አዲስ አበባ ኃሙስ ዕለት ቀትር ልክ ከቀኑ ስድስት ሰዓት፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን።
ቀትር የፀሐይ ብርሃን ከማንኛውም ሰዓት በበለጠ የሚደምቅበት እና ፀሐይ በራሳችን ትክክል የምትሆንበት ሰዓት ነው። በቀትር በራስ ጥላ ምክኒያት እንኳ ጨለማ የለም። እነሆ ፀሐይ ጽድቅ እግዚአብሔር ያለ ምንም ግርዶሽ በሚያበራበት፡ የኃጢአት ጨላማ ገና ባላወቃት በኤደን ገነት ውስጥ “በቀትር” ሆነው ወላጆቻችን “ነፍሳችን የወደደችው አንተ ንገረን፡ ወዴት ታስማራላህ? እዘዘን፡ ትእዛዝህን በደስታ እንፈጽማለን” ይሉት ነበር። ነገር ግን ፈጣሪ እግዚአብሔርን የምትወድን ነፍስ ከክብሯ ለማዋረድ፡ ከፍቅሯ ለማብረድ ቀን ተሌት የሚደክመው ጠላት ዲያብሎስ ለአምላካቸው በፍቅር እና በእውነት ይታዘዙባት ከነበረች “ቀትር” ከተባለች የገነት ኑሮአቸው አውጥቶ “ወደ ጨለማ እና የሞት ጥላ” አወረዳቸው፡ “ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” የተባለው ወልድ ከልጅ ልጃቸው ተወልዶ እስኪያድናቸው ድረስ። ]ፊልጵ. ፪ ፥ ፰}
አበ ብዙኃን አብርሃም እንደ ቀትር ፀሐይ የሚንቦገበግ አምልኮተ እግዚአብሔር በምድር ሰውነቱ ባየ ጊዜ “ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ሥፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፤ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ” (ዕብ. ፲፩፥፰)። በዚህ ጊዜ ዘመዶቹን፡ አገሩን እና የአባቱን ቤት ትቶ የሚወድደውን እግዚአብሔርን ይታዘዝ ዘንድ የወጣ የአባታችን የአብርሃም ነፍስ “ነፍሴ የወደደችህ ፈጣሪዬ አንተ ንገረኝ፡ ወዴት ትመሰጋለህ? ብቻ አንተ እረኛዬ የምትሆን ከሆነ ያደግሁበትን አገር ለቅቄ እንደ በግ እከተልሃለሁ፡ በድንኳንም ቢሆን እኖራለሁ” እያለች ነበር።
እረኛው እግዚአብሔር መለሰ። “በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት።…እግዚአብሔርም አለ፦ እኔ የማደርገውን ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናልና፡ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በእርሱ ይባረካልና” (ዘፍ. ፲፰፥፩)
ይህ ቪዲዮው ላይ የሚታየው ወንድማችን ቀትር ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ–ክርስቲያን ቅዱስ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ተመበርክኮ ጸሎቱን በጩኸት ለፈጣሪ ያደርሳል። አብዛኛውን ሁኔታ ቪዲዮው ውስጥ አላስገባሁትም እንጂ ያጋጣሚ ሆኖ የልጁን ሁኔታ ትንሽ ራቅ ብዬ በጥሞና እከታተል ነበር። ልጁም፡ “ጎርጊስ፡ የት አለህ? ና እንጂ?….ኧረ ጎርጊስ…..ኧረ ጎርጊስ….ና እንጂ…የት አለህ?” በማለት እጆቹን ወዲያ ወዲህ እያወዛወዘና እየተንጠራራ ያለማቋረጥ ይጮህ ነበር። በመሃልም፡ የእስላሞችን አምላክ እየጠራ “አላህ ወአክበር! አላህ ወአክበር!” በማለት ሲጮህ የሰሙ ምዕመናያን፡ ቪዲዮው ላይ እንደሚታየው ጠጋ በማለት፡ “ምንድን ነው ነገሩ፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ነው፡ አላህን ከፈለግክ ውጣ እና ወደ መስጊድ ሂድ” ይሉታል።
እኔም በበኩሌ ይህ ወንድማችን ለምን ቤተክርስቲያን መጥቶ የሌላ አምላክ ስም ይጠራል? በማለት ከቤተክርስቲያን ሊወጣ ሲዘጋጅ በትህትና ጠየቅኩት። ወንድማችን በቅርቡ ከእስልምና ወጥቶ ወደ ክርስትና እንደገባ በጥቂቱ አወሳኝ። ቀጥዬም “እግዚአብሔር መንገዱን ይምራህ፡ ለተቀሩት ሙስሊም ወገኖቻችንንም ጌታችን ክርስቶስ ከጨለማ አውጥቶ ብርሃኑን ያሳያቸው። እንደ አብርሃምም በትህትና የሚማጸኑ ከሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ይገለጥላቸዋል፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይርዳቸው” በማለት ተሰናበትኩት።