ኪዳነምሕረት ማርያም | ከመረጥሑት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on September 26, 2021
ኪዳነምሕረት ስንል የምሕረት ቃልኪዳን ማለት ነው።በዚህ ውስጥም ምህረት አድራጊው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ምሕረት ተቀባይም መላው የአዳም ዘር ነው።
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድራዊ ቆይታዋ ዘውትር ወደ ክርስቶስ መካነ መቃብር ጎለጎታ እየወረደች ትፀልይ ነበር። ልጇ እና ወዳጇ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገችው ልመናና ፀሎት ተመልክቶና ሰምቶ የምህረት ቃል ኪዳን ገባለት ።
እንኳን የእናቱን ፀሎት እና ልመና ቀርቶ ዘውትር በሀጥያት የምንዘፈቀውን እኛን ክፉዎቹን የሚሰማ አምላክ ስለ አንቺ ፣ ስለ እናቴ ክብርና ፀጋ ስል ይኸው ቃሌ ብሎ ቃልኪዳን አደረገ።
« ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ። … » [መዝ. ፹፰፥፫] እንዲል መፅሐፉ።
ስሟን ለሚጠሩ፣ በእርሷ አማላጅነት ለሚታመኑ በምድር በረከትን በሰማይ የዘለዓለም መንግስትን እንደሚወርሱ የምህረት እና የቸርነት ቃልኪዳን ሰጥቷታል ።
ታላቁ መፅሐፍ እንዲህ ይላል፦
“. . . ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ። ” [ኦሪት ዘፍ. ፱፥፲፮]
በዚህም መሠረት ቃልኪዳኗን ምክንያት በማድረግ ኪዳነ–ምህረት እያልን እንጠራታለን!
እንኳን ለ “ኪዳነምሕረት” አደረሰን። የእመቤታችን ምህረት እና ረድዔት፤ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን!
ስንቱ ቀስት አለፈ ስንቱ ሰንሰለት፡ መከታዬ ሆና የጌታዬ እናት!
____________________________
Leave a Reply