አቤቱ፥ አሕዛብ ስምህን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ፤ እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና፥ በክብሩም ይገለጣልና
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on June 6, 2021
✞ “አንተ ተነሥ ጽዮንንም ይቅር በላት፥ የምሕረትዋ ጊዜ ነውና፥ ዘመንዋም ደርሶአልና፤ ባሪያዎችህም ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ ለመሬትዋም አዝነዋልና።”✞
✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻፩]✞✞✞
፩ አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ ጩኸቴም ወደ አንተ ይድረስ።
፪ በመከራዬ ቀን ፊትህን ከኔ አትመልስ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ በጠራሁህ ቀን ፈጥነህ ስማኝ።
፫ ዘመኔ እንደ ጢስ አልቃለችና፥ አጥንቶቼም እንደ መቃጠያ ተቃጥለዋልና።
፬ እህል መብላት ተረስቶኛልና ተቀሠፍሁ ልቤም እንደ ሣር ደረቀ።
፭ ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ አጥንቶቼ ከሥጋዬ ጋር ተጣበቁ።
፮ እንደ ምድረ በዳ እርኩም መሰልሁ፤ በፈረሰ ቤት እንዳለ እንደ ጕጕት ሆንሁ።
፯ ተጋሁ፥ በሰገነትም እንደሚኖር ብቸኛ ድንቢጥ ሆንሁ።
፰ ጠላቶቼ ሁልጊዜ ይሰድቡኛል፥ የሚያሳድዱኝም ተማማሉብኝ።
፱ አመድን እንደ እህል ቅሜአለሁና፥ መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና፥
፲ ከቍጣህና ከመዓትህም የተነሣ፤ አንሥተኸኛልና፥ ጥለኸኝማልና።
፲፩ ዘመኖቼ እንደ ጥላ አዘንብለዋል፤ እኔም እንደ ሣር ደርቄአለሁ።
፲፪ አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ለዘላለም ትኖራለህ፥ መታሰቢያህም ለልጅ ልጅ ነው።
፲፫ አንተ ተነሥ ጽዮንንም ይቅር በላት፥ የምሕረትዋ ጊዜ ነውና፥ ዘመንዋም ደርሶአልና፤
፲፬ ባሪያዎችህም ድንጋዮችዋን ወድደዋልና፥ ለመሬትዋም አዝነዋልና።
፲፭ አቤቱ፥ አሕዛብ ስምህን፥ ነገሥታትም ሁሉ ክብርህን ይፈራሉ፤
፲፮ እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና፥ በክብሩም ይገለጣልና።
፲፯ ወደ ችግረኞች ጸሎት ተመለከተ፥ ልመናቸውንም አልናቀም።
፲፰ ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ፥ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር እልል ይላል፤
፲፱ እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ሆኖ ተመልክቶአልና፥ ከሰማይ ሆኖ ምድርን አይቶአልና፤
፳ የእስረኞችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ፥ ሊገድሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ፤
፳፩ የእግዚአብሔርን ስም በጽዮን ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ፤
፳፪ አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ።
፳፫ በኃይሉ ጎዳና መለሰለት። የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ።
፳፬ በዘመኔ እኵሌታ አትውሰደኝ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው።
፳፭ አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው።
፳፮ እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤
፳፯ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።
፳፰ የባሪያዎችህም ልጆች ይኖራሉ፥ ዘራቸውም ለዘላለም ትጸናለች።
_____________________________________
Leave a Reply