ዛሬ፡ ቅዱስ ሚካኤል፡ ድል በተነሳውና በወደቀው በዲያብሎስ ምትክ፡ ሊቀ መላእክት ሆኖ የተሾመበት ዕለት ነው
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on June 19, 2019
እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል አመታዊ በዓል አደረሰን።
ላፍቶ ቅዱስ ሚካኤል ፥ ፳፻፲ ወ ፩ ዓ.ም
መንፍሰን የሚያድስ ሌላ ልዩና ውብ የቤተክርስቲያን ግቢ…ቤተክርስቲያኗን እና ሕፃናት ልጆቿን እንዲህ በትዕግሥት፣ በትጋትና ፍቅር ለሚንከባከቧቸው አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞች እና እህቶች ምስጋና ይገባል። በእውነት አዲስ አበባ የተዋሕዶ ዓብያተክርስቲያናት ባይኖሩ ኖሮ ከተማዋ አዲስ በረሃ ትባል ነበር።
ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖም ጣዕሙ ወታእምሩ ከመኄር እግዚአብሔር። መዝ.፴፫ (፴፬)፯–፰
መላእክት የሚለው ቃል መልእክተኞች ‘ተላላኪዎች‘የእግዚአብሔር ይቅርታ ወደ ሰው የሰውን ልመና ወደእግዚአብሔር የሚያደርሱ‘ የእግዚአብሔር ልዩ ወዳጆች ማለት ነው፡፡ በሌላ መልኩ አለቆች ገዥዎች ወይም የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ማለት ይሆናል፡፡ ሚካኤል ማለት “መኑ ከመ እግዚአብሔር ‘እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?” ማለት ነው፡፡ ሚካኤል በስም ተለይቶ መጠቀስ የተጀመረው በመጽሐፈ ዳንኤል /ዳን.፲፥፲፫‘ ፪፥፩/ ውስጥ ነው፡፡ በመጽሐፈ ሄኖክም ለበርካታ ጊዜያት ተጠቅሷል፡፡ከዚህ ሌላ በብሉይ ኪዳን አዋልድ መጽሐፍት በኪዳነ አብርሃም ውስጥ ተጠቅሶም ይገኛል፡፡
ቅዱስ ሚካኤል ለፍጥረታት ሁሉ የሚራዳና የሚያዝን የምሕረትና የመዳኛ፤ የሰላም መልአክ ነው፡፡ “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል” /ዳን.፲፪፥፩/ በማለት በነቢዩ ዳንኤል የተነገረ ሲሆን በሌላ ቦታ “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ” /ዳን. ፲፥፲፫/ በማለት ያስረዳል፡፡ በዚህ ቃል ላይ ከዋንኞቹ አለቆች አንዱ የሚለውን በመያዝ ሚካኤል ብቻ የመላእክት አለቃ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን የሌሎች አለቅነት የተወሰነ ወይም ዝቅተኛ ሲሆን በአንድ ነገድ ላይ በአንድ የመላእክት ከተማ ላይ ነው፡፡ የቅዱስ ሚካኤል አለቅነት ግን በመላእክት ሁሉ ላይከሆነ ከሌሎቹ ይለያል፡፡ በድርሳነ ሩፋኤል ላይ እንደተገለጸው ሰባት ሊቃነ መላእክት ቢኖሩም አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡
ቅዱስ ሚካኤል አርምሞ ትዕግሥትን የሚወድ መልአክ ነው፡፡ “የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም” ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር በተሰጠው ኃይል ዲያብሎስን ድል የነሣ መልአክ ነው፡፡ “በሰማይ ጦርነት ተነሣ ሚካኤልና እርሱ መላእክት ከዘንዶው ከመላእክቱም ጋር ተዋጉ” /ራእ. ፲፪፥፯/ ይላል፡፡
የቅዱስ ሚካኤል በዓል ሰኔ ፲፪ የሚከበርበት ምክንያት ዲያብሎስን በፈቃደ እግዚአብሔር ተዋግቶ ያሸነፈበት አምላክነትን ሽቶ በወደቀው በዲያብሎስ ምትክ ሊቀ መላእክት ሆኖ የተሾመበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ “ክብር ይግባውና እግዚአብሔር በዚህች ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ከወገኞቹ ከመላእክት ሁሉ በላይ አክብሮ ሹሞታል” ይላል ድርሳነ ሚካኤል
ከዚህ በተጨማሪ ይህ ዕለት ቅዱስ ሚካኤል አፎምያን ያዳነበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ በአንዲት አገር ሃይማኖቱ የቀና ታላቅ መኮንን ከሙ አስተራኒቆስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ሚስቱም አፎምያ ትባላለች፡፡አፎምያ ባልዋ አስተራኒቆስ ታሞ እያለ የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አስሎ እንዲሰጣት ለመነችው፤ እንዳለችው አደረገላትና ባልዋ ሞተ፡፡ ከዚህ በኋላ አፎምያ ባልዋ ያሠራላትን ሥዕል ይዛ በሃይማኖት ጻንታ ስትኖር ዲያብሎስ በተለያየ መልኩ ይፈትናት ጀመር፡፡ አንድ ጊዜ ባልቴት እየመሰለ ሌላጊዜ ሌላ እየሆነ ባል ማግባት እንዳለባት መከራት፡፡ መጽሐፍም ጠቀሰላት፡፡ ከንጉሡ ጋር ማጋባት እንዳሰበ ነገራት እርሷ ግን ማግባት እንደማትሻ እግዚአብሔርን እያገለገለች ኖራ ማለፍ እንደምትፈልግ ነገረችው፡፡ ዲያብሎስ ግን ፈተናውን እያባሰ እያባሰ መጣ፡፡ በመጨረሻ ግን በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል አሳፍራ አዋረደችው፡፡
የሰኔ ሚካኤል ዕለት ዲያብሎስ ዳግመኛ ሊፈትናት መጣ፡፡ ሚካኤል ነኝ አላት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል“/፪ቆሮ.፲፩፥፲፫/ እንዳለ በዚህን ዕለት የቀረባት ራሱን ለውጦ የብርሃን መልአክ መስሎ ነበር፡፡ አፎምያ ግን አስተዋይ ስለነበረች “የብርሃን መልአክ ከሆንክ የመስቀል ምልክት ያለበት በትርህ ወዴት አለ?“ አለችው፡፡ በኛ በመላእክት ዘንድ የመስቀል ምልክት አይደረግም አላት፡፡ እርሷም ስለተጠራጠረችው የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ልታመጣ ወደ ሥዕል ቤቷ ስትገባ ዘለለና አነቃት፡፡ አፎምያ ጮኸች፤ ቅዱስ ሚካኤልም ፈጥኖ ደርሶ አዳናት ዲያብሎስንም አዋረደላት፡፡
ዲያብሎስ አፎምያ ያሰበችውን ጸጋ ሆኖ የተሰጣትን ኑሮ ትታ በተለየ ዓለም እንድትኖር እንደ መከራት በእኛም ሕይወት እንዲህ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በጋብቻ ወቅት ምንኵስናን እንድናስብ‘ በዕርቅ ሰዓት ጥላቻ እንዲሰማን‘ በሰላም ጊዜ ጦርነትን‘ በጾም ጊዜ ምግብን‘ በትዕግሥት ጊዜ ቁጣን በመረጋጋት ጊዜ አድመኝነትን በውስጣችን ሊያኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደ አፎምያ በእምነትና በምግባር ጸንተን በማስተዋል ልንኖር ይገባል፡፡
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
ምንጭ፡– ሐመር ፲፻፺፭ ግንቦት/ሰኔ
…………ሚካኤል ሆይ! የችግረኛውን ሁሉ ጸሎት ፈጥነው ለሚሰሙ አዕዛኖችህ ሰላምታ ይገባል። የይቅርታ መልአክ ሆይ! ችግሬን አቃልልኝ፤ ጭንቀቴንም አስወግድልኝ። ምክርን ትለግሰኝ ጥበብንም ታስተምረኝ ዘንድ አባት እንዳደረግሁህ አንተም ልጅ አድርገኝ።…………
ሚካኤል ሆይ ! ዳንኤል በአምሳለ አናብስት ምሳሌ ያየውን ሥውሩን ራእይ አብራርቶና ግልጥልጥ አድርጎ ለተረጎመለት አንደበትህ ሰላምታ ይገባል። የሰላም መልአክ ሆይ የምስጋናን መሥዋዕት የምታዘጋጅ አንተ ነህና ጠላት ዲያብሎስ ተረማምዶ በእደ ፃዕረ ሞት እንዳያፍነኝ በአፌ ላይ ጥበቃህን አጠንክር።…………
የቅዱስ ሚካኤል አምላክ ሆይ! በአርአያህ በአምሣልህ የፈጠርከን ሕዝቦችህን ሁሉ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሠውረን ለዘላለሙ አሜን።
ቅዱስ ሚካኤል ወዳጅ ነህ ለሁሉ
ዛሬም ቆመሃል በኪዳንህ ላሉ
ክንፍህን ዘርጋ ሚካኤል ቅደም ከፍቴ
ምራኝ መንገዱን እንዳይመሽ ልድረስ አባቴ
እንደት ይገፋል ጎዳናው ያላንተ እርዳታ
ጥመን ቁረጠው በቤትርህ “ጭንጫውን ምታ“(፪)
ተጠመጠመ ጠላት በሳት ሰንሰለት
የጌታ መላአክ ሚካኤል በሰይፍ ወድቆበት
የለም በቦታው ስመለስ አጥቸዋለሁ
የምረዳኝን ተሹሞ “አይቸዋለሁ“(፪)
ከመቃብሩ ድንጋዩን አንከባለሃል
ስለረዳህው ዳንኤል እጅግ ወዶሃል
ይነዋወጣል ባህሩ አንተ ስትመጣ
እግዚአብሔር ይንገስ ድያብሎስ “መድረሻ ይጣ“(፫)
አለኝ ትዝታ በቤትህ ከልጅነቴ
ስትራራልኝ እያየው ጸንቷል ጉልበቴ
ልዘምር እንጅ ላመስግን ታላቁን ጌታ
አንተን የሰጠኝ ጠባቅ “በቀን በማታ“(፪)
ቅዱስ ሚካኤል ወዳጅ ነህ ለሁሉ፤ ዛሬም ቆመሃል በኪዳንህ ላሉ። አሜን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ስለ እኛ ስለሰው ልጆች በጌታ ፊት ቁምልን ምልጃና ጸሎትህ ተራዳእነትህ ጥበቃህ ለዘወትር አይለየን!! አሜንንንንንን።
Leave a Reply