Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • April 2021
    M T W T F S S
     1234
    567891011
    12131415161718
    19202122232425
    2627282930  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው ፥ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on April 11, 2021

✞✞✞“ዋልድባ ሐጢአት አይሻገርብሽ እህል እንዳይበላብሽ”✞✞✞

✞✞✞ደብረ ዋሊ ወይም ዋልድባ ገዳም በ ፬ /4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ተመሰረተ✞✞✞

✞✞✞ ስለ ዋልድባ ገዳም ታሪክ (አቀማመጥና ስያሜ)✞✞✞

ዋልድባ ገዳም በሰሜን ጎንደር በምዕራብ ትግራይ በተከዜ ወንዝ በዛሬማ ወንዝ በእንስያ ወንዝ በወልቃይት በጠለምት በፅንብላ በስሜን ጃናሞራ በአርማጭሆ በነዚህ ቦታዎችና ወንዞች ተከቦ ተከብሮና ታጥሮ በአስደናቂ የመሬት ተፎጥራዊ አቀማመጥ ልዩ በሆነ የምድር ካርታ በወንዞች ብቻ የታጠረ ነው ዋልድባ አብረንታንት ገዳም በኢየሱስ ክርስቶስ የተገደመ ነው።

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ ፬ /4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ከተገደሙት ገዳማት አንዱ የሆነው ይህ ገዳም፤ምድር ስትፈጠር ጌታ ባወቀ ያዘጋጀው ቅዱስ ቦታ ነው፡፡ የትንቢቱ ቃል የተነገረለት ዋልድባ ወይም ዋሊ ማለት ምን ማለት ነው? እመቤታችን ዋሊ የሚባል ገዳም ደረስን ብላ ተናገረችው በውስጡ ባለችው ዕፅ ምክንያት ሲሆን፤ ይቺ ዋሊ የተሰኝች ዕፅ በገነት የምተገኝ ናት፡፡

የርሷም ቅጠሎች ሰፋፊና ቅርንጫፎቿ የበዙ፣ ሁል ጊዜ ጠዋት አብባ በ፱ ሰዓት የምታፈራ ዕፅ ናት፡፡ ዋሊ ዱባ የሚያክል ፍሬ በመያዟ በተለምዶ ዋሊዱባ በማለት ስትጠራ ቆይታ በኋላ ዋልድባ ለመባል በቅታለች፡፡ ዛሬም ቢሆን የቅዱሳን ምግብ ሆና የምታገለግለውን ዕፅ ከሥጋ ህፀፅ የራቀ ሁሉ በዓይነ ኅሊናው የብቃት መጽሔት ሊያያት ይችላል፡፡

በዚች ዕፅ ስያሜ የተጠራው የዋልድባ ገዳም የቆዳ ስፋት ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ከ፴ እስከ ፵ ኪሎሜትር ርቀት ስኖረው ከሰሜን ወደ ደቡብ ከ፹—፺ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ ገዳሙን እንደ ገነት ዙሪያውን በአራት አፍላጋት(ወንዞች) የተከበበ ሲሆን በምስራቅ የእንስያ፣በምእራብ የዛሬማ፣በደቡብ የማይወባ፣በሰሜን የተከዜ ወንዞች አጥር ቅጥር ሆነው ገዳሙን ይከልሉታል፡፡አዋሳኝ ቦታዎቹም በምስራቅ የፀለምት ወረዳ፣ በምዕራብ ወልቃይት፣በደቡብ የዛሬማ ወረዳ፣በሰሜን ፅምብላ ናቸው፡፡

በዚህ ስፋት ወስጥ እህል አይበላም፣ጠላና የመሳሰሉት መጠጣት አይፈቀድም፣የሞቀ ደመቀ አይለበስም፡፡ይህ ገዳም ብዙ ዋሻዎች፣ፍርክታዎችና ገደላማ ስፍራዎች ያሉበት ሲሆን፤በየውኃ ምንጮችም ጭምር የጥንት የአበው ቅሪት ምልክቶች እስከ ዛሬ ድረስ ይታዩበታል፡፡

