዲሁም ደግሞ በኤርትራ የሚገኘዉን ገዳም ከመሰረቱት ከአቡነ ፊልጶስ ጋር እንደተገናኙና የእግዚአብሔርን ክብር ይጨዋወቱ እንደነበር በገድላቸው ተጽፏል።
ጻድቁ አባታችን በሰኔ ፳፩/21 በእመቤታችን የእረፍት ቀን በመካነ ጸሎታቸው ላይ እያሉ ጌታችን መድኃኒታችን ተገለጸላቸው። ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ ሰላምታ ይገባሃል ። የሚል ድምጽ ሰሙና ደንግጠው ቆሙ። ጌታችን ቀረብ ብሎ የእናቴ የድንግል ማርያም በዓል ነውና እንድትቀድስ ብሎ አዘዛቸው። አባታችንም እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ለመቀደስ አልበቃሁም በማለት ነው ከቤተ መቅደስ አገልግሎት የተለየሁት ብለው መለሱለት። ጌታችንም ስለዚህ ትህትናህ ነው እንድትቀድስ የመረጥኩህ አላቸው። ወዲያዉኑ አባታችን ከፈጣሪያችን ሥርየትና ቡራኬ ተቀብለው ቅዳሴ ገቡ። ሥርዓተ ቅዳሴዉን አድርሰው ከፍሬ ቅዳሴው ደርሰው ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ፣ ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ፣ ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ባሉ ጊዜ የሚቀድሱበት ቤተ ክርስቲያን አንድ ክንድ ከስንዝር ከምድር ለቅቆ እንደ ደመና በአየር ላይ ቆመ። ቅዳሴው ተፈጽሞ እትው እስኪባልም ድረስ እንደቆመ ቆይቷል። ከቅዳሴው በኋላም ጌታችን ከሰው ልጆች የተወለዱትን ሁሉ ወደፊትም እስከ ምጽዓት ድረስ የሚወለዱትንም እልፍ አእላፋት መናንያን መነኮሳት ሰብስቦ በአምላካዊ ሥራው ሕያዋን አድርጎ አሳያቸው።አቡነ ሳሙኤልም በመገረም አምላኬ ፈጣሪየ ሆይ ይህንን ያህል ግዛት ያለው ሰው ከምን የመጣ ነው? ብለው ጠየቁት። እነዚህ እስከ እለተ ምጽዓት ድረስ የሚወለዱ ልጆችህ ናቸው።በአንተ እጅ እንዲባረኩም አምጥቻቸዋለሁ ባርካቸው በማለት ነግሯቸዋል። የአቡነ ሳሙኤልን ስም የሚጠራ መታሰቢያቸዉን የሚያደርግ በአማላጅነታቸው የሚያምን ሁሉ ተባርኳል።
የአባታችን በረከት ከሁላችን ጋር ይደር። የአባ ሳሙኤል ቃል ኪዳናቸው፣ እረፍታቸውና ዓመታዊ ክብረ በዓላቸው የአባታችን የእረፍት ጊዜ ሲደርስም በተወለዱ በአንድ መቶ ዓመት በምናኔ በተባህትዎ እና በምንኩስና ከዚህ ዓለም ተለይተው ግርማ ሌሊትን ድምፀ አራዊትን ፀብአ አጋንንትን የቀን ሐሩር የሌሊት ቁሩን ታግሰው ራቡን ጥሙን ችለው መላ ዘመናቸውን የተቀበሉትን ፀዋትወ መከራ አይቶ ገነት መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸው ዘንድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባታችን ካሉበት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማእታትን አስከትሎ መጥቶ በህይወት ሳሉ የሰጣቸዉን ቃል ኪዳን በእረፍታቸዉም
ደግሞ ስምህን የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በጸሎትህ በአማላጅነትህ ያመነ፣ በመቃብርህ በመካነ አፅምህ የተማፀነ የአንተ ቤተሰብ ሆኖ አንተ የገባህበት አገባዋለሁ። ርስት መንግሥተ ሰማይን አወርሰዋለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። ንጽሕት ጽዕድት ነፍሳቸው በእደ መላእክት በመዓዛ ገነት ከሥጋዋ ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በነብዩ በዳዊት ቃል መዝ.፻፲፮፥፲፭ “ክቡር ሞቱ ለጻድቅ
በቅድመ እግዚአብሔር” እያሉ በታላቅ ዝማሬ፣ በይባቤ፣ በእልልታና በሕይወት ወደ ዘለዓለም የእረፍት ቦታ አስገቧት። ጻድቁ አባታችን በተወለዱ በመቶ ዓመታቸው ታህሳስ ፲፪/12 ቀን ማክሰኞ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዋልድባ አብረንታንት አርፈዋል።
ስለ አባታችን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ይህንን አጭር ጽሁፍ ስናቀርብ አቅጣጫ ለማመላከት ያህል ሲሆን መላዉን በገድል መጽሐፋቸውና በስንክሳር ያገኙታል።
በመስከረም ፮/6 ፍልሰተ አጽማቸው ነው፤ ይህም ከአብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ነው፣ ታህሳስ ፲፪/12 እረፍታቸው ነው እንዲሁም ወር በገባ ፲፪/12 ደግሞ ወርኃዊ በዓላቸው ነው።
የጻድቁ አባታችን የአቡነ ሳሙኤል ረድኤት በረከት አማላጅነት አይለየን!!!
👉 ሙሉውን ለማንበብ
________ _______
Like this: Like Loading...