Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • November 2019
    M T W T F S S
     123
    45678910
    11121314151617
    18192021222324
    252627282930  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

እጹብ ድንቅ ነው | ህመምተኞች በንቡ የሚፈውሱበት ተዓምረኛው “ንቡ ቅዱስ ሚካኤል”

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on November 21, 2019

በእውነት እናት ኢትዮጵያ ብዙ እጹብ ድንቅ የሆኑ ምስጢሮችን የያዘች ተዓምረኛ አገር ናት።

ንቡ ሚካኤል” በአዲስ አበባ፡ አያት የሚባለውን ቦታ አለፍ ብሎ በሻሌ ኮረብታ ላይ የሚገኝ ቤተክርስቲያን ነው። ወደዚህ ቤተክርስቲያን እንዴት እነደመጣሁ ሁሉ አላውቅም፤ ቅዱስ ሚካኤል ነው ያመጣኝ።

የንቡ ቀፎ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ነው ያለው። የንቡም መንጋ ቤተልሔም ውስጥ ገብቶ እስከአሁን ድረስ ሰፍሮ ይገኛል። በቅዳሴ ሰዓትና ታቦት በሚወጣበትም ጊዜ ሁሉ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ንቡ ይወጣል። በንብ የሚነደፍ ከተለያዩ በሽታዎች ይፈወሳል። ንቦቹ ዝም ብለው አይናድፉም፤ የተፈቀደለት ሰው ነው ሊነደፍ የሚችለው። ይሄን እንደሰማሁ በጣም ተደስቼ ጢናማ ያደረገኝ ቸሩ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ዶክተር ካየሁ ሃያ ዓመት ገደማ ሆኖኛል ፥ ግን ሳጥናኤል አገር እየተኖረ ጋኔን መግቢያ ቀዳዳ አያጣምና በቃ ንቦቹ በውስጤ ሊኖር የሚችለውን መርዝ ነቅለው ሊያወጡልኝ ነው ብዬ ቤተክርስቲይኑን መዞር እንደጀመርኩ ከየት እንደመጣ ያላየሁት አንድ ጎረመሳ ልጅ አብሮኝ ይዞር ጀመር(አልፎ አልፎ ቪዲዮው ላይ ይሰማል)“ከየት መጣህ? ትምህርት ቤት የለህም እንዴ? እንዴት ወደዚህ ብዙ ሰው ወደ ሌለበት ቦታ መጣህ?” ብዬ ጠየቅኩት። እርሱም፡ አይ መንገድ ላይ ከጓደኞቼ ጋር በመኪና መጥተን ተጠፋፋን፣ ከዚያም እኔ ዝም ብዬ ወደዚህ መጣሁአለኝ። ትህትና ያለው ስለነበር አመንኩት። ንቦቹ ቢነድፉኝ በማለት ቤተክርስቲያኑን መዞሩን ቀጠልኩ ግን አሁንም አብሮኝ ይዞራል። በቃ ስላልተነደፍኩ ራመድ ብዬ ከአንዲት ሱባኤ ከያዙና ደስ ከሚሉ እናት ጋር ማውራት ጀመርኩ። ስለቤተክርስቲያኑ በይበልጥ ማወቅ ከፈለግክ በጥቅምት ተመልሰህ ና፤ ያኔም ማር ይቆረጣል ፈውስ ነው ይዘህ ትሄዳለህ አሉኝ። እኔም ከምስጋና ጋር በጥቅምት ስለምጓዝ እንደማልችል አሳውቂያቸውና ተሰናብቻቸው ድንቅ የሆነ ቦታ ላይ ካለው የቤተክርስቲያን ግቢ ወጣሁ። አሁንም ያ ጎረምሳ ተከትሎኝ መጣ፤ እስኪ ባክህ ወደ አያት የሚወሰደው ታክሲ የሚቆምበትን ቦታ አሳየኝአልኩት፤ ቦታውን ካሳየኝ በኋል ሞባይሉን አውጥቶ መደወል ጀመረ። መንገዱ በጣም ጭር ያለ ነው፣ መኪናም ብዙ የለም። በዚህ ጊዜ ከአውቶብስ ማቆሚያው ፊት ለፊት አንድ የስልክ ምሰሶ ላይ ነጭና ጥቁር ቀለም ያለው ቁራ ወደ እኛ አቅጣጫ ሲጮህ ይሰማል። በጣም የሚገርም ነው፤ ጉሮሮው እስኪወጣድርስ በኃይል ነበር የሚጮኸው። ምን እያለን ይሆን?” አልኩት ለልጁ፡ በዚህ ሰዓት መልስ ሳይሰጠኝ ፊቱ ሲለዋወጥ አየሁት። በዚህ ጊዘ አንድ ታክሲ ከች አለ። እንደገባሁ ታክሲው በቅዱስ ሚካኤል እና ቅዱስ ገብርኤል ስዕሎች የደመቀ ነበር። ዋው! ቅዱስ ሚካኤል በቁራው በኩል ስለሆነ ነገር እያስጠነቀቀኝ ነበርአልኩ፤ በጣም በመገረምና በመደሰት።