የታተሙ ህንፃዎች፣የምድር ውስጥ ቤቶች፣የታሸጉ ዋሻዎች፣ዝጉሃን የሚኖሩባቸው ጉድጓዶችና የድንጋይ ስር ቤቶች ይገኛሉ፡፡እልፍ አእላፈት ስውራን ይኖሩበታል፡፡እነዚህም ለብቁአን፣ ለእረኞች ይከሰታሉ፣በአብዛኛው ደግሞ ከእይታ ውጭ በድምፅ ብቻ ጽንሐ ደውልና ይሰማል የእጣን ሽታ ይሸታል፡፡

ቀድሞ የነበረው የሁል ጊዜ ምግባቸው፤ ለእመቤታችን ቆፍሮ የሰጣት ባለ ሶስት መቶ አስራ ስምንት ሥር ያለው ገመሎ፣ሣዳ፣ፃሌብ፣አጽግቢት ሲሆኑ፣ከቅጠላ ቅጠሎች ሓምለ አበው የተባለ፣ክረምት ብቻ የሚበቅል፣ጎመንን የሚተካ የፀጋይቶ የሚባል እጅግ መራራ ቅጠል፣ሰብኣ የሚባል ቅጠል ሌሎችም ናቸው፡፡ ፀጋይቶ ቅጠል ሁለቴና ሶስቴ ተቀቅሎ ምሬቱና መርዙ ሲቀንስ ሚበላ ነው፡፡ እስከመጨረሻው ቢቀቀል ምሬቱ አይጠፋም፡፡ ከመሬት ተቆፍሮ ከሚወጡት ውስጥ ፃብሌ የድንች መልክ የያዘ ሆኖ ለጊዜው ቀቅለው ቢበሉት ልብን ያጠፋል፣አምሮን ያናውዛል፣ለእብደት ያደርሳል፡፡ይህ ተቆፍሮ ከወጣ በኋላ ከሳምንት ያለነሰ ጊዜ በውኃ ውስጥ እየተዘፈዘፈና እየታጠበ ተቀቅሎ ከቆየ በኋላ በፀሀይ ደርቆ በማጠራቀሚያ ጎተራ ይቀመጣል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ለምግብነት የሚጠቀሙበት፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሥራ ሥሮች ዛሬም ቢሆን በመነኮሳቱ እየተዘጋጁ ከሚበላው ቋርፍ በተጨማሪ ለመጠባበቂያ ለእለታዊ ምግብ ይጠቀማሉ፡፡

✞ ከዱር አራዊትና እንስሳት ወገን፤

አጋዘን፣ድኩላ፣ወደምቢ፣ተኩላ፣ዘንዶ፣ጊንጥ፣ቀበሮ፣ጅብ፣ጉሬዛ፣ዝንጀሮ፣ጦጣ፣ሰስ፣ሚዳቋ፣የመሳሰሉት ሲኖሩ፤ አንበሶች(ከስውራኖቹ በስተቀር) እና ዝሆኖች፤በአድን ገዳሙን በየአመቱ ጥርግ አድርጎ በሚበላው ሰድድ እሳትና በአደን ምክንያት ተሰቅቀው በወልቃይት አደርገው ወደ መተማና ሱዳን ተሰደዋል፡፡

✞ ከእጽዋትም ወገን፤

ሰርኪን፣ደማቅ፣እንኮይ፣የእጣን ዛፍ(መቀር)፣ሐሴን፣ሑመር፣ዋንዛ፣ሳላና፣ልዩ ልዩ አበቦች፣የሌሎችም እፅዋት ዝርያ ያለበት ገዳም ነው፡፡ በገዳሙ አንድ ክፍል በሆነው በአምርሓ ደጋ /አብርሃ ደጋ/ በተባለው ተራራማ ስፍራ ቁስቋም ማርያም ተብሎ የሚጠራ ስውር ቤተ-ክርስቲያን እንዳለ ይታወቃል፡፡

