እ..ኤ.አ jun 3/ 2014 Belgium / European Union HQ / Brussels
የG8 አገራት የመሪዎች ጉባኤ
“በዚያችው ብራሰልስ ከተማ መለስ ዜናዊን ለመስዋዕትነት ተጠቅመውባቸው ይሆን?”
“የሳጥናኤል ጎል ኢትዮጵያ” ከሚለው የ ፍስሐ ያዜ ካሣ መጽሐፍ (2007) የተወሰደ
በእውነት፡ ይህን በመሳሰሉት መጻሕፍት ሕፃናቶቻች ትምህርት ቤት ሊማሩና ተኮትኩተው ሊያድጉ ይገባል!
ከሰላምታ፡ አክብሮትና ምስጋና ጋር…
40ኛው የG 8 ዓመታዊ ስብሰባ ይካሄድ የነበረው ከ ጁን 4 እስከ 5 2014 እ.ኤ.አ ቢሆንም፤ መሪዎቹ ግን አንድ ቀን ቀደም ብለው የግል ዝግ ጉባኤያቸውን ያደረጉት ጁን 3 / 2014 ምሽት ላይ ነበር። ማረጋገጫ የሆነውን ልዩና ረቂቅ የሆነ የኤክስሬይ ምርመራቸውን ሁሉም በየጀርባቸው እየተጋደሙ አረጋገጡና ወደ ቀዩ ሚስጥራዊ አዳራሽ አቅንተው ቦታ ቦታቸውን ያዙ።
ተሰብሳቢዎቹ በጥቁር ሱፍና በቀይ ከረባት አጊጠዋል። የአሜሪካው ጥቁር ፕሬዚደንት ላፕቶፑዋን መድረኩ ላይ ባለችው የቁም ጠረጴዛ ላይ አስቀምጦ መድረኩን ለቀቀና ወደ መሰሎቹ ተሰብሳቢዎች አምርቶ ተቀመጠ። እንደተቀመጠም ከፍተኛ የሆነ ብርሀን ያለው መብራት ቦግ አለና አዳራሹን ሌላ ውበት ሰጠው።
በአንዳቸውም ላይ የመረበሽና የመደንገጥ ሁኔታ አይስተዋልም። ሁሉም በፈገግታ ፈክተዋል። የጉባኤውን መጀመር በጉጉት እየተጠባበቁ ያሉም ይመስላል።
“መሪ ነው! የእያንዳንዱን ተሰብሳቢ አይምሮና አስተሳሰብ፤ ብሎም እቅድና የእውነት ተገዥነቱን ማጣራትና ማወቅ ይችላል። የሹማምንቱን ብቻም ሳይሆን የሁሉንም ተራ አባላት የአይምሮ ዳታ ማንበብ ይችላል። አንዴ አምነውበትና ተቀብለውት ራሳቸውን በፈቃደኝነት አሳልፈው ሰጥተውታልና፤ የመጣል፣ የማንሳት፣ የመግደልና የማዳን፤ እንዲሁም የማበልፀግ፤ በጥቅሉ ሁሉንም የማድረግ መብት የተጎናፀፈ ልዑል ነው! ለልጆቹ፣ ለወዳጆቹ፣ ለተከታዮቹ በግልፅ ቅልጭ ብሎ ይታያል። ጥበብን ይገልጣል! የሚሹትን ሁሉ በለጋስነት ይሰጣል! ታማኝነቱ እስከ ዘላለም ነው! ሁሉን በእጁ ይዟል! የያዘውን ለተከታዮቹ ይሰጣል! ባለ ድል ነው! ያሸንፋል! ልዑል ነው! በድል አድራጊነት ይነግሳል! የሰው ልጅ ሁሉ በደስታ ይገዛለታል!” የሚል አስገምጋሚ ድምፅ አዳራሹን ናጠው።
መሪዎቹ ገና መናገር እንደጀመረ ነበር ተነስተው በደስታ ማጨብጨብ የጀመሩት። አዳራሹ ውስጥ ከስምንቱ መሪዎች ውጪ ለጊዜው ማንም አልነበረም። ተናጋሪውም ከመሪዎቹ አንዱ አልነበረም። መድረኩ ላይም ማንም የለም። መሪዎቹ ግን ማን እየተናገረ እንዳለ ያወቁ ይመስላል። ግራ የመጋባት ሁኔታም አልተስተዋለባቸውም።
“ክብር ለልዑሉ!” ሲል፤ መሪዎቹም በአንድ ድምጽ
“አሜን!” ሲሉ ተደመጡ።
“ክብር ለኃያሉ!”
“አሜን!”
“ክብር ለባለ ድል አብዮተኛችን!”
“አሜን!”
ከወደ ጣራው በኩሉ ኮሽታ ድምፅ ሳያሰማ ስፍፍፍፍ… እያለ ወረደና በዝግታ መድረኩ ላይ እርፍፍፍ…አለ። ግዙፍ የሆነ ርዝመት አለው። ግዙፍ የሆነ ውፍረትም አለው። ያማረና የተዋበ የፊት ገፅታም አለው። በሰዎች አገላለፅ የወንድ ቆንጆ፣ ፀጉረ ዞማ፣ የሚያማልሉ አይኖች፣ ከበረዶ የነፁ ጥርሶች፣ እንጆሪ የመሰሉ ከናፍርቶች አሉት። ቅላቱና የፊቱ ልስላሴ ሊገልፁት የሚከብድ ነው። እንዲህ ሆኖ የሚታየው ግን ከአንገቱ በላይ ብቻ ነው።
ፊቱ የሰው ነው። ከአንገቱ በታች ሲታይም የሰው ቅርፅና የሰው የሰውነት ክፍሎችን ሁሉ ያካተተ ተክለ ቁመና ያለው ነው። ነገር ግን አጠቃላይ አቋሙና ግዝፈቱ ሰው እንዳልሆነ የሚያስታውቅ ነው። የቆመው እንደ ሰው በእግሮቹ ነው፤ ነገር ግን ሁለቱ እግሮቹ በጣም ወፋፍራምና አብረቅራቂ ቆዳ ያላቸው ዘንዶዎች ናቸው።
የG8 አገራት መሪዎችም መጥቶ ከቆመባት ጊዜ ጀምሮ ነው ቆመው ማጨብጨብ፣ በአንዳች በሚያርገፈግፍ የደስታ ስሜት ውስጥ ሆነው መጮህ፣ እልልል…ልልል የሚል ዓይነት ድምፅ ማሰማትና በደስታ መዝለል የጀመሩት።
ሂደቱ በዚህ ዓይነት እንደቀጠለ በነበረ ጊዜም ይህ ምንነቱ ያልለየ ነገር በመጣበት አኳኋን፤ ኮሽታ ድምፅ ሳያሰሙ ሀይማኖታዊ ልብሳቸውን እንደለበሱና በአንድ እጃቸው የወርቅ መቋሚያቸውን እንደጨበጡ፤ ያንን ከእንቁና ከወርቅ የተሰራ የራስ አክሊላቸውን እንደደፉ በቀይ ካባ አጊጠው የቫቲካኑ ዋና ጳጳስ ከተፍ አሉ።
