Addis Ethiopia Weblog

Ethiopia's World / የኢትዮጵያ ዓለም

  • July 2018
    M T W T F S S
     1
    2345678
    9101112131415
    16171819202122
    23242526272829
    3031  
  • Archives

  • Categories

  • Recent Posts

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደመና ተጭነው ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው

Posted by addisethiopia / አዲስ ኢትዮጵያ on July 28, 2018

እንኳን አደረሰን! የሊቀ መለአክት ቅዱስ ዑራኤል ፀሎት በያለንበት ይድረስ!

ድርሳነ ዑራኤል

ምድረ ኢትዮጵያ ፦ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሴፍና ሰሎሜ በደመና ተጭነው ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ናግራን ከተባለ ሀገር ደረሱ፡፡ በናግራን ሳሉ ጌታ እንዲህ አለ፡፡ ከቀኝ ጎኔ የሚፈሰው ደሜ በብርሃናት አለቃ በዑራኤል እጅ ተቀድቶ በቅድሚያ በዚች ሀገር ይፈሳል ወይም ይረጫል፡፡ እናቱንም እንዲህ አላት አንቺ በድንግልና ጸንሰሽ በድንግልና እንደወለድሽኝ አምነው የሚያከብሩሽ በእኔም የሚያምኑ ብዙ የተቀደሱ ሰዎች በዚህ ሀገር ይወለዳሉ፡፡ ከናግራን ተነስተው ለትግራይ ትይዩ ከሚሆን ሐማሴን ከሚባለው ሀገር ሲደርሱ በምሥራቅ በኩል ከፍተኛ ተራራ ተመለከቱና ወደ ተራራው ሄዱ፡፡ ጌታም በተራራው ላይ ሳሉ እናቱን እንዲህ አላት ይቺ ተራራ ምስጋናሽ የሚነገርባት ቦታ ትሆናለች፡፡ የተራራዋም ስም ደብረ ሃሌ ሉያ ወይም ደብረ ዳሞ ይባላል፡፡ ትርጓሜውም የአምላክ ልጅ የመስቀሉ ቦታና የስሙ መገኛ ወይም አደባባይ ማለት ነው፡፡ከዚያም በኋላ ታቦተ ጽዮን ወደምትኖርበት ወደ አክሱም ደረሱ፡፡ ታቦተ ጽዮን ባለችበት ቦታ ሳሉ ባዚን የተባለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ታቦተ ጽዮንን ለመሳለም መጣ፡፡ የካህናቱ አለቃ አኪን ለንጉሡ የኢሳይያስን መጽሐፍ አነበበለት፡፡ የተነበበውም የመጽሐፍ ክፍል ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ወንድ ልጅ ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች የሚል ነበር፡፡ ስደተኞቹ ግን ለንጉሡም ሆነ ለካህናቱ ሳይገለጡ የመጽሐፉን ቃል ከሰሙ በኋላ በደመና ተጭነው ወደ ደብረ ዐባይ ሄዱ ፡፡ ጌታም እናቱን እንዲህ አላት ይህች ሀገር እንደአክሱም ለስምሽ መጠሪያ ርስት ትሁን በኋላ ዘመን በቀናች ሃይማኖት ጸንተው ሕጌን የሚያስተምሩ አንቺን የሚወዱ ሰዎች ይኖሩባታል፡፡ ከዚያም በኋላ ከደብረ ዐባይ ተነስተው ዋሊ ወደ ሚባለው ገዳም /ወደ ዋልድባ / ሄዱ፡፡ በዋልድባ በረሃም ሳሉ በራባቸው ጊዜ ጌታ በዮሴፍ ብትር የአንዱን ዕንጨት ስር ቆፈረ፡፡ ሦስት መቶ አስራ ስምንት ስሮችን አወጣና ለእናቱ ብይ ብሎ ሰጣት፡፡ እናቱም ይህን የሚመር ዕንጨት አልበላም አለችው፡፡ ጌታም በኋላ ዘመን ስምሺን የሚጠሩ አንቺን የሚያከብሩ ብዙ መናንያን ይህን እየበሉ በዚህ ቦታ ይኖራሉ፡፡ ዕንጨቱም የሚጣፍጥ ይሆንላቸዋል አላት፡፡ ከዚህ በኋላ በደመና ተጭነው ከዋልድባ ወደ ጣና የባሕር ወደብ ሄዱ፡፡ በጣና ደሴትም ደጋግ ሰዎች ተቀብለዋቸው ሦስት ወር ከአስር ቀን ተቀመጡ፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች በደስታ ተቀብለዋቸዋል እንደ ግብፃውያን አላሰቃዩአቸውም ፡፡ በጥር አስራ ስምንት /18/ ቀን ዑራኤል መጥቶ የሄሮድስን መሞት ነገራቸው ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ዘንድ በደመና ከተጫኑ በኋላ ጌታ እናቱን እንዲህ አላት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎች ሁሉ ለስምሽ መታሰቢያ ይሆኑሽ ዘንድ አሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ ፡፡ ብሎ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን ተራራዎችን ሜዳዎችን ኮረብታዎችን አሳያት፡፡ እመቤታችን ሁሉንም ቦታዎች እየተዘዋወረች እንድታይ ልጅዋን ጠየቀችው፡፡ ልጅዋም የሚመለሱበት ጊዜ እንደደረሰ ነገራት፡፡ በብሩህ ደመና ላይ ተቀምጠው ክፍላተ አህጉር እየተዘዋወሩ ተራራዎችን ወንዞቸን አስጐበኛት የኢትዮጵያን ምድር ከጐበኙ በኋላ በደመና ተጭነው ጥር 29 ቀን ምድረ ግብፅ ደረሱ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በቅዱስ ዑራኤል መሪነት ነው፡፡ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ታሪክ በድርሳነ ዑራኤል ላይ በስፋት ተጽፏል፡፡

______

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: