የጌታችን ስቅለት ከ፸፫/73 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ ኡራኤል ዕለት ዋለ
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on April 30, 2021
✞✞✞ዓርብ ስቅለት ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ነው✞✞✞
ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን) –የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት
ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ “ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?” ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡
“ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር“ በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተ ወስዳችሁ እንደሕጋችሁ ፍረዱበት፤“ አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት “ኢትቅትል ብእሴጻድቀወኀ ጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድ አታድን፤“ ትላለችና “እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤” ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ “በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይ ክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤” ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድዳ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡
ዓርብ ስቅለት | ተፈጸመ! | ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ ወጣን
ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ “የድኅነት ቀን” ይባላል፡
👉 ጌታችን ሲሰቅል የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤
፩. ፀሐይ ጨለመ፤
፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤
፫. ከዋክብት ረገፉ፤
፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤
፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤
፮. መቃብራት ተከፈቱ፤
፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩–፶፬)፡፡
👉 ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤
፩. “ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)”፤
፪. “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ“፤
፫. “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው“፤
፬. እመቤታችንን “ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ”፤ ደቀ መዝሙሩንም “እናትህ እነኋት” በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤
፭. “አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ”
፮. “ተጠማሁ“፤
፯. “ዅሉ ተፈጸመ“ (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡
ከሰድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ሁኖአል፡፡ “ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነፀሐይ” እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡
ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም “ንሴብሖለእግዚአብሔር“ እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
👉 ገብርኤል 👉 ማርያም 👉 ኡራኤል 👉 ጊዮርጊስ 👉 ተክለ ሐይማኖት 👉 ዮሴፍ 👉 መድኃኔ ዓለም
✞በዕለተ ሥቅለት በደመ ወልድ ዓለምን ለመቀደስ ከሁሉ ይልቅ የተሰየመው ቅዱስ ኡራኤል ነው።✞
❖ቅዱስ ኡራኤል❖
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

በፍጹም መጠበቅን ጠብቆ ለዚህ ያደረሰን አምላካችን ክብርና ምስጋን አምልኮትና ውዳሴ ይድረሰውና ይህን ታላቅ መልአክ በችሎታችን መጠን እንድናመሰግን እግዚአብሔር ይርዳን፤ አምላክ ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን፤ ምስጢሩን ይግለጥልን አሜን፡፡
“ዑራኤል የተባለ መልአክ ሊረዳኝ መጣ፡፡” [መ/ዕዝ. ሱቱ. ፪፡፩]
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።
በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ።
በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋራ እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውለሁ። ረጅምን ዕድሜ አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። መዝ. [፺/፺፩/፥፲፩፡፲፮]
አፈቅሮ ፈድፋደ፡– ዑራኤል ሆይ፣ ከመልኮች ሁሉ ይልቅ ያንተን መልክአ ጸሎት እወዳለሁ፡፡ የመልክህ ስነ ጸዳል በደመ ወልድ እግዚአብሔር የታተመ ነውና፡፡
ዑራኤል ሆይ፣ እግዚአብሔር ሀይሉን የሚገልጽብን መልአከ ብርሃናት አንተ ነህ፡፡ በዕለተ ሥቅለት በደመ ወልድ ዓለምን ለመቀደስ ከሁሉ ይልቅ አንተ ተሰይመሃልና፡፡ ስለክብርህ የሰማይ መላእክት አደነቁ፡፡
ለተፈጥሮትከ፡–
ዑራኤል ሆይ፡– ያለ መናገር በጥንት አርምሞ ከነፋስና ከእሳት ለተፈጠረ ተፈጥሮህ ሰላም እላለሁ፡፡ ዑራኤል ሆይ የተፈጥሮና የይቅርታና የቸርነት ክቡር መልአክ ነህና ስለኛ ስለሰው ልጆች ወደ ልዑል እግዚአብሔር ማልድ አማላጅነትህ ዘወትር ከጥፋት ያድናልና፡፡
ለዝክረ ስምከ፡–
ዑራኤል ሆይ፡– ከማርና ከወተት ይልቅ ለሚጥመው ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፡፡
ዑራኤል ሆይ፡– ክፍልህ /ክንፍህ/ በደመ ወልድ እግዚአብሔር የተከበረ /የታለለ/ ነውና፡፡ ለዓለሙ ሁሉ መድሃኒት ትሆን ዘንድ ግሩም የሚሆን የእግዚአብሔር ሥልጣን በክብር ከፍ ከፍ አደረገ፡፡ (መልክአ ዑራኤል)
“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” [መዝ.፴፫/፴፬/፥፯]የሊቀ መልአኩ የክዱስ ዑራኤል ረድኤቱ በረከቱ ፍጹም አማላጅነቱ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡
ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡
በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡ ሌሊትና ቀን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑና ሳይሰለቹ የሚጠብቁን ሊቀነ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሩፋኤል ቅዱስ ዑራኤል ቅዱስ ራጉኤል ቅዱስ ፋኑኤል እልፍ አእላፋት የሆኑ ጠባቂ መላእክት ሳመሰግን በደስታ ነው፡፡
በጸሎታቸው ያልተለዩኝን ጻድቃን አባቶቼን አቡነ ተክለሃይማኖትን አቡነ ገብረምንፈስ ቅዱስን አቡነ ሀብተማርያምን አቡነ አረጋዊን አቡነ ኪሮስንና ሌሎች ቅዱሳን አባቶቼን እንዲሁም እናቶቼን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራን ቅድስት አርሴማን ብዙ ያልጠቀስኳቸው ቅዱሳንን ለማመስገን ቃላት የለኝም፡፡
በሰማኝትነታቸው የጥንካሬ ምሳሌ የሆኑልኝ በጸሎታቸው የረዱኝን ቅዱሳን ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቅዱስ እስጢፋኖን መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስንና ሌሎችን ቅዱሳን ሰማዕታትን ሁሉ በእጅጉ አመሰግናለሁ ለዘላለሙ አሜን፡፡
የተከዱትንና የተገፉትን የአክሱም ጽዮን ልጆችን፤ በፈተና፣ በመከራ፣ በድካምና በስቃይ ላይ ያሉትን ወገኖቻችንን ሁሉ ያለ ደዌና ያለ ከፋ ሕማም ለክርስቶስ ትንሣኤ ያድርሰልን ፤ ቀናተኞችና አረመኔዎች የሆኑትን እርጉም ጠላቶቻቸውን/ጠላቶቻችንን ሁሉ በቶሎ ያንበርክክልን!!! አሜን።
___________________________________
Leave a Reply