ልደታ ለማርያም | ማርያምስ ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች (ቅዱስ ያሬድ)
Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on May 8, 2019
እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በአል በሰላም አደረሰን!
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለእመቤታችን ልደት “ማርያምሰ ተኀቱ እምትካት ውስተ ከርሱ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዓዳ/ ማርያምስ (ማርያም ግን) ከጥንት ጀምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቁ ታበራለች፡፡” በማለት እርሷ በደፈረሰው ዓለም በንጽሕና፣ በቅድስናና በድንግልና ስታበራ እንደነበርና ኋላም የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መውለዷን አመስጥሮ ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም ስለ ሥርወ ልደቷ “እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕጹቂሃ…ሐረገ ወይን/ ሥሮቿ በምድር ጫፎቿም በሰማይ ያሉ…የወይን ሐረግ” በማለት የተወለደችው በምድር ከነበሩት ኢያቄምና ሐና መሆኑን የወለደችው ግን ሰማያዊውን ንጉሥ እንደሆነ በማመስጠር ዘምሯል፡፡ በዚህም ሰውና እግዚአብሔርን ያገናኘች መሰላል መሆኗል ገልጾ አስተምሯል፡፡
“ልደታ” በመባል በተለምዶ በማሳጠር የሚጠራው እና ወር በገባ በአንደኛው ቀን የሚከበረው የወላዲተ አምላክ የቅድስት ድንግል ማርያም ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና በሊባኖስ ተራራ በግንቦት አንድ ቀን የተወለደችበትን ቀን የሚያስታውስ ትልቅ በዓል ነው፡፡ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና ልጅ ስላልነበራቸው እግዚአብሔርን በጾም እና በጸሎት በጠየቁት ወቅት የዓለሙ መድኅን የሆነውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ስጣቸው፡፡
Leave a Reply