በአሁኑ ሰአት እጅግ ብዙ ሊሒቃን ሙሁራን መናንያን መነኮሳት ያሉበት ቦታ ነው ዋልድባ እህል አይበላም በገዳሙ ቛርፍ የሚባል ከሙዝ የሚዘጋጅ ምግብ ይመገባሉ በተጨማሪም ግመሎ ሳዳ ጫብሌ ፃብሌ የሚባሉ ስራ ስሮች ከመሬት ከጫካው በመቆፈር መነኮሳቱ የሚመገቡት ምግብ ነው። ሌላ ስኳር ጨው በርበሬ ተልባ ኑግ ማር ብቻ በገዳሙ የሚፈቀዱ ናቸው ሌላ የእህል አይነት ፈፅሞ አይገባም ክልክል ነው።

ዋልድባ በዓለማችን ካሉ ገዳማት በስርአተ ገዳም በመነኮሳት ስምሪት እና በስርአተ ቤተ ክርስቲያን መሰረት የዋልድባ ገዳም ግንባር ቀደም ነው። ዋልድባ ገዳም በሶስት ታላላቅ ቦታዎች በአራት የአንድነት ማህበር ተከፍሎ የሚገኝ ብቸኛው በኢትዮጵያ የምናኔ ቦታ ነው። ዋልድባ በስሩ ብዙ ቅርጫፎች አነስተኛ ገዳማት ያሉት ሲሆን የእርሻ ቤቶች ሞፈር ቤቶች የአትክልት ቦታዎች የንብ ቤቶችና ወፍጮ ቤቶች በመባል የሚታወቁ ብዙ ቦታዎች ይገኛሉ። በአንዱ ሞፈር ቤት ከሁለት መቶ በላይ መነኮሳት ይኖሩበታል። ለምሳሌ በዶንዶሮቛ ሁለት መቶ ሐምሳ መነኮሳት በመዘጋ እጣኖ ማርያም መቶ ሰላሳ፣ በማይ ሐርገፅ መቶ ስድሳ፣ አባነፃ ሰማንያ ቤት ሙሉ በአሁኑ ማይገባ አምሳ በማይለበጣ ሁለት መቶ የሚኖሩ መናንያን አሉ።

በነዚህ ገዳማት የሚኖሩ መነኮሳት ሁሉ ተጠሪነታቸው ለዋናው አብረንታንት ነው። ዋልድባ አንድ አይነት ልብስ ነው የሚለበሰው፤ ስሙ ወይባ ይባላል። ዋልድቦች በምናኔ በመንፈሳዊ አስተዳደር ሊሒቃን ናቸው። ገዳሙ ፍፁም የመናኞች ቦታ ነው። እጅግ ፀሎተኞች ናቸው በስራም ቢሆን ዋልድቦች እጅግ አስደናቂ ተአምር ሰሪ ናቸው የዋልድባ መነኩሴ ሰውነታቸው ቀጫጭን ለፀሎት የሚተጉ አዕምሮአቸው በመንፈስ ሙጡቃን ናቸው። ዋልድባ ስርአተ ዐበው በሚባለው መፅሐፍ እንደተፃፈው “ዋልድባ ሐጢአት አይሻገርብሽ እህል እንዳይበላብሽ” የሚል ትዕዛዝ እስካሁን ገዳሙ ውስጥ እህል አይበላም እርሻም አይታረስም ያረሰ ካለ ራሱ ቀድሞ ይጠፋል።

በጋላማራ ቃኤላውያን ከዋልድባ ገዳም የተባረሩት አባቶቻችንን የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያጽናናቸው የእግዚአብሔር መላእክት ይጠብቋቸው፤ ይንከባከቧቸው!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፤ አባታችን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል በረከታችውና ረድኤታቸው ይደርብንና በሰሜኑ የሀገራችን የኢትዮጵያ ክፍል በ ፬ /4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ እንደ ተመሰረተ በሚነገርለት በደብረ ዋሊ ወይም ዋልድባ ገዳም የተነሱ ስመጥር መነኩሴ መናኝና የጽድቅ መምህር ናቸው።

የገዳማዊ ሕይወት እጅግ ተስፋፍቶ በነበረበት በ፲፫/13ኛው እና በ፲፬/14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እነ አባ ኢየሱስ ሞዓ፣ ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሆኑ የእነዚህም የቆብ ልጅ በሆኑት በገዳመ በንኮል በአባ መድኃኒነ እግዚእ እጅ ምንኩስናን

