Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • May 2020
    M T W T F S S
     123
    45678910
    11121314151617
    18192021222324
    25262728293031
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

ድንቁ አባታችን ቅዱስ ያሬድ እዚህ ነው የተሠወረው

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on May 20, 2020

በሰሜን ኢትዮጵያ በጠለምት ደብረ ሐዊ የሚገኘውና ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበት ድንቅ ገዳም ይህ ነው።

  • ቅዱስ ያሬድ የዜማ ሊቅ ብቻ አይደለም። አቡነ ያሬድ የቅድስት ቤተክርስቲያን ጌጧና መሠረቷ ሕይወቷና እስትንፋሷ ነው።
  • አቡነ ያሬድ የመጽሐፍ መምህር(ብሉያትንና ሐዲሳትን የሊቃውንትንም መጻሕፍት አስማምቶ የተረጐመ) ነው።
  • አቡነ ያሬድ ባለቅኔ (የቅኔ ጀማሪ) ነው።
  • አቡነ ያሬድ ልዑለ ስብከት ነው።
  • አቡነ ያሬድ ሰማዕት ነው።
  • አቡነ ያሬድ ባሕታዊ ነው።
  • አቡነ ያሬድ መናኝ ነው።
  • አቡነ ያሬድ የሱራፌል አምሳያ ነው።
  • አቡነ ያሬድ ጥዑመ ልሳን ነው።
  • ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያን እንዚራ ነው።
  • ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ነው።
  • ቅዱስ ያሬድ መዓርዒረ ዜማ ነው።
  • አቡነ ያሬድ ካህን (ካህነ ስብሐት) ነው።
  • ቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ ነው።
  • ቅዱስ ያሬድ መዘምር ዘበድርሳን
  • ቅዱስ ያሬድ ሊቅ (ርእሰ ሊቃውንት)
  • ቅዱስ ያሬድ ዓርከ ሊቃውንት
  • አቡነ ያሬድ መንፈሳዊ ደራሲ ነው።
  • ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ብርሃን ነው።
  • አንደበቱ ጣፋጭ (ጥዑም) የኾነ
  • እግሮቹ በመልካም መንገድ የሚጓዙና ወደ መልካም መንገድ የሚያስጕዙ
  • ልቡናው የቅድስና ማኅደር የኾነ
  • ሕሊናው የምሥጢራት ሠረገላ የኾነ
  • አእምሮው የመጠቀ
  • ድርሰቱ የተራቀቀ
  • እስከ አርያም ተነጥቆ ዕፁብ ድንቅ ምሥጢራትን የተመገበ የሱራፌል አምሳያቸው ነው።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ቅዱስ ያሬድን እንዲህ ሲል ያመሰገነው፦

የመንፈስ ቅዱስ ምግብን የጠገበ፤ ከመጻሕፍት ኹሉ ትርጓሜያተ ድርሰትን ያሰባሰበ፤ ሃሌ ሉያ በሚል ምስጋና የኢትዮጵያ ሀገርን በጥዑም ማሕሌትና በሚያምር ምስጋና ያስጌጠ፤ የመለኮት ቃልን በላይዋ ላይ እንደ ንጹሕ የወርቅ ሻሻቴ ያፈሰሰ ለኾነ ለካህኑ ያሬድ ሰላምታ ይገባል

ሰላም ለያሬድ ቀሲስ ዘጽጉብ እክለ መንፈስ ቅዱስ፤ ዘአስተጋብአ ምድራሳተ እምኲሎሙ መጻሕፍት

ወአሰርገዋ በሐዋዝ ስብሐት ወበጥዑም ማሕሌት ለብሔረ ኢትዮጵያ በስብሐት ሃሌ ሉያ ዘከዐወ ቃለ መለኮት ዲቤሃ ከመ አስራበ ወርቅ ንጹሐ።

ቅዱስ ያሬድ አክሱም ጽዮንን እየተሳለማት ሣለ ክብርት እመቤታችን ለቅዱስ ያሬድ ተገልጣለት ቅዱስ ኤፍሬምንና ቅዱስ አባ ሕርያቆስን በአካለ ነፍስ አምጥታ ድርሰታቸውንና ቅዳሴያቸውን እንዲያሰሙት በማድረግ ቅዱስ ያሬድንም ዜማውን እንዲደርስ እረድታዋለች፡፡ ኹለቱንም ታላላቅ ቅዱሳን ነጥቃ ወደ ቅዱስ ያሬድ ካመጣቻቸው በኃላ “አንተ ውዳሴዬን፣ አንተ ቅዳሴዬን ነግራችሁት በዜማ ያድርስ” ብላቸው እነርሱም ለቅዱስ ያሬድ ነግረውት በዜማ አድርሶታል፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመልክ በመልኩ እያደረገ ዜማውን ደረሰው፡፡ ዜማውንም ሲጨርስ የብርሃን እናቱ እመ አምላክ በያዘችው የብርሃን ባርካው ተስፋውን ነግራው ዐርጋለች፡፡