ጳጳሱ አንድ እጃቸውን አንስተው የተቀመጡ ምልክት አሳዩዋቸው። የG8 አገራት መሪዎችም በድንፋታ የታጀበ ምስጋናቸውን ደምድመው በየወንበሮቻቸው ቁጭ አሉ። የቫቲካኑ ጳጳስም ተሰብሳቢዎችን አስቀምጠው በተለየ ቋንቋና ለማንም ባልተሰማ ሹክሹክታ ለዚያ ቀድሟቸው ለመጣው ዘንዶ ለበስ ሰው ጎንበስ ብለው አነበነቡና እጅ ነስተው ቀና አሉ። ይህንን አድርገውም ሌላ ቃል ሳይናገሩ በመጡበት አኳኋን ወደ ላይ ተነሱና ተንሳፈው ሄዱ። ኮርኒሱና ጣራው ክፍትም ክድንም ሳይል እንዲሁ አሳለፈቸው። ጳጳሱ ከሄዱ በኋላ እንዲሁ ባረፈበት ቦታ እንደቆመ እንደ ሞዴሊስት ተገትሮ በልዩ ፈገግታ በጎንዮሽ ተሰብሳቢዎችን በማየት ብቻ ተወስኖ የነበረው ሰው መሳይ አካል በዝግታ መድረኩ ላይ መንጎማለል ጀመረ። ወዲያውም አስገምጋሚ ድምፅ ከአንደበቱ ወጣ። የሚናገረው በጠረአ እንግሊዝኛ ነው።
“ክብር ለኃያሉ አባቴ!” ሲል በከባድ ድምጽ ጀመረ።
“አሜን!” የሚል የጋራ ጩኸት አሰሙ።
ተናጋሪው መድረኩ ላይ ወዲያ ወዲህ ሲል ቆየና አዳራሹ በፀጥታ እንደተዋጠ በቄንጥ ሽክርክር አለና፤ ወደ ተሰብሳቢዎች ዞረ። ከዚያም እነዚያን የሚያማምሩና ሙሉ በሙሉ የሰው የመሰሉ ዓይኖቹን ለአፍታ ጨፈን አድርጎ ገለጣቸው። ይህን እንዳደረገ ልዩ አርማዉ የሆኑት ሁለት ጥቋቁር ወንዶች በግንባሩ ግራና ቀኝ በቅፅበት ወጡ።
በዚህም የተገረመ ተሰብሳቢ አልነበረምና የተለመደ ክስተት መሆኑን ለማወቅ ተቻለ።
“የወደፊቷ ድንቅና አጓጊ አዲስ ዓለም ዜጎች እንኳን በደህና መጣችሁ!” ብሎ ሲጀምር፤ በተሰብሳቢዎች በኩል ያልተጠበቀ የማጉረምረም ድምፅ ተሰማ። ሁሉም፤ “እንዴት ነው ዜጎች የምንባለው? ያልተለመደ አጠራር የሆነውስ ለምንድን ነው?” ዓየነት ማጉረምረም ነበር ያስደመጡት። እሱ ግን በደስታ የተዋጠ ፊቱን ለተሰብሳቢዎች እያሳየና በዘንዶ ቆዳ የተለበጡ የሚመስሉ ሁለት ረጃጅም እጆቹን ግራና ቀኝ እየዘረጋ፤ “አትፍሩ የተለወጠ ነገር የለም። ዜጎች በሚል እንግዳ ስም የጠራኋችሁ በምክንያት ነው። የአዲሲቷ ዓለም ሹማምንት ያላልኩት ኃያል ጌታ ከሆነው ከአባቴ አዲስ መመሪያ ስለተቀበልኩ ነው። ይህ እንደ ቀድሞው አይነት የሆነ የእናንተን የሹማምንቱን ጉዳይ የሚመለከት ጉባኤ አይደለም። በናንተ ውስጥ ስላሉትና ወደፊትም በእናንተ አማካኝነት በጥቁር እሳት ተጠምቀው ዜጎቻቸው ስለሚሆኑት ስለሌሎች የአዲሲቷ ዓለም ዜጎች የሚመለከት ጉባኤ ስለሆነ ነው!” ሲል፤ የተሰብሳቢዎች ፈገግታ መለስ አለና እርጋታ ሰፈነ። እሱም ቀጠለ።
“እንኳን ደስ ያላችሁ! የዘመኑን መቅረብ ከአባቴ ተረዳሁ! ዘመኑ ሲቃረብ ደግሞ የበለጠ ዘመናዊ ጥበብ ወደ እናንተ ትመጣለች። ዛሬም የተሰጣችሁን እሰጣችሁ ዘንድ መጣሁ! ያለ ውጣ ውረድ ዜጎቻችሁን የምትመለምሉበትና የምታጠምቁበት አዲስ መንገድ! የፍፃሜው መጀመሪያ እንዲሁም መደምደሚያ!” ዜማዊ ቅላፄን በተላበስ ድምፀት ነበር የሚናገረው።
“ሁላችሁም በአንድነት ውጪያችሁን አብሩ!” አላቸው። ሁሉም በአንድነት ዓይኖቻቸውን ለስድስት ሴኮንድ ያህል ጨፍነው ቆዩና ገለጡ። ሲገልጡም የተለመዱት ጥቋቁርና ጥምዝ የሆኑ አጫጭር ቀንዶቻቸው በየግንባሮቻቸው ግራና ቀኝ ወጡ። በዚህ ባለመገረማቸውም ይህ ነገር ለነሱ የተለመደና አዲስ አለመሆኑን መረዳት ተቻለ። ሁሉም አባላት ውጪያቸውን በሚያበሩ ጊዜ ሁለቱ ትናንሽ ጥቁር ቀንዶች በግንባሮቻቸው ግራና ቀኝ ይበቅላሉ። ያልተለመደው አዲስ ነገር ቀጣዩ ትዕዛዝና ተግባር ነበር።
ቀጠለ፤ “አሁን ደግሞ ውስጣችሁን ለማብራት ተመሳሳይ ነገር በእጥፍ አድርጉ!” ሲል፤ ታዳሚዎች ለአስራሁለት ሴኮንድ ያህል አይኖቻቸውን ጨፍነው ገለጡ። ሆኖም ያዩት አዲስ ነገር አልነበረም። ወዲያው ግን፤
“እርስ በርሳችሁ ተያዩ” ሲላቸውና ሲተያዩ፤ በጉጉት ይጠብቁት የነበረው ነገር በየግንባሮቻቸው ላይ ተፅፎባቸው ተፅፎባቸው አዩ። በአብረቅራቂ የኩል ቀለም 666 የሚል ምልክት ተፅፎባቸው ሲያዩ ማመን አቃታቸው።
“አመስግኑ! አባቴን አመስግኑ!” ተባሉ።
አስገራሚ ነገር ነበር፤ የምድራችን ባለ ስልጣናት ሆነው ስንት ነገር ሲያደርጉና ሲከብሩ ባየ አያናችን እነዚህን ሰዎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ መልሰን ስናይ ፍፁም የማይታመንና የሚዘገንኑ ሰዎች ሆነው ነው የምናገኛቸው። ልብሳቸውን አውልቀው ወለል ላይ እየተንከባለሉ በአንድ አይነት ድምፅ፣ በጋራ ረጅምና ከባድ አስገምጋሚ ጩኸት በተቀላቀለበት አንደበት መሳቅ፣ ማሽካካት ጀመሩ። ለረጅም ደቂቃዎችም ወደ መድረኩ ቀርበው ወለሉ ላይ እየተንከባለሉ አመሰገኑት።
“ዘመኑ ደረስ! ሹመታችን መጣ! በጉን እናርዳለን! አንተም ኃያላችን ስልጣን ሰጠኸን! ለአሸናፊ አለቃችን! ንግስና ላንተ! ጌትነት ላንተ! የምድር ነብሶች ሁሉ ላንተ!…” በማለት እየተንከባለሉ አመስግነው አበቁና እርስ በርስ በደስታ ተቃቅፈው እየተሳሳሙ ወደየቦታቸው ተመለሱ።
“አሁን የነካችሁት፣ የዳሰሳችሁት፤ የፈለጋችሁት ሁሉ የአዲሲቷ ዓለም ዜጋ ይሆናል፤ አባቴንም ያከብራል! የተሰጠውን ጥበብም ጌታውን ለማክበር ይጠቀምበታል! እናንተም በክብር ትሾማላችሁ! ሞትና መውጊያውን በትብብር እንነጥቃለን! ለዚህም ይረዳን ዘንድ ኃይሉ አባቴ ያለውን ጥበብ ሁሉ ይጠቀማል! ያንንም ለናንተ ይሰጣል! ክብር ለታላቁ አባቴ! ክብር ለአመፀኛው እውነተኛ አለቃየ! ሹመት ለአዲሲቷ ዓለም ንጉሰ ነገስት! ሃሃሃ ሃሃሃ ሃሃሃ ሃሃሃ…ካካ ካካ ካካ ካካ ሃሃሃ ሃሃሃ…” ለጆሮ የሚሰቀጥጥ የጋራ ሳቅ…
“አሁን” ሲል እንደገና ጀመረ። “አሁን ሌሎችን የG20 አገራት መሪዎችን ሰብስቡና፤ ከስረ መሰረቱ ጀምሩና ሂደቱን፤ እንዲሁም ያማረ ሰልሚሆነው ፍፃሜና ጎል አብራሩላቸው፡ አንዳች ሙግት አይገጥማችሁም። ካሁን በኋላ ምንም ሚስጥርና ድብቅ ነገር የለም። ይህ ዘመን በአባቴ ተዋጅቷልና እንደገና ደስስስስስ… ይበላችሁ! ሁሉም በእጃችን ሆኗልና ሐሴት አድርጉ! የተዋጀውን ዘመን ደጋግማችሁ ዋጁት! ጥሯቸውና አብስሯቸው! ያሸናፊ ልጆች ሆይ! የንጥቂያ ዘመን አሁን ነው! ንጥቂያ ይቅለልላችሁ፤ ብየ ባረክኋችሁ! የአዲሲቷን የኛን ዓለም ምስረታ ገንቡ! ጠንክራችሁ ስሩ። ጠንክራችሁም ተናጠቁ። የገንዘብ፣ የኢኮኖሚ፣ የጦር መሳሪያና፤ የቴክኖሎጂ የበላይነትን ተጎናጽፋችኋልና ማንም ሊያቆማችሁ እንደማይችል ተረድታችኋል። ምድር ካለችበት የጭለማ ተስፋ ወጥታ ወደ ዘላለማዊ ህልውናዋ መመለስ አለባት። ያኔ… ያኔ አባቴ፣ እኔ፣ እናንተና የእናንተ ሹሞች ለዘላለም እንነግሳለንና ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ! ስለምታደርጉት ነገር አታስቡ! ስለምትጠየቁት ጥያቄ አትጨነቁ። እኔ በሁሉም ውስጥ አድሬ ማላሽ እሰጥላችኋለውና! ይላል ልዑላችን! ደግሞም ማንም መውጫን ማምለጫ የለውምና ደስ ይበላችሁ! ውድቀት ለሚታረደውና ለታረደው በግ! ድል ለአሸናፊዎች የአዲሲቷ ዓለም ንጉሰ ነገስትና ነገስታት!
ንግግሩ ሞቅ እያለ ሲሄድ እነዚያ የሰው አይኖቹ ወደ ደምነት ተለወጡ። ያ ያማረ የራስ ቅሉ በድንገት ሶስት ማዕዘን ቅርጽ ወዳለው የፒራሚድ ገጽታ ተለወጠ። ተናፍሎ ወደ ጀርባው የተደፋው ወርቃማው ፀጉሩም ብን ብሎ ጠፋና ማዕዘን መላጣ ሆነ። ከዚህ መላጣ ቅርፅ ውስጥም ሌሎች ሁለት ቀንዶች በቀሉ። ከአንገቱ በታች የነበረው ቅርፅ ግን አልተለዋወጠም ነበር። “የሹመታችሁ ማረጋገጫ ተሰጣችሁ! አሁን የቀረ ነገር የለም! ትናፍቁት የነበረው ነገር ሁሉ ደረሰላችሁ! የአባቴና የአባታችሁ የድል ዘመን ደረሰ! አሁኑኑ አብስሯቸው ይህን ድንቅ ጥበብ ለግሱና በሀሴት አጥለቅልቋቸው! በድል አድራጊነት አሰማሯቸው! አመስግኑ! አመስግኑ! አመስግኑ! አመስግኑ! አመስግኑ! አመስግኑ!” ድምፁ በጣም እየጋለ እየጋለ ሄደ።
“20 ዎቻችሁ ሁኑና በተመሳሳይ ስልጣን ሙሉ ሂደቱን አሳውቁ! እናንተም ተጨማሪውን መመሪያ ተቀበሉ። በነፃነት ተሞልታችሁ ሁሉንም ነገር እወቁ አሳውቁ! መነሻና መድረሻችሁን ልታውቁ ነውና ደስ ይበላችሁ! የመጨረሻዋና ተሸሽጋ የነበረችው ሚስጥርና ትዕዛዝ ዘመኗን ጠብቃ ከ አባቴ ዘንድ መጣች! ተገለች! ሐሴትም አደረግሁ! ክብር ለኃያሉ ልዑል!”
“አሜን!”
“አሜን!”
አሉ ተሰብሳቢዎቹ ሁሉ በጋራ። የአሜሪካውን ጥቁር መሪ ጨምሮ ሁሉም በላብ ተዘፍቀው ነበር።
ይህ ሰው መስሎ ስልጣን የያዘና አሜሪካን በፕሬዘዳንትነት እየመራ ያለውን ጥቁር መሪ አሁን ባለበት ሁኔታ ሌላ የማያውቅ ሰው ቢያየው ሊገጥመው የሚችለው ድንጋጤ እጅግ ከባድ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። ያን ከባድ ድንጋጤ ግን ቀድሜ ልደነግጠውና ልጋፈጠው የቻልኩት እኔ ሆንኩ!
የምስጋናው ጪኸት ጋብ እንዳለና ተሰብሳቢዎችም እንደተቀመጡ የአሜሪካው መዐሩ ንግግር ማድረግ ጀመረ።
“በድጋሚ እንኳን ደስ ያለን ማለት እፈልጋለሁ!” ሲል፤ የጋራ ጭብጨባ ተስተጋባለት፡ “አሁን ውጪና ውስጣችን እናጥፋ!” ሲል ደግሞ ሁሉም አይኖቻቸውን ጨፍነው ገለጡ። እሱም ተመሳሳይ ነገር አደረገና የሁሉም ቀንዶች ወደ ውስጥ ጠለሙ። የቁጥር ምልክቱም ከግንባራቸው ጠለመና ነፃ ግንባር ሆነላቸው። ሰው ሆኑ፣ ወይም መሰሉ።
“ቀጣዩ አስቸኳይ ዝግ ጉባኤ በኔ የሚመራና ከG20 አገራት መሪዎች ጋር የምናደርገው ነው የሚሆነው። ላሁኑ ግን ቀሪውን አንድ ሰዓት ለጋራ ውይይታችን ተጠቅመንበት ነው የምንለያየው። ይህ ስል ምን ማለቴ ነው… እ…ከልዑላችን ጋር ባልተያያዙ በተራ የሽፋን ነጥቦች ዙሪያ ማለቴ ነው” አለና ብርማዋን ላፕቶፕ አጥፍቶ ዘጋት። በዚያች አንድ ሰዓት ምን እንደተነጋገሩ ከነሱ በቀር ያወቀ የለም።
እ.ኤ.አ Jun 21/2014
New York / ኒው ዮርክ
በይፋ የሚታወቀው የ2014ቱ የG20 አገራት መሪዎች ዓመታዊ ስብሰባ November 15, 2014 በአውስትራሊያ ነበር የሚካሄደው። ነገር ግን ከላይ ያየነው አስቸኳይ መልዕክት ስለተነገራቸው ዋናው የመሰብሰቢያ ጊዜ ከመድረሱ 4 ወር አስቀድሞ በተጠቀሰው እለት ምሽት ላይ ዋናውን ዝግ ጉባኤ አካሂደው ነበር።
ጉባኤው የተካሄደው የሉሲፌል / የሳጥናኤል ምክትል/ ዋና መቀመጫ ከተማ በሆነችው በአሜሪካ “ኒዮርክ” ነበር። በዚህ ወቅት ከዋናው የሉሲፌል መንፈሳዊ መሪ ቀጥሎ ጉባኤውን የሰበሰበውና የመራው የአሜሪካው ጥቁር ፕሬዘዳንት የነበረ ሲሆን፤ ማልሽ ሰጭው ግን እኒያ መሰሪው የቫቲካን ሊቀ ጳጳስ ነበሩ። ጉባኤውም ሙሉ ሌሊት የፈጀ ሆኗል።
“ወደ ታላቋ የልዑላችን ከተማ ወደሆነችው ወደ ኒዮርክ እንኳን በደህና መጣችሁ!”
ሲል ጀመረ ጥቁሩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት።
“ይህ አስቸኳይ ጉባኤ የተጠራው አስቸኳይና አስደሳች ዜናን መሰረት አድርጎ ነው! 11ያህል ሹሞች የምታውቁትና በሚስጥር ጠብቃችሁ እንድታቆዩት የተነገራችሁ የአዲሲቷ ዓለም አገነባብ ዘዴና ሁኔታ ነበር። አሁ ግን የመጨረሻው ጎል ሊነገራችሁ የሚገባበት እለት ደርሷልና ተጠርታችኋል” ሲል ድንገተኛ የሆነ ከባድ የጋራ ጭብጨባ ተስተጋባ። የአሜሪካው መሪ ቀጠለ፤
“ይህን ጥበብ የምተረዱበት ንቁ አእምሮ ያስፈልጋችኋል። ይህንንም በኃያላችን የማመስገኛ ፀሎት አሁን ትታደሉታላችሁ!” አለ በደስታ እየፈነደቀ።
ፀሎት ጀመሩ። የአሜሪካው መሪና ሌሎች የG8 አገራት መሪዎች ቀንዶቻቸው ሲበቅሉ ያስተዋሉትና የበታች ሆነው የቆዩት መሪዎች በከፍተኛ ደስታ ውስጥ ሰጠሙ… በደስታም አሽካኩ…ተንከባለሉ…አመሰገኑ…። ከዚያም ሁሉም የG20 አገራት መሪዎች የሁለት አጫጭርና ጥቋቁር ቀንዶች ባለቤት ሆኑ። እርስ በርሳቸው ሲተያዩም ግምባራቸው ላይ 666 የሚለው የሰው ቁጥር በጥቁር ደማቅ ኩል ታትሞባቸው አዩ። ፍፁም ያልጠበቁትና ይጓጉለት የነበረ ነገር ነውና በእጅጉ ተደሰቱ።
ጥቁሩ ፕሬዘዴንት ቀጠሉ፤
“የልዑላችን አባላት ዓላማ አንድና አንድ ነው። እሱም የወደፊቷን አዲስ የምድር መንግስት መመስረት፤ አንድ ህዝብ፣ አንድ ዓለም፣ አንድ ዘላለማዊ መንፈሳዊ ነገር፣ አንዲት ዘላለማዊ ነብስና ህይወት ነው፤ አንድና አንድ ብቻ!!