ተቀብለው ቤተ ክርስቲያንን በተሰጣቸው መንፈሳዊ ጸጋ አገልግለዋል።

ትውልዳቸውና ቤተሰቦቻቸው፤ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ የተወለዱት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ አክሱም በ፲፪፻፺፭/1295 ሲሆን አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተ ማርያም ይባሉ። እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ የተመሰገኑ ክርስቲያኖች እንደነበሩና በኋላም በምንኩስና ህይወት እንዳለፉ በአባታችን የገድል መጽሐፍና በስንክሳር ላይ በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል።

መንፈሳዊ ትምህርታቸውና ገዳማዊ ህይወታቸው እንዲሁም የተማሩበት ቦታ፤ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ አባታቸው ለአክሱም ቄሰ ገበዝ እንደሰጧቸውና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከፊደል ጀምረው የቅዱስ ያሬድን ጸዋትወ ዜማና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አጠናቀው ለአገልግሎትም ዲቁናን ተቀብለው በንቃትና በልባምነትም ቤተ ክርስቲያንን ለሰባት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ጌታችን በወንጌል “ፍጹም ልትሆን ብትወድ…”ማቴ.፲፱፣፳፩፡፳፪ ያለዉን ለመተግበር

ለአክሱም ከተማ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ሚገኘው ደብረ በንኮል ገዳም ገብተው ከገዳሙ ሊቃዉንት የብሉያትንና የሐዲሳትን ትርጓሜ እንዲሁም ስርዓተ ምንኩስናን ተምረዋል። ከዚያም ብፁዕነታቸው አባ ሳሙእል ዘዋልድባ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ቅዱስ ሄኖክ የመረጠውን ምናኔ፤ አባ እንጦንስና መቃርስ የተከተሉትን የምንኩስና ሕይወት በሰፊው ተጓዘበት።

ነፍሱን ነፍሴ ሆይ እነሆ ለክርስቶስ ታጨሽ የቅዱሳንን ቀንበር እነሆ ተሸከምሽ የመላእክትን ንጽህና ትጠብቂ ዘንድ ዛሬ በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ፊት ቃል ኪዳን ገባሽ ቃልኪዳንሽን ብትጥብቂ እግዚአብሔር ይደሰትብሻል ባትጠብቂ ግን አጋንንት ይዘብቱብሻል በማለት መከራን በራሱ ላይ ያበዛ ነበር የጣመ የላመም አይመገብም ነበር ይልቁንም ከገዳሙ የሚሰጠዉን መቁኑን ተቀብሎ ለሌሎች

ሰጥቶ የዱር ቅጠል ይመገብ ነበር። ትጋቱንና የምናኔ ሕይወቱን ያዩ መናንያን አበው መነኮሳት የእነሱን የምንኩስና አክሊል እንዲቀበል ፈልገው የገዳሙን አበ ምኔት /ኃላፊ/ አባ መድኃኒነ እግዚእን ይመክሩና ይለምኑ ነበር አባ መድኃኒነ እግዚእም የሚያየዉንና ከመነኮሳቱም የሰማዉን ተቀብሎ በጊዜው ለምንኩስና ከተዘጋጁት አስራ ሁለት ከዋክብት ደቀ መዛሙርት ዉስጥ አንደኛው እንዲሆን ወስኗል።

ከምንኩስና ሥርዓቱም በኋላ እነዚህ አስራ ሁለት ከዋክብት ለሁለት ተከፍለው አምስቱን ከዋክብት በወሎ፣ ትግራይ እና ኤርትራ ሲመድቧቸው ሰባቱን ከዋክብት ደግሞ በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በበዛዉም በጎጃም በጎንደር እንዲሁም በጣና አካባቢ እንዲያገለግሉ እንዲያስተምሩ አሰማርተዋል። አባታችን አባ ሳሙኤል በገድላቸው እንደምንመለከተው “ፀሐይ ሳሙኤል ዘዋሊ” ይላል ‘ዋሊ’ የዋልድባ ገዳም የቀድሞ መጠሪያ ስሙ ነው ዋልድባ ገዳም በጣም ተዳክሞ በነበረበት ዘመን ተነስተው ዋልድባን ከጥፋት የታደጉ መናንያንን በማሰባሰብ እንደገና ያስፋፉ በመሆናቸው ዘዋሊ ይሏቸዋል፤ ሳሙኤል ዘደብረ ዓባይም ይሏቸዋል የደብረ ዓባይን ገዳም የመሰረቱት እሳቸው ስለሆኑ።