ይኽም የቅዱስ ያሬድ ድርሰቱ መነሻውም ሆነ መድረሻው ፍጹም መንፈሳዊ እንደሆነ ያሳያል። አባቶቻችንም ይኽን መንፈሳዊ መገለጥ በሥዕልም ጭምር ገልጠውታል። (ሽሬ መድኃኔዓለም ቤ/ክ ይኽ ዓይነት ሥዕል ከሚገኙበት ገዳማት ውስጥ የሚገኘው አንዱ ነው።)

አቡነ ያሬድ ይባርክበት የነበረው የእጅ መስቀሉ በ1985 .ም በሆድ አደር ሌቦች አማካኝነት ተሰርቆ ከሀገር ወጥቶ ነበር። በፈረንሳይ ሀገር ለጨረታ ቀርቦ በ15 ሚሊዮን ዶላር ተሸጦ ነበር። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ተሰርቆ ከወጣ ከ18 ዓመት በኃላ በ2003 ወደ አገራችን ተመልሶ መጥቷል። ሊመለስ የቻለውም ሚስተር ዣክየተባሉ በጎ አሳቢ ሰው “…ይህን መስቀል ኢትዮጵያ ውስጥ ጎብኝቼዋለሁ፣ የኢትዮጵያ ንብረት ነውበማለት ወደ ሀገራችን እንዲመለስ ከሌሎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ልጆች ጋር በተደረገ ርብርብ ጨረታውን በ15 ሚሊዮን ዶላር አሸንፈው የአቡነ ያሬድን የእጅ መስቀል ወደ አገራችን መልሰውታል። አምላከ ቅዱስ ያሬድ ክብር ያድልልን በእውነት!

አቡነ ያሬድ በምናኔ በኖረበት ቅዱስ ቦታ ላይ በስሙ ገዳም ተገድሞ መናንያን አሰረ ፍኖቱን ተከትለው ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው፣ በረዶውንና ውርጩን ታግሠው በስሙ እየተማጸኑ ይኖራሉ፡፡ በቦታው እሁድ እሁድ ከመሬት ውስጥ የከበሮ ድምጽ ይሰማል፣ ቅዱስ ያሬድ መቋሚያውን ወርውሮ ያፈለቀው ፀበል ዛሬም አለ፡፡ ጻድቁ በተሰወረበት በደብረ ሐዊ ተራራ ላይ ብርድ በእጅጉ በጸናበትና በረዶ በሚፈላበት በዚያ አስቸጋሪ ቦታ ላይ እጅግ አስቸጋሪውን የአየር ጠባይ ተቋቁሞ በቦታው ላይ ቢያንስ 7 ቀን ሱባዔ የሚይዝ ካለ ራሱ ቅዱስ ያሬድ እንደሚገለጥለት በቦታው ላይ የሚገኙ አባቶች ይናገራሉ።

አክሱም አቅራቢያ ቁጭ ብሎ ከትሏ ምሳሌ ወስዶ በተማረበት ቦታ ላይ አንዲት እናት ብቻዋን ለቅዱስ ያሬድ አስደናቂ ቤ/ክ በ2010 .ም አሠርታለታለች። ይኽም ለጻድቁ ለአቡነ ያሬድ ተስላ ስለቷ ደርሶላት እንደሆነ በቦታው ላይ ተነግሮናል። ይኽም ድንቅ ምስክርነት አቡነ ያሬድ ከዜማ ደራሲም በላይ መሆኑን አንድ ማሳያ ነው። በጸሎቱ ሀገርን የሚጠብቅ ባሕታዊ፣ በስሙ ለሚማጸኑት ሁሉ ከአምላኩ ዘንድ ምሕረትን የሚለምን ደገኛ ጻድቅ መሆኑን አንድ ማሳያ ነው።

የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ አካሏና ብርሃኗ የኾነው አቡነ ያሬድ እንደነ ሄኖክና ኤልያስ ሞትን ሳያይ የተሰወረው በዛሬዋ ዕለት ነው። የከበረች በረከቱ ትደርብን! በጸሎቱ ይማረን!!!

___________________________________

Leave a comment