ከሁለት ቀን በኋላ፡ ማታ ላይ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስቲያን አካባቢ ሦስት ቻይናዎች ወደ ዘረጓቸው እጆቻቸው ሞባይላቸውን አብርተው አየሁና እንግሊዝኛ ትችሉ ይሆን ምን ችግር ገጠማችሁ?” አልኳቸው። እነርሱም በጠራ እንግሊዝኛ እጃችንን ቢንቢዎችን ልናስነክስ ፈልገን ነው፤ ቢንቢዎች ጎጂ ባክቴሪያዎችን ያጠፉልናል፤ እዚህ አገር አየሩ ቆንጆ ስለሆነ ጤናማ ቢንቢዎች ናቸውአሉኝ። ቻይኖቹ ትክክል ናቸው፤ በቅድስት ኢትዮጵያ ንቦቹና ቢንቢዎቹ መድኃኒቶቻችን ናቸው፣ አዕዋፋቱና እንስሳቱ ረዳቶቻችን ናቸው። ቸሩ እግዚአብሔር ለሕዝባችን ሁሉንም ነገር በነፃ አዘጋጅቶለት ሳለ፡ ከወጣት እስከ አዛውንቱ ለቀላል በሽታ የፈረንጁን ኪኒንና መርፌ በውድ ገንዘብ ሲሸምት ሳይ በጣም አዝናለሁ።

በአውሬው መዳፍ ሥር የሚሰቃዩትን ወገኖቻችንን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በዕለተ ቀኑ ይድረስላቸዉ ካሉበት መከራና ስቃይ በምልጃው ያውጣቸው! የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከመከራ ታዳጊ ቅዱስ ሚካኤል ነውና የሃገራችን ጠባቂ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ረድኤት በረከቱ ከሁላችን አይለየን!!!


ተዓምረኛው በሻሌ ንቡ ቅ/ሚካኤል እናሰማዕቱ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን


በንብ መንጋ የተከበበው የበሻሌ(ንቡ) /ሚካኤል፣ ቅ/እስጢፋኖስ እና ወአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ቤተክርስቲያን አመሰራረትና ገቢረ ተዓምራት አጭር መግለጫ

ቤተክርስቲያኑ ከመመስረቱ በፊት በቦታው ላይ ሲከናወኑ የነበሩ ልዩ ልዩ ተዓምራት፡

1. ለብዙ ዓመታት ከተለያየ ቦታ ተጣልተው የነበሩ ምዕመናን ቦታው ላይ እየመጡ እርቀ ሰላም ሲፈጽሙበት ኖረዋል፤

2. ቤተክርስቲያኑ ከተተከለበት ቦታ ትልቅ የጽድ ዛፍ ላይ የሚወጣው ሙጫ እንደ እጣን ጢስ ሽታ ለብዙ ዓመታት አካባቢውን መዓዛው (ሽታው) ያውድ ነበር፡፡

3. በዚሁ ቦታ ላይ ሌሊት ሌሊት የመላዕክት ዝማሬ (ጣዕመ ዜማ) የከበሮ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ በዕድሜ የገፉ የአካባቢው አዛውንቶች ተናግረዋል፡፡

4. በአካባቢው ከሚኖሩ ምዕመናን መካከል በመልካም ስራቸው የታወቁና ከ90 ዓመት በላይ ዕድሜ የነበራቸው እናት የቅዱስ ሚካኤል ታቦት(ጽላት) እንደሚተከል በተደጋጋሚ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይናገሩ ነበር፡፡

5. ቀደም ሲል በእነ አብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት አካባቢ ጀምሮ ከተለያየ አካባቢ የሞቱ አባቶች አስከሬናቸው እየመጣ በቤተመቅደሱ ስለሚገኘው የንብ መንጋ አገባብ(አመጣጥ)