አባታችን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከዚህ ዓለም በምናኔ ተለይተው ግርማ ሌሊቱን ድምፀ አራዊቱን ፀብዓ አጋንትን የሌሊት ቁር የቀን ሐሩርን ታግሰው የጽድቅን ጎዳና ተከትለው ብዙ የብዙ ብዙ ገድል በመሥራት ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርገዋል ይህም በገድልና በተአምራት መጽሐፋቸው በሰፊው ተመዝግቦ ይገኛል። ከነዚሁም ጥቂቶቹን ብንጠቅስ አባታችን አቡነ ሳሙኤል፤ ባሕርን የከፈለበት ጊዜ አለ፣በጌታ መንበር ፊት እየቀረበ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ጋርም የሚያጥንበት ጊዜ አለ፣

በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ሆኖ ከእነ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ከሁሉ ቅዱሳን ጋር አንድ ላይ ማዕድ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፣ በእጆቹ የያዛቸው መጻሕፍትም ሳይርሱ ወንዝ የሚሻገርበት ጊዜ አለ፣ በተለይ በጸሎቱ ሰዓት የእምቤታችንን ምስጋና ሲጀምር ከምድር አንድ ክንድ ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ፣ በቤትም ሆኖ ምስጋናዋን ሲጀምር የቤቱ መሰረት እየተናወጠ ዝናብ እንደያዘ ደመና፤ ቤቱ ከምድር ከፍ ብሎ የሚቆምበት ጊዜ አለ፣ መንፈስ ቅዱስም በብርሃን ሰረገላ እየወሰደው ወደ ተለያዩ ገዳማት ያደርሰዉና የጌታን ሥጋ እና ደም እንዲቀበልና እንዲያቀብል ያደርገው ነበር።

ብፁእ አባታችን ዉዳሴዋን ቅዳሴዋን ሲያደርስ እመቤታችን የፍቅሯ ምልክት ይሆነው ዘንድ ነጭ እጣንና የሚያበራ እንቁ ሰጥታቸዋለች። አባታችንም እነዚህን ስጦታዋች የምትሰጭኝ ምን ስላደረግሁ ነው? ብለው በጠየቋት ጊዜ እጣኑ የምኡዝ ክህነትህ ዕንቁው የንጽህናህ የድንግልናህ የቅድስናህ ናቸው ብላ ተርጉማላቸዋለች።

መራሄ ብሉይ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልም የሁል ጊዜ ጠባቂው ነዉና በሁሉም ነገር ይረዳዉና እንደ ጓደኛም ያማክረው ነበር።

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባን የዱር አራዊት ሁሉ ይገዙለትና ይታዘዙለት እንደነበረ በዚሁ በገድል መጽሃፋቸው በሰፊዉ ተተንትኗል ይልቁንም ሁለት አናብስት የሁል ጊዜ አገልጋዮቹ ነበሩ። ከአንዱ ገዳም ወደ አንዱ ገዳም ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ እሳቸው በአንዱ አንበሳ ተቀምጠው ጻሕፍቶቻቸውን በሌላው አንበሳ ላይ ጭነው እንደሚጓዙ ገድላቸው ያስረዳል። ሌሎቹም አራዊት አባታችንን ሲያዩአቸው እናቱን እንዳየ እንቦሳ በደስታ ይፈነጩ ነበር።

