ሕዳር ፳፩/21 | ዕግትዋ ለጽዮን | ጽዮንን ከበቧት | ስለ ጽዮን ዝም አልልም!
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on November 30, 2021
👉ገብርኤል 😇 ማርያም 👉 ኡራኤል 👉 ጊዮርጊስ 👉 ተክለ ሐይማኖት 👉 ዮሴፍ 👉መድኃኔ ዓለም
እግዚአብሔር አምላካችን እስራኤላውያንን ከፈርዖን ቀንበር በተዓምራት ካወጣቸው በኋላ ሙሴ በሲና ተራራ ፵/ 40 ቀንና ሌሊት ቆይቶ በእግዚአብሔር እጅ የተቀረጹ ሁለት ጽላቶችን
በውስጣቸው እስራኤላውያን እንዲመሩባቸው ፲/10ቱ ትእዛዛት የተጻፉባቸውን ጽላት ይዞ ሲመጣ እስራኤላውያን አምልኮተ እግዚአብሔርን ትተው፤ ውለታውን ረስተው በጣዖት አምልኮት ቢያገኛቸው ከካህን እጅ መስቀል እንዲወድቅ ደንግጾ ጽላቱ ከእጁ ወድቆ ጣዖቱን ደምስሶታል። እግዚአብሔርም እንደቀደሙት ዓይነት ሁለት ጽላት ቀርጾ እንዲያመጣ ባዘዘው መሰረት ጽላቱን እግዚአብሔር ባዘዘው መሰረት ሰርቶ አቅርቧል፤ እግዚአብሔርም አሠርቱን ትዕዛዛት ጽፎበታል። ይህም የሆነው ለምሥጢር ነው የቀደመው ጽላት የአዳም ምሳሌ ሲሆን የመጀመሪያው ሰው አዳም በታላቅ ክብር ተፈጥሮ ሳለ ክብሩን ሕገ እግዚአብሔርን በመጣስ ወድቋል፤ ከክብር ቦታው ተሰዷል። ሁለተኛው ጽላት ምሳሌ ከሰው ወገን የሆነች በእግዚአብሔር የተመረጠች፤ ምክንያተ ድኅነት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ስትሆን የተጻፈው ቃል የቀዳማዊው ቃል ሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ የሆነው የጌታችን የመድኃኒታችን ምሳሌ ነው። [ዮሐ. ፩፥፩፡፫] ታቦተ ጽዮን ፵/40 ዘመናት መናን ከደመና ውሐን ከጭንጫ እያፈለቀ በሠናይ መግቦት ምድረ ርስት አግብቷቸዋል፣ እግዚአብሔር በጽላቱ ላይ ያነጋግራቸው የልባቸውንም መሻት ይፈጽምላቸው ነበር።
ታቦተ ጽዮን በአፍኒንና ፊንሐስ በኃጢአት በካህኑ ኤሊ ቸልተኝነት ምክንያት ተማርካ በፍልስጤማውያን እጅ ከተማረከች በኋላ ፍልስጤማውያን አዛጦን ወስደው በቤተ ጣዖታቸው ከዳጎን ጋር አስቀመጧት። በማግስቱ ሊያጥኑለት ሊሰውለት ቢገቡ ዳጎን በታቦተ ጽዮን ፊት በግምባሩ ወድቆ አገኙት። ከቦታው መልሰውት ሄዱ። በሌላው ቀን ሲመለሱ እጅ እግሩ ተቆራርጦ ደረቱ ለብቻው ቀርቶ አገኙ ፤ ሰዎቹም በእባጭ ተመቱ። መቅሰፍቱ ቢጸናባቸው ወደጌት ወሰዷት። የጌት ሰዎችም እንዲሁ በመቅሰፍት ተመቱ። ወደ አስቀሎና ቢወስዷት “ልታስፈጁን ነው ወደ ሀገሯ መልሱልን” ብለው ጮሁ። ከሰባት ወር በኋላ ወደ ሀገሯ ትመለስ ብለው ቀንበር ባልተጫነባቸው በሚያጠቡ ላሞች በሚሳብ አዲስ ጋሪ አድርገው የበደል መስዋዕት እንዲሆን በአምስቱ ከተሞቻቸው አምሳል አምስት የወርቅ አይጦች አድርገው ሰደዷት። ላሞቹ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ሳይሉ ከኢያሱ እርሻ ደርሰው ቆመዋል። ታቦተ ጽዮንን ከሐውልተ ስምዕ አኑረው ሠረገላውን ፈልጠው ላሞቹን አርደው መስዋዕት አቀረቡ። ነገር ግን ሕዝቡ ታቦተ ጽዮንን በድፍረት በማየታቸው ፭/5 ሺህ ያህሉ ተቀስፈዋል። ወስደውም በአሚናዳብ ቤት አድርገዋት ልጁ አልዓዛር ፳/20 ዓመት አገልግሏታል።
____________________
Leave a Reply