ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና። እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ። ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ፤ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ።
የቃል ኪዳኗ እምቤት ሆይ፤ በቃል ኪዳንሽ ጽኑ አጥርነት ከጠላት ጥፋት ጠብቂን። ያ ክፉ አውሬ ዲያብሎስም ሊውጠን አፉን በከፈተ ጊዜ በበትረ መዓት ራስ ራሱን ቀጥቅጠሽ አጥፊው።
✞✞✞ [መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፮]✞✞✞
፩ አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።
፪ ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ፤ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ።
፫ ነፍሴም እጅግ ታወከች፤ አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው?
፬ አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ።
፭ በሞት የሚያስብህ የለምና፥ በሲኦልም የሚያመሰግንህ ማን ነው?
፮ በጭንቀቴ ደክሜያለሁ፤ ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ።
፯ ዓይኔ ከቍጡ ዕንባ የተነሣ ታወከች፤ ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ አረጀሁ።
፰ ዓመፃን የምታደርጉ ሁሉ፥ ከእኔ ራቁ፥ እግዚአብሔር የልቅሶዬን ቃል ሰምቶአልና።
፱ እግዚአብሔር ልመናዬን ሰማኝ፤ እግዚአብሔር ጸሎቴን ተቀበለ።
፲ ጠላቶቼ ሁሉ ይፈሩ እጅግም ይጐስቍሉ፤ ወደ ኋላቸው ይመለሱ፥ በፍጥነትም ይፈሩ።
✞✞✞ [መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፯]✞✞✞
፩ አቤቱ አምላኬ፥ በአንተ ታመንሁ፤ ከሚያሳድዱኝ ሁሉ አድነኝና አውጣኝ፥
፪ ነፍሴን እንደ አንበሳ ነጥቀው እንዳይሰብሩዋት፥ የሚያድንና የሚታደግ ሳይኖር።
፫ አቤቱ አምላኬ፥ እንዲህስ ካደረግሁ፥ ዓመፃም በእጄ ቢኖር፥
፬ ክፉ ላደረጉብኝም ክፉን መልሼላቸው ብሆን፥ ጠላቴንም በከንቱ ገፍቼው ብሆን፥
፭ ጠላት ነፍሴን ያሳድዳት ያግኛትም፥ ሕይወቴንም በምድር ላይ ይርገጣት፥ ክብሬንም በትቢያ ላይ ያዋርዳት።
፮ አቤቱ፥ በመዓትህ ተነሥ፥ በጠላቶቼ ላይ በቍጣ ተነሣባቸው፤ አቤቱ አምላኬ፥ ባዘዝኸው ትእዛዝ ንቃ።
፯ የአሕዛብም ጉባኤ ይከብብሃል፥ በእነርሱም ላይ ወደ ከፍታ ተመለስ።
፰ እግዚአብሔር በአሕዛብ ይፈርዳል፤ አቤቱ፥ እንደ ጽድቄ ፍረድልኝ፥ እንደ የዋህነቴም ይሁንልኝ።
፱ የኃጥኣን ክፋት ይጥፋ፥ ጻድቁን ግን አቅና፤ እግዚአብሔር ልቡናንና ኵላሊትን ይመረምራል።
፲ እግዚአብሔር የጽድቅ ጋሻዬ ነው ልበ ቅኖችን የሚያድናቸው።
፲፩ እግዚአብሔር የእውነት ዳኛ ነው፥ ኃይለኛም ታጋሽም ነው፥ ሁልጊዜም አይቈጣም።
፲፪ ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይስላል፥ ቀስቱን ገተረ አዘጋጀም፤
፲፫ የሞት መሣርያንም አዘጋጀበት፥ ፍላጻዎቹንም የሚቃጠሉ አደረገ።
፲፬ እነሆ፥ በዓመፃ ተጨነቀ ጉዳትን ፀነሰ ኃጢአትንም ወለደ።
፲፭ ጕድጓድን ማሰ ቈፈረም። ባደረገውም ጕድጓድ ይወድቃል።
፲፮ ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዓመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች።
፲፯ እግዚአብሔርን እንደ ጽድቁ መጠን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔርም ስም እዘምራለሁ።
✞✞✞ [መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፱/ ፲]✞✞✞
፩ አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ።
፪ በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ።
፫ ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ።
፬ ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ።
፭ አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘላለም ደመሰስህ።
፮ ጠላቶች በጦር ለዘላለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም በአንድነት ጠፋ።
፯ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፤
፰ እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል።
፱ እግዚአብሔርም ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው።
፲ ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
፲፩ በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ በአሕዛብም መካከል አደራረጉን ንገሩ፤
፲፪ ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና።
፲፫ አቤቱ፥ እዘንልኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ፤
፲፬ ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፤ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ በማዳንህ ደስ ይለኛል።
፲፭ አሕዛብ በሠሩት ጕድጓድ ወደቁ፥ በዚያችም በሸሸጓት ወጥመድ እግራቸው ተጠመደች።
፲፮ እግዚአብሔር ፍርድን በማድረግ የታወቀ ነው፤ ኃጢአተኛው በእጆቹ ሥራ ተጠመደ።
፲፯ ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ።
፲፰ ድሀ ለዘላለም አይረሳምና፥ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘላለም አይጠፋም።
፲፱ አቤቱ፥ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ፥ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው።
፳ አቤቱ፥ ፍርሃትን በላያቸው ጫንባቸው፤ አሕዛብ ሰዎች እንደ ሆኑ ይወቁ።
✞✞✞ [መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፲/፲፩]✞✞✞
፩ በእግዚአብሔር ታመንሁ፤ ነፍሴን። እንደ ወፍ ወደ ተራሮች ተቅበዝበዢ እንዴት ትሉአታላችሁ?
፪ ኃጢአተኞች እነሆ ቀስታቸውን ገትረዋልና፥ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና፥ ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ።
፫ አንተ የሠራኸውን እነሆ እነርሱ አፍርሰዋልና፤ ጻድቅ ግን ምን አደረገ?
፬ እግዚአብሔር በተቀደሰው መቅደሱ ነው፤ እግዚአብሔር፥ ዙፋኑ በሰማይ ነው፤ ዓይኖቹ ወደ ድሃ ይመለከታሉ፥ ቅንድቦቹም የሰው ልጆችን ይመረምራሉ።
፭ እግዚአብሔር ጻድቅንና ኅጥእን ይመረምራል፤ ዓመፃን የወደዳት ግን ነፍሱን ጠልቶአል።
፮ ወጥመድ በኅጥኣን ላይ ያዘንባል እሳትና ዲን ዐውሎ ነፋስም የጽዋቸው እድል ፈንታ ነው።
፯ እግዚአብሔር ጻድቅ ነውና፥ ጽድቅንም ይወድዳል፤ ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች።
፩ አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ?
፪ በኃጢአተኛ ትዕቢት ድሀ ይናደዳል፤ ባሰቡት ተንኰላቸው ተጠመዱ።
፫ ኃጢአተኛ በነፍሱ ፈቃድ ይወደሳልና፥ ዓመፀኛም ይባርካል።
፬ ኃጢአተኛ እግዚአብሔርን አበሳጨው፥ እንደ ቍጣውም ብዛት አይመራመረውም በእርሱ ፊት እግዚአብሔር የለም።
፭ መንገዱ ሁሉ የረከሰ ነው፥ ፍርድህም በፊቱ የፈረሰ ነው፥ ጠላቶችንም ሁሉ ይገዛቸዋል።
፮ በልቡ ይላል። ለልጅ ልጅ አልታወክም ክፉም አያገኘኝም።
፯ አፉ መርገምንና ሽንገላን ተንኰልን የተመላ ነው፤ ከምላሱ በታች ጉዳትና መከራ ነው።
፰ በመንደሮች መሸመቅያ ይቀመጣል ንጹሓንን በስውር ይገድል ዘንድ፤ ዓይኖቹም ወደ ድኃ ይመለከታሉ።
፱ እንደ አንበሳ በችፍግ ዱር በስውር ይሸምቃል፤ ድሀውን ለመንጠቅ ያደባል፤ ድሀውን ይነጥቀዋል በአሽክላውም ይስበዋል።
፲ ድሀ ይዋረዳል፥ ይጐብጣል፤ በኃያላኑም እጅግ ይወድቃል።
፲፩ በልቡም ይላል። እግዚአብሔር ረስቶኛል፤ ፈጽሞም እንዳያይ ፊቱን ሰወረ።
፲፪ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ እጅህም ከፍ ከፍ ትበል፤ ድሆችን አትርሳ።
፲፫ ኃጢአተኛ ስለ ምን እግዚአብሔርን አስቈጣው? በልቡ። አይመራመረኝም ይላልና።
፲፬ አየኸው፥ አንተ ክፋትንና ቍጣን ትመለከታለህና በእጅህ ፍዳውን ለመስጠት፤ ድሀ ራሱን ለአንተ ይተዋል፥ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።
፲፭ የኃጢአተኛንና የክፉን ክንድ ስበር፥ የኃጢአቱንም ብድራት ክፈል ሌላ እስከማይገኝ ድረስ።
፲፮ እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ።
፲፯ እግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን አሳብ አደመጠች፥
፲፰ ፍርዱ ለድሀ አደግና ለችግረኛ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ አፋቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ እንዳይደግሙ።
______________________________________