በመግቢያችን እንደገለጽነው የዋልድባ ገዳም የተመሰረተው በጥንታውያን አበው ቢሆንም አባታችን አባ ሳሙኤል ሲገቡ ገዳሙ ምድረ በዳ ሆኖ እስከ መጥፋት ደርሶ ቋያ በቅሎበት የወባ ትንኝ መፈልፈያ ሆኖ እንደ ነበረና ቅዱስነታቸው ሲገቡ ግን የተበተኑትን መነኮሳት ሰብስበው ዋልድባን እንደገና አደራጅተዉና አድሰው አቀኑት የተባህትዎ ኑሮንም አጠናክረው የመናንያን መነኮሳት አበው መሰባሰቢያና መፍለቂያ ከማድረጋቸውም በላይ ዋልድባን እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋታል።

ጻድቁ አባታችን ወንጌልን ለማስፋፋት በየሀገሩ ዞረው አስተምረዋል ብዙ የትሩፋትንም ሥራ ሠርተዋል ጣና ውስጥ በሚገኙ ገዳማትና ማን እንደአባ ያሳይ እንዲሁም ገሊላ ቦታዎች በምድር ዉስጥ ጉድጓድ ቆፍረው እየገቡ ከእህልና ዉሀ ተለይተው ሁለትና ሦስት ሱባኤ ይፈጽሙ ነበረ።

ከሁለት ቅዱሳን ወንድሞቻቸው ከአባ ሳሙኤል ዘወገግና ከአባ ብንያም ዘታህታይ በጌምድር ጋር በመሆን ምድረ ከብድና ዝቋላ በመሄድ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር በተገናኙ ጊዜ ብዙ ተአምራት እንደተደረገላቸው መጽሐፈ ገድላቸው ያስረዳል እንዲሁም ደግሞ በኤርትራ

የሚገኘዉን ገዳም ከመሰረቱት ከአቡነ ፊልጶስ ጋር እንደተገናኙና የእግዚአብሔርን ክብር ይጨዋወቱ እንደነበር በገድላቸው ተጽፏል።

ጻድቁ አባታችን በሰኔ 21 በእመቤታችን የእረፍት ቀን በመካነ ጸሎታቸው ላይ እያሉ ጌታችን መድኃኒታችን ተገለጸላቸው። ወዳጄ ሳሙኤል ሆይ ሰላምታ ይገባሃል ። የሚል ድምጽ ሰሙና ደንግጠው ቆሙ። ጌታችን ቀረብ ብሎ የእናቴ የድንግል ማርያም በዓል ነውና እንድትቀድስ ብሎ አዘዛቸው። አባታችንም እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ለመቀደስ አልበቃሁም በማለት ነው ከቤተ መቅደስ አገልግሎት የተለየሁት ብለው መለሱለት። ጌታችንም ስለዚህ ትህትናህ ነው እንድትቀድስ የመረጥኩህ አላቸው። ወዲያዉኑ አባታችን ከፈጣሪያችን ሥርየትና ቡራኬ ተቀብለው ቅዳሴ

ገቡ። ሥርዓተ ቅዳሴዉን አድርሰው ከፍሬ ቅዳሴው ደርሰው ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ፣ ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ፣ ጎሥዓ ልብየ ቃለ ሠናየ ባሉ ጊዜ የሚቀድሱበት ቤተ ክርስቲያን አንድ ክንድ ከስንዝር ከምድር ለቅቆ እንደ ደመና በአየር ላይ ቆመ። ቅዳሴው ተፈጽሞ እትው እስኪባልም ድረስ እንደቆመ ቆይቷል። ከቅዳሴው በኋላም ጌታችን ከሰው ልጆች የተወለዱትን ሁሉ ወደፊትም እስከ

ምጽዓት ድረስ የሚወለዱትንም እልፍ አእላፋት መናንያን መነኮሳት ሰብስቦ በአምላካዊ ሥራው ሕያዋን አድርጎ አሳያቸው።አቡነ ሳሙኤልም በመገረም አምላኬ ፈጣሪየ ሆይ ይህንን ያህል ግዛት ያለው ሰው ከምን የመጣ ነው? ብለው ጠየቁት። እነዚህ እስከ እለተ ምጽዓት ድረስ የሚወለዱ ልጆችህ ናቸው።በአንተ እጅ እንዲባረኩም አምጥቻቸዋለሁ ባርካቸው በማለት ነግሯቸዋል። የአቡነ

ሳሙኤልን ስም የሚጠራ መታሰቢያቸዉን የሚያደርግ በአማላጅነታቸው የሚያምን ሁሉ ተባርኳል።

የአባታችን በረከት ከሁላችን ጋር ይደር። የአባ ሳሙኤል ቃል ኪዳናቸው፣ እረፍታቸውና

ዓመታዊ ክብረ በዓላቸው የአባታችን የእረፍት ጊዜ ሲደርስም በተወለዱ በአንድ መቶ ዓመት በምናኔ በተባህትዎ እና በምንኩስና ከዚህ ዓለም ተለይተው ግርማ ሌሊትን ድምፀ አራዊትን ፀብአ

አጋንንትን የቀን ሐሩር የሌሊት ቁሩን ታግሰው ራቡን ጥሙን ችለው መላ ዘመናቸውን የተቀበሉትን ፀዋትወ መከራ አይቶ ገነት መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸው ዘንድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባታችን ካሉበት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማእታትን አስከትሎ መጥቶ በህይወት ሳሉ የሰጣቸዉን ቃል ኪዳን በእረፍታቸዉም

ደግሞ ስምህን የጠራ፣ መታሰቢያህን ያደረገ፣ በጸሎትህ በአማላጅነትህ ያመነ፣ በመቃብርህ በመካነ አፅምህ የተማፀነ የአንተ ቤተሰብ ሆኖ አንተ የገባህበት አገባዋለሁ። ርስት መንግሥተ ሰማይን አወርሰዋለሁ ብሎ ቃል ኪዳን ሰጣቸው። ንጽሕት ጽዕድት ነፍሳቸው በእደ መላእክት በመዓዛ ገነት ከሥጋዋ ተለየች። ቅዱሳን መላእክትም በነብዩ በዳዊት ቃል መዝ.፻፲፮፥፲፭ “ክቡር ሞቱ ለጻድቅ

በቅድመ እግዚአብሔር” እያሉ በታላቅ ዝማሬ፣ በይባቤ፣ በእልልታና በሕይወት ወደ ዘለዓለም የእረፍት ቦታ አስገቧት። ጻድቁ አባታችን በተወለዱ በመቶ ዓመታቸው ታህሳስ ፲፪/12 ቀን ማክሰኞ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዋልድባ አብረንታንት አርፈዋል።

ስለ አባታችን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ይህንን አጭር ጽሁፍ ስናቀርብ አቅጣጫ ለማመላከት ያህል ሲሆን መላዉን በገድል መጽሐፋቸውና በስንክሳር ያገኙታል።

በመስከረም ፮/6 ፍልሰተ አጽማቸው ነው፤ ይህም ከአብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ነው፣ ታህሳስ ፲፪/12 እረፍታቸው ነው እንዲሁም ወር በገባ ፲፪/12 ደግሞ ወርኃዊ በዓላቸው ነው።

የጻድቁ አባታችን የአቡነ ሳሙኤል ረድኤት በረከት አማላጅነት አይለየን!!!

ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

ወለወላዲቱ ድንግል!

ወለመስቀሉ ክቡር!

ይትባረክ አምላክ አበዊነ!

👉 ሙሉውን በPDF ለማንበብ

✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፯፥፭፡፮]✞✞✞

“እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።

እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።”

✞✞✞[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፷፯፥፴፡፴፩]✞✞✞

“በሸምበቆ ውስጥ ያሉትን አራዊት፥ በአሕዛብ ውስጥ ያሉትን የበሬዎችንና የወይፈኖችን ጉባኤ ገሥጽ፥ እንደ ብር የተፈተኑት አሕዛብ እንዳይዘጉ፤ ሰልፍን የሚወድዱትን አሕዛብን በትናቸው።

መኳንንት ከግብጽ ይመጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።

እግዚአብሔር በቅዱስ ቦታው ለድሀ አደጎች አባት፥ ለባልቴቶችም ዳኛ ነው።

እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤት ያሳድራቸዋል፥ እስረኞችንም በኃይሉ ያወጣቸዋል፤ ዓመፀኞች ግን በምድረ በዳ ይኖራሉ።”

______________________________________

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: