ድሀ ይዋረዳል፥ ይጐብጣል፤ በኃያላኑም እጅግ ይወድቃል። እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on January 10, 2021
[መዝሙረ ዳዊት ከ ምዕራፍ ፮ እስከ ፲]
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፱]
፩ አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ።
፪ በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ።
፫ ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ።
፬ ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ።
፭ አሕዛብን ገሠጽህ፥ ዝንጉዎችንም አጠፋህ፥ ስማቸውንም ለዘላለም ደመሰስህ።
፮ ጠላቶች በጦር ለዘላለም ጠፉ፥ ከተሞቻቸውንም አፈረስህ፥ ዝክራቸውም በአንድነት ጠፋ።
፯ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ይኖራል፥ ዙፋኑንም ለመፍረድ አዘጋጀ፤
፰ እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል።
፱ እግዚአብሔርም ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው።
፲ ስምህን የሚያውቁ ሁሉ በአንተ ይታመናሉ፥ አቤቱ፥ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
፲፩ በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ በአሕዛብም መካከል አደራረጉን ንገሩ፤
፲፪ ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቦአልና፥ የድሆችንም ጩኸት አልረሳምና።
፲፫ አቤቱ፥ እዘንልኝ፥ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፥ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ፤
፲፬ ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፤ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ በማዳንህ ደስ ይለኛል።
፲፭ አሕዛብ በሠሩት ጕድጓድ ወደቁ፥ በዚያችም በሸሸጓት ወጥመድ እግራቸው ተጠመደች።
፲፮ እግዚአብሔር ፍርድን በማድረግ የታወቀ ነው፤ ኃጢአተኛው በእጆቹ ሥራ ተጠመደ።
፲፯ ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ።
፲፰ ድሀ ለዘላለም አይረሳምና፥ የችግረኞችም ተስፋቸው ለዘላለም አይጠፋም።
፲፱ አቤቱ፥ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ፥ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው።
፳ አቤቱ፥ ፍርሃትን በላያቸው ጫንባቸው፤ አሕዛብ ሰዎች እንደ ሆኑ ይወቁ።
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፲]
፩ አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ? በመከራም ጊዜ ለምን ትሰወራለህ?
፪ በኃጢአተኛ ትዕቢት ድሀ ይናደዳል፤ ባሰቡት ተንኰላቸው ተጠመዱ።
፫ ኃጢአተኛ በነፍሱ ፈቃድ ይወደሳልና፥ ዓመፀኛም ይባርካል።
፬ ኃጢአተኛ እግዚአብሔርን አበሳጨው፥ እንደ ቍጣውም ብዛት አይመራመረውም በእርሱ ፊት እግዚአብሔር የለም።
፭ መንገዱ ሁሉ የረከሰ ነው፥ ፍርድህም በፊቱ የፈረሰ ነው፥ ጠላቶችንም ሁሉ ይገዛቸዋል።
፮ በልቡ ይላል። ለልጅ ልጅ አልታወክም ክፉም አያገኘኝም።
፯ አፉ መርገምንና ሽንገላን ተንኰልን የተመላ ነው፤ ከምላሱ በታች ጉዳትና መከራ ነው።
፰ በመንደሮች መሸመቅያ ይቀመጣል ንጹሓንን በስውር ይገድል ዘንድ፤ ዓይኖቹም ወደ ድኃ ይመለከታሉ።
፱ እንደ አንበሳ በችፍግ ዱር በስውር ይሸምቃል፤ ድሀውን ለመንጠቅ ያደባል፤ ድሀውን ይነጥቀዋል በአሽክላውም ይስበዋል።
፲ ድሀ ይዋረዳል፥ ይጐብጣል፤ በኃያላኑም እጅግ ይወድቃል።
፲፩ በልቡም ይላል። እግዚአብሔር ረስቶኛል፤ ፈጽሞም እንዳያይ ፊቱን ሰወረ።
፲፪ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ተነሥ እጅህም ከፍ ከፍ ትበል፤ ድሆችን አትርሳ።
፲፫ ኃጢአተኛ ስለ ምን እግዚአብሔርን አስቈጣው? በልቡ። አይመራመረኝም ይላልና።
፲፬ አየኸው፥ አንተ ክፋትንና ቍጣን ትመለከታለህና በእጅህ ፍዳውን ለመስጠት፤ ድሀ ራሱን ለአንተ ይተዋል፥ ለድሀ አደግም ረዳቱ አንተ ነህ።
፲፭ የኃጢአተኛንና የክፉን ክንድ ስበር፥ የኃጢአቱንም ብድራት ክፈል ሌላ እስከማይገኝ ድረስ።
፲፮ እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ አሕዛብ ከምድሩ ይጠፋሉ።
፲፯ እግዚአብሔር የድሆችን ምኞት ሰማ፥ ጆሮውም የልባቸውን አሳብ አደመጠች፥
፲፰ ፍርዱ ለድሀ አደግና ለችግረኛ ይደረግ ዘንድ፥ ሰዎች በምድር ላይ አፋቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ እንዳይደግሙ።
_____________________________
Leave a Reply