አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ሞት ጕድጓድ ታወርዳቸዋለህ፤ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፤ እኔ ግን፥ አቤቱ፥ እታመንሃለሁ።
[መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ፶፬]
፩ አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል።
፪ ተመልከተኝ ስማኝም። በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፤
፫ ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፤ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና።
፬ ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ።
፭ ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ።
፮ በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ!
፯ እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፤
፰ ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ።
፱ አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው እንደበታቸውንም ቍረጥ።
፲ በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፤ ዓመፃና ድካም ኃጢአትም በመካከልዋ ነው፤
፲፩ ተንኰልና ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቁም።
፲፪ ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፤ የሚጠላኝም ራሱን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር።
፲፫ አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፤
፲፬ መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፤ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን።
፲፭ ሞት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና።
፲፮ እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እግዚአብሔርም ሰማኝ።
፲፯ በማታና በጥዋት በቀትርም እናገራለሁ እጮኽማለሁ፥ ቃሌንም ይሰማኛል።
፲፰ በእኔ ላይ ብዙ ነበሩና ከሚቃረቡኝ ነፍሴን በሰላም አድናት።
፲፱ ቤዛ የላቸውምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ከጥንት ጀምሮ የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቍላቸዋል።
፳ ከእርሱ ጋር ሰላም በነበሩት ላይ እጁን ዘረጋ፤ ኪዳኑንም አረከሱ።
፳፩ አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው።
፳፪ ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።
፳፫ አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ሞት ጕድጓድ ታወርዳቸዋለህ፤ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፤ እኔ ግን፥ አቤቱ፥ እታመንሃለሁ።
_________________________