ጠላቶችህ መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፤ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on November 29, 2020
“አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው“
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፸፫]
፩ አቤቱ፥ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ?
፪ አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዤሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርስዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ።
፫ ጠላት በቅዱሳንህ ላይ እንደ ከፋ መጠን፥ ሁልጊዜም በትዕቢታቸው ላይ እጅህን አንሣ።
፬ ጠላቶችህ በበዓል መካከል ተመኩ፤ የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ።
፭ እንደ ላይኛው መግቢያ ውስጥ በዱር እንዳሉም እንጨቶች፥ በመጥረቢያ በሮችዋን ሰበሩ።
፮ እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት።
፯ መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፤ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ።
፰ አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ።
፱ ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ የለም፤ እስከ መቼ እንዲኖር የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም።
፲ አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ሁልጊዜ ያቃልላልን?
፲፩ ቀኝህንም በብብትህ መካከል፥ እጅህንም ፈጽመህ ለምን ትመልሳለህ?
፲፪ እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።
፲፫ አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ።
፲፬ አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።
፲፭ አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፤ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ።
፲፮ ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፤ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ።
፲፯ አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።
፲፰ ይህን ፍጥረትህን አስብ። ጠላት እግዚአብሔርን ተላገደ፥ ሰነፍ ሕዝብም ስሙን አስቈጣ።
፲፱ የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፤ የችግረኞችህን ነፍስ ለዘወትር አትርሳ።
፳ ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በኅጥኣን ቤቶች ተሞልተዋልና።
፳፩ ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፤ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ።
፳፪ አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፤ ሰነፎች ሁልጊዜም የተላገዱህን አስብ።
፳፫ የባሪያዎችህን ቃል አትርሳ፤ የጠላቶችህ ኵራት ሁልጊዜ ወደ አንተ ይወጣል።
______________________
Leave a Reply