እግዚአብሔር አስቀድሞ ቦታውን ስለመረጠው፡

1. ሕዳር 12 ቀን 2002 .ም የቅዱስ ሚካኤል በዓል ሲከበር በዋዜማው ሊቃውንቱ በአገልግሎት ላይ እንዳሉ ማለትም ሕዳር 11 ቀን 2002 .ም ከቀኑ 900 ሰዓት ገደማ ከምስራቅ አቅጣጫ የንብ መንጋ መጥቶ የቃል ኪዳኑ ታቦት በሚገኝበት በመንበሩ ውስጥ ገብቶ ካደረ በኋላ በነጋታው ታቦቱ ወጥቶ በሚከበረበት ጊዜ ንቡ ከመንበሩ ወጥቶ እንደ ደመና ረቦ ካሉት

ምዕመናን ጋር ታቦቱን ዙሮ አክብሯል፡፡ በዕለቱም ይህን አስደናቂ ታምር ያዩና የተመለከቱ ምዕመናንም በከፍተኛ ድምጽ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡

2. ሕዳር 11 ቀን 2004 .ም የድንግል ማርያም ዕለት ካህናቱ ቅዳሴ ገብተው በሚቀድሱበት ጊዜ ቅዱስ ወንጌል ሲነበብ የንብ መንጋ መጥቶ ከቤተክርስቲያኑ ጉልላት ላይ የመስቀል ምልክት ሰርቶ ከሰፈረ በኋላ ከቀኑ 1100 ሰዓት ላይ ተነስቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ወደ ቤተልሔም ውስጥ ገብቶ እስከአሁን ድረስ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

3. ታህሳስ 9 ቀን 2004 .ም ከቀኑ 900 ሰዓት የንብ መንጋ መጥቶ ከቤተክርስቲያኑ ጎን ላይ ከሰፈረ በኋላ ከቀኑ 1130 ተነስቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ወደ ግብር ቤት ገብቶ እስከአሁን

ድረስ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

4. ታህሳስ 19 ቀን 2005 .ም የቅዱስ ገብርኤል ዕለት ካህናት ቅዳሴ ገብተው በሚቀድሱበት ጊዜ ቅዱስ ወንጌል ሲነበብ የንብ መንጋ መጥቶ በሴቶች መግቢያ በር ወደቤተክርስቲያኑ ከገባ በኋላ በቀጥታ ወደ ቤተመቅደሱ ውስጥ ገብቶ በአጎበሩ ላይ ሰፍሯል፡፡ ይህ በቤተክርስቲያናችን ላይ ያለው የንብ መንጋ ማሩ ተቆርጦ በተለያየ ጊዜ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ተሰጥቶ ከአገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በጉበት፣ በካንሰር፣ በኪንታሮት፣ በስኳር፣ በአስም፣ በጨጓራ፣ በኩላሊት፣ በደም ግፊት፣ በኤች አይ ቪ፣ ሽባዎች፣ አይነስውራን፣ አፈ ዲዳዎወች፣ መስማት የተሳናቸው፣ በጭንቀትና በልዩ ልዩ በሽታ የታመሙ ሰዎች ማሩን በልተው ጸበሉን ጠጥተው እምነቱን ተቀብተው ከበሽታቸው ተፈውሰው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እንዲሁም ለብዙ ዓመታት ልጅ አጥተው የነበሩ ሰዎች (መካኖች) በአንድ ጊዜ ሁለት ልጆች መንታ እንዲሁም በአንድ ጊዜ ሶስት ልጆች መንታ ወልደው

ታቅፈው መጥተው ጥምቀተ ክርስትናቸውን በዚሁ ቤተክርስቲያን እንዲፈፀም ማድረጋቸውና ሌሎች በዚህ አነስተኛ ጽሁፍ ሊገለፁ የማይችሉ በርካታ ገቢረ ተዓምራትና ፈውሶች እስከአሁኗ ሰዓት እየተደረጉ ናቸው፡፡ ክብርና ምስጋና ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ይሁን አሜን፡፡

በእግዚአብሔር ፈቃድ በንቦቹ የተደረገው ተዓምራት በከፊል

1. ሕዳር 12 ቀን 2002 .ም የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል ታቦቱ ወጥቶ በሚከበርበት ጊዜ ከቤተመቅደሱ ያለው ንብ ወጥቶ ታቦቱን አክብሯል፡፡

2. 2003 .ም የስቅለት በዓል ሲከበር ንሴብሆ እየተባለ በሚዘምርበት ጊዜ ንቡ ወጥቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ገብቷል፡፡

3. መጋቢት 12 ቀን 2004 .ም የቅዱስ ሚካኤል ወርሃዊ በዓል ቅዳሴ እየተቀደሰ ሳለ የቤተመቅደሱ ንብ ከመንበሩ ላይ የመስቀል ምልክት ሰርቶ (ሰፍሮ) ታይቷል፡፡

