ፍኖተ መስቀል – የመስቀል መንገድ
ፍኖተ መስቀል ማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጲላጦስ ዐደባባይ አንሥቶ መስቀሉን ተሸክሞ እስከተሰቀለበት ተራራ ቀራንዮ ድረስ የተጓዘበት መንገድ ማለት ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሙስ ማታ እንደተያዘ ሌሊቱን ሁሉ መከራ ሲቀበል አድሮ ዓርብ ጧት የአይሁድ ሽማግሌዎችና አለቆች ተሰብስበው ወደ ሹሙ ወደ ጲላጦስ ቤት ይዘውት ሔዱ፡፡ ከዚያም ይህ ሰው ከሕጋችን ጋር የማይስማማ ትምህርት ሕዝቡን ያስተምራልና እንደ ሕጋችን ሞት ይገባዋል፡፡ ንጉሥ ነኝ፣ እያለም ያታልላል በማለት በሹሙ ፊት ቀርበው ከሰሱት፡፡ ጲላጦስ ግን ብዙ ቢዋሹበትና ቢከሱት አላመናቸውም ነበር፡፡ ምክንያቱም መርምሮ በደል አላገኘበትምና ሊያድነው አስቦ ነበር፡፡ ግን ሊያድነው አልተቻለውም፡፡
ጲላጦስ ጌታችንን ሲመረምር ለብቻው አቁሞ መጠየቅ የሮማውያን ልማድ ነበርና አዳራሽ አስገብቶ ለብቻው የተከሰሰበትን ነገር ጠየቀው፡፡ አይሁድ ግን በዓለ ፋሲካ ደርሶባቸው ነበርና ስለ በዓሉ ክብር ሲሉ ወደ ፍርድ ቤት አልገቡም፡፡ ከውጪ ተሰብስበው እርስ በእርሳቸው እንደፈቃዳቸውና እንደምኞታቸው ጌታን ለመስቀል ያስቡ ነበር፡፡
ጲላጦስም ጌታን ለብቻው በጥያቄ ከመረመረው በኋላ ከአዳራሹ ወደ ውጭ ብቅ ብሎ በዚህ ሰው ለሞት የሚያበቃ በደል ወይም ምክንያት አላገኘሁበትም ያውላችሁ አላቸው፡፡ እነሱም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሏልና ሞት ይገባዋል፡፡ ስቀለው፣ ስቀለው እያሉ መለሱለት፡፡ እሱም እንደገና ለብቻው ጠይቆና መርምሮ የሚሞትበት በደል ስላላገኘበት ከአዳራሹ ወደ ውጭ ወጣና ውኃ አስመጥቶ በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ፡፡ ከዚህም ሰው ደም ንጹሕ ነኝ ሞት አልፈርድበትም እያለ ሐቁን መሰከረ፡፡
አይሁድ ግን ይህ ሰው ንጉሥ ሳይሆን ንጉሥ ነኝ ብሏል፤ ንጉሥ ነኝ የሚል ሁሉ የቄሳር ተቃዋሚ ጠላት ነው፡፡ የቄሳር ወደረኛ መሆኑን እኛ እየመሰከርን አንተ ግን የቄሳር ሹም ሆነህ ብትለቀው አንተ ታውቃለህ እያሉ ጲላጦስን አስፈራርተውታል፡፡ ጲላጦስም ይህን ሲሰማ በራሱ ላይ ክስ እንዳይመጣበት ጌታችንን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ጌታችንን ወታደሮቹ ተቀብለው ወደ ሌላ አዳራሽ አስገቡት፡፡ ልብሱን ገፍፈው፣ ሌላ ቀይ ልብስ አልብሰው፣ የሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፍተው፣ ዘንግ በእጁ አስይዘው፣ ሎቱ ስብሐት ንጉሥ ከሆንህ ለአንተ ስግደት ይገባል፡፡ ልብሰ መንግሥት ያምርብህ ይሆን? ክርስቶስ ከሆንህ ትንቢት ንገረንእያሉ ፊቱን ሸፍነው ራስ ራሱን በዘንግ እየመቱ ተሳለቁበት፡፡
ከያለበሱትንም ልብስ ገፍፈው የቀድሞ ልብሱን አልብሰው፣ መስቀሉን አሸክመው ወደሚሰቀልበት ቦታ ወደ ቀራንዮ ሲወስዱት የተነሡበት ቦታ ገበታ /ገበጣ/ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዚህ ቦታ ተነሥቶም መስቀሉን ተሸክሞ መከራውን ታግሶ እስከ ቀራንዮ የተጓዘበት ፍኖተ መስቀል ይባላል፡፡