እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on February 7, 2021
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፳፮]
፩ እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር የሕይወቴ መታመኛዋ ነው፤ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው?
፪ ክፉዎች፥ አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ።
፫ ሠራዊትም ቢሰፍርብኝ ልቤ አይፈራም፤ ሰልፍም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ።
፬ እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።
፭ በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና።
፮ እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፤ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ።
፯ አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ። ማረኝና አድምጠኝ።
፰ አንተ ፊቴን እሹት ባልህ ጊዜ። አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ ልቤ አንተን አለ።
፱ ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባሪያህ ፈቀቅ አትበል፤ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተውኝ።
፲ አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ።
፲፩ አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ።
፲፪ የሐሰት ምስክሮችና ዓመፀኞች ተነሥተውብኛልና ለጠላቶቼ ፈቃድ አትስጠኝ።
፲፫ የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር አይ ዘንድ አምናለሁ።
፲፬ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፥ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።
_________________________________
Leave a Reply