4. ሕዳር 11 ቀን 2005 .ም ንቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባበትን ዕለት ለማስታወስ ከቀኑ 400 ሰዓት ላይ ንቡ ወጥቶ ቤተክርስቲያኑን ዙሮ ገብቷል፡፡

5. 2005 .ም ፀሎተ ሐሙስ የሕጽበተ እግር ጸሎት ሲከናወን የመቅደሱ ንብ ወጥቶ ፀበሉ ላይ ሰፍሮ (ረቦ)ታይቷል፡፡

6. 2006 .ም እሁድ የሆሳዕና በዓል ሲከበር ሆሳዕና በአርያም እየተባለ እየተዘመረ ዑደት በሚደረግበት ጊዜ ብዙ ምዕመናን ባለቡት የቤተመቅደሱ ንብ ወጥቶ ዞሮ ገብቷል፡፡ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ ለዘላለሙ አሜን፡፡

ሥርዓተ ቀብር ሲፈጸምበት የቆየ እና በተለያየ ጊዜ የቀስተ ደመና ብርሃን በመቃብሩ ላይ ይታይ እንደነበር በአካባቢው የሚኖሩ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች በግልጽ መስክረዋል፡፡ ዛሬም መቃብሩ በግልጽ ይታያል፡፡ ይህ ሁሉ ታሪክ ሲከናወን ከቆየ በኋላ እግዚአብሔር የፈቀደው ጊዜ ሲደርስ በአካባቢው ከሚኖሩ በዕድሜ ከገፉ አዛውንቶች መካከል በአንድ አርሶ አደር ምዕመን አማካኝነት በእግዚአብሔር ፈቃድ በተደጋጋሚ ራዕይ ተገልጾላቸው ያርሱበት የነበረውን ይዞታቸውን መሬት

ለዚህ ታቦት መትከያ ቤተክርስቲያን እንዲሰራ መሬት በመስጠት አሁን በሚገኘው መቃኞ ቤተክርስቲያን ግንቦት 12 ቀን 2001.ም ታቦቱ ሊገባ ችሏል፡፡

አድራሻ፡

በአዲስ አበባ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 10 የሚገኝ ሲሆን ከተለያየ አቅጣጫ ተነስተው መገናኛ ከመገናኛ ሲ.ኤም.ሲ መሪ አያት የሚለውን ትራንስፖርት ይዘው አያት አደባባይ ይውረዱ፡፡ ከአያት አደባባይ ባጃጆች እና ታክሲዎች በሻሌ ንቡ ሚካኤል እና እስጢፋኖስ ካሉ እስከ ቤተክርስቲያኑ ያደርሰዎታል፡፡

እንኳን ለቅዱስ ሚካኤል አመታዊ በዓል አደረሰን!

ይልቃል እርሱ❖

ይልቃል እርሱ ከመላእክት

ትሑት ነው አዛኝ ለፍጥረታት

በክብሩ ምድር ትበራለች

ታላቅ ነህ ሚካኤል እያለች

✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞

ማን እንደ እግዚአብሔር ስሙ ነው የከበረ

ያስጨነቀንን በምልጃው የሰበረ

አለቃ የሆነ ለአእላፍ መላእክት

ታማኝ ባለሟል የምንዱባን አባት

ሚካኤል ነው እርሱ ሚካኤል ነው

ያሳደገን በረከት ያደለን

✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞

መጎናፀፊያው እሳት ነበልባላዊ

ከምድር ያይደለ ክቡር ነው ሰማያዊ

አሸናፊ ነው ጠላትን ድል አድራጊ

የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከመከራ ታዳጊ

ሚካኤል ነው እርሱ ሚካኤል ነው

ያሳደገን በረከት ያደለን

✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞

ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጠው ኪዳን

በጥልቅ ያሉትን ይሄዳል ለማዳን

ሺዎች በክንፉ ሺዎችን በአክናፉ

ከእሳት የሚያድን ሸሽጎ በእቅፉ

ሚካኤል ነው እርሱ ሚካኤል ነው

ያሳደገን በረከት ያደለን

✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞

አርምሞ ጽርአትት ሳይኖረው መሰልቸት

የሚያሳርገው ተወዳጁን መስዋዕት

በልዑል ዙፋን በፊቱ በሰጊድ

ማነው ስለእኛ በፅኑ ሚማልድ

ሚካኤል ነው እርሱ ሚካኤል ነው

ያሳደገን በረከት ያደለን

✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞ ✞

________________________

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: