👉 መዝሙረ ዳዊት ከምዕራፍ ፺፩ እስከ ምዕራፍ ፻
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፺፩]
፩ እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፥ ልዑል ሆይ፥ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤
፪ በማለዳ ምሕረትን፥ በሌሊትም እውነትህን ማውራት
፫ አሥር አውታር ባለው በበገና፥ ከምስጋና ጋርም በመሰንቆ።
፬ አቤቱ፥ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና።
፭ አቤቱ፥ ሥራህ እጅግ ትልቅ ነው፥ አሳብህም እጅግ ጥልቅ ነው።
፮ ሰነፍ ሰው አያውቅም። ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም።
፯ ኃጢአተኞች እንደ ሣር ሲበቅሉ ዓመፃ የሚያደርጉ ሁሉ ሲለመልሙ፥ ለዘላለም ዓለም እንዲጠፋ ነው።
፰ አቤቱ፥ አንተ ግን ለዘላለም ልዑል ነህ፤
፱ አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዓመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና።
፲ ቀንዴ አንድ ቀንድ እንዳለው ከፍ ከፍ ይላል፤ ሽምግልናዬም በዘይት ይለመልማል።
፲፩ ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አየች፥ ጆሮዬም በእኔ ላይ በቆሙ በክፉዎች ላይ ሰማች።
፲፪ ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፥ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል።
፲፫ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል፥ በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ።
፲፬ ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ።
፲፭ አምላኬ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ሆነ ይነግራሉ፥ በእርሱም ዘንድ ዓመፃ የለም።
👉 አቤቱ፥ እነሆ፥ ጠላቶችህ ይጠፋሉና፥ ዓመፃንም የሚሠሩ ሁሉ ይበተናሉና
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፻]
፩ አቤቱ፥ ምሕረትንና ፍርድን እቀኝልሃለሁ።
፪ እዘምራለሁ፥ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ፤ ወደ እኔ መቼ ትመጣለህ? በቤቴ መካከል በልቤ ቅንነት እሄዳለሁ።
፫ በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም፤ ሕግ ተላላፊዎችን ጠላሁ።
፬ ጠማማ ልብም አልተጠጋኝም፤ ክፉ ከእኔ በራቀ ጊዜ አላወቅሁም።
፭ ባልንጀራውን በቀስታ የሚያማን እርሱን አሳደድሁ፤ በዓይኑ ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም።
፮ ከእኔ ጋር ይኖሩ ዘንድ፤ ዓይኖቼ በምድር ምእመናን ላይ ናቸው፤ በቀና መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል።
፯ ትዕቢትን የሚያደርግ በቤቴ መካከል አይኖርም፤ ዓመፅን የሚናገር በዓይኔ ፊት አይቀናም።
፰ ዓመፃ የሚያደርጉትን ሁሉ ከእግዚአብሔር ከተማ አጠፋቸው ዘንድ፥ የምድርን ኃጢአተኞች ሁሉ በማለዳ እገድላቸዋለሁ።
__________________________