ሥሉስ ቅዱስ የናምሩድ ባቢሎን ግንብን እንዳፈረሱት የዋቄዮ-አላህ ወረርሽኝንም ቶሎ ያጥፋልን
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on January 15, 2022
✞✞✞ስብሃት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፡፡ አሜን፡፡✞✞✞
❖ ጥር ፯/7-ሥሉስ ቅዱስ የባቢሎንን ግንብ ያፈረሱበት ዕለት ነው፣ በሀገራችንም ቅዳሴ ቤታቸው የከበረበት ዕለት ነው።
❖❖❖
ሥሉስ ቅዱስ፡– ምሥጢራት በእምነት ለማይኖር በትሕትናም ለማይቀርብ የሚገለጡ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር አንድም ነው ሦስትም ነው፡፡ ጊዜ ሣይሠፈር ዘመንም ሳይቆጠር እግዚአብሔር በስም በአካል በግብር ሦስትነቱ በባሕርይ በሕልውና በመለኮትና በሥልጣን አንድነቱ የጸና አምላክ ነው፡፡ ከዓለም መፈጠር በፊት ስለ ነበረው ነገር የሚያውቅ ራሱ ሥላሴ ብቻ ነው፡፡ ዓለምን ከፈጠረ በኋላም ምሥጢረ ሥላሴ (መለኮት) ብለን የምንማረው ትምህርት እንድንና እንጠቀም ዘንድ እርሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ ነው፡፡ ይኸውም በየጊዜው እርሱ ለወደዳቸውና ደስ ላሰኙት ቅዱሳኑ የገለጠው ምሥጢር ነው፡፡ ከዚህ አልፈን በሥጋዊ አዕምሯችን ጌታን “እንመርምርህ” ብንለው ግን ፍጻሜአችን ሞት፣ ማደሪያችንም ገሃነመ እሳት ነው፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በአንድነቱና በሦስትነቱ ሳለ ይህንን ዓለም ፈጠረ፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን ለምን ፈጠረ ቢሉ ስሙን ቀድሰን ክብሩን እንድንወርስ ነው፡፡ ከዚህ የተረፈውን ምክንያት እርሱ ራሱ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት) በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት) የሌለበት የዘለዓለም አምላክ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም በአካል በግብር ሦስትነት በባሕርይ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ተገኙ፣ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና፡፡ ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት “ቅድስት ሥላሴ” እንላቸዋለን፡፡ የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም። የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል፣ በቤቱም መጥተው ያድራሉ፡፡ ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም፡፡ አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡ አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ፡፡ አብርሃም እግራቸውን አጠበ፡፡ በጀርባውም አዘላቸው፡፡ ምሳቸውንም አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም እንደሚበሉ ሆኑለት፡፡ በዚያው ዕለትም የይስሃቅን መወለድ አበሠሩት፡፡ ሥላሴን ያስተናገደች ድንኳን (ሐይመት) የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ በድንግል ላይ አብ ለአጽንኦ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ ወልድ በተለየ አካሉ ለሥጋዌ በእርሷ አድረዋል፡፡ በዓለ ሥላሴ በዚህ ቀን የሚከበረው ስለ ሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ ቀዳሚው ሕንጻ ሰናዖርን ማፍረሳቸው ሲሆን 2ኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤታቸው ነው፡፡
ሰናዖር ከሺዎች ዓመታት በፊት በአሁኗ ኢራቅ አካባቢ እንደነበረ የሚነገርለት ግዛት ሲሆን ስሙ ለሃገሪቱም ለንጉሡም በተመሳሳይ ያገለግል ነበር፡፡ ከናምሩድ ክፋት በኋላ ሰናዖርና ወገኖቹ ከሰይጣን ተወዳጁ፡፡ ከጥፋት ውሃ (ከኖኅ ዕረፍት) በኋላ በሥፍራው በአንድነት ይኖሩ ነበርና እርስ በርሳቸው “ኑ ሳንበተን ስማችን የሚጠራበትን ሕንጻ እንሥራ፣ በዚያውም አባቶቻችንን በውኃ ያጠፋ እግዚአብሔርን እንውጋው” ተባባሉ፡፡ ቀጥለውም ሰማይ ጠቀስ ፎቅን ገነቡ፡፡ ከሕንጻው መርዘም የተነሳ በጸሐይ አብስለው በልተዋል ይባላል፡፡ ቀጥለውም ጦር እያነሱ ፈጣሪን ሊወጉ ወርውረዋል፡፡ መቼም የእነዚህን ሰዎች ክፋትና ቂልነት ስንሰማ ይገርመን ይሆናል፡፡ ግንኮ ዛሬ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም እየተሠራ ያለው ከዚህ የከፋ ነው፡፡ ቸርነቱ ቢጠብቀን እንጂ እንደ ክፋታችንስ በጠፋን ነበር፡፡ ርሕሩሐን ሥላሴ ግን የሰናዖር ሰዎች የሠሩትን አይተው ማጥፋት ሲችሉ አላደረጉትም የባሪያቸውን የኖኅን ቃል ኪዳን አስበዋልና፡፡ ይልቁንም “ኑ እንውረድ ቋንቋቸው እንደባልቀው” አሉ እንጂ፡፡ በመሆኑም ከለዳውያን ልሳናቸው ተደበላልቆ 71 ቋንቋዎች ተፈጠሩ፡፡ እነርሱም ስምምነት አጥተው ተበተኑ፡፡ ሥላሴም ያን ሕንጻ በነፋስ ትቢያ አድርገው በተኑት፡፡ ስለዚህም እስከ ዛሬ ሥፍራው “ባቢሎን” ሲባል ይኖራል፡፡
😈 የአርዮስ ክህደት (Arianism): ይህ ደግሞ የወልድን ፍጹም አምላክነት የሚክድ ትምህርት ነው፡፡ ወልድ በአብ በልዕልና የተፈጠረ ነው ይላል፡፡ ፈጥሮ ፈጠረበት ይላል፡፡ አብ ወልድን ስለፈጠረው አብ ይቀድመዋል ይላል፡፡ስለዚህም ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ነበር የሚል ክህደት ነው፡፡ ለዚህም ክህደቱ በምሳ 8፡22-25 ቆላ 1፡15 ዮሐ 14፡28 ያሉትን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ተጠቅሞባቸዋል፡፡ የአርዮስ ክህደትም በኒቅያ ጉባዔ (በ325 ዓ.ም) የተወገዘ ትምህርት ነው፡፡ እኛም እንደ አባቶቻችን “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ “የሚለውን መሠረት አድርገን “የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ” የሚለውን የኒቅያ ጉባዔ ድንጋጌ እንከተላለን፡፡
________________
Leave a Reply