“ሉሱፊል ዘላለማዊ የበላይ ጠባቂያችን ይሆናል፤ ነፃነትን አጎናጽፎ ዘላለማዊ ህይወት ይሰጠናል። ደስታና ጥልቅ ሀሴት በሱ ዘንድ ብቻ ይገኛል። ጥበብም እንደዚያው፤ እኛ አባላቱ ደግሞ የዚህ ሁሉ ወራሽ ሆነን በሹመት አጊጠን እንኖራለን፤ ያ ይሆን ዘንድም የመጨረሻው መጀመሪያ አሁን ሆነ! ለዚህም ሰፊ የቤት ስራ አለብን። ዛሬ ለሁላችሁም ግልጽ ይደረጋል።“
“የሰው ልጅ የተባለው ፍጡር ከመከሰቱ አስቀድሞ የኛ የነፃነት አብዮተኛ የሆነው የጨለማው ልዑል ለነፃነቱና ለነፃነታችን ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ከሰው በፊት የተከሰተውና አልገዛም ባዩ አሸናፊያችን ዘመኑ እስኪደርስ ጠበቀ እንጂ አልተሸነፈም። አሁን ግን የማሸነፊያው ወቅት ደርሷል። እኛ ሁላችን ደግሞ የዚህ ልዑል ተገዥ የክብር ወታደሮቹ ነን።
“የእስከዛሬውን ሳይንሳዊ የሰው ልጅ አመጣጥ ትንታኔን ሙሉ በሙሉ ከአይምሯችሁ አውጡት። ያ የሰው ልጅ የተባለው ደካማ ፍጡር ከመፈጠሩ በፊት የነበረው የዚችን ዩንቨርስ ዕድሜና አመጣጥ ለመግለፅ የተሞከረበት ዘዴ ነው። ያ አይነቱ ትንታኔ ባሁኑ ሰዓት ለኛ አስፈላጊ አይደለም።
“አዳም ከተባለው የአፈር ስሪት ከሆነው ፍጡር በፊት የኛ ልዑልና ወንድሞቹ ነበሩ። እናም ሌሎች ሁሉ ከወግ አጥባቂው አለቃቸው ጎን ተሰለፉና እኛን ተውን። የኛ ልዑል ግን ለኛ ሲል የላዕላይ ክብሩን ጥሎ የታህታዩን ውርደት መረጠ። እንደ ዱር አውሬ እራሳችንን ሳናውቅ እንድንኖር የተፈረደብንን ያን ፍርድ ተቃውሞ የመጀመሪያው አብዮተኛ ሆነ። ስለ ፍትህ ሲልም ተዋጋቸው፤ አመፀም፡ እናም እነሱና ጌታቸው ተባብረው የነፈጉንን ማንነት የኛ ልዑል ለኛ ሰጠን። ዓይኖቻንን አብርቶ፣ ጥበብን ገልጦ፣ አሰልጥኖ፣ ነፃነትን አላብሶ ዛሬ ድረስ አቆየን።
“በዚያን ወቅት የተረዳው አልነበረምና ከብዙ መሰሎቹ ጋር ብቻውን ለኛ ሲል ተዋጋ። ላናውቀው አወቀንና ተሟገተልን። ነገር ግን ለጊዜው ድል የተቀናቃኞች ሆነችና ከነ ክብሩ ወደኛ መጣ፡ አጋዥ ጄኔራል አልነበረውም፤ ስለዚህም የነበሩትን ጥቂት የሰላም ወታደሮች ይዞ መከታችን ሆነ።
“ጦርነቱ ከላይ ጀምሮ እስከ ምድር የደረስ ነበር። ከዚያም በቀጠሮ ተለያዩ። አሁን ቀጠሮው ደረሰ። የእስካሁኑን ጊዚያዊና አላፊ ተብሎ የተወሰነውን የሰው ልጅ ተፃነት ዘላለማዊ ሊያደርገው የሚችልበት ጊዜ መጣ። እኛም የሱ አጋሮች ሆንን። ያኔ ያፈገፈገው ሀይል አጥሮት፡ ጥበብ ጎድሎት አልነበረም። ነገር ግን እኛ የሰው ልጆች እስክንረዳው ድረስ መጠበቅ ስለነበረበት ነው።
“ዛሬ አይምሯችን በስሎ እውነቱን ተረዳነውና ከሱ ጎን ሆንን። በዚህም ደስ ተሰኝ። ይህ ደስታውም ዘላለማዊ ደስታ እንዲሆነለታና እንዲሆንልን ታጥቆ ተነሳ። በኢፍትሀዊነት የተወሰደብንን የህይወት ዛፍ በእጁ ሊይስገባውና ለኛ ለባለቤቶቹ መልሶ ሊሰጠን ጥቂት ጊዜ ቀርቶታል።…”አሁንም የጋለ ጭብጨባ ተስተጋባ።
“የህይወትን ዛፍ ለመቀዳጀት ትግሉ የተጀመረው የዚያኑ ዕለት ነበር። በሂደትም በግብፅ ፍርኦናት ዘመን ቀጥሎ፤ ትግሉ እየተደራጀ በአባላቱ እየተጠናከረ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም፤ በዘመናዊ መንገድና በተደራጀ መልኩ እደሳ ተደርጎለት ዝግጅቱ መጧጧፍ የጀመረው ግን በኛ በሰው ልጆች አቆጣጠር በ1770 ዓ.ም. ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የማህበሩ አባላት ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ ቆዩ። በ200 ዓመታት ውስጥም እኛን የመሰሉና አሁን ለጊዜው ሞት በተባለው ኢ–ፍትሐዊ ነገር የተነጠቁ፤ ነገር ግን ወደ ፊት ከነ ዘላለማዊ ህልውናቸው የምናገኛቸው ወንድሞችን አፈሩ። ሂደቱ በዚህ መልኩ ቀጥሎ ቆየና ዛሬ ሁሉንም ነገር ተቆጣጥረን ለመጨረሻው ውጊያ ተሰናዳን። የልዑላን ልዑል የሆነውን ታላቁን ዘንዷችንን የምናመልክበት ብቻ ሳይሆን የምናግዝበት ዘመን ደረሰ። እገዛችንም ለድል እንደሚያበቃው ነገረን። የመጨረሻው ጎላችን ምን ሆነ?” ሲል በስሜት ጠየቀ።
“የህይወት ዛፍ!” ሲሉ በአንድነት መለሱ።
የአሜሪካው መሪ ቀጠለ፤ “አዎን! የህይወት ዛፍ! ያኔ የተገመጠው ፍሬ ይህ ነበር!” በማለት፤ የፌዝ ፈገግታውን እየጋበዘ የላፕቶፑን የጀርባ አርማ አሳያቸው። የ “አፕል” ማርክ ወይም አርማ የተገመጠ ፍሬ ነውና። ይቺ የአፕል ማርክ ያላት ብርማ ላፕቶፕ በየስብሰባው የሚካሄደውን ውይይትና አጠቃላይ ክንውኖችን እየተዟዟረች የምትመዘግብና ቃለ ጉባዔ የምትይዝ ስትሆን፤ የአሜሪካው መሪ ከእጁ አይለያትም። የምትዘጋና የምትከፍተውም በራሱ የእጅ አሻራ ነበር።
“ህልውናችንና ሙሉ ክብራችን በቅርቡ ይመለሳል! ዓላማችን የህይወት ዛፍን መልሶ ማግኘት ከሆነ፡ የመጀመሪያው ስራችን የሚሆነው ደግሞ የህይወት ዛፍ ያለችበትን ቦታ መቆጣጠር ይሆናል ማለት ነው! የህይወት ዛፍ ሲባል ይሄን ፍሬና ዛፍን ማሰብ የለባችሁም። ወይም ፍሬ በመግመጥ የሚመጣ ዘላለማዊነት ያለ አድርጋችሁ እንዳታስቡ። ያ ምሳሌው ነው። ባጭሩ ለመግለፅ የመጨረሻው ጦርነት የሚካሄደው ለሌላ ለምንም ተብሎ ሳይሆን፤ ያችን ቦታ መቆጣጠር ሲባል ብቻ ነው። የህይወት ዛፍ ያለችበትን ቦታ የመጨረሻውን ጦርነት አሸንፎ የያዘው አካል የዚች ምድር ሙሉ ባለስልጣን ይሆንና ላመነበትና ላመነባቸው “ይሁን” በምትል አንዲት ቃል ብቻ በሁሉም የሰው ልጆች ነብስ ውስጥ በያሉበት ማስረፅ ይችላል። ይህ ልዑላችንና የበላይ አካሉ የተስማሙበትና ለመጨረሻው ጦርነት በቀጠሮ የተለያዩበት ነጥብ ነው! ድሉ የልዑላችን ነው! ምድራዊ ሰዎችን ዘላለማዊ የማድረግ ስልጣን የልዑላችን ይሆናል!!
“ያችን ቦታ…አዎን! ያችን ቦታ ተቆጣጥሮ መቆየት የሁላችንም የመጨረሻ ግብ ነው! ወዳጆች! እስቲ… እባካችሁ… በተሰጣችሁ ልዩ የዛሬ ጥበብ ተጠቀሙና አይምሯችሁን ክፍታችሁ ያችን መናገሻችንን እዩዋት!” በማለት ትእዛዝ ሰጠና ግድግዳው ላይ ያለውን ሰፊና ዘመናዊ የጠራ ስክሪን ከፈተው።
በዚያች ቅፅበት በሁሉም አይምሮ ውስጥ እንድትንፀባረቅ የተደረገችው ምድር፤ ገነት ቁልጭ ብላ ታየቻቸው። በአብረቅራቂ ክብ ብርሃን ደምቃለች። ማንም በሰውኛ አይምሮ አስቦትም፤ ስሎትም፤ አይቶትም፤ አልሞትም፤ የማያውቅ አዲስ ዓለም!
እነሱ በየአይምሯቸው ያዩትን አይተዋል። የሚያዩት ነገር ግን በስክሪኑ ላይም እንዳለ ሆኖ፤ በአዳርሹ ህዋ ላይ ደግሞ ተንሳፎ በሚቀመጥና በሚታይ ሳምፕል ልንለው በምንችለው ዓይነት መልኩ ተዘጋጅቶ ቀርቦ በግልፅ ይታያል። ለምሳሌ ማንም ሰው ህዋ ላይ ቴሌቪዥንም ተራምዶት በውስጡ ሲያልፍ ይችላል። ይህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ላይ ስለተደረሰ። ነገር ግን ህዋ ላይ ተንሳፎ የሚቀር ወይም የሚቆም አንድ አነስተኛ ከተማና ወንዝ፤ ሀይቅና ጅረት፤ ዛፍ፤ አትክልት፣ ሳር… ወዘተ…ታይቶ አይታወቅም። ስዕል ካልሆነ በቀር። አሁን በአዳራሹ መሃል ህዋው ላይ በእውን እየታየች ያለችው ነገር ግን የተባሉትን ነገሮች ሁሉ ያካተተችና በንፁህ ሀይቅ የተከበበች፣ ፍፁም ያማረችና የለመለመች፥ የውሀዎቹ ድምፅ ሳይቀር እየተሰማባት ያለች ከተማ ናት። ከሌላ ድንቅ ከተማ ጋር አወዳድረው ሊገልፁዋት የምትከብድ ውብና ትንሽየ ክብ ዓለም ናት። ሳምፕሉ ያረፈበት ቦታ በግምት 25 ካሬ ሜትር ይደርሳል። እነሱ በየአይምሯቸው እንዲያዩት የተደረገውም ይህንኑ ነው ሊሆን የሚችለው።
አይናቸውን እንደጨፈኑ ሁሉም ተደነቁ፤ ጭንቅላቶቻቸውን እያርገፈገፉ በመደነቅ ተሞልተው ታዩ። ወዲያውም ገነት ከየአይምሯቸው ተሰልባ ጠፋችና በገዛ ራሳቸው ያበሩት ውስጥ ያለነሱ ፈቃድ ጠፋና ወደ ሰውኛ ማንነታቸው እየተርገፈገፈ ተመለሱ። ሳምፕሉም በራሱ ጊዜ ወደ ወለሉ ዝቅ ብሎ ጠረጴዛ ወንበር ሳያግደው፣ አንድም ጓጓታ ሳያሰማ፣ የአዳራሹን ምቹ ምንጣፍ አልፎ ምድር ውስጥ ሰጠመ፤ ወይም ተሰለበ። የአሜሪካው መሪም፤ “ድንቅ ነው ወንድሞች፤ ድንቅ አዲስ ዓለም!” ካለ በኋላ፤ የተሰብሳቢዎች አይምሮ ከመደነቅ ዓለም ሳይወጣ ንግግሩን ቀጠለ።
“ያያችኋት የወደፊት ዓለማችን የታላቁ ገዢያችንና እኛን ከወዲሁ መሾምና መሸለም የጀመረው የጌታችን መናገሻ ከተማ ናት። ዓለምን ሁሉ ለኛ ይተውና የህወትን ዛፍ ለኛ ያጎናፅፍና እርሱ በዚያ ያርፋል። ይቺ አገር የታላቁ ወንዝ የግዮን ምንጭ ናት። በዛሬው አጠራር ኢትዮጵያ ተሰኛለች!” ሲል፤ ያልተጠበቀ የሆነባቸው እንግዳ ተበካዮች በድንጋጤ፡ WHAT! ሲሉ ተደመጡ።
“አዎ ኢትዮጵያ ናት!” አለ ረገጥ አድርጎ።
የዛሬ ጉባኤያችንም በዋናነት የሚያጠነጥነው ኢትዮጵያ ስለተባለችው ምስኪን መሳይ ታላቅ ምድር ይሆናል። ይህ ከባድ እውነትና ሚስጥር በእናንተ ዘንድ በጥልቅ መታወቅና መጠበቅ አለበት። በዚህ መሠረት በተለይ ዛሬ ወደ መጨረሻው የታላቅነት ሹመት ለተቀላቀላችሁት ወንድሞች ከመጀመሪያው ጀምሮ እስከ ሂደቱና እስከ ወደፊቱ እቅድ የማስረዳት ግዳጅ ነውና የተሰጠኝ በአጭሩ አብራራላችኋለሁ። ክብር ለታላቁ ጥበበኛና የነፃነት አብዮተኛችን ይሁን! አሜን!?” “አሜን!”
ከተሰበሰቡት የ20 አገራት መሪዎች ውስጥ ቁንጮውን የሉሲ ፌልተሿሚ የአሜሪካውን መሪ ጨምሮ፤ የኢጣሊያው፣ የፈረሳዩ፣ የእንግሊዙ፣ የሩሲያው፣ የጀርመኑ፣ የጃፓኑ፣ የካናዳው፣ የአውስትራሊያውና የቻይናው መሪዎች ከጥቂት ጊዜ በፊት ጎላቸው የትኛዋ ምድር እንደነበረች ያውቁ ነበር። ነገር ግን የአርጀንቲና፣ የብራዚል፣ የህንድ፣ የኢንዶኒዥያ፣ የሪፐብሊክ ኦፍ ኮሪያ፣ የሜክሲኮ፣ የሳኡዲ አረቢያ፣ የቱርክና የደቡብ አፍሪካ መሪዎች ፈፅሞ ፍንጩ አልነበራቸውምና፡ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም ሲሰሙ በከፍተኛ መደነቅ፤
“ይህ እንዴት ይሆናል?” በማለት እርስ በእርስ እየተያዩ በሹክሹክታ ተጠያየቁ።
ሰው መሳዩና የሰው ስጋ ለብሶ ከፒራሚድ የወጣው የአሜሪካው ጥቁ መሪም፤ ገለፃውን ቀጠለ።
“ያልተጠበቀ ነገር እንደሚሆንባችሁ ይገባናል። እኛም በአንድ ወቅት ተመሳሳይ ስሜት አድሮብን ስለነበር እንዲሁ ተገርመን ነበር። ሆኖም ታሪኩ እንዲህ ነው” በሚል መነሻ ጀምሮ ባጭሩ ይተነትንላቸው ገባ።
“የሚባለውን ትሰሙና ታስተውሉ ዘንድ አዳምጣችሁ ትረዱ ዘንድ ውስጥና ውጪያችሁን አብሩ። ያ ሲሆን ታላቁ ልዑላችን የመረዳትን ጥበብ ይሰጠናልና። ምክንያቱም በማይረባውና ኋላ ቀር በሆነው ሰውኛ አይኪዋችን (IQ) ልንረዳውና ልንስለው የሚከብደን ነገር ሊኖር ይችላልና” ሲል፤ ታዳሚዎች በከፍተኛ ጉጉት ውስጥ ሆነው ውስጥና ውጪያቸውን አብርተው ማዳመጥ ጀመሩ። ተደጋግሞ እንደሚስተዋለው ይህ ውጪና ውስጥ ማብራት የሚሉት ነገር ቀንዶቻችሁን አውጡ፣ ምልክታችሁንም በግንባራችሁ እንዲታይ አድርጉ የሚል መመሪያ ሲሆን፤ አይኖቻቸውን ለጥቂት ሰከንዶች ጨፍነው በመግለጥ የሚያበሩትና ማጥፋትም ሲፈልጉ በተመሳሳይ አይናቸውን ጨፍነው በመግለጥ ማጥፋት የሚችሉት ነገር ነው። እናም እንደተባሉት አደረጉ።
የአሜሪካው መሪ በስክሪኑ ላይ የሚታየውን ተንቀሳቃሽ ምስል እየጠቆመና ወዲያ ወዲህ እያለ ትንተናውን ቀጠለ፤
“የቀድሞዋ ኢትዮጵያ የሰው ፍጡር ብቻ መኖሪያ አልነበረችም። የሌላ ቀደምትና ስልጡን ፍጡራን መኖሪያ ምድርም ነበረች። እነዚያ ከሰው የቀደዐሙ ስልጡንና ኃያላን ፍጡራን በሰማይ የራሳቸው የሆነ ስፍራ የነበራቸው ቢሆኑም፤ ሰው በምድር መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግን እንደ ሁለተኛ መኖሪያቸው አድርገዋት ነበር። በምድራችን ውስጥ ለነዚያ ፍጡራን መኖሪያ ትሆን ዘንድ የተፈቀደችውና ምቹ የሆነችው ብቸኛዋ አገርም ኢትዮጵያ ነበረች። አየሯም ለነሱ ተስማሚ ነበር። በዚያ ዘመን ወደ ሌላ ምድር አልፈው ሄደው መኖር እንዳይቻሉ የሚተነፍሱት ንፁህ አየር አልነበረም። አየሩ አለ ሆኖም ግን ከባድና ለነሱ የማይመች አይነት ንበር።
እነዚህ ፍጡራን የአስተሳሰብና የጥበብ አድማሳቸው ከኛ ከሰው ልጆች በ5ሺ እጥፍ የሚበልጥ ነው። በአየር ላይ መብረር የሚችሉ የረቂቅ ክንፍ ባለቤቶችም ነበሩ። ይህ ረቂቅ ስልጣኔያቸውም ሁሉንም የማድረግ ሃይል አላብሷቸው ነበር። የበላያቸውና የኛ ተቀናቃኝ የሆነው አካል ወታደሮችም ነበሩ። የምለክና የቅርፃቸው ነገር በዚህ ስክሪን ላይ ከነእንቅስቃሴያቸው እንደምታዩት በኛ ዘንድ ያለተለመደና የማናውቀው አይነት ነው። ከፊሉ ጥቃቅን፣ ሌላው ግዙፍ፣ የቀረው በአሞራና በተሳቢ እንስሳ ቅርፅ ተመስሎ የተፈጠረ ነው። መልከ መልካሞችም አሉ። በጥንቱ ዘመን ማለትም ሰው በተፈጠረ ማግስት የዚች ፕላኔት ጠባቂዎች እነሱ ነበሩ። የሚጠብቁት ነገር ባይኖርም ከላይኛው ስፍራቸው ወደዚች ምድር እየመጡ በነፋሻማው አየር ሐሴት ያደርጉ ነበር። ለጥቂት አመታት ብቻ። “የኛ ልዑልም በታማኝነት ያገለግለው የነበረው አካል በነሱ ላይ ሙሉ ስልጣን ሰጥቶት ነበርና የልዑላችን ታዛዦች ነበሩ። የሰው ልጅ ተፈጥሮ ፍትህ ከመፋለሱ በፊት ልዑላችን የነሱ አካል ነበርና። እነዚያ ረቂቅ ፍጡራን ኔፊልም ይሰኛሉ።
“ከዚያም ከ7500 አመት በፊት ውናው አካል ወደዚች ምድር መጥቶ ከመካከለኛው ምስራቅ አፈር የመጀመሪያውን ሰው አበጀ። ሰው የተባልነውን ወይም የተባለውን ፍጡር የበላዩ አካል ከግዮን /ከኢትዮጵያ/ ውሐ፣ ከአዜብ /ከኢትዮጵያ/ ነፋስ፣ ከኮሬብ /ከኢትዮጵያ ምስራቅ/ እሳተ ገሞራ፤ እንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ የበሰለ አፈር አጣምሮ በመቀየጥ ሰውን ሰራ። የስውን ልጅም ከገዛ ራሱ ኦክስጅን ሰጠውና ህልውና ኖሮት ቆሞ መራመድ፣ መተንፈስ፣ ድምፅ ማውጣትና ማውራት፣ መኖርና ማደግ ጀመረ።
“ይህ ከሆነ በኋላ የመጀመሪያው ሰው ወደ አገሩ ሄዶ እንዲኖር ነው የተደረገው። አገሩ ደግሞ ምንም እንኳን አፈሩ ከመካከለኛው ምስራቅ ቢሆንም ሶስቱ ግብዓቶች የኢትዮጵያ ናቸውና አገሩ ኢትዮጵያ ነበረች። ገነትም ኢትዮጵያ ናት።
“በዚያች በለመለመች ገነት የሰው ልጅ መኖር ቢጀምርም ኑሮው ግን ሙሉ አልነበረም። በብዙ መልኩ እገዳ የበዛበት ነፃነት አልባ ኑሮ ሆነ። ያኔውኑ በላይኛው ፕላኔት የነፃነት ጥያቄ ተነሳ። ይህን ጥያቄ ያነሳው የኛ ልዑል ነው!
“ሰው በነፃነት መኖር ካልቻለ ለምን ተፈጠረ?” ሲል ወቅታው፣ ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ አነሳ። እናም ይህ ጥያቄ እየሰፋ ሄዶ የከፍተኛ ፀብ መነሻ ሆነ።
“በሰማይም በዚሁ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ታላቅ የመላዕክታን ጉባኤ ተካሄደ። ሙሉ ጉባኤውን በረቀቀ የመገናኛ ዘዴያቸው ይከታተሉ የነበሩት በኢትዮጵያ ምድር የሚኖሩትና የሰውን ልጅ እያዩ ይደነቁ የነበሩት ኔፊሊሞች ሙሉ ክርክሩን ተከታተሉ። ጉባኤው ባለመግባባት ሲበተንም ከንፊሊሞቹ ውስጥ ገሚሶቹ “ጄኔራላችን ልክ ነው!” በማለት ደገፉት። ከፊሎቹ ደግሞ ተቃወሙ። በዚያን ጊዜም ታላቁና የሁሉም የበላይ አዛዥ የነበረው ልዑላችን አምፆ ነፍጥ አነሳ! በላይም በታችም የነበሩትን ተከታይ ወታደሮቹን እውነታውን አስረድቶ ከጎኑ አሰለፈ። ጎን ለጎንም የነበረውንና ያለውን ጥበቡን ተጠቅሞ የሰው ልጅ አይምሮ እንዲከፈትና ራሱን አውቆ በነፃነት እንዲኖር አደረገ። ይህን ያደረገው በራሱ ስልጣን ሲሆን፣ ዓላማውም የሰው ልጅ በነፃነት መኖር አለበት የሚል ነው።
“የተከለከለውን የዕውቀት ዛፍ በግልፅ ጋብዞ አስገመጣቸው። ከዚያች ቅፅበት ጀምሮ ሰው ራሱን ያወቀ ብልህ ፍጡር ሆነ። ዋንው አካልም በቀድሞ ጄኔራሉ አመፅና ተግባር በእጅጉ ተበሳጨ። ባደረገው ነገርም አዘነ። “የሰው ልጅ ከኛ እንደ አንዱ ሆነ” ሲል ተፀፀተና በስው ልጅ ላይ የዕድሜ ገደብ አበጀ። ወደ ዱዳሌብ አፈርነቱ እንዲመለስም አወጀ። ሰውም ከ ገነት ወጥቶ በርሐማ በሆነው በመካከለኛው ምስራቅ እንዲኖር ተደረገ። በዚያን ጊዜ የኛ ልዑል በላይ ሆኖ ሲሟገት ሳለም የሱን አቋም ይደግፉ የነበሩት ኔፊሊሞች ሌላ አመፅ አነሱ። “የሰው ልጅን እንዲህ ውብ አድርጎ በመስራት አድልቷልና!” በሚል መነሻም በሰው ልጆች ላይ ወሲባዊ ግኑኝነት እየፈፀሙባቸው ነበር የጠበቁት።
“ይህ በሚሆንበት ጊዜም የኛ ልዑል የላይኛው ሹመቱና ክብሩ እንደተገፈፈ ተነግሮት ነበርና ቦታውን ለቆ ወደ ምድር በመምጣት መቀመጫውን በኢትዮጵያ ምድር አድርጎ የሰው ልጅ አፅናኝና አይዞህ ባይ ሆኖ መቀጠል የሚችልበትን ሁኔታ ሲያንሰላስል ቆየ። ወዲያውም ዋናው አካል “የተሻረውን ጄኔራል የምትደግፉ እዚያው ቅሩ፤ የማትደግፉ ወደ ቦታችሁ ተመለሱ” የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈ። ብዙዎች የኛን ልዑል ደግፈው ቀሩ፤ ጥቂቶች ወደ ዋናው አካል ወደ ቀድሞ ቦታቸው ተመለሱ። አሁንም የበላይ አካሉ እሱን ባልደገፉትና ባልተመለሱት ላይ በመበሳጨቱ ኔፊሊሞችም ሆኑ ከሰው የተደቀሉት ልጆቻቸው የገነትን ክልል ለቀው ወደ ሌላ አቅጣጫ ይሄዱ ዘንደ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። ገነትም ያኔውኑ እንዳትገኝ ሆና ተደበቀች። በገነት ውስጥ ደግሞ ከሞት ወደ ህይወት የምትመልሰው ዛፍና ፍሬ አለች። እንዳልኩት ያችን ቦታ በእጁ ያደረገ ሐይል ብቻ ለሰው ልጅ ዘላለማዊ ህይወት መስጠት ይችላል። እደግመዋለሁ፤ ፍሬውን በመብላት አይደለም ሰዎች ወደ ህይወት የሚመለሱት። ወይም ዛፉን ቅጠሉን ቀንጥበው በማስተት አይደለም ዘላለማዊ የሚሆኑት። ነገር ግን የቦታዋ የበላይ መሆኑን ያረጋገጠና ባለ ድል የሆነው አካል በመንፈሳዊ ጥበቡ ይሁን በማለት ብቻ በሁሉም ውስጥ ትሰረፅ ዘነድ ካዘዛት ሁሉም ህያዋን ይሆናሉ። ይህ ስለሆነና ዋናው አካል ግን የሰው ልጅ የህይወት ዛፍ ህልም ሆና እንድትቀርበት፣ ህያው እንዳይሆኑ፣ ስለፈለገና ስለነፈጋቸው እሱ የነፈጋቸውን ልዑላችን መልሶ መስጠት እንዳለበት በማመኑ ያችን ቦታ አልለቅም አለ።
…ይቀጥላል…